71.98 F
Washington DC
May 17, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

የግብርና ውጤቶች አቅርቦት እና የዋጋ አለመመጣጠን ችግር መኖሩን ሸማቾች ተናገሩ።

የግብርና ውጤቶች አቅርቦት እና የዋጋ አለመመጣጠን ችግር መኖሩን ሸማቾች ተናገሩ።

ነጋዴዎች በበኩላቸው የዋጋ ጭማሪውን ያመጣው የአቅርቦት ችግር ነው ብለዋል።

ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 22/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በዐቢይ ጾም ለ55 ቀን ከስጋና ከስጋ ተዋጽኦ ምግብ ርቆ የቆየ ማንኛውም ሰው ለጾሙ መፈሰኪያ ያሻውን ለመሸመት ወደ ገበያ ማቅናት የተለመደ ነው፡፡ በዓል ሲመጣ ደሮ፣ እንቁላል፣ ቅቤ ከፍ ሲልም ሙክትና ሰንጋ መግዛት የኢትዮያውያን የቆየ ባህል ነው፡፡

የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን በባሕር ዳር ከተማ አስተዳድር በተለምዶ ቀበሌ አራት (ዶሮ ተራ) ተብሎ በሚጠራው የገበያ ማዕከል ተገኝቶ የገበያ ቅኝት አካሂዷል፡፡ ለትንሣኤ በዓል መዋያ የሚሆኑ እንደ ዶሮ፣ ቅቤ እና ዘይት የመሳሰሉ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶች ገበያው ላይ በአግባቡ ቀርበው ገዥና ሻጭ እየተገበያዩ ተመልክተናል፡፡

በጾም ወቅት ዝቅተኛ የነበረው የዶሮ እና የቅቤ ዋጋ አንጻራዊ መጨመር ሲያሳይ ከፍተኛ ጭማሪ ታይቶበት የነበረው ዘይት ከ560 ብር ወደ 540 ብር ዝቅ ብሎ እየተሸጠ ነው፡፡

የበዓሉን መቃረብ ተከትሎ በግብይት ቦታው በሚፈለገው መጠን አቅርቦት አለመኖሩ በሸማቾች ላይ ተፅዕኖ ሊፈጥር እንደሚችል ታዝበናል። በተለይ የቅቤ ዋጋ መጨመርና የደሮ አቅርቦት አለመኖር ሸማቹን ከወዲያ ወዲህ እንዲዘዋወር ሲያደርግ ተመልክተናል።

ወይዘሮ ስፈልግ መንግሥቴ በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የቀበሌ 16 ነዋሪ ናቸው፡፡ ወይዘሮዋ የትንሣኤ በዓል መዋያ ዶሮ እና ሌሎች ሸቀጣ ሸቀጦችን ሲገዙ አግኘናቸው፡፡ እንደ ወይዘሮ ስፈልግ ገለጻ የበዓል ዋዜማ የዶሮ ዋጋ ስለሚያሻቅብና ግርግር ስለሚበዛ ቀደም ብለው ለመግዛት ወደ ገበያ ወጥተዋል፡፡

ይሁን እንጂ ከጠበቁት በላይ ዋጋ ጨምሯል፤ አንድ ዶሮ እስከ 400 ብር ይጠራል፤ ይህ ደግሞ ከኑሯቸው ጋር ተመጣጣኝ አልሆነም፡፡ የትንሣኤ በዓል ሲከበር እንቁላልና ዶሮ መሥራት የተለመደ ነው ያሉት ወይዘሮ ስፈልግ እንደአቅማቸው ገዝተው ለመጠቀም አስቸጋሪ እንደሆነባቸው ተናግረዋል፡፡ ዋጋው ከመጨመሩ ባሻገር አቅርቦቱም አነስተኛ በመሆኑ ተዟዙረው መግዛት እንዳልቻሉ ጠቁመዋል፡፡

ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር በማርና ቅቤ ንግድ ላይ የተሰማራችው ወይዘሪት ረድኤት ከሰተ ናት፡፡ ረድኤት የትንሳኤ በዓል መቃረቡን ተከትሎ የቅቤ ዋጋ መጨመሩን ነግራናለች፡፡ ተጠቃሚው የጊዜውን ሁኔታ ተመልክቶ እየገዛ ቢሆንም የምርቱ አለመኖር ዋጋው እንዳይረጋጋ አድርጎታል ብላለች፡፡ ማኅበረሰቡ ከበዓል ቀድሞ የመግዛት ልምዱን ቢያዳብር ስትልም መልዕክት አስተላልፋለች፡፡

አቶ ባንቴ አንተነህ በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ቀበሌ አራት ላይ ዘይትን ጨምሮ ሌሎች ሸቀጣ ሸቀጦችን ይሸጣሉ፡፡ አቶ ባንቴ የዘይት፣ የሽንኩርትና የቲማቲም ዋጋ መቀነሱን ነግረውናል፡፡ የዘይት ዋጋ ግን ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የጨመረ ቢሆንም ካለፈው ወር ጋር ሲነጻጸር ግን የ20 ብር ቅናሽ አለው ብለዋል፡፡ ይህም ተጠቃሚው በዓልን ሳይቸገር እንዲውል ያግዛል ነው ያሉት፡፡

የበዓል ወቅትን ተከትሎ የሚከሰትን የዋጋ ጭማሪና የገበያ ግርግር ለማለፍ ተጠቃሚው የማይበላሹ ሸቀጣ ሸቀጦችን ቀድሞ መግዛት ቢችል ሲሉም አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

Source link

Related posts

‹‹ተለመነኝ መዛርድ፣ ተለመነኝ ዘወልድ ባክህ ስንየ ስገድ እሺ በለኝ ክፍሎ፣ ራያና ቆቦ ዋጃና አላማጣ መሆኒና ጨርጨር ከደጋጎች ሀገር ልቤ ይርጋ ወሎ።››

admin

ፈረጅን  በመለማመጥ  ለኢትዮጵያ  ምንም ጠብ የሚል  መና  አይኖርም    (በአሥማማው  ተሻማሁ)

admin

በአንኮበር ወረዳ የወፍ ዋሻ ተብሎ በሚጠራው ደን ላይ የተነሳውን የእሳት ቃጠሎ ለመቆጣጠር ከአቅም በላይ እንደሆነበት የወረዳው አስተዳደር ገለጸ፡፡

admin