ህዝብ የሚተማመንበት ፓርቲ እስካልተፈጠረ ድረስ ለውጥ አይመጣም:: (አብርሃ ደስታ)

• ሰላማዊ ትግል ትክክለኛው መንገድ ነው የሚል አቋም አለኝ
• “ኢህአዴግ በሰላማዊ ትግል አይወርድም” የሚል ሃሳብ ስላለ ነው ሰዎች ተስፋ የሚቆርጡት
• ህዝብ የሚተማመንበት ፓርቲ እስካልተፈጠረ ድረስ ለውጥ አይመጣም

አብርሃ ደስታ
አብርሃ ደስታ

በሽብር ተከሰው በፍ/ቤት ነፃ ከተባሉ በኋላ ይግባኝ የተጠየቀባቸው የአረና ፓርቲ አመራር አቶብርሃ ደስታ ከሁለት አመት የማረሚያ ቤት ቆይታ በኋላ ከሰሞኑ ከእስር ተለቀዋል፡፡
አቶ አብርሃ ለ8 ዓመታት በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ በስነ ዜጋና ስነ ምግባር እንዲሁም በፖለቲካ
ሳይንስና ስትራቴጂክ ስተዲስ የትምህርት ዘርፎች ያስተማሩ ሲሆን በታሰሩ ወቅትም የፒኤችዲ ጥናታቸውን እየሰሩ ነበር፡፡ የፖለቲካል ሳይንስ ምሩቁ አቶ አብርሃ፤ወደ ፖለቲካ ትግል እንዴት እንደገቡና በፖለቲካአስተሳሰባቸው ዙሪያ፣ እንዲሁም ስለ እስር ቤት ቆይታቸው ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ተከታዩን ቃለምልልስ አድርገዋል፡፡

እንዴት ነው ወደ ተቃውሞ ፖለቲካ  የገቡት?
ያጠናሁት ፖለቲካል ሳይንስ ነው፡፡ በእርግጥ አሁን ያለሁበት አቋም ከትምህርቱ የመጣ አይደለም። አንዳንድ ችግሮችን ሳይ እቃወማለሁ፡፡ ኢ-ፍትሃዊ የሆኑ ነገሮችን ሳይ ከድሮውም እቃወም ነበር፡፡ ከሃይስኩል ጀምሮ ነው ይሄን ጥያቄ አነሣ የነበረው። ከፍተኛ ትምህርት ስማርም የበለጠ የህውሓት ኢህአዴግን ክፍተቶች ማየት ጀመርኩ፡፡ መስተካከል ያለበትን ነገር እንዲያስተካክሉ መናገር ደግሞ ይጠበቅብናል፡፡ ይሄን ስል የነሱን ሃሳብ ተቃወምኩ ማለት ነው፡፡ አስተካክሉ የተባሉትን ሳያስተካክሉ ሲቀሩ፣እነዚህ ሰዎች የህዝብ ድምፅ መስማት አይፈልጉም ወደሚል ድምዳሜ ይኬዳል። ከዚያ እነሱ ካልሰሙ ምንድን ነው መፍትሄው የሚለው ይመጣል፡፡  ሀገሪቱ በዚህ መንገድ ብትሄድ ይበጃል የሚለውን የራሴን ሃሳብ መያዝ ጀመርኩ።  በዚህ መንገድ ነው ወደ ተቃውሞ ፖለቲካ የመጣሁት፡፡
የተቃውሞ ፖለቲካ በአብዛኛው ከደርግ ውድቀት በኋላ በትግራይ የማይሞከር ነው፤“ህዝቡና ህውሓት የተሳሰሩ ናቸው”—የሚሉ አንዳንድ ፖለቲከኞች አሉ፡፡ እርስዎ በዚህ አመለካከት ላይ ያለዎት አስተያየት ምንድን ነው?
ህዝብና ፓርቲ አንድ አይደለም፡፡ ይሄ አመለካከት ትክክል አይደለም፡፡ የትግራይ ህዝብና ህውሓት አንድ አይደሉም፡፡ ህዝብ ሊደግፍ ይችላል ግን አንድ ናቸው ማለት አይደለም፡፡ በነገራችን ላይ በስልጣን ላይ ያሉት ወገኖች፤“የትግራይ ህዝብና ህውሓት አንድ ናቸው” የሚሉት፣ተቃዋሚዎች በክልሉ ቦታ እንዳይኖራቸው ለማስፈራራት ነው፣ ለፕሮፓጋንዳ ጥቅም ነው፡፡ ህዝብ የሚፈልገው ፍትህ፣ ዲሞክራሲ፣ ነፃነትና ልማት ነው፡፡ ይሄን ያጣ የትኛውም ህዝብ መቃወሙ አይቀርም፡፡ የትግራይ ህዝብ እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በደልና ግፍ ስለሚደርስበት ይቃወማል፡፡ ምናልባት በማህበራዊ ሚዲያዎች የኔ ተቃውሞ ጎልቶ ወጥቶ ይሆናል እንጂ በክልሉ ብዙ ወጣቶች ያለውን ስርአት አጥብቀው ይቃወማሉ፡፡ በክልሉ አፈናው ጠንከር ስለሚል ተቃውሞውም ብዙ መስዋዕነትነት የሚያስከፍል ነው፡፡ ህውሓት እውነቱን ለመናገር ከበፊትም ጀምሮ ለትግራይ ህዝብ የቆመ አይደለም፡፡ በህውሓት ህዝቡ ከፍተኛ በደል ደርሶበታል፤እየደረሰበትም ነው፡፡ ይህ የህወሐት አፈና በክልሉ ፍርሃት እንዲነግስም አድርጓል፡፡
ዲሞክራሲን እንዴት ነው ማስፈን የሚቻለው ብለው ያስባሉ?
ህዝብን በማስተማር ነው ዲሞክራሲን ማምጣት የሚቻለው፡፡ ህዝብን ከአፋኝ ሥርዓት ነፃ ማውጣት ብቻውን ዲሞክራሲን ማስፈን ማለት አይደለም፡፡ ዲሞክራሲ በተከታታይ በሚሰጥ ትምህርት የህዝብ ንቃተ ህሊናን ማዳበር ይጠይቃል፡፡ ዲሞክራሲን በአዋጅ ማስፈን አይቻልም፡፡ ህዝብ መብቱን እንዲያስከብር መደራጀት አለበት፡፡ ለውጥ የመጣው በህዝቡ የተደራጀ አቅም እንደመሆኑ ስልጣንም መምጣት ያለበት በህዝቡ የተደራጀ እንቅስቃሴ ነው፡፡ በህዝብ የመጣ ስልጣን ዲሞክራሲን ሊያሰፍን ይችላል፡፡ ምክንያቱም ስልጣኑን የሰጠው ህዝብ ስለሆነ መልሶ ሊቀበለው እንደሚችል ያውቃል። በጠመንጃ ከመጣ ግን አስቸጋሪ ነው፡፡ ህዝብን ከአንድ ጭቆና  በጠመንጃ ነፃ ያወጣ አካል፣ዲሞክራሲ ያሰፍናል ብሎ ለመናገርም አያስደፍርም፡፡ ጠመንጃ ስርአት መቀየር ይችላል፤ነገር ግን ስልጣኑን ለህዝብ መስጠት ካልቻለ ከባለ ጠመንጃው ስልጣን ሊሸጋገር የሚችልበት አማራጭ ጠመንጃ እንዲሆን ሊያስገድድ ይችላል፡፡ በኛ ሀገር ስልጣን በህዝብ ይሁንታ አግኝቶ፣ በስጋት የሚኖር መንግስት መፈጠር ነበረበት፡፡ ካልሰራ እንደሚባረር አውቆ የሚተጋ፣ የህዝብን መብት አክብሮ የሚያስከብር መንግስት መምጣት ነበረበት፡፡ ለዚህ ነው እኔም ሆንኩ የትግል ጓዶቼ ስልጣን መምጣት ያለበት በሰላማዊ የህዝብ ትግል ነው ብለን የምንከራከረው፡፡ ህውሓት-ኢህአዴግ ከመጀመሪያውኑ ደርግን እንዳስወገዱ በሰላማዊ መንገድ ለህዝብ ስልጣን ቢሰጡ ኖሮ፣ የዲሞክራሲያዊ ሂደቱን ያፋጥኑት ነበር፡፡ በአብዛኛው የህዝብን የትግል ሂደት የሚወስነው በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ነው፡፡ ደርግ ጨቋኝና መድብለ ፓርቲ ሥርዓትን የማይፈቅድ ስለነበር፣ታጣቂ ነፃ አውጪዎች እንዲፈጠሩ አድርጓል፡፡
አሁን ላይ ያለው የተቃውሞ እንቅስቃሴ የተደራጀ አይደለም፣ለውጥ የማምጣት አቅም የለውም የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ እርስዎ ምን ይላሉ?
ሰላማዊ ትግል ትክክለኛው መንገድ ነው የሚል አቋም አለኝ፡፡ ግን ቀላል አይሆንም፡፡ ብዙ ውጣ ውረድ ይኖረዋል፡፡ አሁን እያየን ያለነው ውጣ ውረዱን ነው፡፡ አንዴ ከፍ ይላል ሌላ ጊዜ ይቀዘቅዛል፡፡ ተስፋ መቁረጥም ሊመጣ ይችላል። ይሄ የሚሆነው የተደራጀ ኃይል ስለሌለ ነው፡፡ በህዝቡ በኩል የለውጥ ፍላጎቱ አለ፤ ግን ኢህአዴግ በሰላማዊ ትግል አይወርድም የሚል ሃሳብ ስላለ ነው ሰዎች ተስፋ የሚቆርጡት፡፡ ተቃዋሚዎች በዚህ በኩል ብዙ የቤት ስራ አለብን፡፡ ህዝቡን እያደራጀን ወደ ትክክለኛ የትግል መንገድ እየመራን ስንሄድ ነው፣ሰላማዊ ትግል ውጤት አምጥቶ ዲሞክራሲን መገንባት የምንችለው፡፡ ሰው የመጨረሻ አማራጩ ሰላማዊ ትግል መሆኑ ገብቶት ተስፋ መቁረጥ ትቶ እስከ መጨረሻው እንዲታገል ማድረግ የፖለቲከኞች ስራ ነው የሚሆነው፡፡ ህዝቡ ተስፋ እንዳይቆርጥ ማድረግና ወደ ትክክለኛ ትግል ማምጣት ከፖለቲከኞች ይጠበቃል፡፡
በዚህ መንገድ ከህዝብ ጋር የተቀራረበ ተቃዋሚ አለ ብለው ያስባሉ?
ከምርጫ በኋላ ሁሌ በተቃዋሚዎች በኩል ተስፋ የመቁረጥና የመፍረክረክ ነገር አለ፡፡ ይሄ ተስፋ መቁረጥ ወደ ሌላ የትግል ስልትም ሊያመራ ይችላል፡፡ ወሳኙ ህዝብን የማደራጀት ጉዳይ ነው፡፡ ህዝብን ማደራጀት ከተቻለ ተስፋ መቁረጡ አይኖርም፡፡ ህዝብ ሲደራጅ ለውጥ ይኖረዋል፡፡ አሁን ገና ነው፤ህዝብ የማደረጃት ስራ አልተሰራም፡፡ የሰላማዊ ትግል ግብ ከምርጫ ጋር መያያዝም የለበትም፡፡ ያለ ጠመንጃ የሚደረግ ትግል ስለሆነ የማሸነፍና የመሸነፍ ጉዳይ አይሆንም፡፡ ሰላማዊ ትግል የዓላማ ፅናት ነው፡፡ ስለዚህ ሰው ስለተገደለ፣ ስለታሰረ የሚቆም አይደለም፡፡ ኢህአዴግ እንደፈለገ ስራውን ይሰራል፤ እኛ ደግሞ በፅናት ህዝቡን እያደራጀን— አላማችን ነፃ ለማውጣት እስከሆነ ድረስ በዚያ መስመር መፅናት አለበት፡፡ በሂደት ህዝቡን ስለ ዲሞክራሲ እያስተማርን ማደራጀት አለብን፡፡ ይሄን እያደረጉ ያሉ ፖለቲከኞች አሉ የሚል ድምዳሜ ላይ ባልደርስም ቢኖሩ በጣም ጥሩ ነው። ህዝቡን ያደራጃሉ፤ ለለውጥ ያነሳሳሉ፡፡ ባይኖሩም በቀጣይ መፍጠር፣ ብቅ ያሉትን እያበረታታን ከህዝቡም መልምለን ማውጣት አለብን፡፡ በዚህ ሂደት ለአላማቸው የፀኑ ጀግና መሪዎችን መፍጠር እንችላለን፡፡
በመሃል ሀገር የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ብዙዎቹ ከአረና በስተቀር በትግራይ ክልል   ሲንቀሳቀሱ አይታይም፡፡ ለምን ይመስልዎታል?
“የትግራይ ህዝብና ህውሓት አንድ ናቸው” የሚለው አመለካከት በራሱ ተፅዕኖ አለው፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ስለ ትግራይ ህዝብ የሚሰጣቸው መረጃ የተሳሳተ ነው፡፡ እዚህ መሃል ሀገር ከባለስልጣናት ጋር ተባብረው የሚዘርፉ ግለሰቦችን ስለሚያዩና እነዚህ ግለሰቦች ሲጠቀሙ የትግራይ ህዝብ ተጠቃሚ ሆኗል ብለው ስለሚደመድሙ፣ ከኛ ጋር ሊሰለፍ አይችልም የሚል የተሳሳተ ግምት ይመስለኛል—-እንቅስቃሴያቸውን የገደበው፡፡ ይሄ የትግራይን ህዝብ አለማወቅ ነው፡፡ የትግራይ ህዝብ በደርግ ሲበደል በትጥቅ ትግሉ ተሳትፏል፡፡ ከዚህ በመነሳት የህውሓትን አገዛዝ የሚፈልግ የሚመስለውም ይኖራል፡፡ የትግራይ ህዝብ ግን ደርግን ስለጠላ እንጂ ህውሓትን ስለደገፈ አይደለም፡፡ ህውሓት ትግሉን አደራጀው እንጂ ህዝቡ ደርግን አስቀድሞ ሲቃወም ነበር፡፡ ያለው እውነታ ህውሓት በትግራይ ህዝብ ልብ ውስጥ እንደሌለ ነው፡፡ ተቃዋሚዎች ወደዚያ አለመንቀሳቀሳቸው ክፍተት ፈጥሯል፡፡ እኔ እንደ መፍትሄ ሁሉም ፓርቲዎች ተዋህደው አንድ ጠንካራ ሃገራዊ ፓርቲ መመስረት አለባቸው እላለሁ፡፡ በዚህ መንገድ ትግራይን ጨምሮ ወደ ሁሉም አካባቢዎች መድረስ ይቻላል፡፡
እርስዎ የሚሉትን አንድነት ለማምጣት ያልተቻለበት ምክንያት ምንድን ነው?
የኢህአዴግ ስትራቴጂ አጥፍቶ መጥፋት ነው። እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል እንደሚለው ተረቱ፣ሀገራዊ አስተሳሰብ ያላቸውን ሰዎች ወደ ማጥፋት ነው የሚሄደው፡፡ ስለዚህ ክፍተት አለ። የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ውሕደት ለመፈፀም ያልቻሉት ስለ ግላቸው ስለሚያስቡ ነው፡፡ ሃገርን ሳይሆን ሠውን ነው የሚያዩት፡፡ ከዚህ ጋር አልሠራም ይላሉ፡፡ ሃገራዊ ፓርቲ ያለመፈጠር  ችግር ለዚህ ነው የኖረው፡፡ አንድ ፓርቲ መሠረቱ መሆን ያለበት  አንድ ግለሠብ ሣይሆን ሃሳብ ነው፡፡ ከሃገር አንፃር ያለው አላማ ነው መሠረቱ መሆን ያለበት፡፡ ስለ አንድ ሃገር ነው ሁሌም ማሠብ ያለብን፡፡ ፓርቲ ስለመሠረትን ስልጣን እንይዛለን ማለት አይደለም፡፡ ህዝብ የሚታማመንበት ፓርቲ እስካልተፈጠረ ድረስ ለውጥ አይመጣም፡፡ ስለዚህ በሂደት ፓርቲዎችን ወደ አንድ በማምጣት፣ሃገራዊ ፓርቲ በመመሥረት ለህዝቡ ተስፋ መሆን አለብን፡፡ ይሄ ሲሆን የህዝብን አመኔታ አግኝተን አላማችንን ማሳካት እንችላለን፡፡ ስለዚህ ዋና ክፍተት ያለው አንድነት መፍጠሩ ላይ ነው፡፡
ወደታሰሩበት ጉዳይ እንምጣና —- በምን አጋጣሚ ነበር በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት?
ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ቢሮዬ ወጥቼ ሻይ ለመጠጣት ወደ ከተማ ስወርድ፣ ብቻዬን በነበርኩበት  ጊዜ ነው ተከታትለው የያዙኝ፡፡ ልክ በፊልም እንደምናየው መንገዴን በመኪና ዘጉት፡፡ ከዚያም ፖሊሶች መጥተው ያዙኝና ወደ መኪናው ግባ አሉኝ፡፡ አልገባም ብዬ ተከራከርኩ፡፡ ግን ያው ገፈታትረው የተሸፈነ መኪና ውስጥ አስገቡኝና ወደ ከተማው ፖሊስ ኮሚሽን ወሰዱኝ፡፡ ቤቴን ሲፈትሹ ውለው “ባዶ ስድስት” ወደሚባለው እስር ቤት አስገቡኝ፡፡ ሌሊት መጥተው ወደ አዲስ አበባ ማዕከላዊ ጉዞ ጀመርን፡፡ ሌሊቱንና ቀኑን ተጉዘን ማታ 3 ሠዓት ማዕከላዊ አስገቡኝ፡፡
ማዕከላዊን እንዴት አገኙት?
እኔ ስለ ማዕከላዊ ስሰማቸው የነበሩ ነገሮች አሉ፡፡ እነሱን እንደጠበኳቸው ስላገኘኋቸው አልደነቀኝም፡፡ ድብደባ የመሣሠሉትን ማለቴ ነው። ግን ያልጠበቅሁት የታሠርኩበት ቦታ  ነው፡፡ በጣም ቅዝቃዜ ያለው ጨለማ ክፍል ነበር ያስገቡኝ። በወቅቱ በተቀመጥኩበት መነሣት እስኪያቅተኝ ታምሜ ነበር፡፡ ለ3 ወር ያህልም ህክምና ተከልክዬ ነበር፡፡ ለእኔ በቦታው ነው ቶርቸር የተፈፀመብኝ፡፡ ጆሮዬም ተመቶ ታሞ ነበር፡፡
ማዕከላዊ ሳለሁ ሳይቤሪያ በሚባለው ቦታ ቆይቻለሁ፡፡ ሃኪሞች ጠዋት ጠዋት እየመጡ ይመክሩኝ ነበር፡፡ ጭንቅላትህን ወደ ግድግዳው አታስጠጋ ይሉኝ ነበር፡፡ እነዚህ ሃኪሞች ማከም እንደማይፈቅድላቸው ይነግሩኝ ነበር፡፡ ግድግዳው ውሃ ነገር ነው የሚያመነጨው፡፡ እዚያ ውስጥ ደግሞ 8 ቁጥር የሚባል አለ፡፡ 24 ሰዓት ይዘጋብሃል፡፡ 2 ደቂቃ ብቻ ነው መውጣት የሚፈቀደው፡፡ ቦታው ለኔ በጣም ከባድ ነበር፡፡
ከሁሉም የእስር ቦታዎች የተሻለው የትኛው ነው?
ከማዕከላዊ ቃሊቲ የተሻለ ነው፡፡ ቂሊንጦ መሄድ ልክ እንደመፈታት ነው፡፡
በቁጥጥር ስር የዋሉበት ምክንያት በወቅቱ ተነግርዎት ነበር?
ምንም  አልተነገረኝም፡፡ ፍ/ቤት  ክሴ ሲነበብልኝ ነው የሰማሁት፡፡ ከዚያ በፊት ምንም የሰማሁት ነገር አልነበረም፡፡ ስለ ደሚህትም የሠማሁት እዛው ፍ/ቤት ነበር፡፡ እኔ በዚህ አልተደናገጥኩም ነበር። የታሠርንበት አላማ ያው ምርጫውን ለማሳለፍ ነው፡፡ ምርጫው አልፏል፡፡ እንግዲህ በነገራችን ላይ ጭቆና እስካለ ድረስ ትግል ይኖራል፡፡ አፈና እስካለ ድረስ ትግል አይቆምም፡፡ ትግል የነጻነት መፈለግ ጥያቄ ነው፤ ነፃነት የመፈለግ ጉዳይ ደግሞ በአፈና ስለሚወለድ አፈና አያቆመውም፡፡ አፈና አቁመው፤ ዲሞክራሲና ነፃነትን ለህዝቡ ይስጡት፡፡
በፖለቲካ ትግሉ ይቀጥላሉ ወይስ —- ሃሳብዎ ምንድን ነው?
በእኔ በኩል የተቀየረ ነገር የለም፡፡ ምርጫውን ለማሳለፍ ሲሉ ለ2 ዓመት በእስር ቤት አቆዩን፡፡ የኛ ስትራቴጂ ደግሞ ስንፈታም ስንታሰርም እንታገላለን የሚል ነው፡፡ ስለዚህ አሁን ዋናው ትኩረት ህዝብን ማደራጀት ነው ሊሆን የሚገባው፡፡
የኢህአዴግን ችግሮች ህዝቡ በደንብ ያውቃል፤ ለውጥም ይፈልጋል፡፡ ለለውጡ ደግሞ ህዝቡ መደራጀት አለበት፡፡ ፓርቲዎችም ወደ አንድ ውህድ ፓርቲ እንዲመጡ ጠንክረን እንሰራለን፡፡ በዚህ መንገድ መጪዋ ኢትዮጵያ ምን መሆን እንዳለባት ገምግመን፣ አቅጣጫ እናስቀምጣለን የሚል እምነት አለን፡፡
የህዝቡን የነፃነት ፍላጎት ለማሳካት እንሰራለን፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.