የኢትዮጵያ አየር መንገድን አለመሣፈር አርበኝነት ነው! (በድንበሩ ደግነቱ)

በዚህ ባለፈው የበጋ ወቅት ጎረቤቴ የሆነች የዚሁ አገር ተወላጅ (አሜርካዊት ነጭ) ወደ ማዳጋስካር ለመሄድ የአየር ቲኬት ለመግዛት ዋጋ ታወዳድር ነበርና፥ ስለ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ጠየቀችኝ። እኔም አየር መንገዱ በደሕንነት አንፃር መጥፎ ሪከርድ ጨርሶም እንደሌለው ጠቅሼ የህወሀትን ኢሰብአዊነት አብራራሁላት። በዚህ አየር መንገድ መሣፈር ላለው መንግሥት የጥይት መግዣ ማቀበል በመሆኑ ሌሎች አየር መንገዶችን እንድትመርጥ ነገርኩዋት። ባለቤቴም በዛኑ ሰሞን ወደ ኢትዮጵያ ታቀና ነበርና፥ ለጎረቤቴ የነገርኩዋትን አጫወትኩዋት። ባለቤቴን እጅግ በጣም ገረማት! “ለኢትዮጵያውያን እሺ ይሁን፥ እንዴት አንድ ኢትዮጵያዊ ለሌላ አገር ዜጋ እንዲህ ይላል?” ብላ ለአገሬ ያለኝን ፍቅር ጥያቄ ውስጥ ከተተችው።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኢትዮጵያ መሆኑ ከቀረ ውሎ አድሮዋል። ደፋ ቀና ብለው ያቀኑትን ምሥኪን ሠራተኞች ሁሉ አበጥሮ ካባረረ በሁዋላ፥ ከአንድ አካባቢ በበቀሉ በህወሀት ታማኞች ተሞልቶዋል። የዐይኑ ቀለም አላማረንም ያሉትን ኢትዮጵያዊ ሁሉ፥ ተገቢውን ጥቅማ ጥቅም ከልክለው በገፍ አባረዋል። አየር መንገዱ ሠራተኞችን የሚያንገላታበትና ሠቆቃ መፈጸሚያ ቦታ በቅጥር ግቢው ውስጥ ያዘጋጀ መሥሪያ ቤት እንጂ – የአገሪቱን የኢኮኖሚ ችግር የሚፈታ ተቁዋም አይደለም።

ኢትዮጵያ ውስጥ ሁለት ቡድኖች አሉ አይጥና ድመት፥ በዪ እና ተበዪ፥ ገዳይና ሙዋች፥ መንግሥትና ሕዝብ። በደቡብ አፍሪካ ከአፓርታይድ ጋር በተደረገው ትንቅንቅ፥ የዓለም ሕዝብና ቀና መንግሥታት በሙሉ የየአቅማቸውን አስተዋፅዖ በአፓርታይድ አንፃር አድርገዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት አውሬነት በምንም መለኪያ ከአፓርታይድ አራማጆች የሚያንስ አይደለም። ለጎረቤቴ የመከርኩዋት ምክር አገሬን አጥብቄ መውደዴን እንጂ የአገር ክህደትን አያሳይም። ኢትዮጵያን የካደው – ታቦቱን በከርቤ ሳይሆን በመርዝ ያጠነው ወያኔ ነው። ሳይጠራ በሕዝብ በዓል ላይ ተገኝቶ (እሬቻን ያስታውሱዋል) በሺ የሚቆጠሩትን በጅምላ የፈጀው አረመኔው ህወሀት ነው – ኢትዮጵያን ያሣነሣት። በሕዝብ ጠላትነት በቁዋሚነት ተሠልፎ ለግማሽ ክፍለ ዘመናት ሲገድል፥ ሲያሥር፥ ሠቆቃ ሲፈፅም የኖረው ወያኔ ነው – አገር የጎዳው። የተቀደሠውን መሥጊድ በወታደር ጫማ ያረከሠው ህወሀት ነው – ሕዝባችንን ያዋረደው።

ብዙ ጊዜ በውጭ አገር ያሉ ኢትዮጵያውያን ለአርበኞች ቀለብ እንዲሠፍሩ ሲጠየቁ፥ ጦርነትን መደገፍ ከእምነታቸው ውጪ እንደሆነ በመናገር ፈቃደኛ አይሆኑም። ጦርነትን ብቻ እንደ አማራጭ ወስዶ ሕዝብን የሚጨፈጭፍ የህወሀት መንግሥት እንጂ የነፃነት አርበኞቹ አይደሉም። የሕዝብ ጥያቄ እንደ ዜጋ በአገሬ ምድር ተከብሬ ልኑር ብቻ ነው። እኔም የአገሬ ሀብት ተቁዋዳሽ ልሁን ብቻ ነው ጥያቄው። የአየር መንገዱ በጁን 2016 ሪፖርት ባደረገው የሂሳብ መዝገብ መሠረት ብር 6,128,872,862.00 የነጠረ ገቢ በተጠቀሰው ዘመን ሪፖርት አድርጎዋል። ይሄ ብር ስንት ጥይት ይገዛ ይሆን? ምን ያህሉስ ለገዳዮቹ ቦነስ ይሰጥ ይሆን። እናንተ በጦርነት የማታምኑ – የኢትዮጵያ አየር መንገድን ስትበሩ፥ ከኢትዮጵያ የሚመጣ ምርትን ስትጠቀሙ፥ ለህወሀት ጥይት መግዣ እያቀበላችሁ መሆኑን ልታስታውሱ ይገባል። ሳይታወቃችሁ በጦርነቱ ውስጥ ተዘፍቃችሁ ሕዝባችሁን እየወጋችሁ መሆኑን ልብ ልትሉት የሚገባ ጉዳይ ነው። ጦርነትን የምትቃወሙ ከሆነ ህወሀትን በማስራብ ለሕዝባችሁ ውለታ ሥሩ።

ባዶ እጃቸውን ሆነው ከገዳዮቹ ጋር የሚጋተሩት ቄሮና ፋኖ ለአንድ ጥይት አንድ ነፍሥ አስልተው በጥይቱ ልክ ነፍሥ ገብረው ጥይቱ ሲያልቅ ህወሀት ጥያቄያችንን ይመልሳል በማለት ነው። በውጭ ያለን ወገኖች የጥይት መግዣውን በተካንለት ቁጥር መግደል የማይሰለቸው እንደውም የሚያስደስተው ወያኔ ህዝቡን በሙሉ ይጨርሰዋል። ካለሕዝቡ እናንተስ እንዴት ሐገር ይኖራችሁዋል? ከእናት ሀገር የሚበልጥ የለምና ሲሆን በጦር ይህን የፋሽስት ቡድን መጋተር ይገባ ነበር። ኢትዮጵያ ያሳደገችና እትብታችን የተቀበረባት ምድር ነችና ልንሞትላት በተገባ ነበር። ይህ ሁሉ ቢቀር እጅግ ጥቂት መስዋዕትነት በማድረግ የወያኔን ዕድሜ በማሳጠር እንተባበር። ይህን ስታደርጉ ብዙ የማይመቹ ነገሮች ሊያጋጥማችሁ እንደሚችል የታወቀ ነው። ራሳችሁን ማወዳደር የሚገባው ደረቱን ለአግአዚ ጦር እየሰጠ ለነፃነቱ ከሚታገለው ቄሮ ጋር መሆን ይገባል። ከወያኔ ጦር ጋር ጉሮሮ ለጉሮሮ በመተናነቅ ላይ ከሚገኘው ፋኖ ጋር መሆን ይገባል። ለነዚህ ነገሮች አማራጮች ሞልተዋል። ወያኔ እየሞተ ነው። አንርዳው። በትንሽ መስዋዕትነት ከሕዝብ ጎን እንቁም። ይህ ገቢ እንዲቀንስ ማድረግ ወያኔን ማሽመድመድ ነው የሕዝብንም የነፃነት ቀንዲል መለኮስ ይሆናል። ይህም አርበኝነት ነው። ከዚህ በተቃራኒው መቆም ሕዝብን ከመካድ ሌላ ምንም የሚሰጠው ትርጉም አይኖርም!

የአገራቸው ጉዳይ ጥብብ ጭንቅ ያላቸው ብርቅ ኢትዮጵያውያን ወደአገር ቤት የሚላከው ሀዋላ ከመንግሥት ተሸሽጎ የሚያልፍበትን መንገድ ወገን ሁሉ እንዲጠቀም በማስተባበር ላይ ይገኛሉ። የተጀመረው ወያኔን በዶላር ማሥራብ ዘመቻ ተጠናክሮ በአየር መንገዱም ላይ ዘመቻው እንዲፋፋም የዜግነት፥ የሞራልም፥ የሃይማኖትም፥ የሰውነትም ግዴታ አለብን። ተባብረን ጉዳዩን የራሳችን አድርገን ከተንቀሳቀስን ለውጡን ያለ ጥርጥር እናፋጥናለን። እጅ ለእጅ ተያይዘን አገራችንን መልሰን የምንገነባበት ቀን ሩቅ አይሆንም። ምንንም ነገር ሳንንቅ በአንድ ሚሊ ግራም እንኩዋን ወያኔ እንዲጎዳ ስናደርግ የነፃነት ቀን በአንድ ማይል ይቀርባል። የልጅዋ አሥከሬን ላይ እንድትቀመጥ ተደርጋ የተደበደበችው ታደሉ ተማም የልጅዋ መቃብር ላይ ቆማ ጮክ ብላ እንድታለቅስ በሞት ሳትቀድመን በፊት እንድረስላት።

የእናት ሀገርን የጭንቅ ቀን ተባብረን እናሣጥር!!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.