73.2 F
Washington DC
June 14, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

የጣና በለስ ቁጥር አንድ ስኳር ፕሮጀክት የስኳር ፍጆታን ከመሸፈን ባለፈ የውጪ ምንዛሬ እጥረትን ይቀንሳል፣ የሥራ ዕድል ይፈጥራል፤ የአካባቢውን ኢኮኖሚም በከፍተኛ ሁኔታ ያነቃቃዋል” የፕሮጀክቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አንተነህ አሰጌ

የጣና በለስ ቁጥር አንድ ስኳር ፕሮጀክት የስኳር ፍጆታን ከመሸፈን ባለፈ የውጪ ምንዛሬ እጥረትን ይቀንሳል፣ የሥራ ዕድል ይፈጥራል፤ የአካባቢውን ኢኮኖሚም በከፍተኛ ሁኔታ ያነቃቃዋል” የፕሮጀክቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አንተነህ አሰጌ

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 29/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የጣና በለስ ቁጥር አንድ ስኳር ፕሮጀክት ሥራ ሲጀመር በ18 ወራት ውስጥ ተጠናቅቆ ምርት እንደሚያመርት ዕቅድ ተይዞ ነበር። በወቅቱ ኮንትራቱን የወሰደው (የቀድሞው የብረታብረት እና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን/ሜቴክ) እንዲገነባ ነበር ውል የተያዘለት፡፡ ፕሮጀክቱ ከዓመታት መጓተት በኋላ ዛሬ ለምረቃ በቅቷል፡፡

የፕሮጀክቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አንተነህ አሰጌ እንዳሉት በክልሉ የልማት ድርጅቶች የተያዙ መሠረተ ልማቶች በተገቢው መንገድ ተሠርተዋል፤ ከ13 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ ተዘጋጅቶ አገዳ መልማቱንም ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ የፋብሪካውን ግንባታ በያዘው ሜቴክ አቅምና ልምድ ማነስ ምክንያት ለግንባታው ምን ያሕል ጊዜ እንደሚያስፈልግ በትክክል ማወቅ አልተቻለም ብለዋል፡፡ በዚህም የፋብሪካ ግንባታውና የአገዳ ልማቱ ተጣጥሞ አልሄደም፤ የለማው አገዳም ለብክነት ተዳርጎ ቆይቷል ነው ያሉት፡፡

ዋና ሥራ አስኪጁ እንዳብራሩት ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በተወሰደው ርምጃ ከሜቴክ ጋር የነበረው ውል ተቋርጦ ፕሮጀክቱ ለቻይና ተቋራጭ ተሰጥቷል፡፡ ከዚያ በኋላ ሥራው በሁለት ምዕራፍ በመክፈል በ14 ወራት ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ለማጠናቅቅ ነበር የታሰበው፡፡ በተለይ የመጀመሪያውን ዙር በስምንት ወራት በማጠናቀቅ የተወሰነውን አገዳ ከብልሽት ለመታደግ ቢታሰብም በውጪ ምንዛሬ እጥረት ምክንያት ሥራው ፈጥኖ አለመጀመሩ፣ ከጀመረ በኋላም በክፍያ መዘግየት እና በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከሰት ምክንያት ግንባታው እንዲጓተት ኾኗል፡፡

ፕሮጀክቱ የገጠሙትን ውጣ ውረዶች አልፎ ስኳር ለማምረት በቅቷል፣ ዛሬም የምረቃ ሥነ ሥርዓቱ እየተከናወነ ነው፡፡ በተሠራው የማስተካከያ ሥራ ማሽኖች በጥሩ ሁኔታ እንዲሠሩ ተደርጓል፤ ለአንድ ሳምንት በተደረው የሙከራ ምርት ጥሩ ውጤት እንደተገኘበትም አስታውቀዋል፡፡ በሙከራ ምርቱም ወደ 200 መቶ ኩንታል ስኳር ተመርቷል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከአራት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ስኳር ወደ ሀገር እያስገባች መኾኑን ያመላከቱት ዋና ሥራ አስኪያጁ ፋብሪካው ሀገሪቱ ከውጪ አስገብታ የምታሟላውን የስኳር ፍጆታ እንደሚቀንስም አስረድተዋል፡፡ በሙሉ አቅሙ ወደ ምርት ሲገባ ወደ 2 ሚሊዮን ኩንታል ገደማ ስኳር በዓመት እንደሚያመርትም ነው የተናገሩት፡፡

የስኳር ፍጆታን ከመሸፈን ባለፈ የውጪ ምንዛሬ እጥረትን ይቀንሳል፣ የሥራ ዕድል ይፈጥራል፣ የአካባቢውን ኢኮኖሚም በከፍተኛ ሁኔታ ያነቃቃዋል ነው ያሉት፡፡ አካባቢው በደንብ ከተሠራበትም ሌሎች ፋብሪካዎችን ጭምር ማስተናገድ የሚያስችል አቅም እንዳለው አብራርተዋል፡፡ ይሁን እንጂ ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ እንዲያመርት በሚቀጥሉት ሦስትና አራት ዓመታት 18 ሺህ ሄክታር የሸንኮር አገዳ መልማት አለበት፡፡ ምንም እንኳን ከ13 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ቢዘጋጅም የለማው 4 ሺህ ሄክታር ብቻ ነው፡፡ አገዳውን ለማልማት መንግሥት በጀት መድቦ ሊሠራ እንደሚገባም ጠይቀዋል፡፡

ጣና በለስ ቁጥር አንድ ስኳር ፋብሪካ ፕሮጀክት በዚህ ጊዜ 1 ሺህ 500 ቋሚና 2 ሺህ 700 ገደማ ጊዜያዊ ሠራተኞች እያስተዳደረ ነው፤ በሙሉ አቅሙ ሥራ ሲጀምር ደግሞ 5 ሺህ ቋሚና 10 ሺህ የሚደርሱ ጊዜያዊ ሠራተኞችን ሊያስተዳድር እንደሚችልም አመላክተዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Source link

Related posts

ዓለምአቀፉ አሸባሪ ትክክለኛ ስሙን አገኘ

admin

የኢትዮ-አውሮፓ ሕብርት የጋራ ምክክር ተካሄደ።

admin

የካፒታል ገበያ ፍትሃዊና ቀልጣፋ የግብይት ስርዓት እንዲኖር የሚያስችል መሆኑ ተገለጸ

admin