59.29 F
Washington DC
April 21, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

“የፌዴራል ምንግሥትን አሳምነን ያመጣናቸዉን የልማት ፕሮጀክቶች መሪዎችና የልማቱ ተጠቃሚዎች ተመልሰን የልማቱ ችግር መሆን የለብንም” የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ፋንታ ማንደፍሮ

“የፌዴራል ምንግሥትን አሳምነን ያመጣናቸዉን የልማት ፕሮጀክቶች መሪዎችና የልማቱ ተጠቃሚዎች ተመልሰን የልማቱ ችግር መሆን የለብንም” የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ፋንታ ማንደፍሮ

ባሕር ዳር ፡ የካቲት 17/2013 ዓ.ም (አብመድ)

በፌዴራል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የባሕር ዳር ኢንዱስትሪ ፓርክ ከአጋር አካላት ጋር በባሕር ዳር ውይይት አድርጓል።

በፌዴራል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የባሕር ዳር ኢንዱስትሪ ፓርክ ዋና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ጥሩዬ ቁሜ ለውይይት የሚሆን የመነሻ ጽሑፍ አቅርበዋል። በዚህም ፓርኩ የሥራ እድልን በመፍጠር፣ ለባለሀብቱ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትን በመገንባት፣ ቅድመ ምርት ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን ወይዘሮ ጥሩዬ አንስተዋል። ሥራ አስኪያጇ ባቀረቡት ጽሑፍ በፓርኩ ውስጥ ለባለሀብቱና ለልማቱ ለተነሱ ሰዎች የጤና አገልግሎት እንዲኖር፣ በፓርኩ አካባቢ የስርቆት ወንጀሎች በተደጋጋሚ ስለተከሰቱ የክልሉ ልዩ ኀይል ጥበቃ እንዲያደርግና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን አንስተዋል።

የኢንዱስትሪ ፓርኩ የትግበራ ሥራዉን ቢጀምርም ከባሕር ዳር ከተማ አስተዳደርና ከባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳ ጋር ተያይዞ የወሰን አከላለል ችግር በመኖሩ በፓርኩ የሚከሰቱ ወንጀሎችን ለመከላከል አስቸጋሪ እንደሆ የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ ረዳት ኮሚሽነር ከፋለ ሙሉዓለም ተናግረዋል። በፓርኩ ውስጥ ሊከሰት የሚችለውን ወንጀል ለመከላከል ከወሰን ጋር ልዩነትን ፈጥሮ ከመገፋፋት ራሱን የቻለ አደረጃጀት ተፈጥሮለት በአንድ አስተዳደር ስር ሊጠቃለል እንደሚገባ ረዳት ኮሚሽነሩ ሀሳብ አቅርበዋል።

በፓርኩ ዙሪያ ለሚኖሩ ሰዎች ፓርኩ የእነሱ እንደሆነና የሚሰጠው ጠቀሜታም ለእነሱ ስለሆነ ግንዛቤ ሊፈጠርላቸው እንደሚገባ በውይይቱ ላይ ሀሳብ ቀርቧል። በኢንደስትሪ ፓርኩ የተገነቡት ሼዶች በቂ እንዳልሆነም ተጠቅሷል።

የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የገበያ ትስስርና ደንበኞች አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ዝናው ልንገርህ በፓርኩ 32 ሼዶች ይገነባሉ ተብሎ ቢታቀድም እስካሁን ስምንት ሼዶች ብቻ መገንባታቸውን ተናግረዋል።

የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ባዬ አለባቸው የፓርኩ ካርታና ፕላን በእጃችን ስለሚገኝ ፓርኩ በእኛ ሥር ይካተታል ብለዋል። “ፓርኩን እኛ ብናስተዳድረዉም የባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳ ከእኛ ጋር በአጋርነት ሊሠራ ይገባል፤ ፓርኩ የአካበቢው ማኅበረሰብ ሀብት ስለሆነ የአካባቢው ሰዎች ተገቢ በሆነ ሁኔታ ተመልምለው የሥራ እድል ሊያገኙ ይገባል፤ በፓርኩ ውስጥ የሚገኙ የአካባቢው ነዋሪዎች በፓርኩ ሕገ ደንብ መተዳደር እንጂ ከውጪ አካላት ጋር በመሆን ፓርኩን የሚጎዳ ተግባር መፈጸም የለባቸውም” ብለዋል።

የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ፋንታ ማንደፍሮ በአማራ ክልል አራት የኢንዱስትሪ ፓርኮች እንደሚገኙ ጠቅሰው ከቁጥር ባለፈ የፌዴራሉ መንግሥት ጥራታቸውን የጠበቁ አደረጃጀቶች እንዲኖራቸው ማድረግ አለበት ብለዋል። ሙያዉንና ቦታውን የሚመጥኑ ለልማት የተነሱ ዜጎች መስፈርቱን ካሟሉ ቅድሚያ ሊሰጣቸው እንደሚገባ አስረድተዋል። ለፓርኩ ልማት የተነሱ ዜጎችም ዘለቄታ ባለው መልኩ ሕይወታቸውን የሚለውጥ አሠራር መሠራት አለበት ብለዋል።

“ከጸጥታ ጋር በተያያዘ ፓርኩን ሙሉ በሙሉ የሚያስተዳድረው የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ነው፤ የባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳም በአጋርነት እንዲሠራ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን በሰነድ ላይ የተደገፈ አሠራር ቀን ሳይዝ ሥራ መጀመር አለበት” ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በፓርኩ ዙሪያ ለሚነሱ ጥያቄዎች አመራሩ ጥበብ በተሞላበት ሁኔታ መፍታት ይኖርበታል” ብለዋል።

“የኢንቨስተር ሀገሩ የሚያለማበት አካባቢ ነው” ያሉት ዶክተር ፋንታ የጸጥታና ሌሎች ችግሮች ካልተፈቱ የኢንዱስትሪ መዳረሻ መሆን አንችልም ብለዋል። አልሚ ባለሀብት የፀጥታ ችግር የሚያጋጥመው ከሆነ ደጃችንን ስለማይረግጥ አመራሩ በመተባበር ችግሮቹን ሁሉ ሊፈታ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ችግር ሲፈጠር ብቻ ሳይሆን በተደጋጋሚ ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር ውይይት ማድረግ እንደሚገባም ዶክተር ፋንታ አስገንዝበዋል።

“አልሚዎች ወደእኛ ሲመጡ መርጠዉን እንጂ ተገድደው አይደለም” በማለት ያስረዱት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር የፌዴራል ምንግሥትን አሳምነን ያመጣናቸዉን የልማት ፕሮጀክቶች መሪዎችና የልማቱ ተጠቃሚዎች ተመልሰን የልማቱ ችግር መሆን የለብንም ብለዋል።

በየመድረኩ ችግሮችን ለመፍታት የሚሰበሰበው አመራር ውይይቱን ወደ ተግባር በመለወጥ ተጽዕኖ ፈጣሪና ችግር ፈቺ መሆን እንደሚገባም ዶክተር ፋንታ መክረዋል።

ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

Source link

Related posts

ጎርጎራ እንደገና ስታበራ። | የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት

admin

የመተከል ዞን ግብረሃይል እስካሁን ውጤታማ ተግባራትን ቢያከናውንም አሁንም ቀሪ ስራዎች ይጠበቁበታል – አቶ ገዱ አንዳርጋቸው

admin

‹‹የዓድዋ ድል ጥቁሮችን ከጭቆና እና ከብዝበዛ፣ ነጮችን ደግሞ ከኢ-ሰብአዊ ድርጊታቸው ነፃ ያወጣ ታላቅ በዓል ነው›› ወጣቶች

admin