76.62 F
Washington DC
June 15, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

የግብጽ ሴራ በዓባይ ላይ …
የግብጽ ሴራ በዓባይ ላይ …
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 07/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታን አስመልክቶ ከታችኛው ተፋሰስ ሀገራት
ጋር ድርድር ሲካሄድ መቆየቱ ይታወሳል፡፡ ኢትዮጵያም የፖለቲካ፣ የሕግ እንዲሁም የውኃ ምሕንድስና ባለሙያዎች ባሉበት ግድቡ
በተፋሰስ ሀገራት ላይ ምንም አይነት ጉዳት እንደማያስከትል ለማሣየት ጥረት አድርጋለች፤ ዓለም አቀፍ ሕጎችን የተከተለ እና
ለወደፊትም የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ ሣይንሳዊ ትንታኔዎችን በማቅረብም ውጤት አስመዝግባለች፡፡ ይሁን እንጅ በዚህ
ያልተሳካላት ግብጽ የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር አሁንም እየሠራች እንደምትገኝ በወሎ
ዩኒቨርሲቲ የመንግሥት አስተዳደር ትምህርት ቤት የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር እና በዓባይና አዋሽ
ተፋሰስ ጥናት ተቋም ውስጥ ደግሞ የውኃ ፖለቲካ እና አስተዳደር አስተባባሪ ጀማል ሰዒድ ገልጸዋል፡፡
መምህር ጀማል እንዳሉት ግብጽ ታሪካዊ ወዳጆቿን እና ጎረቤት ሀገራትን ከጎኗ በማሰለፍ በእጅ አዙር ኢትዮጵያን ለማዳከም
እየሠራች ትገኛለች፡፡ ከእነዚህ ሀገራት መካከል ደግሞ ሱዳን አንዷ ናት፡፡ በአባይ ድርድር ላይ በሕግ፣ በሣይንሳዊ እና በፖለቲካዊ
መንገድ ያልተሳካላት ግብጽ የሱዳንን እና የኢትዮጵያን ውስጣዊ ችግሮች እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም የመሬት ይገባኛል
ውዝግብ በማስነሳት በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለመፍጠር እየሠራች መሆኑን ነግረውናል፡፡
ሱዳን በቀድሞው ፕሬዝዳንት በኦማር አልበሽር ዘመን የታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ በታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ላይ
ምንም አይነት ጉዳት እንደማያመጣ በማመን ስትደግፍ ቆይታለች ነው ያሉት፡፡ ይሁን እንጅ ከኦማር አልበሽር የስልጣን መወገድ
በኋላ ማእከላዊ መንግሥቱ በመዳከሙ ምክንያት ሱዳን በግብጽ እና በአረብ ሊግ ተጽዕኖ በመውደቋ የሚሰጣትን አጀንዳ
አስፈጻሚ መሆኗን አንስተዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ሱዳን በቅርቡ ያነሳችው ያልተገባ የድንበር ይገባኛልን እንደማሳያነት አንስተዋል፡፡
የሱዳን አሁናዊ ሁኔታ ማእከላዊ መንግሥቱ የተዳከመ፣ ውስጣዊ የፖለቲካ መረጋጋት ችግር ያለበት፣ ኢኮኖሚያዊ እና ወታደራዊ
አቅሟም ቢሆን የድንበር ይገባኛል ጥያቄ ለማንሳት የማያስችል ቁመና ላይ መሆኗ በሌሎች የምትዘወር ስለመሆኑ የሚያሳዩ
እንደሆኑ አንስተዋል፡፡
የሱዳን ወታደራዊ ክንፍ የግብጽን እና የአረብ ሊግን ተልዕኮ በመሽከም የድንበር ይገባኛል ጥያቄ በማንሳት የታላቁን የኢትዮጵያ
ሕዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውኃ ሙሌትን ለማደናቀፍ እየሠራ ይገኛል ብለዋል፡፡ ይህ ያልተገባ የመሬት ይገባኛል ጥያቄ
ኢትዮጵያን አስገድዶ አሳሪ ስምምነት እንድትፈርም ለማድርግ ጭምር ያለመ ሴራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ኢትዮጵያ ይህንን
የማታደርግ ከሆነ ደግሞ በኢትዮጵያ ላይ ግጭት እና ዲፕሎማሲያዊ ጫና ለማሳረፍ የተዘየደ ስልት ነው ብለዋል፡፡
መምህር ጀማል እንዳሉት ግብጽ ለመካከለኛው ምስራቅ እና ለአፍሪካ ካላት ስትራቴጅካዊ አቀማመጥ እና የእስራኤልን ህልውና
ለማስጠበቅ ካለ ፍላጎት አሜሪካ እና ግብጽ የቆየ ግንኙነት መፍጠራቸውን አንስተዋል፡፡ ለዚህም አሜሪካ ለግብጽ ከፍተኛ የሆነ
ወታደራዊ ድጋፍ እንደምታደርግ አመላክተዋል፡፡ ግብጽም ይህንን ግንኙነት እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም አሜሪካ
በኢትዮጵያ ላይ ጫና እንድታደርግ ስትሠራ መቆየቷን አንስተዋል፡፡ አሜሪካ ደግሞ ቻይና ወደ አፍሪካ ለምታደርገው እንቅስቃሴ
ኢትዮጵያን እንደመንደርደሪያ ትጠቀማለች የሚል እሳቤ እንዳላትም መምህር ጀማል ጠቁመዋል፡፡ ይህም ቻይና በአፍሪካ
የበላይነት እንዳይኖራት ለማድረግ አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለመፍጠር በይፋ እና በህቡዕ ስትሠራ መቆየቷን አንስተዋል፡፡
የግብጽ ፍርሃት የሕዳሴው ግድብ የውኃ ሙሌት ሳይሆን ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካዊ እና ወታደራዊ አቅሟን መገንባት
ከቻለች የቀጣናውን የበላይነት ትቆጣጠራለች የሚል ነው፡፡
የላይኛው ተፋሰስ ሀገራትም በዓባይ ላይ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን እንዲሠሩ አርዓያ ትሆናለች የሚል ስጋት ስላላት እንደሆነ
አንስተዋል፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያ ጠል ቡድኖችን በማስታጠቅ ግጭት ማስነሳት እና በውጭም ጫና በማሳደር ሀገርን
የማዳከም፣ ከቻሉም ለማፍረስ እየሠሩ መሆኑን አንስተዋል፡፡ ይህን ደግሞ ውስጣዊ አንድነትን በማጠናከር፣ ሀገራዊ መግባባት
በመፍጠር፣ እውነተኛ የሕግ የበላይነትን በማስፈን እና የውጭ ዲፕማሲን በማጎልበት ማክሽፍ እንደሚገባ በመፍትሔነት
አስቀምጠዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m


Previous article“ሀገር ጀግና ወልዳለች ከሚባሉት ውስጥ ብርጋዴር ጄኔራል ኃይሌ መለሰ አንዱ ናቸው” የትግል ጓደኞቻቸው


Source link

Related posts

የህወሓት ቡድን ተላላኪዎች የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለመረበሽ በህገወጥ ተግባራት መሰማራታቸው ተገለጸ

admin

የሸኔን እንቅስቃሴ ለማምከን የፌደራል ፖሊስ አባላት ከአካባቢው ሚሊሻ ጋር እየሰሩ ነው

admin

መንግሥት ከስድስት ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በመተባበር በትግራይ ክልል ለተፈናቃዮች እና ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች የሚሰጠው ሁሉአቀፍ ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉ ተገለጸ፡፡

admin