52.39 F
Washington DC
February 25, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

የፈሪሳውያን እርሾ – መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ | ዘ-ሐበሻ (ZeHabesha)

“In the mean time, when there were gathered together an innumerable multitude of people, insomuch that they strode one upon another, he began to say unto his disciples first of all, Beware ye of the leaven of the Pharisees, which is hypocrisy.”

— Luke 12፥1

ትላንት ጨካኝ፣ግፈኛ ና ፈሪሃ እግዛብሔር የሌላቸውየአገር መሪዎችና አሥተዳዳሪዎች በዜጎች ላይ የፈፀሙትን እኩይ ፣ ነውረኛ እና አፀያፊ ተግባር የመነጨው ከግብዝነት ነው። ዛሬም ጥላቻን አሥፋፊው ግብዝነት በባሰ መልኩ ተሥፋፍቷል ። ዛሬም በግብዝነት የተሞላው የቆዳ ማዋደድ ፖለቲካና የእበላ ባይ አጨብጫቢዎች አሸሸ ገዳሚ ደምቆል። ”

በማዓት ግብዞች የተሞለው ፖለቲካችን ፣ ብለህ አርቆ አሳቢ ፣አሥተዋይ ፣አገር ወዳድ ወዘተ። ” የሚባለውን መሪ እንኳን ለማጃጃል የሚችል ቡድን እስከመፍጠር ደርሰዋል። እነዚህ ራሳቸው ግብዝ ሆነው፣ እንደጠጅ ቤት አዝማሪ ከውዳሴ በሥተቀር በፊሥ ቡክ ቡድናቸው ገንቢ የሆነ ትችት የማያቀርቡ፣ ብልሁን ሰው ሞኝ ለማድረግ የሚጥሩ ከመሆናቸውም በላይ፣ በየሥርዓቱ ውሥጥ እየተጠናከረ የመጣውን የግብዝነት ትምህርትን የሚሰብኩ ሆነው አግኝቻቸዋለሁ።

ማሥረጃውን ከፈለክ እዛው የግሩፕ የፊሥ ቡክ ገፃቸው ላይ ታገኘዋለህ ። ማድነቅን ሣይሆን ማምለክን እያሥተማሩ እንደሆነ ለመገንዘብ በየጊዜው የሚለጥፎቸውን መልዕክቶች በማንበብ መረዳትም አያዳግትህም ። መሪውን ፈጣሪ ነው ። ለማለት ሲዳዳቸው፣ ቀዳማይት እመቤቷን እምዬማርያም ናት ብለው ለመሥበክ ሲፍጨረጨሩ በቀላሉ ትታዘባለህ። …

ለእኔ እና ለመሰሎቼ የእውነት አቀንቃኞች የእነዚህ ጭፍን ደጋፊዎች ድርጊት በግብዝነት የተሞላ በመሆኑ ፣የለውጡን መሪ የወደፊት ቀና ሃሳብ ና ድርጊት አጨናጋፊ ሆኖ ታይቷናል ። ከዚህም ባሻገር በማመዛዘን ከጠቅላዩ ጎን የቆሙትን የአሥተዋይ ምሁራን ድጋፍ በማሳጣት የጠቅላዩ መሥተዋል ፈፅሞ እንዲጠፋ የሚያደርግ ከንቱ ድራማ ነው።

በእውነቱ ” የፊሥ ቡኮቹ የጠቅላዩ ደጋፊዎች ” ድርጊት ብሥለት የሌሌው የልጆች ጫወታ ነው። እናም መሪው የልጆች ጫወታን የሚፀየፍ ከሆነ ( ይህ ፀሐፊ የሚፀየፍ ነው ፡፡ብሎ ያምናል።) “ግብዝ አይደለሁም ። ግብዝነትንም እጠየፋለሁ።  ” በማለት ከፊሥ ቡክ ገፅ እነዚህን ህፃናት መሪው ገለል ቢያረጋቸው ለለውጡ ጉዞ ይበጃል ብዬ አስባለሁ።

አብዛኞቹ የዚህ የፊሥ ቡክ ቡድን ዓባላት በገፁ የሚለቁት ፁሁፍ ከትላንቱ የወያኔ ፕሮፖጋንዲሥቶች የተኮረጀ ነው ። የቀድሞው እውቁ የአገሬ ጠ/ሚ አቶ መለሥ ዜናዊ እንደ ዶ/ር አብይ ይወደሱ ነበር። ” ሺ የኢህአዴግ ካድሬ ና ሺ የተቃዋሚ ምሁር ከመለሥ ጭንቅላት ጋር ከቶም አይወዳደርም። ” ይባል ነበር። የጠ/ሚሩን የአእምሮ ግዝፈት ለማሳየት።…

በነገራችን ላይ ይህቺን አገር ባለችበት እንድትረግጥ የሚያደርጋት ፣ተጨባጩን እውነት አውቆ እንዳላወቀ የሚያደርገው በየቀበሌው ያለ ካድሬና በትንሽ ጥቅም ለመበጥረቅ ወደ ኋላ የማይለው ተላላ እና ሥሜታዊ ደጋፊ ነው ። ይህ ፈፅሞ ከእውነት ጋር የሚጋጭ ድርጊት በ1997 ዓ/ም በ3 ኛው አገር አቀፍ ምርጫ ወቀት በወያኔ የድጋፍ ሰልፍ ላይ ተንፀባርቋል። የጨዋውን የኢትዮጵያ ህዝብ ማንነትም መረዳት የሚቻለው መሻገሪያው ድልድይ ላይ ህዝብ በነፃነት ሲደርስ ብቻ ነው። …

በዚች አገር ነፃነትን እና ነፃ አሥተሳሰብን ለማጥፋት እውነትን እና ቅንነትን በግብዝነት ለመቀየር የሚደረገው ትግል ዛሬም በመቀጠሉ የዛሬው መንግሥታችን የሚሾፍረው የለውጥ ባቡር ሐዲዱን ለመሣት እየተንገራገጨ መሆኑንን እያሥተዋልኩ ነው። የመንገራገጩ ምልክትም በአንዳንድ የኦሮሚያ ዞኖች እና በትግራይ ክልል ጎልቶ ይታያል። ይህ የመንገራገጭ እና ባቡሩ ከመሥመሩ ወጥቶ የመገልበጡ አደጋ እንዳይከሰት ያለው ብቸኛ አማራጭ ከደርግና ከወያኔ ኢህአዴግ በውሸት ፕሮፖጋንዳ ላይ ከተመሠረተ የካድሬ ፖለቲካ ፈፅሞ መውጣት አማራጭ የሌለው መፍትሄነው። እራሳቸውን መምራት የማይችሉ ግለሰቦችንም ከመሪ ወንበር ላይ ሣይረፍድ ማንሳት ያሥፈልጋል። ከራሳቸው ጥቅም ይልቅ ለደሃ ህዝባቸው በብርቱ የሚጨነቁ። ሰውን በጎሣ ሣይከፋፍሉ ለዜጎች ነፃነት፣ ፍትህ፣ እኩልነት መከበር የሚታገሉ ።በተግባር ደሃውን ለማበልፀግ እንጂ ራሳቸውን ከበርቴ ለማድረግ ህዝብና አገርን የማይበዘብዙ ግለሰቦችን ለሥልጣን ማብቃት፣ ከቃላት በላይ ወደብልፅግና እንደሚያሻግ ርመረዳትም ከመቼውም ጊዜ ይብልጥ ዛሬ አገር እንደምትፈልግ መገንዘብ መልካም ነው። ካለፉት መንግሥታት ካድሪያዊ አደንቆሪ ፖለቲካ አብይ መራሹ ” ወደብልፅግና አሻጋሪ መንግሥት ”  መሠረታዊ ለውጥ በማድረግ እሥካልወጣ ጊዜ ድረሥ የመላውን ህዝብን ልባዊ ድጋፍ ለማግኘት አይችልም።

በነገራችን ላይ ፣በካድሬ ቅሥቀሰ ፣ልክ እንደደርግ ና ኢህአዴግ ገብያና የሱቅ ንግድ ከድጋፍ ሰልፍ በኋላ በማለትም ፣የህዝብን ልብ በማግኘት ለቀጣዩ የህዝብ አገልግሎት ዘመን እበቃለሁ ማለት ያንኑ የወያኔ ፖለቲካ መድገም ይሆናል። ሌሎችም በግብዝነት በማሥመሠል ፣በዱላ፣ በገጀራ ፣ና በጥይት ሥልጣንን ለጊዜው ይዞ መቆየት ቢቻልም ለመሰንበት ግን ፈፅሞ እንደማይቻል ከወዲሁ መገንዘብ አለባቸው።

በፖለቲካው ዓለም ግብዝ መሆን እና ማሥመሰል የኋላ ኋላ አደጋ እንደሚያሥከትል ከታሪክ መገንዘብ ይቻላል። እንደምሳሌም የ1997 ዓ/ም ምርጫን ዞር ብሎ በመመልከት ከትላንት የወያኔ/ኢህአዴግ ውድቀት ለመማር ይቻላል።

ዛሬ ከ18 እሥከ  30 ዓመት የዕድሜ ክልል ውሥጥ የሆናችሁ ወጣቶች የ 3 ኛውን የአገር አቀፍ ምርጫ ሂደትና ፍፃሜውን ካላነበባችሁ አታውቁምና ላላነበባችሁ ታሪኩን ባሥታውሳችሁ ለነገ 6ኛው አገራዊ ምርጫ መነፅራችሁን ቀይራችሁ ሁኔታውን በአንክሮ ለማየት ይበጃችኋል ብዬ አሥባለሁ። …

የ3ኛው ዙር አገር አቀፍ ምርጫ ግንቦት 7 ነበር የተካሄደው። ምርጫው ከመካሄዱ በፊት በተደረገው የምረጡኝ ቅሥቀሣና የመድረክ ፖለቲካዊ ግጥሚያ ቅንጅት የተሰኘ ፖርቲ ኢህአዴጎችን በዝረራ አሸንፎ ነበር። እነፕሮፊሰር መሥፍን ፣ፕሮፊሰር ብርሃኑ፣ኢንጂነር ኃይሉ ሻውል ና ኢንጂነ ርግዛቸው ፣ልደቱ አያሌውን ጨምሮ አያሌ ምሁራን የተቀናጁበት ፖርቲ ኢህአዴግን በምርጫ ቅሥቀሣና በፖለቲካዊ ፣በማህበራዊውና በፖለታካዊ ክርክሩ በዝረራ እንዳሸነፈ ሁሉ በግንቦት 7 ምርጫ ማሸነፍ እንደሚችል ገዢው ፖርቲ በመጠርጠሩ ፣የአዲስ አበባን ህዝብ የድጋፍ ሠልፍ ኢህአዴግ ፣ሚያዚያ 29 ቀን ጠራ። በድጋፍ ሠልፉ የተገኙ በሰልፉ መሀል ውሥጥ ሆነው፣ ” ዛሬ ለእንጀራችን ነገ ለአገራችን ፣ዛሬ ለቲሸርት ነገ ለነፃነት ፣ዛሬ ለሆዳችን ነገ ለክብራችን…” የሚሉ ሰልፈኞችም ነበሩ። በሰልፉም እንደኢቲቪ ዘገባ አንድሚሊዮን ተኩል ይሆናል የተባለ ሰልፈኛ ተገኝቶ ነበር።

በማግሥቱ ሚያዚያ 30 ቀን 1997 ዓ/ም ደሞ ቅንጅት በጠራው የድጋፍ ሰልፍ ከሚያዚያ 29 የሚበልጥ ህዝብ (የዋሁ ና በልህ የሆነው በፍቅር እዮነረ ያለው የአዶ ገነት ነዋሪ   ) በመሥቀል አደባባይ ተገኝቶ ለቅንጅት ፖርቲ ያለውን ድጋፍ ገልፆል።

በሚያዚያ 29 ቀኑ የህዝብ ልብ ባልታወቀበት፣ በቀበሌ ካድሬ ቅሥቀሣ በአደባባይ የተገኘ ጨዋ ዜጋ የእሳቸው ደጋፊ መስሎቸው  ” ይህ ማዕበል ኢህአዴግ ምርጫውን ሳያጭበረብር ለማሸነፍ ያሥችለዋል።.. .ምርጫውም እንከን የለሽ ይሆናል።…” በማለት በሥሜት እየተወራጩ መለሥ ዜናዊ ተናግረው ነበር። መለሥ ከግንቦት 7 በኋላ ግን በከፍተኛ አመራሮቻቸው፣ በካድሬዎቻቸውና በድህንነት ኃላፊው ሳያዝኑ እንዳልቀሩ በተከታታይ ያደረጓቸው ለውጦች ያመላክታሉ።

መለሥ ከምርጫ ሽንፈታቸው ማግሥት ጀምሮ፣ የሆዳቸውን በሆዳቸው ይዘው “ጣታችሁን የምትቀሰሩ ጣታቸሁ ይቆረጣል። በትግል ያገኘነውን ወንበር በወረቀት አሳልፈን አንሰጥም። አርፋችሁ ቁጭ በሉ። በነውጥ መንግሥት መሆን አትችሉም። በቢላዋ ቀልድ እንደሌለም እወቁ። ” በማለት በጥይት የግንቦት ሰባትን ውጤት የመቀልበሥ የኃይል እርምጃ ወሰዱ። ታላቅ የቅልበሳ የፖለታካ ሥራ ሰሩ። (የተረፈውን አቶ ልደቱ የናገር። ማን ይናገር የነበረ…እንዲሉ። )

የህዝብን እውነተኛ ፍላጎት ከደረሰባቸው ሽንፈት በመገንዘብ ከዚህ ሽንፈት በኋላ አብዛኞቹን የቅንጅት ሃሳቦች ማራመድ ጀመሩ። የተቸከሉት የመሬት ፣የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ፣አንቀፅ 39 ና የጎሣ ፖለቲካ እና የጠመንጃ አገዛዝ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አደረጉ።  …የባንዲራ ቀን እና የአባይ ግድብ የመሠረት ዲንጋይ፣ በአቶ መለሥ የአገዛዝ ዘመን እውን ሆነ። የህዝብን ሥነ ልቡናም ተሠረቀ። “አባይን የደፈረ ጀግና መሪ ” መለሥነው። ተብሎ ተጨበጨበ።

ያም ሆነ ይህ ብቸኛው የኢህአዴግ መሪ ድንገት በሞት ሲለዩ ፣ኢህአዴጎች የግል ሀብት በየፊናቸው ለማከማቸት መሯሯጥን አብይ ሥራ አድርገውት አረፉ። የመለሥ ሌጋሲም ተረት፣ተረት፣ ሆኖ ቀረ። በእርግጥ ኢህአዴጎች የመለሥ ሌጋሲ ጉዳያቸው አልነበረም። መለሥ በህይወት እያለ የሚፈሩትና የሚያመልኩት ህልቆ ወመሣፍርት ካድሬዎች ሁሉ፣ ከመለሥ በኋላ መንግሥት እንደሌለ በመቁጠር በዘረፋ ላይ ተሰማሩ። ባጋበሱት ሀብትም በትዕቢት ተወጠሩ። ሲበዛ ግብዝ ሆኑ።ግብዝነታቸውም አጠፋቸው።

በጣም የሚገርመው እነዚህ ሰዎች ግብዝነታቸው እንዳጠፋቸው፣ ዛሬም አይገነዘቡም።_ እነሱ ከሰው ሁሉ በላይ የሆኑ፣ ለመሪነት የተፈጠሩ ሌላው ተገዢ ሆኖ ለመኖር የተፈጠረ ነው።_ብለው የሚመፃደቁ ናቸው። ዛሬም በዳቦ እጦት የሚሰቃየውን ዜጋ ዳቦ እያሳየን እንገዛዋለን። አይቶ የማያውቀውን ብር በመሥጠትም ነፍሰ ገዳይ እናደርገዋለን።ብለው የሚመፃደቁ ናቸው። ዛሬም ከሞት የተረፉት የእናት ጡት ነካሽ የገንጣዩ የህውሃት ቡድን ሥብሥቦች ሥለከንቱነታቸው ነው የሚያወሩት። ሥለጅብነት ነው የሚያወሩት። (ህወሃቶች በጅብነት ቀምተው ሲበሉ የነበሩትን ግጠው ሳይጨርሱ መባረራቸውን አንዘንጋ።)

ለሕወሓቶች ፣የህግ የበላይነት ፣እኩልነት ፣ሰብአዊ መብት ወዘተ። ተረት፣ተረት ነው። ዛሬም እነሱ ከጠገቡ ደሃው የትግራይ ህዝብ ለምን አራት እግሩን አይበላም። ” ባዮች ናቸው ። በተግባርም ይህንኑ ነው ያረጋገጡልን ፡፡

ግብዞቹ ህውሃቶች ደሃው የትግራይ ህዝብ ከጎናቸው ባለመቆሙ ሊበቀሉት ይፈልጋሉ። የኤሌትሪክ አገልግሎትን ጨምሮ መሠረተ ልማትን ማውደም ቀጣይ የበቀል ተግባራቸው ነው። በዚህ እኩይ ተግባራቸው የትግራይ ደሃ ህዝብ የዕለት ምግቡን አብስሎ መመገብ ሲያቅተው ይደሰታሉ። ግብዞች ሁሌም እንዲህ ናቸው። በሰው ቁሥል ውሥጥ የሾለ ብረት መሥደድ ና ማሠቃየትን እንደፅድቅ ሥራ የሚቆጥሩ  ናቸው። ያሳዝናል። መቼ ይሆን ይህቺ አገር ከእነዚህ መሠል ግብዞች የምትፀዳው??? በመላው አገራችን የተዘራው የግብዝነት አረም መቼ ይሆን ተነቅሎና ተቃጥሎ የሚጠፋው ? …

ኮለኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ( ፕሬዝዳንት ) ጠ/ሚ መለሥ ዜናዊ ዛሬ ደግሞ ዶ/ር አብይ አህመድ ግብዝ እንዲሆኑ በየወቅቱ አዳዲስ ከንቱ ውዳሴ የበዛበት መፈክር በሥማቸው የሚያወጡላቸው እበላ ባይ ካዲሬዎች ነበሯቸው። ትላንት ለኢሠፖ ያልተደረተለት በትክክል የማይገልጸው ሥም አልነበረም።

ትላንት ለወያኔ /ኢህአዴግም ጨካኝነቱን መደበቅያ ያልተሰፋለት የወርቅ ካባ አልነበረም። ዛሬ ለመሞት አያጣጣረ እንኳን ፣የጎሣ አቀንቃኝ የኃይማኖት ካድሬዎቹ ቆባቸውን በአደባባይ ረግጠው በውጫ አገር ሲያወድሱት ስናይና ስንሰማ ይህንንኑ የግብዝነት ፖለቲካ ና ቀውሱን እናረጋግጣለን። …

ገዢው የብልፅግና ፓርቲ ፣ዛሬ ከዚህ ግብዝነት ከሚያስከትለው ቀውሥ እንዴት መውጣት እንደሚችል ዛሬ ቆም ብሎ ማሰብ አለበት። ብዝበዛቸው የተቋረጠባቸው እና የዛሬ አዳዲስ ግብዞች ሊውጦት እያደቡ መሆኑንም የተደበቀውን በመግለጥ የሚችለው ቆም ብሎ ማሰብ ሲችል ብቻ ነው፡፡እነዚህ ያደፈጡ የጎሳ ፖለቲካው የደበቃቸው ህሊና ቢስ ግብዞች   ግንባር ፈጥረው ይህቺን አገር ወደ ከፋ ችግር እንዳይ ወሥዷትም አሥፈላጊውን ጥንቃቄ እና ህጋዊ እርምጃ መውሰድ ይኖርበታል፡፡ ትግራይም እስከምረጫው ድረስ ከወገኑ የፖለቲካ ሰዎች ነጻ መሆን አለባት፡፡ትግራይ በጥብቅ ወታደራዊ ኮማንድ ውስጥ ካልሆነች የተረጋጋ ሰላም ማምጣ የሚከብድ ይመስለኛል፡፡ …

ለማንኛውም.. ይህንን ጥቅስ ጋብዣቸው ፅሁፌን እቋጫለሁ ፡፡

“በዚያን ጊዜ የሕዝብ አእላፍ እርስ በርሳቸው እስኪረጋገጡ ድረስ ተሰብስበው ሳሉ፥ ለደቀመዛሙርቱ እንዲህ ይል ጀመር፦ አስቀድማችሁ ከፈሪሳውያን እርሾ ተጠበቁ፥ እርሱም ግብዝነት ነው።”

— ሉቃስ 12፥1

ይህን ቃል ኢየሱስ የተነገረው ፣እውነትን ለመሥማት ለመጣ ቁጥሩ እጅግ ለበዛ ህዝብ ነው። ከፈሪሳውያን እርሾ አሥቀድሞ መጠበቅ ልብን ድፍን ከማድረግ ይታደጋል። በፈሪሳውያን እርሾ ከተላቆጣችሁ በኋላ ግን ረብ አይኖራችሁም።

 

Source link

Related posts

ቋሚ ኮሚቴው የባለስልጣኑን የስድስት ወራት እቅድ አፈፃፀም ገመገመ

admin

በነዳጅ ምርት አቅርቦትና ስርጭት ያሉ እጥረቶችን ለመፍታት እንደሚሠራ የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ገለፀ፡፡

admin

የብሄራዊ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በትውልድ መካከል ኢትዮጵያዊ በጎነት መተሳሰብና መከባበር እንዲጠነክር የሚያስችል ነው- ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል

admin