61.99 F
Washington DC
May 11, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

የጸጥታ ችግር የተፈጠረባቸው የሰሜን ሸዋ ዞንና የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር አዳራቸው ሰላማዊ መሆኑን አስተዳደሮቹ ገለፁ፡፡

የጸጥታ ችግር የተፈጠረባቸው የሰሜን ሸዋ ዞንና የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር አዳራቸው ሰላማዊ መሆኑን አስተዳደሮቹ ገለፁ፡፡

ባሕር ዳር፡ መጋቢት 15/2013 ዓ.ም (አብመድ) በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን እና ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር በተፈጠረ የጸጥታ ችግር የሰው ሕይወት ጠፍቷል፣ አካል ጎድሏል፣ ንብረት ወድሟል፣ ንፁሃንም በስጋት እንዲቀመጡና አካባቢያቸውን ለቀው እንዲወጡ አድርጓል፡፡ የተፈጠረውን ችግርና እየተወሰደ ያለውን የመፍትሔ እርምጃ እየተከታተልን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ዛሬም የሰሜን ሸዋ ዞንና የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዋና አስተዳዳሪዎች አዳሩን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዋና አስተዳዳሪ አሕመድ ሀሰን በአካባቢው አንጻራዊ ሰላም ተፈጥሯል ነው ያሉት፡፡ ነዋሪዎቹ ከስጋት እንዲወጡ እየሰሩ መሆናቸውን የተናገሩት ዋና አስተዳዳሪው በመጀመሪያ ተኩስ እንዲቆም ወደ ሥፍራው ከገባው የፀጥታ አካል ጋር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ማኅበረሰቡ እንዲረጋጋ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና ከታዋቂ ግለሰቦች ጋር እየሰራን ነው ብለዋል፡፡ የሃይማኖት ተቋማት መልዕክት እንዲያስተላልፉ ወደ ስፍራው በቂ የሆነ የፀጥታ ኃይል እንደገባና ምንም አይነት የፀጥታ ችግር ሊፈጠር እንደማይችል፣ የመንግሥት አካላትም እየሰሩ መሆናቸውን ለማኅበረሰቡ የማሳወቅ ሥራ እየተሰራ ነውም ብለዋል፡፡

ለጥቃት ሊያጋላጡ የሚችሉ ሁኔታዎችን የመቀነስ ሥራ እየተከናወነ ነው ያሉት፡፡ ዋና አስተዳዳሪው ከሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደር ጋር በተቻለ አቅም እየተገናኘን በጋራ እየሰራን ነውም ብለዋል፡፡

ማኅበረሰቡ እንዲረጋጋ የማድረግ ሥራዎች በቅንጅት ይቀጥላሉም ብለዋል፡፡ የተፈጠረው ችግር መነሻው ምን እንደሆነ በቅንጅት እንሰራለን ነው ያሉት፡፡

ከአሁን በፊት ችግሮች የተፈቱበትን መንገድ እንደሚከተሉም ተናግረዋል፡፡ በየአባቢው መድረክ ለማዘጋጄት እቅድ እንዳዘጋጁም ጠቁመዋል፡፡

መልዕክቶች ሲተላለፉ መሬት ላይ ያለውን እውነታ ማዕከል በማድረግ ማኅበረሰብን የማይጎዳና በፍትሃዊነት የሚያዩ መሆን አለባቸውም ብለዋል፡፡ ሕዝብን የሚያባላ ሐሳብ ከየትኛውም የስልጣን እርከን ቢነሳም ተቀባይነት የለውም ብለዋል፡፡

የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ታደሰ ገብረጻዲቅ በበኩላቸው ባለፉት 24 ሰዓት የጥይት ድምፅ ቆሟል፣ የበለጠ አካባቢውን ለማረጋጋት ካለፉት ሰኞ እና ማክሰኞ ጀምሮ ሥራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል፡፡ የጸጥታ ስጋት ባለበት አካባቢ ተጨማሪ የፀጥታ ኃይል እየገባ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ የሥራ ኀላፊዎችም ሕዝቡን የማረጋጋት ሥራ እንዲሰሩ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አካባቢው ሰላም እንዳይሆን የሚፈልጉ ኀይሎች በማኅበራዊ ሚዲያ የሚያናፍሱት አሉባልታ ፍፁም መሬት ላይ የሌለ እንደሆነም ዋና አስተዳዳሪው አስገንዝበዋል፡፡

ትናንት በነበረው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ አንዳንድ የሕዝብ እንደራሴዎች ያነሱት ሀሳብ ፍፁም አፀያፊና እውነታውን ያላገናዘበ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ በምክር ቤቱ የተነገረው ሀሳብ ሀገርን የሚያጠፋ፣ ተቀባይነት የሌለው፣ የሚወገዝና ተጠያቂ የሚያደርግ ነውም ብለዋል፡፡ ዋና አስተዳዳሪው “ሀሳቡንም አጥብቀን የምንቃወመው ነው፣ መሬት ላይ ካለው እውነታ የተለየ ነገር የሚያራግቡ ኀይሎች ለማንም እንደማይጠቅም አውቀው እጃቸውን ይሰብስቡ” ብለዋል፡፡

ጉዳዩ ዘላቂ መፍትሔ እንዲያገኝ በተቀናጄ መንገድ መሥራት ይገባልም ያሉት ዋና አስተዳዳሪው በአካባቢው በየጊዜው የሚነሳው ጥፋት መደገም የለበትም ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅትም ከኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ጋር እየሰሩ መሆናቸውን ዋና አስተዳዳሪው አቶ ታደሰ ገልጸዋል፡፡

ዘጋቢ፡-ታርቆ ክንዴ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Source link

Related posts

አድዋ ይመስክር (ከአሁንገና ዓለማየሁ)

admin

ኢትዮጵያ እና ጂቡቲ በቴሌኮምዩኒኬሽን ዘርፍ ያላቸውን አጋርነት ለማጠናከር ተስማሙ።

admin

”የመደመር መንገድ‘ መጽሐፍ ከሥነ ጽሑፋዊ ይዘቱ ባሻገር ከፍልስፍና እና ፖለቲካ አንፃርም የላቀ ስራ ነው- ደራሲያን እና ምሁራን

admin