56.68 F
Washington DC
April 21, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

ገደሉ ሜዳ ሆነ፤ ምድረበዳውም በደን ተሸፈነ፡፡

ገደሉ ሜዳ ሆነ፤ ምድረበዳውም በደን ተሸፈነ፡፡

ባሕር ዳር: የካቲት 28/2013 ዓ.ም (አብመድ) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ለዘመናት የዳበረ የአረንጓዴ አሻራ ልማት ልምድ አላት፡፡ ከጥንቱ የኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ጠብቆ በማቆየት፣ በሥነ ሕንፃ፣ በሥነ ጥበብ፣ በታሪክ ስነዳ፣ በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በልዩ ልዩ ዘርፎችም ፋና ወጊ የልማት አብነት ነች፡፡ በዚህ ዘመንም የሃይማኖት አባቶች በሀገራዊ የልማት ሥራዎች ምሳሌ የሚሆን ሥራ እየሠሩ ነው፡፡

ለዚህም በጭንጫ ላይ ደን የለማበት፣ ገደሉ ተደልድሎ ሜዳማ ቦታ የተገኘበት የደብረ ከርቤ ዳግማዊ ጎለጎታ ማዕዶተ ቅድስት አርሴማ አንድነት ገዳም ሁነኛ ማሳያ ነው፡፡ ገዳሙ ከደብረ ብርሃን ከተማ በሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ በሰባት ኪሎሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ አባ ገብረኪዳን ገብረማርያም የተባሉ አባት ናቸው በሚደንቅ ጥበብ ከአለት የፈለፈሉት፡፡

እሳቸው በ1986 ዓ.ም ዓለትን በምሳር ፈልፍለው አምስት ቤተ መቅደሶችን እና 50 ልዩልዩ ዋሻዎችን በአጠቃላይ 55 ዋሻዎችን ለአገልግሎት አበቁ፤ ገደሉን ደልድለው ምድረበዳው በደን እንዲሸፈን አደረጉ፡፡ በወቅቱ ደቀ መዝሙራቸው የነበሩና አሁን ገዳሙን እያስተዳደሩት ያሚገኙት አባ ተክለዮሐንስ ገብረወልድም ዋሻው ሲፈለፈል፣ ገደሉን ወደ ሜዳ ለመቀየር ጥረት ሲደረግ፣ ምድረበዳውም በአጸድ ሲለማ አብረው ሠርተዋል፡፡ አካባቢውን ቀድሞ ለሚያውቀው እንደዚያ ተለውጦ በአረንጓዴ ልማት ደምቆ መመልከት ያስደንቃል፡፡

የገዳሙን ቦታ በአጸዱ ብቻ መለየት ይቻላል፡፡ በምድረበዳነት የሚታወቀው አካባቢው አሁን የጥንካሬና የጽናት ውጤት በተግባር የታየበት እንዲሁም በአባቶች ጥረት ተስፋ የለመለመበት ሆኗል፡፡ አባ ተክለዮሐንስ ገብረወልድ ገደሉን ሜዳ በማድረግ በጭንጫ ላይ ያውም ውኃ በሌለበት እንዴት ማልማት እንደተቻለ አብራርተዋል፡፡ ገደሉን እንዴት ሜዳ ማድረግ ተቻለ? አባ ተክለዮሐንስ እንዳሉት ገዳሙ የተመሠረተው በገደል ላይ ነው፡፡ ገደል የነበረውን ቦታ ከብዙ ድካም በኋላ ሜዳማ ቦታዎች እንዲኖሩት ተደርጓል፡፡

ሜዳማ ቦታ እንዲኖሩት በማድረግ ሂደቱ 12 ደረጃ ያላቸው እርከኖች ተሠርተውለታል፡፡ የእያንዳንዳቸው እርከን ስፋት ደግሞ ሁለት ሜትር ነው፡፡ ሁለት ሜትር ስፋት ያለውን ሜዳማ ቦታ ለማግኘትም እስከ ስድስት ሜትር ከፍታ ያላቸው ካቦች ተሠርተዋል፡፡ በዚህም ቀጥ ካለ ገደል ላይ ሜዳነት ያለው ቦታ ማግኘት ተችሏል፤ ለአጸድ ልማት በሚመች መልኩም ተዘጋጅቷል፡፡

ጭንጫ ላይ እንዴት ማልማት ተቻለ? ገደሉን ወደ ሜዳነት ለመቀየር ዓለቱ ሲፈለፈል የሚወጣውን ኮረት ለእርከን፤ ደቃቁን አፈር ደግሞ ለመደልደያ ተጠቅመውበታል፡፡ ከዚያም በውስን አፈር ድንጋያማ ቦታ ላይ መልማት የሚችልና የአካባቢውን የአፈር ለምነት የሚጨምር ተክል እንዲለማ ተደርጓል፡፡ አበምኔቱ እንደገለጹት የልማት ሥራው የተጀመረው ከበርሃ ቦታ በለስ (ቁልቋል) በማምጣት ነው፡፡ ከዚያም እንደ እሬት፣ ከስከሶና የመሳሰሉ ትናንሽ ቁጥቋጦዎች ተተከሉ፡፡ በሂደት ትላልቅ ዛፎች የለሙ ሲሆን በዚህ ወቅት ትላልቅ ዛፎችን በስፋት ማልማት ተችሏል፡፡

በአሁኑ ወቅት አትክልትና ፍራፍሬ፣ የዛፍ ዝርያም ለምቶበታል፡፡ አቮካዶ፣ ካዝሚር፣ ዘይቱናና ሌሎች የፍራፍሬ ዝርያዎች እንዲሁም የዛፍ አይነቶችም እንዲለሙ ብዙ ጥረት ተደርጓል፡፡ ምን ትምህርት ይወሰድበት? በመንግሥት ትኩረት የተሰጠውን የአረንጓዴ ልማት ቤተክርስቲያን የጀመረችው ቀድማ ነው፡፡

ቤተ መቅደስ ታንጾ በሚተርፍ ቦታ ላይ አጸድ የማልማት የዳበረ ልምድ አላት፡፡ እንደ ገዳሙ አስተዳዳሪ ማብራሪያ ቢቻል እስከ 80 በመቶ ካልተቻለ ደግሞ ከ50 በመቶ በላይ የሚሆነው የቤተ ክርስቲያን ትርፍ ቦታ በደን እንዲሸፈን ይሠራል፤ ተገቢው እንክብካቤም ይደረጋል፡፡ ገዳሙ በደን የተሸፈነው በቀላሉ አይደለም፤ በከፍተኛ ድካም አፈርና ውኃ በትከሻ ተግዞ እንጂ፡፡ አድካሚው ትጋትና ጽናትም መና አልቀረም፤ ይልቁንም ውጤቱ ያማረ ሆኗል፡፡ ይህም የአካባቢውን ስነ-ምሕዳር ከማሻሻል አልፎ ለገዳሙ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ማስገኘት ጀምሯል፡፡

ገዳሙ በሠራው የአካባቢ ጥበቃና የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራ በክልል እና በፌዴራል ደረጃ አንደኛ በመውጣት ተሸላሚ መሆን ችሏል፡፡ የማይለማ መስሎ የሚታይ ቦታ በአረንጓዴ ተሸፍኖ ቢታይም ቅሉ ለም አፈር ያለባቸው፣ ዓመቱን ሙሉ የወንዝ ውኃ የሚፈስባቸው አካባቢዎች ምድረ በዳ ሆነው ይታያሉ፡፡

ቤተ ክርስቲያን ልማትን ብታስተምርም የትኩረት ማነስና በባለቤትነት የመሥራት ችግሮች መኖራቸውን አንስተዋል፡፡ በመሆኑም አባቶች ከበርሃ አትክልት አቅርበው ገደል ደልድለው ማልማታቸውን እንደ ትልቅ አብነት ወስዶ መተግበር እንደሚገባ መክረዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

Source link

Related posts

በቲቢ በሽታ የመያዝ መጠንን በ90 በመቶና የመሞት መጠንን በ95 በመቶ ለመቀነስ አቅዶ እየሠራ መሆኑን የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ገለጸ፡፡

admin

በቻይና በትምህርት ላይ ከሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ጋር በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት ተካሄደ

admin

“ከዚህ በኋላ ህወሓት ማለት በነፋስ የተበተነ ዱቄት ነው” ጠ/ሚ/ር ዐቢይ

admin