ርጥቡ ሬሳ ደረቅ ያስነሳ፤ [ይገረም አለሙ]

pp002ዛሬ ጥቅምት አንድ ቀን 2009 ዓም ቀትር ላይ በሞት የተለዩንን ኢ/ር ኃይሉን ወደ ዘለዓለማዊው ቤት ለመሸኘት አዲስ አበባ አራት ኪሎ ከሚገኘው ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ቤተ ክርስቲያን ተገኝተናል፡፡ እዛው የተገናኘን ሰዎች ዝናቡ መቆሚያ ቢያሳጥንም አንድ ጥግ ይዘን አስክሬናቸው እስኪደርስ ወግ ይዘናል፡፡ ኢ/ር ኃይሉን ለመጀመሪያ ግዜ ያወቅናቸው በመአህድ ከዚያም በመኢአድ ቀጥሎም በቅንጅት እንደገና ተመልሶ በመኢአድ በመሆኑ ከዚህ እውቀታችን በመነሳት ከፊት ወደ ኋላ እያስታወስን ስናነሳ ስንጥል የመአህድ መስራችና ፕሬዝዳንት የነበሩትንና በእስር ተሰቃይተው በግፍ የሞቱትን ፕ/ር ዓሥራት ወልደየስን አስታወስን፡፡ የገደሉንንም የሞቱልንንም እኩል የምንረሳ ምን ጉዶችን በማለትም ራሳችንን ወቀስን፡፡

ለኢ/ር ኃይሉ አስክሬን ማረፊያ የተዘጋጀው የቅድስት ስላሴ ቤተ ክርስቲያን መካነ መቃብር ርጥቡ ሬሳ ደረቅ ያስነሳ እንዲሉ ሆኖ 18 አመት ወደ ኋላ  አስጉዞ የአስራት አስክሬን በዚህ ቦታ እንዳያርፍ መደረጉን አስታወሰን፡፡  ክፋቱ ገደብ፣ የበቀል ስሜቱ ርካታ የለሽ የሆነው ወያኔ ገድሎ ባለመርካት የቀብር ቦታ መከልከሉ አረመኔነቱን የሚያሳይ ቢሆንም ምን ያህሎቻችን ነን ይህን እምናስታውስ ብለን ራሳችንን ጠየቅን፡፡ ከቀብር ፍጻሜ በኋላም ወረድ ብለን ባለወልድ የሚገኘውን የአሥራት የቀብር ቦታ አየን፡፡ ሀይሉን ልንቀብር ሄደን አስራትን አስታውሰን ይበልጥ አዝነን ራሳችንን ወቅሰንና የመኢአድ ሰዎችን ታዝበን ተመለስን፡፡ ለምን ብትሉ እነርሱም አንደማንኛውም ሰው አስራትን በመርሳታቸው፡፡

የወያኔው አብዮት በፈጠረው የፖለቲካ ስካር ሀገሬ ወገኔ ብሎ በኢትዮጵያ ሁሉ ተበትኖ በሚኖረው አማራ ላይ በአንዳንድ ቦታዎች የተፈጸመበት ጥቃት ነበር እውቁን ቀዳጅ ሀኪም በህክምና የተያያዙትን ነፍስ አዳኝነት ወደ በፖለቲካ ትግል ህይወት ታዳጊነት ለመለወጥ አስገድዶ የመአህድ ፕሬዝዳንት ለመሆን ያበቃቸው፡፡ መዐህድም በአጭር ግዜ ገነነ፡፡

hailu-shawe

የከፍተኛ ትምህርት ተቋምን በመወከል በሰኔው ኮንፈረንስ ላይ ተገኝተው ይህ ጉባኤ በኤርትራ ጉዳይ የመወሰን ሥልጣን የለውም ብለው የተቃወሙና ድምጸ ተአቅቦ ያደረጉ ብቸኛ ሰው በመሆናቸው በወያኔ ተጋዳላዮች አይን የገቡት አሥራት በሳቸው ፕሬዝዳንትነት የመአህድ ባልተጠበቀ ፍጥነት ጎልቶ መውጣት ጥርስ አስነከሰባቸው፡፡

ትናንትን እየረሱ በእለት በእለቱ በመጮህ በሽታ የተለከፍን በመሆናችን እንጂ ወያኔ ማንነቱንም ምንነቱንም በፕ/ር ዓስራት ላይ በፈጸመው ህገ ወጥና ኢሰብአዊ ድርጊት አሳይቶን ነበር፡፡ ከዛ በኋላ በፖለቲከኞችም ሆነ በጋዜጠኞች ላይ የተፈጸመው ሁሉም በዓሥራት ላይ የደረሰ ነው፡፡

በደብረ ብርሀን በተጠራ ሰብሰባ ላይ ካደረጉት ንግግር አንድ አረፍተ ነገር ተመዞ ህዝብን ለአመጽ የማነሳሳት ንግግር አደረጉ ተብሎ ተከሰሱ፣ይሄ ጉድ ሲባል ከጎጃም ከመጡ ገበሬዎች ጋር በጽ/ቤታቸው አመጽ ስለማስነሳት መክረዋል የሚል ክስ ተጨመረ፡፡ በየፖሊስ ጣቢያው እየተጠሩ በዋስ ሲመለሱ ቆይተው 86 መጨረሻ ግድም ዳግም ላይመለሱ ወህኒ ወረዱ፡፡የሀሰት ምስክር አሰልጥኖና አስፈራርቶ ማስመስከር፣ በትእዛዝ የሚፈርዱ ዳኞችን መድቦ ማስፈረድ፣ ጠያቂን ማንገላታት ሲላቸውም መከልከል የመሳሰሉት እስከ ዛሬም የሚጮኽባቸው ህገ ወጥና ኢሰብአዊ ድርቶች ሁሉ በዓሥራት ላይ ተፈጽመዋል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም የስንቱን ህይወት የታደጉ ሰው ህክምና ተከልክለው በሽታቸው ከተባባሰ በኋላ ለይስሙላ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል እንዲተኙ ተደርጎ መጨረሻም የማይድኑበት ደረጃ መድረሳቸው ሲረጋገጥ እጃችን ላይ ከሚሞቱ ተብሎ አሜሪካን ሀገር ተልከው ብዙም ሳይቆዩ ነበር አስክሬናቸው የተመለሰው፡፡

በወቅቱ ርሳቸውም በከፍተኛ የጤና መታወክ ላይ የነበሩትና ብዙም ሳይቆዩ የተከተሉዋቸው ሎሬት ጸጋየ ገብረ መድህን አሜሪካን ሀገር በተካሄደው የአስክሬን ሽኝት ላይ በድጋፍ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር በሽታህ ምን አንደሆነ አንኳን ሳይታወቅ ተለየኸን በማለት አንደገለጹት አስራት በእስር ቤት ተሰቃይተው ህክምና ተነፍገው መሞታቸው ብቻ ሳይሆን ለሞት ያበቃቸው በሽታ ምንነት እንኳን አለመታወቁ የሚቆጭ የሚያንገበግብ ነበር፡፡ ቁጭት መንገብገባችን ከአንድ ሳምንት አላለፈም እንጂ፡፡

ድርጅታቸው መአህድ በሀሰት ክስ የታሰሩት መሪያችን ይፈቱ ማለት ቀርቶ ህክምና ያግኙ ብሎ የሰላማዊ ሰለፍ ጥሪ አለማድረጉ ከሞቱም በኋላ በሽታቸው አልታወቀም እየተባለ የአስክሬን ምርመር አንዲደረግ አለመጠየቁ ይህ ሁሉ ቀርቶ ወያኔ ሊያዝበት በማይገባው ቅድስት ስላሴ ቤተክርስቲያን አስክሬናቸው እንዳያርፍ ሲከለክል ለምን ብሎ አለመከራከሩ ባሰቡት ቁጥር ልብ የሚያደማ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ወጣቶች ግን ቀብራቸውን በደማቸው ጭምር አደመቁት፣ በሆታና በመፈክር ሸኑዋቸው ሁለት ወጣቶችም ተከተሉዋቸው፡፡ ለሚገጥመው ተቃውሞ ሁሉ ምላሹ ጥይት በሆነው ወያኔ ከቀብር መልስ ፓርላማው ጀርባ በር ላይ ነበር ሁለት ወጣቶች በጥይት የተመቱትና አንዱ ወዲያው ሲሞት ሁለተኛው ሆስፒታል ደርሶ ያረፈው፡፡ የወቅቱ የመኢአድ መሪዎች ግን ይህን የወያኔን ድርጊት ለማውገዝና የወጣቶቹን መስዋዕትነት ለማድነቅ ወይ ድፍረቱ ወይንም ፍላጎቱ አልነበራቸውም፡፡

ወያኔ በበቀል የአስክሬን ማረፊያ ቢከለክላቸው፣ ድርጅታቸው በእስር ለመሳሰቃየታቸውም ሆነ በግፍ ለመገደላቸው ትኩረት ባይሰጠው፤ እኛም እስከ እስር ቤት አጨብጭበን እስከ ቀብር አልቅሰን ሸኝተን ብንረሳቸውም  ለሀገራቸውና ለወገናቸው የከፈሉትን መስዋዕትነት ልናስንሰውም ሆነ ልናኮስሰው አንችልም፡፡  እኛ ለመስዋእትነታቸው ክብር ሰጥተን ባናስታውሳቸው ለውለታቸው ባለ አደራ ሆነን ባንገኝ ነገ ታሪካቸውን እያወሳ የሚዘክራቸው አርአያነታቸውን እያደነቀ የሚከተላቸው ትውልድ ሊመጣ ይችላል፡፡ መጥኔ ለእኛ እንጂ የሚገድሉንንም የሚሞቱልንም እኩል  ለምንረሳው፡፡

የኢ/ር ኃይሉንም የፕ/ር ኣስራትንም ነብስ ይማር፡

14712830_1119110381508317_896864865168607641_o

14589605_1119110648174957_4851018302031621787_o

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.