ለቸኮለ! የዛሬ ማክሰኞ ነሐሴ 5/2012 የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች

1. በወላይታ ዞን ለተቃውሞ በወጡ ዜጎች ላይ የመንግሥት ጸጥታ ሃይሎች በወሰዱት የሃይል ርምጃ 21 ሰዎች ተገድለው 105 እንደቆሰሉ DW የወላይታ ብሄራዊ ንቅናቄ አመራሮችን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡ አብዛኛዎቹ የተገደሉት ከሶዶ ከተማ ወጣ ብሎ በምትገኘው ቦዲቲ ከተማ ነው፡፡ የደቡብ ክልል ጸጥታ ቢሮ ሃላፊ ደሞ፣ 5 ሰዎች ብቻ እንደሞቱ እና 15 እንደቆሰሉ ተናግረዋል፡፡ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች እና አገልግሎት ሰጭ ተቋማት እና ከሶዶ ወደ አዲስ አበባ፣ ሀዋሳ እና አርባ ምንጭ የሚወስዱ መንገዶች ዝግ እንደሆኑ የዐይን እማኞች ለDW ተናግረዋል፡፡
2. በድምጻዊ ሐጫሉ ሁንዴሳ ግድያ የተጠረጠረው ከበደ ገመቹ ዛሬ ፍርድ ቤት መቅረቡን ፋና ብሮድካስት ዘግቧል፡፡ ፖሊስ የተጠርጣሪውን የስልክ የድምጽ እና መልዕክት ልውውጦች እንደመረመረ ለችሎቱ አስረድቷል፡፡ ፖሊስ ለተጨማሪ ምርመራ የጠየቀውን 14 የምርመራ ቀናት ችሎቱ ፈቅዷል፡፡ በተያያዘ፣ የኦሮሞ ሜዲያ ኔትወርክ ጋዜጠኛ ጉዮ ዋርዮ ላይ፣ ፖሊስ የሰነድ ማስረጃዎችን ማሰባሰቡን እና የምስክሮችን ቃል መቀበሉን ገልጾ፣ 14 ተጨማሪ ቀናት ጠይቋል፡፡ ችሎቱም የምርመራ መዝገቡን ተመልክቼ ነሐሴ 8 ውሳኔ እሰጣለሁ ብሏል፡፡
3. የመንግሥት ጸጥታ ሃይሎች በወላይታ ዞን ሰላማዊ ተቃዋሚዎች ላይ የወሰዱት የሃይል ርምጃ ተመጣጣኝነቱ አጠያያቂ ነው- ብሏል የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ዛሬ በፌስቡክ ገጹ፡፡ በግጭቱ በሶዶ ከተማ 1 በቦዲቲ ደሞ 5 ሰዎች መሞታቸውንም ጠቅሶ፣ በአሟሟታቸው ላይ ፈጣን ምርመራ እንዲደረግ አሳስቧል፡፡ የክልሉ ፖሊስ ከዞኑ በጠቅላላው 28 የዞን አመራሮችን ጨምሮ 178 ሰዎችን በቁጥጥር ስር አውሏል፡፡
4. በዋስ ከተለቀቁ በኋላ ይግባኝ ተጠይቆባቸው እስር ቤት ያሉት የሕወሃት አባላት ዛሬ እንደገና ፍርድ ቤት እንደቀረቡ የመንግሥት ዜና አውታሮች ዘግበዋል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ የሀገር ሚስጢርን ለአሸባሪዎች አሳልፈው ስለመስጠጣቸው ማስረጃ እንዳሰባሰበ ፖሊስ ለችሎቱ በማስረዳት፣ የ14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ቀናት እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡ ችሎቱም በፖሊስ ጥያቄ ላይ ነሐሴ 11 ውሳኔ እሰጣለሁ ብሏል፡፡ እስር ላይ ያሉት ተጠርጣሪዎች፣ አዲስ አበባ የሕወሃት ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ተወልደ ገብረ ጻዲቅ፣ የደኅንነቱ መስሪያ ቤት ባልደረባ አጽብሃ አለማየሁ፣ የሕግ ጥናት እና ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር ተስፋለም ይኸድጎ እና የማዕከሉ 2 ሹፌሮች ናቸው፡፡
5. በደቡብ ክልል በወላይታ ዞን የተፈጠረው አለመረጋጋት በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ የኢትዮጵያ ዜጎች ማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲ አሳስቧል፡፡ በግጭቱ የጠፋውን ሕይወት መንግሥት አጣርቶ እንዲያሳውቅም ጠይቋል፡፡ የዞኑ አመራሮች ደሞ የሀገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ለክልልነት ሕዝበ ውሳኔ ምቹ እንዳልሆነ መገንዘብ አለባቸው ብሏል፡፡
6. በሀገሪቱ የጦር መሳሪያ ምዝገባ ለማካሄድ ዝግጅቶች እየተደረጉ እንደሆነ ሰላም ሚንስትር ሙፈሪያት ከሚል መናገራቸውን ኢቢሲ ዘግቧል፡፡ የምዝገባው ዐለማ ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርን መቆጣጠር ነው፡፡ የሕገ ወጥ ጦር መሳሪያ ዝውውርን ለመቆጣጠር እና ለማስተዳደር ዘንድሮ የወጣው አዋጅ፣ ዜጎች በይዞታቸው ስር ያለውን ጦር መሳሪያ በ2 ዐመታት ውስጥ እንዲያስመዘግቡ ያዛል፡፡
7. የመንግሥት ጸጥታ ሃይሎች በጽሕፈት ቤቴ ላይ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ያደረጉትን ብርበራ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ያጣራልኝ ሲል ኦነግ አቤቱታውን አሰምቷል፡፡ የግንባሩ ሊቀመንበር ዳውድ ኢብሳን ጨምሮ የድርጅቱ አባላት ማስፈራራያ እና አፈና እየደረሰባቸው እንደሆነም ግንባሩ በፌስቡክ ገጹ ትናንት ባሰራጨው መግለጫ አስታውቋል፡፡ ቦርዱ በግንባሩ ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት መርምሮ ለዐቃቤ ሕግ እንዲመራውም ጠይቋል፡፡ ዳውድ በበኩላቸው የግንባሩ አመራሮች ትናንት ስለሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ምንም እንደማያውቁ ለቢቢሲ አማርኛ ተናግረዋል፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]

1 COMMENT

  1. Comment: Comment: yih chigign yabiy genzeb mezrefiya legosaw makberiya new. Landit chigign asr bir woch hone yilna le5 billion 50 billion bir yiwosdal. Gin ewnetaw chigignu meto million wochu 1 bilion lihon yichilal. Yihn yahl woch angebgabi lalhone fuday ayasfelgm, yasfelgal kalem Lemn betederaj komishin neglt aymeram? Yadis abeban bajet leadebabay wonz maswab ledsat lementisie eyalu endiet endemiqerametut eneabiy takel lib blachuhal?

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.