“በአንድ ድንጋይ ሦስት ወፍ” (ተፈራ ድንበሩ)

  በፒ.ዲ.ኤፍ ለማንበብ ይህንን ይጫኑ

ወያኔ እንደቆሰለ አውሬ መግቢያ መውጫው ጠፍቶበት የሚፈራውን ሁሉ እየገደለ ነፍሱን በማሰንበት ላይ ነው፤ ሆኖም ከብዙሃን ኢትዮጵያውያን ጋር ይበልጥ ደም በተቃባ መጠን ዕድሜውን እያሳጠረውና አወዳደቁን እያበላሸው መሄዱ ሐቅ ነው። ዛሬ ወያኔ ከሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ የተለየ ጠላት ሆኗል፤ የራሱ ኅልውና የለውም፤ በጥገኛ ነፍሳት (parasites)፣ ግብረበላዎች፣ የነገውን በማያውቁ የዕለት ቅጥረኞች ድጋፍ ብቻ ነው ያለው ። ወያኔዎች በስግብግብነት ላይ ተመሥርተው በሥልጣን ተቅበዝብዘው እንደነ ስሎቮዳን ሚሎሰቪክና ራዶቫን ካራድዚክ በአልቤኒያና ፕሮሺያ የተደረገውን በትግራይ ላይ ለመድገም ያልማሉ እንጂ ኢትዮጵያ ዩጎዝላቪያ እንዳልሆነች ካለመረዳታቸውም በላይ በአገር ላይ እያደረሱት ያለው ጥፋት “በሬ ሆይ በሬ ሆይ ሣሩን አየህና ገደሉን ሳታይ….” እንደተባለው የኋላ ኋላ ራሳቸውን የሚያጠፋቸው መሆኑን አልተረዱትም። ዛሬ ከምን ጊዜውም በላይ በሕዝብ የተተፉት የወያኔ መሪዎች ከተፈጥሮ እድገትና ከታሪክ ተምረው የስንብታቸውን ሁኔታ ባለማመቻቸታቸው መስዋዕትነቱን ከፍተኛ እንዲሆን ባደረጉት መጠን አወዳደቃቸውንም ክፉኛ ያደርጉታል። አስተዋይ ቢሆኑ ኖሮ በሰላማዊ የሽግግር ሥርዓት ሥልጣናቸውን ለባለቤቱ ለሕዝብ አስረክበው በሰላም የሚኖሩበትን መንገድ በማመቻቸት ቆመንለታል የሚሉትንም የትግራይ ሕዝብ በሌላው ሕዝብ ከመጠላት ያድነት ነበር፤ “አልጠግብ ባይ የኋላ ኋላ ሲተፋ ያድራል “ እንደሚባለው ለራሳቸውም አላወቁበትም። አንድ የእንግሊዞች ሥነቃል እንደሚገልጸው “አንዳንድ ሰዎችን አንዳንድ ጊዜ ማታለል ይቻላል፤ ሕዝብን ግን ሁልጊዜ እያታለሉ መቀጠል አይቻልም።” ስለሆነም አንዲት የኪነት ባለሙያ

እንደገለጸችው ・ጠላትማ ምን ጊዜም ጠላት ነው፤ አስቀድሞ…  “ብላለች።  ስለዚህ ስለወያኔ ጥፋት ስፋትና

ጥልቀት በማውሳት ጊዜን ከማባከን የወያኔን ተቀጽላዎች ብናስተውል፤ ቆሞባቸው ሕይወት የሚዛራባቸውን ሥራሥሮችና ቅርንጫፎቹ የሚደርቁበትን መንገድ በመፈለግ የማይቀርለትን ግብአተሞት ማፋጠን ወቅታዊ ጉዳይ ነው፡፡ ማፍረስ የማስፈለጉን ያህል በሌላ በኩል ደግሞ የመገንባት ራዕይ ከሌለን እንቅስቃሴው ከእሳት ወደረመጥ እንዳይሆን ከፍተኛ ማስተዋልን ይጠይቃል።

 

በማንኛውም የለውጥ ሒደት ውስጣዊ ኃይል ወሳኝነት አለው፤  በአገራችን ውስጥ ዲሞክራሲ፣ እኩልነት፣ ፍትሕ ለማምጣት የሚደረግን ትግል ሕዝቡ ራሱ በባለቤትነት ተንቀሳቅሶ ለነዚህ ዓላማዎች እንደ አንድ አካል ካልቆመ ማንም የውጭ አካል መጥቶ ሊረዳው አይችልም፤ እንዲየውም ልዩነት ካለ በሚፈጠረው ቀዳዳ ሾልኮ ገብቶ የራሱን ጥቅም ለማሳካት ጥረት ያደርጋል እንጂ። ለዲሞክራሲና ፍትሕ ቆመናል የሚሉ ኃያላን መንግሥታት ድሮም ሆነ ዛሬ የየአገራቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ ካልሆነ በስተቀር በምንም መልኩ በነፃ አመለካከትና በበጎ አድርጊነት በአገራችን ላይ ፍትሐዊ ሥርዓት እንዲመጣ ዓላማቸው አድርገው ሊረዱን እንደማይፈልጉ ለምሳሌ በብዙ ሀገሮችና በራሳችንም ሀገር በተደጋጋሚ የተረጋገጠ ነው። አንድነት እንዳይኖረን የሚያደርጉን ዋና ዋና ችግሮቻችን ደግሞ ቀጥሎ የተመለከቱ ሲሆን፣ የተደቀኑብን ችግሮቻችን ትኩረት ተደርጎባቸው ሁለንተናዊ መፍትሔዎቻቸውንም በመፈለግ ያለንበትን የትግል ዳገት ወደቁልቁለት በመለወጥ በአነስተኛ መስዋዕትነት ከፍተኛ ድል ማስገኘት የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት ነው።

 

የፖሊቲካ ተዋናዮችና ቀጥተኛ የዓላማ ጽናት፦ ለውጥን እናመጣለን ብለው የፖሊቲካ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ አንዳንድ ተዋናዮች ስለአገራችንም ሆነ ሰለዓለም ኅብረተሰብ እድገት ያላቸው ዕውቀት/አመለካከት ውሱን መሆን ብዙ ችግሮችን አስከትሏል፤ የፍትሕን ዓላማ የሚያነግብ አካል ራሱ ከጎሣ፣ ዘር፣ ሃይማኖት፣ ቋንቋ፣ ወዘተ ወገንተኛነት ነፃ ሆኖ ፍትሐዊ መሆን ይጠበቅበታል። ታሪኮችን ማወቅ የሚያስፈልገው ካለፉት ድክመቶች ትምህርት ወስዶ የተሻለ ነገር ለመሥራት መሆን ሲገባ፤ የእኩልነትን መፈክር አንግቦ ራሱ ሕዝብን በዘር ለሚከፋፍል የጎሣ ፖሊቲካ አራማጅ አካል የሚሠራ እና የገዥው ሥርዓት ባዘጋጀለት የአወቃቀር ሥልት ተደራጅቶ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የአፓርታይድን ሥርዓት አስፈጻሚ ከሆነ፤ ፍትሐዊ ስለማይሆን በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም። በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው በኅብረተሰቡ ውስጥ ፍትሐዊነትና ሕዝብን የሚያፋቅር ፈለግ ማሳየት ይኖርበታል፤ ስለአንድነት የሚሰብክ ድርጅት ልዩ ልዩ አመለካከቶችን አቅፎ አብሮ መሥራትን ማሳየት ይኖርበታል። የፖሊቲካ ድርጅቶቻችን ራሳቸው ከጎሣ ፖሊቲካ ነፃ ሳያወጡ ሕዝቡን ነፃ እናወጣለን በማለት ሌተቀን ቢቀባጥሩ በሕዝቡ ዘንድ ተቀባይነት አይኖራቸውም፤ ስለአንድ አገር ሕዝብ ነፃነትና እኩልነት እየሰበኩ የብሔርብሔረሰብ መስመር የሚከተሉ ከሆነ ድርጅታቸው ሁሉንም ሕዝብ ስለማያቅፍ ስብከታቸውን ከንቱ ይሆናል። አብሮት በጉርብትና ካለው ኅብረተሰብ ጋር አስማምቶት የመምራት ተግባር የማያመለክት መሪ በነፃ ተንቀሳቅሶ መሥራትና በፈለገበት አካባቢ በነፃነት የመኖርን ስጋት ስለሚያስከትልበት ሕዝቡ በጥርጣሬ የየዋል እንጂ አቅፎት ወይም ዓላማውን ደግፎ ከጎኑ ሊሰለፍና መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁነት ሊኖረው አይችልም። ስለሆነም ዛሬ በአገራችን ውስጥ የሚንቀሳቀሱት ድርጅቶች ብዙዎች ከላይ የተጠቀሱት ችግሮች ጎትተው ስለያዙዋቸው ስለአገር ጉዳይ ብለው፤ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እያገለገሉት ካለው ከገዥው ሥርዓት የፖሊቲካ መስመር ወጥተው ፕሮግራሞቻቸውን አስተካክለውና አቻችለው ለሕዝባዊ ዓላማ ጥምረት በመፍጠር ለአንድ የእውነተኛ ዲሞክራሲና ፍትሐዊነት ግብ በመቆም በተቃዋሚ ደረጃም እያሉ ጠላታቸውን ለማስወገድ በጋራ መሥራት ይጠበቅባቸዋል፤ ከሌሎች የአንድ አገር ድርጅቶች ጋር ካልተስማሙ አገር የመምራት ብቃታቸውን ማየት ስለማይችል ሕዝብ አመኔታ ሊያሳድርባቸው አይችልም። በቅርቡ ያለው የሕዝብ እምቢተኝነት ሲታይ የወያኔን ከፋፍለህ ግዛ መርህ ተረድቶ ከፖሊቲካ ድርጅቶች በመቅደም የጎሣ አጥርን ሰብሮ አንዱነቱን እያሳየ ሲሆን ከጎኑ ቆመው ለጋራ ግብ ካልመሩት ኅልውናቸው ጥያቄ ውስጥ ይገባል። እነሱ ራሳቸው ደካማ ሆነው ሳለ ይህን በአንድነት ተባብሮ አገር የጋራ ነች ብሎ በአድዋ፣ በሶማሌያና ሊሎች በኢትዮጵያ ላይ የተቃጡ ጥቃቶችንና ጦርነቶችን ያላንዳች ልዩነት ተባብሮ ጠላትን ድል በማድረግ ይህችን አገር

 

ያቆየውን ሕዝብ ደንቆሮ አድርገው በማየት በዘጎሣና ሃይማኖት ገመድ እየሳቡ ገደል ሊከቱት ሲፈልጉ በተደጋጋሚ እንደከብት አልሳብም ብሎ ከወንድም እህቶቹ ኢትዮጵያውያን ጋር መተባበር እንደሚሻል በተግባር አሳይቷል። ሆኖም በስሙ ያሉት የፖሊቲካ ድርጅቶች ተባብረው በአገር ጉዳይ አንድ ሆነው እንዲመሩት ይጠበቅባቸዋል። የየራሳቸውን ተምኔታዊ ራዕይ በማየት ፋንታ የአገር ራዕይ ከሌላቸውና ከዲሞክራሲያዊ ድርጅቶች ጋር የማይተባበሩ አካሎች አገርን ለመገንባት አይረዱም። የአገር መገንባት ግቡ የሕዝቡን ሰብአዊ መብት፣ ፍትሕ፣ ብልፅግናና ሰላም ማስፈን ነው። ለጋራ ሕዝባዊ ዲሞክራሲ ድል እና አገርን ለመገንባት በተናጥል ከመሮጥ አንድነት አማራጭ የለውም።

 

ተማሩ በሚባሉ ሰዎች እንደሚጠብቅባቸው ሆነው አለመገኘት:- ሕዝባችን በተማረ ሰው ያምናል፤ ሆኖም በሰዎች ሙያ (professional Shallowness) መሳሳትና የትምህርት ካባ በማጥለቅ የሙያ ማዕረግ ይዘው የሐሰት/ልበወለድ/ ታሪክ የሚጽፉ ምሁራን እየበዙ ሄደዋል፤ የነበረውን ታሪክ  እየፋቁ ያልተፈጠሩ ታሪኮችን ይጽፋሉ፤ ሕዝብን የሚያቀራርብና የሚያፋቅር ድርጊት በመፈጸም ፋንታ ለምሳሌ የጥላቻ ሐውልት ከማሠራት ጀምሮ ሕዝቡን የሚያሳስት ትምህርት/ፕሮፓግንዳ/ ሰለባ ላይ ጥለውታል፤ ኢትዮጵያ የምትባል አገር አልነበረችም በማለት ከመጽሐፍ ቅዱስም ውስጥ ስሟን በማውጣት በሰዎች እምነት ውስጥ ገብተው የአገርን ታሪክ በመበረዝ ጥንታዊ የጎሣ ፖሊቲካ ለማራመድ የሚፈልጉ ግለሰቦችም ታይተዋል። ሌላው ደግሞ በየጎረቦቱ የሚጨሰው ጭስ ሊበክለው እንደሚችል ዘንግቶ ለበጎ ዓላማ እጁን ሳያነሳ በአድርባይነት የራሱን ምቾት ብቻ ይጠብቃል። አገር ጤና ሳይሆን ደህንነት ያለ የሚመስለን ጥፋት ሲፈጸም እያየን እየሰማን በምኞት ዓለም የምንቆዝመው ሁሉ ጥፋቱ እንዲቀጥል የምንረዳው ማስተዋል ያቃተን ወገኖችንም አለን፡፡ በደሀው የኢት. ሕዝብ ታክስ ተምሮ በተለያዩ አጋጣሚዎች ካገር ወጥቶ ዕውቀቱንና ማንነነቱን ሸጦ የበለፀገውን ዓለም በማበልፀግ፤ የአገሩ ሕዝብ ግን ሲጎሳቆልና ሲዋረድ እንዳላየና እንዳልሰማ ሆኖ ኅሊናውንም ሸጦ በሁለተኛ ዜግነት የሚኖርም የተማረ ሰው አለ፤ የዕውቀትን ማህበራዊነት ዘንግተው በጋን ውስጥ እንደሚበራ መብራት ሙያቸውን ከዕለት ጉርሳቸው አሳልፈው ለማህበራዊ አገልግሎት ያላዋሉ ምሁራንም አለን። ምእራባውያን አገሮች ከኋላችን ተነሥተው በከፍተኛ ፍጥነት በቴክኖሎጂና በማህበራዊ እድገት ከፍተኛ እምርታ ሊያደርጉ የቻሉት ትንሽ ያወቁ ዜጎቻቸው ዕውቀታቸውን ለሌሎች በማካፈልና በመተጋገዝ ነው፤ ብዙዎች የኛ ምሁራን ግን ዕውቀታቸውን አፋጭተው በመተራረምና በመደጋገፍ ፋንታ አንዱ ሌላውን በማጣጣል የግል ወዳሴ (personality cult) ለመገንባት በሚያደርጉት የመጣጣል ትርዒት ተራውን ሕዝብ የሚይዘው የሚጭብጠው አሳጥተው ግራ ያጋቡታል፤ ሙያቸውን ተከትለው ያለምንም አድልዎና ፖሊቲካዊ ተፅዕኖ ለኅብረተሰቡ ዕውቀታቸውን ማካፈል የሚችሉ ምሁራን በተለይም በነፃው ዓለም ውስጥ እንደሚታየው ተደራጅተው ለሙያቸው እንኳ ሲንቀሳቀሱ አይታዩም። ጥቂት ምሁራን ለሕዝቡ ጠቃሚ ጮራ እየፈነጠቁ ቢሆንም በነፃ ሙያቸውን ለሕዝብ የሚያካፍሉበት መድረክ በአገር ውስጥ ስላላገኙና በውጭውም ዓለም ስላልተደራጁ በተናጥልና በግል የሚያደርጉት እንቅስቃሴ የሕዝባችንንም ሆነ የዓለም አቀፍ ኅብረተሰብን ቀልብ ሊሰብ አልቻለም። በተደራጀ መልኩ በኅብረት ቢንቀሳቀሱ ኖሮ ተደማጭነታቸው ሊያስከትለው የሚችለው አዎንታዊ ተፅዕኖ አያጠያይቅም። ለምሳሌ የሰብአዊ መብት ጉባኤና የጋዜጠኞች ማህበር እንደሚያደርጉት የሕግ ባለሙያዎች፣ የሂሣብ ባለሙያዎች… ወዘተ በየሙያቸው ተደራጅተው ባገራቸው የሚከናወነውን ጥፋት ለማስወገድ ጥረት ሲያደርጉ አይታዩም። በውጭው ዓለም እንዲህ ያሉ የሙያ ድርጅቶች ናቸው ሰብአዊ መብት እንዲከበር፣ ፋይናንስ አያያዝን ሥርዓት በማስያዝ፣ የሕግ የበላይነት እንዲከበር፣ አድሏዊ አሠራር እንዳይፈጠር፣ ሙስና ከእንጭጩ እንዲቀጭ በሚያደርጉት ክትትልና የማጋለጥ እርምጃዎች እንዲሁም ባለሥልጣናትን በተጠያቂነት እስከ ፍርድ ቤት ድረስ በማቅረብ ፍትሐዊ አሠራር እንዲሰፍን የሚያደርጉት።

ጠንካራ የሙያ ተቋማት በአገራችን ውስጥም ሆነ በውጭ በየትኛውም የሙያ ዲሲፕሊን ተደራጅተው ቢንቀሳቀሱ

በአገራችን ውስጥ የሥነምግባር ባህል (ethics) እንዲዳብር አስተዋጽኦ ሊያደርጉ ያስችላቸዋል፤ ሥነምግባር በተንሰራፋበት ኅብረተሰብ ደግሞ በሥነምግባር ባህል የታነፁ የሕዝብ እገልጋዮች ወይም መሪዎች ይወለዳሉ፡፡

 

የአመለካከት ለውጥ ማድረግ ስለማስፈለጉ፦ እድገት ማለት የአዳዲስ ሕንፃዎች መገንባት፣ትላልቅ መንገዶች መሠራት፣ አዳዲስ ፋብሪካዎች መከፈት፣ በሴሌፎንና በኮምፒዩተር መጠቀም የሚመስላቸው ተራ ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ ተማርን የሚሉ ሰዎችም ጭምር አሉ። የግንባታዎቹ አስፈላጊነት አያጠያይቅም፤ ሆኖም እድገቱ የተራውን ሰው የኑሮ ደረጃ ማሻሻል ላይ ነው።  በአጠቃላይ በስታቲስቲክስ መለኪያ (ጂዲፒ)  የአገር ልማት  አድጓል ተብሎ በጭፍኑ የሚገለፀው አሳሳች ነው፤ የአገር ውስጥ እና የውጭ አገር ባለሀብቶችን ያደባለቀ፣ የሥራአጡን ቁጥር፣ የተራውን ሕዝብ የነፍስ ወከፍ ገቢና የመግዛት አቅም የማያሳይ ስታቲስቲካዊ መረጃ በግርድፉ እድገት ሊባል ይችላል። ጥቂት ባለሀብቶች በተለይም የገዥው ክፍል ቤተሰቦችና ደጋፊዎቻቸው 90% እና ከዚያ በላይ ያለውን የአገር ሀብት በግላቸውና በቋንቋ ድንበር ከልለው ይዘው ሌላው ሰፊው ሕዝብ ግን የመግዛት አቅም አጥቶ፤ የሚጠጣው ንጹሕ ውሀ ሳይኖረው በረሀብ፣ በእርዛትና በበሽታ እየተጎሣቆለ መኖር እድገት መባሉ አሳሳች ነው። ባለፉት 26 ዓመታት በረሀብና በልዩልዩ ሰውሠራሽ ምክንያቶች የቀነሰው እንኳ ሳይታሰብ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር ቢያንስ 20% ያደገ ሲሆን የሕዝብ ቁጥር ዕድገት ለልማት ጠቃሚ ሊሆን ሲገባ፤ የታየው ግን የሥራአጥ ቁጥር መጨመር ሆኖ ነው። እድገቱ ሚዛናዊና ከሕዝብ ፍላጎት ጋር የተጣጣመ አይደለም። ባጭሩ ሕዝቡ ራሱን በራሱ ስለማያስተዳድርና በራሱ ሀብት የመጠቀም መብት ስለሌለው የስታቲስቲክስ ቁጥር ከማሳየት በስተቀር ከድህነት ያወጣው አይደለም። በግርድፉ የሚቀርቡት የስታትስቲክስ መረጃዎች ትክክለኛውን ሁኔታ ስለማያመለክቱ የውጭውንም ዓለም አመለካከት የሚያሳስቱ ናቸው። ከሕዝብ የሚሰበሰበው ግብር እንኳ ለልማት መዋሉ እንቆቅልሽ ነው እንጂ እንደ ሕዝቡ ጥረት የአገሪቷ ልማታዊ እድገት እጅግ ከፍተኛ ይሆን ነበር። ሕዝቡ ነፃ ቢሆንና የራሱን ሀብት የማስተዳደር መብት ቢኖረው ኖሮ

 

አገራችን ሌሎች አገሮች ከደረሱበት የዕድገት ደረጃ መድረስ ትችል ነበር።

እንዲሁም አሮጌ “ጉልቻ” በዘመናዊ  “ጉልቻ” መቀየሩ የሚያስፈነድቃቸው እሉ፤ ድሮ ነጭ ለባሾች፣ ጭቃሹሞች፣ ምስለኔዎች፣ ባላባቶች፤  ቆሮዎች… ወዘተ የፊውዳል ሥርዓቶችን አጠናክረው ይዘው ሕዝቡን አፍነው ሲበዘብዙትና ሲያስጨቁኑት እንደነበረ ሁሉ ዛሬ ደግሞ ካድሬዎች፣ የድርጅት ሠራተኞች ወይም ሰላዮች፣ ወያኔ በአምሳሉ የፈጠራቸው የፖሊቲካ ድርጅቶች ከቀበሌ እስከ ክልል በመንግሥት መዋቅር ውስጥ አባሎቻቸውን ሰግስገው የሕዝቡን ጥሪት እየመጠጡ አዲሱን የጭቆና ሥርዓት በመጠበቅ ላይ ይገኛሉ። ሕዝቡ የራሱን ሕይወት መሥዋዕት በማድረግ አገሪቱን እንዳቆየ ሁሉ እነዚህን የውስጥ ጠላቶች ለይቶ ማወቅ ይኖርበታል። የለውጥ ዓላማ የሕዝብን መሠረታዊ ፍላጎቶች ዲሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቶች ማስከበር፣ እኩልነት፣ ሰላምና ብልጽግና እንዲገኝ ማድረግ ሲሆን፤ በንጹሕ አስተሳሰብ ላይ ያልተመራ ጥላቻ፤ የዘለቄታ ጠቃሚ ውጤት በማያስከትል ቂምበቀል ማሳደግ፣ በአብሮ መኖር ፋንታ የተለዩ በመሆን መራራቅና ቅራኔዎችን መፍጠር ለውጥ የሚመስላቸው ፖሊቲከኞች የአገራችንን ዕድገት ወደኋላ እየጎተቱ ይገኛሉ። ስለዓለም ዕድገት ባላቸው ዉሱን ዕውቀት አዳዲስ አምባገነኖችን ማወደስ የሚመስላቸው ግለሰቦች በሕዝቡ ውስጥ ያደረሱትና እያደረሱ ያሉት አሉታዊ ክስተቶች በቀላሉ ሊታረሙ የሚችሉ አይደሉም፤ ለምሳሌ ለብዙ ዘመናት በጡትና ብልት መቆረጥ ዘመናትን ያስቆጠረው ምን እንደሆነ እየታወቀ በዚህ ላይ ምንም የተወሰደ ቂምበቀልም ሆነ የጥላቻ ሐውልት ያልተሠራ መሆኑ የሕዝባችንን ከፍተኛ የመቻቻል ባህል ያመለክታል፤ በሌላ በኩል ምንሊክ የአርሲዎችን ጡት ቆርጠዋል በማለት የሻቢያ ቅጥረኛ በሆነው በተስፋዬ ገ/አብ በተጻፈ ድርሰት በተጨባጭ ባልተረጋገጠና በቀጣይነትም ተፈጽሞ በማይታወቅ ሁኔታ ሐውልት አሠርቶ ጥላቻን ለሕዝብ ማስተማር የመሠልጠን ሳይሆን ታሪክን ወዳኋላ መጎተት፣ ለፍትሕ መታገል ሳይሆን ጥላቻና ቂምበቀል እንዲስፋፋ ማድረግ ነው።

ዛሬም የ・ፈረንጅ-አምላኩ・እምነት ተማርን ከሚሉ ሰዎች አስተሳሰብ እንኳ አለመውጣቱ ያስደንቃል፤ ለምሳሌ ዶክተር ፍቅሬ ቶሎሳ የታሪክ መረጃዎችን በዋቢነት እያመለከቱ፣ ከታሪካችን ጋር ግንኙነት ከነበረው ጎረቤት አገር የተገኙ ተጨባጭ ሰነዶችን በተጨባጭ የሚታዩ የድሮ ካርታዎችን አስደግፈው እና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጻፉ መረጃዎችን በመውሰድ ስለኢትዮጵያ የጻፉትን በምሁራዊ አቀራረብ ለማወቅ የፈለጉ ግለሰቦች የመኖራቸውን ያህል፤ ማስረጃ እስደግፈው መተቸት ሲገባቸው በጭፍኑ በመቃወም ተገቢውን ዕውቅና ሊሰጧቸው ያልፈለጉ ምሁራን ታይተዋል፤ ያንን ጥናት አንድ የውጭ አገር ምሁር ቢያቀርበው ኖሮ ለትችትም አይዳፈሩም ነበር፡፡

 

ብሔር-ብሔረሰብን ከአገር ጋር ማምታታት:- አንድ ተራ ሰው አገርህ የት ነው ቢባል ሽዋ (ወይም መንዝ፣ ቡልጋ፣ ጅባት፣ ሰላሌ..ወዘተ)፣ ወለጋ (ወይም ደምቢዶሎ፣ ሆሮ፣ ግምቢ…ወዘተ)፣ ወሎ (ወይም ዋድላ፥ ላስታ፣ ሳይንት)፣ ጎንደር (ወይም ደባርቅ፣ ደምቢያ፣ መተማ…ወዘተ)፣ ባሌ (ወይም አጋርፋ፣ ዲንሾ፣ ጎሎልቻ)፣ ወይም በቀጥታ ብቸና፣ ደጀን፣ ፍቼ፣ መኢሶ፣ ጉርሱም፣ ሞያሌ፣ ጅማ፣ ሐረር… ሊል ይችላል፤ ኢትዮጵያ የምትባል ትልቅ አገር እንዳለችው ጠፍቶት ሳይሆን ከአንድ ኢትዮጵያዊ ጋር ሲነጋገር የሚገልጸው መለያው ነው። ቋንቋ ግን ያለምንም ድንበር ተናጋሪው በሄደበት ሁሉ አብሮት የሚከተለው እንጂ የራሱ ድንበር ኖሮት አያውቅም። ሆኖም በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በባህል ሕዝቦችን ነጥሎ በማየት አገር የመፍጠር ችግር አለ። በፀጉር አበጣጠር፣ አመጋገብ፣ አለባበስና በመሳሰሉት የአኗኗር ፈሊጦች ጥቃቅን ልዩነት ይኑረን እንጂ ኢትዮጵያውያን ከብዙ ምዕተዓመታት በፊት ጀምሮ በደም የተዋሀድን መሆናችንን ቆዳችን፣ ቅርጻችንና ባህርያችንም ይመሰክራል። ነገር ግን ትውልድ እየጨመረ ሲሄድ አዳዲስ ቋንቋዎች መፈጠራቸውና ከሌላው ዓለም የሚገቡ እምነቶች መጨመር የተለያየን አያደርገንም፤ ባገራችን መጤ ሕዝብ የለም፤ አፋር፣ ኦሮሞ፣ ሶማሊ፣ ሲዳማ፥ ትግሬ፣ አደሬ፣ …ወዘተ በቋንቋ፣ ሃይማኖት፣ በፀጉር አበጣጠር በአለባበስና በመሳሰሉት የአኗኗር ፈሊጦቻችንን ብዛትና ውበት የሳያሉ እንጂ የሚያራርቁን ነገሮች አይደሉም፤ ሆነውም አያውቁም። እንደ አንድ አገር ሕዝብ የተፈጥሮና ስው ሠራሽ የጋራ ችግሮችን የተካፈሉ፣ በጋራ ጠላቶቻቸው አብረው ሲጠቁ የኖሩ፣ የተጋቡ የተዛመዱ ናቸው፤ ወደፊትም ዕድላቸውን በጋራ ለማምጣት ተባብርው መታገል ያለባቸውና ሲበለፅጉም አብረው የሚያድጉ መሆናቸው ሳይታለም የተፈታ ነው። ሆኖም አንዳንዶቹን ለምሳሌም ኦሮሞዎችን እንደመጤ የማየት ስህተት  አለ። አዎን ኦሮሞ ኦርማ (የሌላ) የሚል ትርጉም አለው፤ በኢትዮጵያ ሥር ከነበረችው የአፍሪቃ ቀንድ በሣር ግጦሽ ከከብት አርብቶ አዳሪው ሶማሊ ኅብረተሰብ ጋር በየጊዜው ሲጋጩ ኖረው ግራኝ መሐመድ በነገሠባቸው ዘመናት በክርስትያን ወንድ ላይ ከፍተኛ እልቂት ስለተፈጸመና ከእልቂቱ ተርፎ እስልምናን ያልተቀበለው ወገን በአብዛኛው ወደሰሜንና ተራራማ ቦታዎች ሸሽቶ ስለሰፈረ፣ ከዚህ በኋላ ባሉት ዘመናት ማዕከላዊ መንግሥት ኃይሉ በመዳከሙ በየአካባቢውና በየመንደሩ የሚፈጸሙትን ግጭቶች የሚጠበቅበትን ያህል የፖሊሳዊ ሥራ በመሥራት መቆጣጠር ስላልቻለ በተፈጠረው ክፍተት የተነሣ በርቱማና ቦረና የተባሉ ቤተሰቦች ወደ መኻል አገር ፈልሰው መጀመሪያ በባሌ ከዚያም ወደሌሎች ክፍሎች ሰፍረዋል፤ እስካሁን ከዚህ ኅብረተሰብ ጋር የሚቀራረብ ነዋሪ በሰሜን ኬንያም ይገኛል፤ እነዚህ የሰፈሩ ወገኖች ራሳቸውን ኦሮሞ ብለው መሰየማቸው ይታወቃል፤  “ኦርማ” (ቀጥታ ትርጉሙ የሌላ)  የሚለውን ቃል በመመልከት ኦሮሞዎች ከሌላ አገር የመጡ የሚያሰኘው ትርጉም እንዳያሳስተን ከላይ አገርህ የት ነው ተብሎ አንድ ኢትዮጵያዊ ሲጠየቅ የሚሰጠው ምላሽ ተውልዶ ያደገበትን አካባቢ ሰላሌ፣ ጅባት፣ ፈዲስ፣ ጎሮ፣ ደጋሀቡር፣ ዋርዴር፣ በርበራ፣ ሞምባሳ… ወዘተ ብሎ ቢገልፅ  ከአንድ አገር ወደሌላ አገር ሄዶ ሰፈረ ማለት አይቻልም::  በዘመኑ ኦሮሞ ባይባሉም ከክርስቶስ ልደት 200 ዓመታት በፊት ጀምሮ የተለያዩ የኦሮሞ ነገሥታት የግዕዝ ቋንቋ እየተጠቀሙ ኢትዮጵያን ይገዙ እንደነበር የሚያሳይ ታሪክ ስላለ ይህ ሕዝብ ጥንታዊ ኢትዮጵያዊ ለመሆኑ አንድ ማስረጃ ነው።

 

የጁዎች ደግሞ ግዕዝና ኦሮምኛ እየተናገሩ ከጎንደር ኢትዮጵያን እንደገዙ ይታወቃል።

ሆኖም ከ16ኛው መቶ ክፍለ-ዘመን በፊት ጋላ እንጂ ኦሮሞ በሚል መጠሪያ የሚታወቅ ኅብረተሰብ በኢትዮጵያም ሆነ በሌላ አገር አልነበረም። ጋላ በሚል መጠሪያ የሚታወቅ ከብት አርቢ ኅብረተሰብ በአፍሪቃ ቀንድ ከዛሬው ኦጋዴን እስከ ዛሬዋ ታንዛኒያ ድረስ ይታወቅ ነበር። ከብት አርቢ ኅብረተሰብ ደግሞ የሣር ግጦሽ ወዳለበት ይዟዟራል እንጂ በአንድ ቦታ ረግቶ አይኖርም። ሆኖም እንቅስቃሴው ከአንድ የኢትዮጵያ ግዛት ወደሌላው የኢትዮጵያ ግዛት የተፈጸመ ስለነበረ ዝውውሩ በሀገር ውስጥ የተደረገ ዝውውር ነበር። እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት በተወሰኑ ዘመናት የአፍሪቃ ቀንድ ሶማሌን ጨምሮ በኢዮጵያ የበላይነት/ግዛት/ ሥር ነበር።  ኢትዮጵያ በየጊዜው በሚነሱ ኃያላን መንግሥታት እየተጠቃች ዳር ድንበሯን ማስከበርና እንደቀድሞ ግብር ማስከፈል ስላልቻለች በተለይም ኦቶማን ቱርክና ግብፅ በኋላም እንግሊዝ፣ ፈረንሳይና ኢጣሊያ ሡልጣን የሚባሉ የአካባቢ መሪዎችን እየደለሉ ውል በማስፈረም ዳርዳር ላይ ያሉትን አካባቢዎች በአብዛኛው ስለተቆጣጠሩ ከዚህ በኋላ ማዕከላዊ የኢትዮጵያ መንግሥት የጠረፍ ግዛቶችን የመቆጣጠር ኃይሉን በየዘመናቱ ካዳከሙ በኋላ በ1960 ዓም የኢትዮጵያ መንግሥት ሶማሊያ ራሷን የቻለች አገር እንድትሆን በተባበሩት መንግሥታት ሰነድ ላይ በፊርማዋ አረጋግጣ እንድትፈቅድ ተገዳለች።

እነዚህ ተዘዋውረው ወደመሀል አገር የገቡ ወገኖች በየሚሄዱባቸው አካባቢዎች የሚያጋጥማቸውን ግጭቶች ገዳ

በሚባል ሥርዓት እየተጠቀሙ መንደሮችን በመውረር ተቆጣጥረው ሰፍረዋል፤ የነዋሪዎችን ንብረት/ከብት ወርሰዋል፤ ከዚያም በኋላ ሞጋሳ፣ሚደቻና ጉዲፈቻ በሚባሉ የመመሳሰል የመሐላ ሥርዓቶች (assimilation proesses) ነዋሪዎች እንዲመሳሰሏቸው/እንዲዛመዱዋቸው/ አድርገዋል፣ ኦሮሞ ስለመሆናቸው በመሐላ ሥነሥርዓት ሲያረጋግጡ የወሰዱባቸውን ንብረት በከፊል በመመለስ በኦሮሞነት ተረጋግተው እንዲኖሩ አድርገዋል። ሆኖም በዘር ሳይሆን በይበልጥም በመመሳሰል ዘዴ ከሌላው ኅብረተሰብ ወደኦሮሞነት የተለወጡት ውስጥ የታቀፉት የአሁኖቹ በኦሮሞነት የሚታወቁ ምሁራን “ጋላ・የሚለውን ታሪካዊ ስም አማራ

የለጠፈባቸው ስድብ አድርገው ወስደውታል፤ አማራ ያወጣው ስም ቢሆን ኖሮ በአማርኛ ወይም በግዕዝ ・ጋላ・ትርጉም

ይኖረው ነበር:: ሆኖም በፈለገው ስም የመጠራት መብቱ የሕዝቡ ቢሆንም ጋላ ስማችን አልነበረም በማለትና ጥንታዊውን የኢትዮጵያ ታሪክ መስማት እንደማይፈልጉ ስለ”ጋላ” ም እስካሁን መመራመር ስላልፈለጉ የዚህ ሕዝብ ጥንታዊ ታሪክ እንዳይታወቅ መጋረጃ ፈጥረውበታል። ኦሮሞዎች ከመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ተቀላቅለው እየኖሩ እያለ አንዳንድ በስማቸው የተቋቋሙ አክራሪ የፖሊቲካ ድርጅቶች ሁሉንም ሕዝብ በእኩልነት በማየት ፋንታ በዘረኛው ወያኔ መሠሪ መረብ ተጠልፈውና በፈጠረው ተንኮል ተመርተው አገሪቷንም ክደው በኦሮሞነት ላይ የተመሠረተ አገር ለመፍጠር የሚያድርጉት ጥረት ከሌላው ኢትዮጵያዊ ወገናቸው መራራቅን አስከትሏል። በቋንቋችን እንናገር፣ እንጻፍ ማለት ያዳም ነው። ሆኖም ኢትዮጵያን የሚክዱት የኦሮሞ አክራሪዎች አያቶቻቸውና የቅድም አያቶቻቸው የተጠቀሙበትን ግዕዝ ንቀው የባዕዱን ላቲን ፊደል በመምረጥ ወገኖቻቸውን ብቻ ሳይሆን አፍሪቃዊነታቸውን ክደዋል፤ አባቶቻቸው በአጥንታቸውና በደማቸው ያቆዩዋትን ኢትዮጵያ ጠልተው ባዕድ ሳይባሉ ራሳቸውን ባዕድ የማድረጋቸውን እንድምታ ያመለክታል። ኢትዮጵያዊነትን ከፈጠሩት ውስጥ አንዱ የኦሮሞ ማህበረሰብ ነው፤ የኦሮሞ ደም የሌለበት ማህበረሰብ የለም፤ ያለኢትዮጵያ ኦሮሞ ያለኦሮሞ ኢትዮጵያ ትርጉም የለውም፡፡

አንድ ግለሰብ ወላጆቹን እንዳልመረጠ ሁሉ ሁላችንም ኢትዮጵይዊነትን ያገኘነው በምርጫ አይደለም፤ ነገር ግን

ስለተፈጠርንበትና ስለኖርንበት የኛ ነው፤ ወደፊትም ትውልዶቻችን ይኖሩበታል፡፡ በአገራችን የተለያዩ ማህበረሰቦች ከአንድ ወንዝ እየጠጡ፤ ተከባብረው በጉርብትናና በአንድ እድር እየተረዳዱ፣ በሥራ መስክ አብረው እየሠሩ፤ ሐዘንና ደስታቸውን በአንድ አዳራሽ ውስጥ ሲያከብሩ በመኖር አብሮነትን ተጠቅመውበታል፤ የብሔር-ብሔረሰብ ድንበር ሳይገድባቸው ተጋብተው ተዋህደዋል፤ ጠላቶቻቸውን በጋራ በመቋቋም ኢትዮጵያን አቆይተልናል፡፡ እነዚህ አኩሪ የጋራ እሴቶቻችን ናቸው። ሆኖም አወቅን ባዮች ፖሊቲከኞች በሕዝቡ መሠረታዊና የጋራ ችግሮችና ግቦች ላይ ከማተኮር ይልቅ ፀጉር እንደመሰንጠቅ በዘር ለሚደረገው የጠላት የከፋፍለህ ግዛ ዓላማ አስፈጻሚ ሆኑ። ይህ ለማንኛውም ወገን ዘላቂ ዓላማ ጎጂ ስለሆነ ኢትዮጵያውያን እንደወትሮው መተባበር ይኖርብናል።

በቅርቡ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ም/ፕሬዘዳንት ዶክተር አቢይ አህመድ እንደገለጹት የአማርኛን ቋንቋ በኦሮሞው ክልል የኦሮምኛንም ቋንቋ በአማራው ክልል ወጣቱ ኅብረተሰብ ቢማር ለመቀራረብ ያመቻል ብለዋል፤ አስተዋይነት ያለው ሐሳብ ነው። ታዲያ ሁለቱም ወገኖች በአንድ ፊደል ቢጠቀሙ ደግሞ የመቀራረቡን ኃይል እንደሚያበረታው አብሮ ቢታይ መልካም ነው።

የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት፦ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ማንኛውም አገር ወይም ግዛት (territory) በቅኝ መያዝ እንደሌለበትና ሕዝቡ በፍላጎቱ ከሚፈልገው አገር ጋር በሚመርጠው የአወቃቀር ሥልት መዋሀድ፣ አንድነት የመፍጠር፣ ወይም በውሳኔ-ሕዝብ ራሱን ችሎ መተዳደር መብት፣ እንዲሁም ብሔራዊ አንድነቱ (ሉዐላዊነቱ) ተጠብቆ ሊኖር እንደሚገባ  በአንቀጽ 1:2፣ 2:4 እና 2:8 ደንግጓል።

ከዚሁ ጎን ለጎን በ1917 ተጀምሮ ከ1990 ዓም ወዲህ እየደበዘዘ የመጣው የነቭላድሚር ኢሊች ነሌንና ጆሲፍ ስታሊን ኮሙኒስታዊ መርህ ( theory) እንደሚያመልክተው ብሔሮች ከጨቋኝ ጉልታዊ ወይም ከበርቴያዊ አገሮች ሥር ነፃ እንዲወጡ/እንዲገነጠሉ ይደግፍ ነበር። ዓላማውም አገሮች እስከነአካቴው ተገነጣጥለው እንዲቀሩ ሳይሆን በዓለም አቀፋዊ የላብ አደሮች አንድነት (proletarian internationalism) በመላው ዓለም የኮሙኒስት ሥርዓትን ለማስፋፋት ለሚደረግ ሂደት የታሰበ የትግል ሥልት ነበር። ሆኖም ይህ ንድፈ ሐሳብ እዚያው ፈጣሪዎቹ አገር ተቀብሮ የቀረ ሲሆን የሥልጣን ሱስ የተጠናወታቸው ብሔርተኞች ግን “ዓለም አቀፋዊ የላብ አደሮች አንድነት” የሚለውን አስተሳሰብ በመፋቅና “የብሔሮች… ነፃነት” የሚለውን ሐረግ በማስመር የመገንጠልን ዓላማ በአንዳንድ አገሮች እስከዛሬ ሲፈክሩበት ይታያል። ዓላማው ሥልጣንና በሥልጣን የሚገኝ በግል

 

ወይም ቡድን ጥቅሞች ላይ የተመሠረተ የስግብግብነት ራዕይ ሲሆን የማሳመኛ ነጥባቸው ከጭቆና ብሔራቸውን ነፃ ለማውጣት በሚል በግልባጩ ግን ቆመንላችኋል የሚሉትን ሕዝብ መገለል፤ ሁለተኛም ሌሎች ብሔሮችን የመጨቆን ጠባብ ዓላማ ያዘለ በመሆኑ ለሠለጠነው ዓለም ሕዝቦች ተፋቅረው እና በአንድ አገር ውስጥ እንደልባቸው ተዘዋውረው ሠርተው በመኖር ነፃነት ላይ ማዕቀብ የሚያስከትል ስለሆነ በተለይም በኢትዮጵያ መተጋገዝ ለሚያስፈልገው ለምጣኔ ሀብት እድገትም ሆነ ለዲሞክራሲ መበልፀግ እንቅፋት የሆነ ጠባብ አስተሳሰብ ነው። በመሠረቱ ኅብረት ከሌለ ለስግብግቦችም የሚሆን ነገር አይገኝም፤ የአገራችንን መልክአምድራዊና የተፈጥሮ ሀብቶች ለመጠቀም ሲሉ ውድቀቷን በጉጉት የሚጠባበቁ የውጭ ኃይሎች እንዳሉ የዋህ ፖሊቲከኞች ስላልተረዱት በጎጥ ጉዳይ ላይ የተኩራሉ፤ ምክንያቱም ሕዝቡ የሀብቱ ባለቤት የሚሆነው የአገር ኅልውናም በጋራ ሲጠበቅ ብቻ ነውና።

 

የማንኛውም ኅብረተሰብ መሠረት የሆነው የምጣኔ ሀብት እድገት የሚመጣው በመነጣጠል ሳይሆን በመተባበር ወይም በመቀላቀል ሲሆን የቋንቋ እና ባህል እድገትም የዚሁ ነፀብራቅ ነው። በቋንቋ፣ ሃይማኖትና በመሳሰሉት የሚፈጠር ክልላዊ ድንበር ግን ለእነዚህ ሁሉ እድገት እንቅፋት መሆኑ የተረጋገጠ ሲሆን በአገራችንም ይኸው እየታየ ነው። በዓለም ላይ (ኤርትራን፣ ኮንጎን፣ የመንን፣ የቦልካን አገሮችን እንደምሳሌ ማየት ይቻላል)። ሌሎች ከእናት አገራቸው ተገንጥለው የተፈጠሩ አገሮች አቅማቸውን በማሳነሳቸው የኢምፔሪያሊሶቶች ጥገኛ ከመሆን በስተቀር በአንድነት ሊገኙ ከሚችሉ ድሎች ሊደርሱ ስላልቻሉ የሕዝቦቻቸውን የኑሮ ደረጃ አላሻሻሉትም። እዚህ ላይ ተጨማሪ ምሳሌዎችን ማንሳት ለግንዛቤ ይመቻል፦ ዛሬ ካሉት ኃያላን መንግሥታት ተፎካካሪ ትሆን የነበረችውን ሕንድ በእንግሊዝ መሪነትና በኢምፔሪያሊስቶች መሠሪነት መጀመሪያ ፓኪስታን ቀጥሎም ባንግላዴሽ ተገንጥለው አገር እንዲሆኑ በማድረግ የታላቂቱን ሕንድ ተፎካካሪነት ሊገቱ ቻሉ። የሶቭየት ኅብረት መፈራረስ ለዩናይትድ ስቴትስ ዓለማቀፋዊ የበላይነት ትልቅ ዕድል ፈጥሮላታል፤ አንድ ሆና የነበረችውን የመን በማፈራርስ የጦር አውድማ አድርገዋታል፤ ደቡብና ሰሜን ኮርያ አንድ ሆነው ኃያል አገር እንዳይፈጥሩ ተከፋፍለው እንዲቆዩ ተደርገዋል። የአገሮች መገነጣጠል የጀርባ ሐቅ ራስን የማስቻል ጉዳይ ሳይሆን ዳካሞችና የምእራባውያን ጥገኞች እንዲሆኑ ነው፤ ነፃ አገር የመፍጠር አስተሳሰብ በኃያላን አገሮች ዘንድ በቅንነት ላይ የተመሠረተ ቢሆን ኖሮ ፍልስጤሞች ከ1948 ዓም ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ በገዛ አገራቸው ስደተኛ ሆነው አይቀሩም ነበር።

ወደአገራችን ስንመለስ እንግዲህ ጠንካራ ህብረብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ አገር ከመገንባትና የግል/የቡድን ሥልጣን

ከመመኘት አንዱን መምረጥ የፖሊቲከኞች ምርጫ ሲሆን፤ በሕዝቦች መሠረታዊ ፍላጎት ላይ ያልተመሠረተ ትግል የኋላ ኋላ ውጤት አልባ ነው የሚሆነው። ኢትዮጵያ የተለያዩ የአየር ንብረቶች፣ በጋራ በመጠቀም ከፍተኛ ጠቀሜታ የሚያስገኙ የተፈጥሮ ሀብቶች፣ ወንዞችና ሊሎች ተፋሰሶች እንዲሁም ለብዙ ዘመናት የጋራ አገራቸውን ጠብቀው የቆዩና በማህበራዊ ኑሮ የተሣሰሩ ማህበረሰቦች ያሉባት አገር በመሆኗ እነዚህ ማህበረሰቦች በአገር ሕዝብ እንድነት ዕድሎቻቸውን ከመጠበቅ ሌላ አማራጭ አያዋጣቸውም።

 

ስለ “ትምክህተኝነት” የተዛባ አመለካከት:- ማንኛውም ኅበረተሰብ በራሱ ባህል ይኮራል፤ በባህሉ እሴቶች ይመካል፤ የራሱን ማህበራዊ እሴቶች ከሌሎች ይመርጣል ወይም አስበልጦ ያያል፤ በመሆኑም ትምክህተኝነት መሠረቱ ኩራት ነው። ሁሉም ኅብረተሰብ የሚኮራበት ነገር ስላለው ሁሉም ኅብረተሰብ የትምክህተኝነት ጥንተነገር (element) አለው። ሆኖም አንዱ ወገን የሌላውን ወገን ኩራት በትምክህተኛነት በመመልከት ራሱን ዝቅ አድርጎ ማየት ካለ በራስ አለመተማመንን ማስፈን ይሆናል። ትምክህተኝነት ሌላውን መናቅም ሊሆን ይችላል፤ በጠባብ መነጽር ተጠቅሞ ሌላውን ዝቅ አድርጎ ሲያይ ይህ የትምክህተኛነት ጎጂ ገጽታው ነው። ስለሆነም ይህን በየኅብረተሰቡ ያለን ጎጂ አስተሳሰብ ማስተካከል የሚቻለው ማንኛውም ኅብረተሰብ የሚኮራበት ባህል፣ እምነት፣ ወዘተ እንዳለው በማመን፤ ራሱ መከበር እንደሚፈልግ ሁሉ የሌላውንም ማህበራዊ እሴቶች አክብሮ መኖር እንዳለበት ሰፋ አድርጎ የማየትን ባህል በማዳበር ነው። ሌላውን ወገን ከመናቅ ወይም ትምክህተኛ ከማለት ሌላው እንደሚኮራው ሁሉ እኔም ሆነ እኛ የምንኮራበት እሴት አለን ብሎ በራስ መተማመንንና በማዳበር በየጎረቤቱ ያሉ ማኅበረሰባዊ ልዩነቶችን በመቀበል ተከባብሮ መኖር የዓለም ሕግ ነው፡፡ ትምክህተኛነት አስተሳሰብ ነው፤ በመሆኑም በዘር ስለማይተላለፍ ኢትዮጵያውን እየተጋቡና እየተዋለዱ የጎሣ ድንበር ጥሰው እያለ የማህበራዊ ኑሮ ዕውቀት ወይም ልምድ የሌላቸው ሰዎች መሪዎች ሲሆኑ ማኅበራዊ/ባህላዊ/ አስተሳሰባቸው ጠባብ ስለሚሆን የተለያዩ ማኅበራዊ እሴቶችን በመቀበል ሕዝብን ያለአድልዎ ሊመሩት አይችሉም። ስለሆነም ሚዛናዊ በመሆን ፋንታ በአንድ ወገን ላይ ብቻ ያተኩራሉ፤ እኩልነትን በማራመድ ፋንታ ሕዝብን ከሕዝብ የሚያለያይን ነገር፣ ስለአንድነት ፋንታ ስለልዩነት፣ ስለፍቅር ፋንታ ጥላቻንና ቂምበቀልን ያራምዳሉ። አንድ ቦታ ላይ ተከባብሮ ለሰላም መቆም ከሌለ የቂምበቀልና ጥላቻ አዙሪት(cycle) መጨረሻ ስለማይኖረው በሕዝቦች መካከል የሚኖር አለመግባባት ያለማቋረጥ ይቀጥላል፤ ይህ የሚጠቅመው ለሕዝቡ የጋራ ጠላቶች ብቻ ሲሆን ለሕዝባችን እድገት ሳይሆን ዝንትዓለም በንትርክ እንዲኖር ማድረግ ነው፡፡

ወያኔን በመንግሥትነት የማየት ችግር፡– ሌላው ችግር ወያኔን መንግሥት አድርጎ የማየት ችግር ነው። አንድ መንግሥት አገርን በመምራት የሀገሩን ዳር ድንበር በማስጠበቅ፤ የሕግ የበላይነት እና ሰብአዊ መብቶች እንዲከበሩ በማድረግ፤ መሠረተልማቶችን፣ ማኅበራዊ አገልግሎቶችን በማሳድግና  ሕዝቡን በማገልገል የአገሪቱን መሠረታዊ ጥቅሞች የሚያስከብር፣ የምግብ ፍላጎቱ እንዲሟላና ጤናው እንዲጠበቅ፣ ሕዝቡን በማስተባብር ብሔራዊ አንድነትን ማጠናከር ሲገባው፤ ሕዝብን እየከፋፈለ፣ የሀገሪቱን መሠረታዊ ጥቅሞች አሳልፎ ለባዕድ እየሰጠና የሀገሩን ዳርድንበር ሆን ብሎ እያስደፈረ፤ ያወጣውን ሕግ ሥራ ላይ እንዳይውል ራሱ ተፅዕኖ የሚፈጥር፣ ሕዝብን ከሕዝብ በዘር ልዩነት የሚገድልና የሚያጋድል፤ ሕዝብን እርስ በርሱ ሆን ብሎ የሚያጋጭ፤ ይህን ሁሉ ሲፈጽም እንደወሮበላ እያታለለ

 

የሚሠራ አካል ፈጽሞ መንግሥት ሊባል አይችልም። ወያኔ ዕድሜ ልኩን ቅን ሆኖ አያውቅም፡፡ ዛሬ በመንግሥት ሥልጣን ላይ ራሱን ያስቀመጠው ወያኔ ሕዝብን በማገለግል ፋንታ በፈላጭ ቆራጭነት ሕዝቡን በሙሉ እሥረኛ ወይም ባሪያ አድርጎ ይኖራል፤ አገልጋይ በመሆን ፋንታ ሕዝቡን የሚገዛ የሚሽጥ የሚለውጥ ሆኖ የወራሪነት ሚና ይጫወታል። የሕዝብ ተወካይ ሳይሆን ወይም ሕዝብን ሳያገለግል ሕዝብን እያታለለ በፈላጭ ቆራጭነት በጫንቃው ላይ የሚኖረውን አካል የፖሊቲካ ድርጅቶች የመንግሥት ስያሜ ሰጥተውት ለአፓርታይድ አገዛዝ እንዲያመቸው ቀደም ሲል እንግሊዝና ኢጣሊያ ካዳደረጉት በባሰ ሁኔታ የፈጠረውን በዘር የተከፋፈለ የአገር መዋቅር ተቀብለውና ያንኑ መስመር ተከትለው በብሔር-ብሔረሰብ በመደራጅት ለሕዝቦች እኩልነት፣ ነፃነትና ፍትሕ መታጣት ከፍ ያለ ሚና ተጫውተውለታል። የአንድን ጎሣ ወይም ዘር ጥቅም ለማስጠበቅ ከሚደረግ ዓላማ የበለጠ አድልዎ (discrimination) የለም።      ተቃዋሚ የሚል ቅጽል ቢኖራቸውም አውቀውም ሆነ ሳያውቁ በወያኔ አሠራር የተቀረጹ ፖሊቲከኞችና የፖሊቲካ ድርጅቶች ከተፈጠረላቸው ጠባብ የብሔርተኝነት መስመር ውጭ አርቆ የማስተዋል አቅም ስለሌላቸው የፈጣሪያቸው አገልጋይ ከመሆን በስተቀር፤ እንቆማለን የሚሉት ለየራሳቸው ብሔረሰብ እስከሆነ ድረስ ፍትሐዊ፣ ዲሞክራሲያዊና የእኩልነት አራማጆች ሊሆኑ አይችሉም። “የኦሮሞ ልጆች”፣ “የአማራ ልጆች”፣ “የሶማሌ ልጆች”፣ “የትግሬ ልጆች”… ወዘተ በሚል ሕዝብን ከሕዝብ መለያየትና አምባገነንን በሌላ አምባገነን የመቀየር ሕልም ያፈጀ ያረጀ የበሰበሰና ወንዝ የማያሻግር አስተሳሰብ ነው። እውነትን መቀበል የሚቸገሩ ዲሞክራሲን/የሕዝብን ድምፅ በጣም ይፈሩታል፤ ምክንያቱም ትክክለኛ ዲሞክራሲ በማንም የበላይነት ፋንታ የሕዝብን የበላይነት መተካት ስለሆነ ነው፤ ዲሞክራሲን የሚፈራ ደግሞ ሥልጣን በአቋራጭ ለማግኘት የሚቅበዘበዝ ብቻ ነው። ሆኖም በዘር፣ ጎሣ ወይም በብሔረሰብ ተካሎ የተመሠረተ ድርጅት ከመሠረቱ ወገናዊ (sectarian) ሆኖ የተቋቋመ ስለሆነ ሁሉንም ሕዝብ በእኩልነት እንዲያይ የተመሠረተ ስለማይሆን ሕዝባዊ፤ ዲሞክራሲያዊ፣ ወይም ፍትሓዊ ሊሆን አይችልም፤ ወገንተኛ ወይም አድሏዊ መሆኑ እርግጥ ነው። ስለሆነም በዚህ መሠረት የተቋቋሙት ድርጅቶች እንኳን የሌሎችን ልዩነቶች በማቀፍ ሕዝቦችን ሊመሩ ቀርቶ ከጎረቤቶቻቸው ጋር ያለጠብና ጥላቻ መኖር የሚፈልጉትን የራሳቸውንም ማኅበረሰብ ማሳመን ስለማይችሉ ሕዝብን አስተባብረው ለድል ሊያሰልፉ አይችሉም።

ሕዝቦችን የማያማክሉ የስም ተቃዋሚ ፖሊቲካ ድርጅቶች :– ከነዚህ ከመቶ በላይ የተቆጠሩ ድርጅቶች ብዙዎቹ ለስሙ የተንቀሳቀሱና የሚንቀሳቀሱ ሲሆን አንዳንዶቹም በአገር ውስጥ ጽሕፈት ቤት ከፍተውና በጣት የሚቆጠሩ አባላትን ይዘው ተመዝግበው አሉ፡፡ ኅልውናቸው አንድም ወደፊት ለውጥ የሚመጣ ቢሆን ዕድሜያቸውን በማስቆጠርና ነበርን በማለት በተስፈኛነት የመኖር ራዕይ ሲሆን፤ ሁለተኛም ሕዝቡን አስተባብረው በገዢው አካል ላይ ምንም ተጽዕኖ ማምጣት የማይችሉ ስለሆነ፤ ገዢው ወገንም በነፃ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚዎች አሉ በማሰኘት ለሚፈጸመው የፕሮፓጋንዳ ፍጆታ የሚያገለግሉት ስለሆነ ይፈልጋቸዋል።

ከላይ በተጠቃቀሱት ውስጥ ከፍተኛ ልጓም ሆኖ የሕዝቦቻችንን ፍትሐዊ ለውጥ ወደኋላ ከሚጎትቱት ውስጥ ራስወዳድነት ከፍተኛውን ሚና ይጫወታል። ለሕዝቦች እውነተኛ እኩልነት፣ ዲሞክራሲ፣ ፍትሕ፣ ብልጽግና እና ሰላም የቆሙ የፖሊቲካ መሪዎች ቢኖሩ ኖሮ ከነዚህ መሠረታዊ ነገሮች የሚበልጥ ነገር እንደሌለ ተገንዝበውና ሌሎች ልዩነቶቻቸውን ወደጎን ትተው ግላዊ ፍሎጎቶችን መስዋዕት በማድረግ ለአንድ አገራዊ ዓላማ ተገዝተው በጽናት ቆመው ለድል በበቁ ነበር። ለነዚህ መርሆች በቅን የቆሙ ጥቂት መሪዎች ቢኖሩም መርሆቹን ለፖሊቲካ ፍጆታ መጠቀሚያ በሚያደርጉና ቅንነት በሌላቸው ሌሎች መሪዎች ስለሚዋጡ፣ ድርጅቶቻቸውም በዲሞክራሲያዊ አመራር ስለማይመሩና ከሌሎች ለኢትዮጵያ ሕዝብ በቅንነት ከሚቆሙ ዲሞክራሲያዊ ድርጅቶች ጋር ተባብረው ወይም ኅብረተሰቡን አስተባብረው ለአንድ ዓላማ ሊያሰልፉ አልቻሉም። ዲሞክራሲያዊ አመራርን ባለመከተላቸው በመካከላቸው አለመግባባት ሲፈጠር መፍታት ስለማይችሉ፤ ወይም አንዳንድ መሪዎቻቸው በተለያዩ ምክንያቶች ከድርጅት ሲለዩ የድርጅታቸውም ህልውና አብሮ ጥያቄ ውስጥ እየገባ በተደጋጋሚ ታይቷል፤ ከዚህ ጋር በተያያዘ በየጊዜው የድርጅት መሰንጠቅና አዳዲስ ድርጅቶች መከፈት ተከሥቷል። ለጋራ ሕዝባዊ ዓላማ ድርጅቶቻቸውን ከማዋኻድ ይልቅ ግለኝነትን ያሰፍናሉ፤ ይህ የሚሆንበት ምክንያት ጠንካራ መስለው የሚታዩ መሪዎች እንጂ፤ የግል ፍላጎታቸውን መስዋዕት በማድረግ ለሕዝባዊ ዓላማ ጽናት ባላቸው መሪዎች የሚመራ በሕዝባዊ መሠረት የታነፀና በዲሞክራሲያዊ አሠራር የተጠናከረ ድርጅት መፍጠር ስላልቻሉ ነው። እንዲዚህ ያሉ መሪዎች ደግሞ የማያስፈልግ መታመንን (personality cult) ስለሚያካብቱ በመሪነት ላይ ቢቆዩ እንኳ ይህ አካሄድ ወደአምባገነንነት ያስኬዳቸዋል እንጂ ድርጅታቸውን ጠንካራ አያደርገውም፤ ተደርጎም አልታየም።

በአንፃሩ ለጋራ ዓላማ የጋራ አስተሳሰብ የመፍጠርና በጋራ እያሰቡ በጋራ የመታገል ልምድ በየጊዜውም ተከሥቶ

ሳይደረጅ ከስሞ ታይቷል። ይህ እንግዲህ ለሀገር ጉዳይ ለሕዝብ ዓላማዎች በቅንነትና ጽናት ሁሉን-አቀፍ ጠንካራ ድርጅት የማበልፀግ ችግር ነው። የሕዝቦችን ልዩነቶች ማማከል የሚችለው ሕዝባዊ ዲሞክራሲ ብቻ ነው፣ ለሕዝቦች የጋራ ዓላማ ብርታት ከህብረታቸው የተሻለ እንደሌለ የታመነበት ሲሆን ያሉትን ተጨባጭ ክስተቶች ስናይ ግን ለሥልጣን የሚሮጡ ግለሰቦችም ሆኑ ብሔርተኞች ቡድኖች ዲሞክራሲን ይፈሩታል፤ ምክንያቱም ሥልጣን በሰፊው ሕዝብ ድምፅ ስለሚወሰን ነው። ሆኖም በአገር ደረጃ የሕዝቡ ልዕልና ካልተጠበቀ እና አገር ጤና ካልሆነ የግልም ሆነ የቡድን ምኞት ሁሉ ከንቱ ስለሆነ የአገርን ጉዳይ ከምንም በላይ የማያስቀደም የፖሊቲካ ድርጅት ባይኖር ይመረጣል።

 

ተተኪ ሥርዓትን ስለማዘጋጀት፦ ከላይ እንደተገለጸው በአገራችን ጉዳይ የሚንቀሳቀሱት ድርጅቶች የየራሳቸው ባህርይ ያለባቸው ሲሆን፣ ስለአገር ጉዳይ ቀና አመለካከት ያላቸው ደግሞ አንድነት ወይም ጥምረት ፈጥረው በቅድመ-ወያኔና በድህረ-ወያኔ ላይ የጋራ ፕሮጀክት አለመፍጠራቸው አሳሳቢ ጉዳዮች ናቸው። ምክንያቱም ማፍረስ ምኞት የመሆኑን ያህል ለመተካት/ለመገንባት ቅድመዝግጅት ከሌለ የሕዝቦችን የወደፊት ጥሩ ራዕይ — ሰላም፣ ኅብረት፣ ፍትሕና

 

ብልፅግና ለማምጣት ያስቸግራል። ሕዝቦችን የሚያቀራርብ የሰከነ ሰላማዊ ግንኙነት ራዕይ ከሌለ ስለብልፅግና ማሰብም አይቻልም። ለኢትዮጵያ ሕዝብ ቆመናል የሚሉ የፖሊቲካ ድርጅቶች ግልፅ በሆነው የጋራ ችግር ላይ አንድነት በመፍጠር በመሬት ላይ የሚታይ የኅብረት እንቅስቃሴ ካላሳዩ፤ ・የማያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል・እንዲሉ ሕዝቦቻችን ልዩነቶቻቸውን በማቻቻል በዲሞክራሲያዊ አመራር ለፍትሕ፣ ሰላምና ብልፅግና ተስፋ የሚያድርጉበት ያጣሉ። ዲሞክራሲ ግትርነት አይደለም፤ ዲሞክራሲ መነጣጥል አይደለም፤ ዲምክራሲ ሰጥቶ መቀበል ነው፤ ዲሞክራሲ ለጋራ ዓላማ መገዛት ነው፤ ትልቁ የዲሞክራሲ ባህርይ በጋራ ፍትሐዊ መርህ ተመርቶና ልዩነቶችን አቻችሎ በልዩነቶች ውስጥ በመኖር ሕዝቦችን እያሰተባበሩ ከሕዝቦች ተውጣጥቶ አገርን በጋራ ለሚመራ ሕዝባዊ ድርጅት ልባዊ እገዛ ማድረግ ነው። ልዩነቶች ለዲሞክራሲ መሠረት ናቸው፤ ምክንያቱም ያለልዩነት ዲሞክራሲ ትርጉም አይኖረውም። በሕዝባዊ ዲሞክራሲ ተመርቶ ለአገር የማይቆም ድርጅት ለሕዝቦቻችን ትግሎች እንቅፋት ስለሚሆን ባይኖር ይመረጣል። ዛሬ ግልፅ በሆነው የአገር ችግር ላይ ለጋራ ሕዝባዊ አመራር ተገዥነትን ያላሳዩ ድርጅቶች ነገ እንዴት አገርን የመምራት ብቃት ይኖራቸዋል ብሎ ሕዝብ እምነት ሊጥልባቸው ይችላል? “የባሰ አታምጣ・የሚለው መንፈስ ለወያኔዎች ማገልገሉን ይመለከቷል! ይህ ብቻ አይደለም፤ እንዲህ ያለ ኃይል  ልዩነቶችን አቻችሎ ሕዝቦችን ሲያስተባብር በተግባር ካልታየ ሌላው የዓለም ኅብረተሰብም  በተፎካካሪነት/ተቃዋሚነት እንኳ ለማን ዕውቅና ለመስጠት እንደሚችል ይቸገራል።

ቀደም ሲል “ኢሕአዴግ”ን እንደ ጥምር (coalition) የፖሊቲካ ድርጅትና በፀረሽበርተኛነት ያዩት የነበሩት ኃያላን መንግሥታት ዛሬ በጨቋኝነት ያለና በሕዝባዊ አመጽ እየተንቀጠቀጠ መሆኑን በአደባባይ እየተናገሩ ሲሆን ሕዝቡን የሚወክል ተቃዋሚ ኃይል በዳሰሳ እየፈለጉ ነው፤ በልዩነት ውስጥ ሕዝብን አስተባብሮ መምራት የሚችል አካል ነው እውቅና ማግኘት የሚችለው፤ የውጭውንም ዓለም የሚቸግረው ይኸው ነው።

“ሁሉ ቃልቻ …ማን ይሸከም ስልቻ?

ይህችን አገር አንዱ ሊያጠፋት ሲገዘግዛት ሌላው ደግሞ ሊያኖራት ይሞትላታል። የሚገዘግዟትና የሚሞቱላት ሚናቸውን ለይተዋል። ሌላው ወገን ደግሞ በየቤቱ ስለፍትሕ መጓደል ይብገነገናል፤ የተመቸው ክትፎ እየበላና አልኮል እየተጎነጨ በውጭ ሬዲዮ የሚሰማውን ወይም በዲሽ ቴሌቪዝን የሕዝብ ሰቆቃ እያየ ከንፈሩን ከመጠጠ በኋላ ተጫማሪ አልኮል በመጠጣት ንዴቱን ለማስወገድ ይሞክራል፤ በቃ አገር ወዳድነቱ እንግዲህ በዚህ ተገለጸ ማለት ነው። በወንድሞቹና እህቶቹ ላይ የሚደርሰው ሰቆቃ፤ በአገር ላይ የደረሰው ከውጭ ጠላት የባሰው ወረራና የባርነት ኑሮ፤ በቋንቋ፣ ዘርና ኅይማኖት ተከፋፍላ የምትተረማመሰው ኢትዮጵያ ወዴት እንደምትሄድ ግራ የገባውና በወጣነትነቱ እና በአፍላ ዕድሜው ራሱን ለውጦ ለወገኑ ተስፋ መሆን እንዳለበት የሚያልመው ኢትዮጵያዊ እና ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት አካሄድ ከጭለማ በስተቀር ብሩህ ተስፋ የማታሳየው ወጣት ደግሞ ለለውጥ የተዘጋጀ ሲሆን ያዙኝ ልቀቁኝ በማለት በሕዝባዊ ትዕይንት ንዴቱን ለመወጣት ይሞክራል፤ በእስር ቤት ያሉ ወንድሞቹንና እህቶቹን እያሰበ የሚመጣውንም መስዋዕትነት ይቀበላል፤ ማድረግ የሚችለው ይህን ብቻ ስለሆነ እጅና እግሩን ተጠቅሞ ማድረግ የሚገባውን ሁሉ የማድረግ ዕድል ስለሌለው አዝኖ በማግሥቱም ያንኑ ሐዘን እየደጋገም ያዝናል። ሌላው ወገን በየዕለቱ የሚወጡትን የአገር ውስጥና የውጭ ጋዜጦች፣ መጽሔቶች በማገላበጥ ሲያነብ ሲያነብንብ፤ አሉ የተባሉትን የተቃዋሚ ሬዲዎ ዜናዎችን እንዲሁም ድረገጾችን በመዳሰስ አዳዲስ ዜናዎችን ሁሉ በመቅሰም ምንም ሳያመልጠው ክትትል ያደርጋል፤ አንድ ሰው የተለየ ዜና ሰምቶ እሱ ግን ካልሰማ ባለማወቁ ይናደዳል፤ ሁሉንም ዜናዎች ተከታትሎ ተከታትሎ ከተረዳ በኋላ የዜና ትንታኔ ያቀርባል፤ ይፈላሰፋል፤ ሲደክመው ይተኛል፤ የየዕለቱ አገር ወዳድነት በዚሁ ያበቃል፤ በነገውም ያንኑ ይደግማል;። ሌሎች ሌሎች ገጸባህራያትም አሉ፤ ለዚህ ገለጻ እነዚህ ምሳሌዎች ይበቃሉ። ወሬ መከታተል አይከፋም፤ አብዛኛዎቻችን ግን ወሬ በመስማትና በማቀባበላችን ብቻ በአገራችን ላይ መልካም ለውጥ እንዲመጣ እንመኛለን፤ ያወቀም መልካም የተመኘም መልካም ነው፤ ነገር ግን ሰምተን፣ አይትንና አውቀን ሳንሠራ ሌሎች ሠርተውልን መልካም ውጤት ማየት እንፈልጋለን፤ የስህተቱ ሁሉ ስህተት ይህ ነው። ጥቁር አሜሪካዊው

የሰብአዊ መብት ተከራካሪ ጆን ሊዊስ ሲናገሩ እንዲህ ብለዋል፤ ・የምታምንበትን ነገር ሌላ ሰው እንዲሠራልህ አትጠብቅ፤ እራስህ የምትችለውን አድርግ ። በነገሥታቱ ዘመን ・…የዶሮ ያህል እንኳ  ደሙ ያልፈሰሰ (ላገሩ) ዘለዓለም ይኖራል ልቡ እየነደደ・ይባል ነበር። ዛሬ ዛሬ ግን ሥራችን ወሬ ማፍሰስ ሆኗል። ታዲያ ሁሉ・ቃልቻ ማን ይቆፍር ማን ያርም ማን ይሸከም ስልቻ?።”

 

ከላይ የተገለፁት በአብዛኛው ራሳችን የፈጠርናቸው ችግሮች ለውጥ እንዳናመጣ ልጓም ሆነው አንቀው ይዘውናል። ላለፈው ክረምት ቤት አይሠራም፤ የፈሰሰ ወተትም አይታፈስም፤ ያለፈውን ታሪክ የምናየው የድሮውን እንደገና ለመተግበር ሳይሆን ካለፉት ጥፋቶችና ስህተቶች ለመማርና ዛሬ በምናደርገው መልካም ነገር ለኅብረተሰባችን የተሻለ ሕይወት አስተዋፅዖ ለማድረግ ነው። ስለዚህ አስተሳሰባችንን ከለወጥን ልጓሙን ፈተን ራሳችንን ነፃ ማውጣት እንችላለን። ያለፈውን መጥፎም ሆነ ደግ ታሪክ በትምህርትነት በፀጋ ወስደን ዛሬ በምናደርገው አንድነት ሰው-ሠራሽና የተፈጥሮ ጠላቶቻችንን እንደምናሸንፍ የታመነ ነው፤ የኸው አንድነታችን ደግሞ ወደፊት ዲሞክራሲንና ብልፅግናን ለመገንባት ያስችለናል። በአንድነታችን በአገራችን ያለውን ጨቋኝ ሥርዓት አስወግደን ዲሞክራሲን መገንባት እንችላለን፤ በአንድነታችን ኢምፔሪያሊስቶችን ተቋቁመን የአገራችንን ልማት ማሳደግ እንችላለን፤ በአንድነታችን ሕዝባችንን አንድ ቤተሰብ አድርገን ፍቅርና ሰላም  ማሳደግ እንችላለን፤  “በአንድ ድንጋይ ሦስት ወፍ!”። “Gratitude makes sense of our past, brings peace  for  today,  and creates a vision for tomorrow.”                               (Melody Beattie)

[gview file=”http://etzena.com/amharic/wp-content/uploads/2018/01/በአንድ-ድንጋይ-ሦስት-ወፍ.pdf”]

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.