78.37 F
Washington DC
June 17, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

“ያልተዘመረላቸው ኢትዮጵያዊ ሌተናል ጀነራል” | አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን
“ያልተዘመረላቸው ኢትዮጵያዊ ሌተናል ጀነራል”
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 27/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜኑ ክፍል የጠላት ጣሊያን ጦር ኢትዮጵያን በድጋሜ ለመውረር ባደረገው
ሙከራ ከሀገሪቱ ከሁሉም አቅጣጫዎች ሀገራቸውን ላለማስደፈር በጀግንነት የተዋደቁ በርካታ አርበኞች ይጠቀሳሉ፡፡ ከእነዚህ
አርበኞች መካከል ሌተናል ጀነራል ደጅአዝማች ኀይሉ ከበደ አንዱ ናቸው፡፡
የጠላት ጦር ይመቸኛል ባለው የሰሜን የሀገሪቱ ክፍል ተነስቶ ወደ መሀል ሀገር ለመገስገስ ባደረገው ጥረት የጠላትን ጦር
ለመመከት የመጀመሪያዎቹ ተሳታፊ የሆኑት የሰሜን አካባቢ አርበኞች ነበሩ፡፡ በተለይ የዋግ አካባቢ አርበኞች በግንባር ቀደምትነት
የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ሀገሪቱን ለመውረር የጣሊያን ጦር በተንቀሳቀሰበት ወቅት አዲስ አበባ ላይ የጠላትን እንቅስቃሴ ለመግታት
የክተት አዋጅ በታወጀበት ጊዜ የዋግ አካባቢ አርበኞች ይህንን የሀገር አደራ ለመወጣት ጨርቄን ማቄን ሳይሉ ሁሉም በአንድነት
ተመሙ፡፡ ይህን በወኔ እና በሀገር ፍቅር የተሞላ ጦር የመሩት ደግሞ አርበኛ ሌተናል ጀነራል ደጅአዝማች ኀይሉ ነበሩ፡፡
በተንቤን፣ አቢአዲ እና ማይጨው በኩል የመጣውን የጣሊያን ጦር ለመመከት የጦር ብልኃታቸውን ያሳዩት አርበኛ ሌተናል
ጀነራል ደጅአዝማች ኀይሉ ድል ቢቀናቸውም የጠላት ጦር የመርዝ ጋዝ በመጠቀም ያገኙትን ድል ቀልብሶባቸዋል፡፡
የታሪክ ምሁር አያሌው ሲሳይ (ዶክተር) እንደነገሩን የጠላት ጦር የዋግ አካባቢን እንዳይቆጣጠር ለማድረግ ከንጉሥ ግርማዊ
ቀዳማዊ ኀይለሥላሴ ጋር በመነጋገር የአርበኝነት ሥራን ይሠሩ ነበር፡፡ የጣሊያን ጦር ዳህናን ይዞ ስለነበር ይህን አካባቢ ከጠላት
እጅ ፈልቅቆ ለማውጣት አርበኛ ሌተናል ጀነራል ደጅአዝማች ኀይሉ የሀገሬውን አርበኞች በማስተባበር የሰርጎ ገብ ጥቃት
በመፈጸም እስረኞችን ከማስፈታት በዘለለ ጠላት ተረጋግቶ እንዳይቀመጥ ረፍት ይነሱት እንደነበር ታሪካቸው ያስረዳል፡፡
ጀነራል ደጅአዝማች ኀይሉ ከበደ “መርቆሪዎስ” በተባለ ዋሻ ለሁለት ዓመታት ከመንፈቅ በመመሸግ ጠላትን ረፍት ነስተዋል፤ አርበኛ
ሌተናል ጀነራል ደጅአዝማች ኀይሉ አርበኞችን በማስተባበር “እምቢ ለሀገሬ” በማለት ይታወቃሉ፡፡
ጣሊያን የመጀመሪያውን የአውሮፕላን የመርዝ ጋዝ ለመጠቀምም የተገደደው አስቸጋሪ እና የእግር እሳት በሆነበት በአርበኛ
ሌተናል ጀነራል ደጅአዝማች ኀይሉ ከበደ ጦር ላይ ነበር ብለዋል የታሪክ ምሁሩ፡፡
እንደ ምሁሩ ገለፃ ከሰቆጣ ወደ ዳህና የጠላት ጦር እየገሰገሰ እንደሆነ የተረዱት አርበኛ ሌተናል ጀነራል ደጅአዝማች ኀይሉ ከበደ
ከመሸጉበት ወጥተው ጉራንባ ቲኩል ወደ ተባለ ቦታ በማቅናት ነሐሴ 19/1929 ዓ.ም የመጀመሪያውን ጦርነት ከጠላት የጣሊያን
ጦር ጋር አካሄዱ፡፡ ከጦራቸው ጋር በመመካከርም የጠላት ጦር እስኪደመሰስ ድረስ መግፋት እንዳለባቸው በመተማመን በሦስት
አቅጣጫ የጠላትን ጦር ተፋልመዋል፤ አምደወርቅ ላይም ድልን ተቀዳጅተዋል፡፡ “አጋዘን መገርሰም” በተባለ ቦታ ላይም
ሦስተኛውን ጦርነት በማካሄድ ጠላትን ድል መትተዋል፡፡ “ድግሪሽ ተራራ” ላይ ለአራተኛ ጊዜ ባካሄዱት ውጊያ ጠላትን ድል
አድርገዋል፤ ጀግንነታቸውንም አሳይተዋል ብለዋል ዶክተር አያሌው፡፡
አርበኛ ሌተናል ጀነራል ደጅአዝማች ኀይሉ ከበደ በ1929 በእለተ አርብ በጠላት ጦር በግፍ ተገደሉ፡፡ በጀግንነት ሕይወታቸው
ያለፈ ቢሆንም የሳቸውን ፈለግ የተከተሉ ጀግና ኢትዮጵያውያን አርበኞች ጣሊያንን ረፍት በመንሳት ሀገራቸውን ነጻ አውጥተዋል፡፡
ከድል በኋላ አፄ ኃይለ ሥላሴ ደጅአዝማች ኀይሉ ከበደ ለፈጸሙት አኩሪ ገድል የሌተናል ጀነራልነት ማዕረግ ሰጥተዋቸዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ምስጋናው ብርሃኔ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m


Previous articleʺአልጎድል ስላለ ብለውት ብለውት የመከራውን ጎርፍ በደም ተሻገሩት”
Next articleʺጎንደር ከግንቡ ላይ ያለው ነጭ አንበጣ ከምን ሊገባ ነው አሞራው ሲመጣ”


Source link

Related posts

የኢትዮጵያ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ተሳትፎ ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ተግባር መሆኑን የተለያዩ አገሮች ወታደራዊ አታሼዎች ገለጹ።

admin

5ኛው የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት 6ኛ ዓመት የስራ ዘመን 8ኛ መደበኛ ስብሰባውን ያካሄዳል

admin

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ለሱዳን የሽግግር መንግሥት ድጋፍ ለማድረግ በተዘጋጀው ጉባዔ ላይ ተሳተፉ

admin