27.09 F
Washington DC
March 8, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

የገንዲ በሽታ አሁንም ትኩረት ይሻል

የገንዲ በሽታ አሁንም ትኩረት ይሻል

ባሕር ዳር፡ የካቲት 04/2013 ዓ.ም (አብመድ) የገንዲ በሽታ በእንስሳቶቻቸው ላይ ጉዳት እያደረሰባቸው እንደሚገኝ አብመድ በስልክ ያነጋገራቸው የቋራ ወረዳ አርሶ አደሮች ገልጸዋል፡፡

አርሶ አደሮች እንደገለጹት ዳልጋ እና የጋማ ከብቶቻቸው በገንዲ በሽታ ተጠቅተዋል፡፡ ይህም በወተት እና ስጋ ምርት ብቻ ሳይሆን በእርሻ እንቅስቃሴያቸው ላይ ችግር መፍጠሩን አንስተዋል፡፡ መንግስት የኬሚካል ርጭት እና ሕክምና በተደራጀ መንገድ እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡

የቋራ ወረዳ እንስሳት ሃብት ጽሕፈት ቤት የእንስሳት ጤና ባለሙያ ኑሩ ይማም እንደገለጹት በወረዳው በሚገኙ በሽታው በታየባቸው 17 በርሃማ ቀበሌዎች ርጭት ተካሂዷል።

ከጥር 19/2013 ዓ.ም ጀምሮ በ14 ቀናት ከ50 ሺህ በላይ የዳልጋ እና የጋማ ከብቶችን የኬሚካል ርጭት ተደርጓል፤ በበሽታው ለተጠቁ እንስሳትም ህክምና እየተሰጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል። ይሁን እንጅ የኬሚካል እጥረት በማጋጠሙ በሽታው የተከሰተባቸውን ቀበሌዎች ሙሉ በሙሉ ርጭት ማካሄድ አለመቻሉን ባለሙያው ነግረውናል፡፡

በአማራ ክልል በሽታውን ለመከላከል የተቋቋመው የፍኖተሰላም ቆላ ዝንብ እና ገንዲ በሽታ ቁጥጥር ማዕከል ተወካይ ኃላፊ ዶክተር አያና ሰላሙ እንደገለጹት ደግሞ በኢትዮጵያ 220 ሺህ ካሬ ኪሎ ሜትር የሚሽፍን ቦታ በቆላ ዝንብ እና የገንዲ በሽታ ተጠቂ ነው፡፡

በአማራ ክልል ደግሞ በአራት ዞኖች የሚገኙ 20 ወረዳዎች በቆላ ዝንብ እና የገንዲ በሽታ ተጠቂዎች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ በእንስሳት ላይም ጉዳት እያስከተለ ይገኛል ተብሏል፡፡ ችግሩንም ለመቅረፍ ማዕከሉ ወደ ተግባር ከገባ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በ11 ወረዳዎች የቁጥጥር እና የመከላከል ሥራ መሥራት ተችሏል፡፡ በዚህ በጀት ዓመትም በ9 ወረዳዎች ለ200 ሺህ የዳልጋ እና የጋማ ከብቶች የኬሚካል ርጭት ሥራ ተከናውኗል፡፡

በሽታውን ለመቆጣጠር ለ8 ወር የሚያገለግል በኬሚካል የተነከረ 2 ሺህ 500 የመከላከያ ቁስ ተዘጋጅቷል ተብሏል፡፡ የእንስሳት ሕክምና መሰጠቱንም ገልጸዋል፡፡ በቀጣይ ከየካቲት እስከ ሰኔ መጨረሻ እንስሳት በማይደርሱባቸው አካባቢዎች ጭምር የመሬት ለመሬት ኬሚካል ርጭት እንደሚካሄድ ዶክተር አያና ነግረውናል፡፡ ይሁን እንጅ የቅንጅት ሥራ ችግር፣ በባለሙያ እና በተሸከርካሪ እጥረት ሁሉንም አካባቢዎች ተደራሽ ማድረግ አለመቻሉን ዶክተር አያና ገልጸዋል፡፡

የአማራ ክልል እንስሳት ሃብት ልማት ማስፋፊያ ኤጀንሲ የእንስሳት ጤና ዳይሬክተር ዶክተር ታምሩ ተሰማ እንዳሉት ደግሞ በሽታው በአባይ ተፋሰስ በሚገኙ ወረዳዎች ላይ ጎልቶ ይታያል፡፡ በሽታውን ለመከላከል ኬሚካል ርጭት ሥራ መሠራቱን ተናግረዋል፡፡ በሽታው መድኃኒቱን በመላመዱ እንደገና እያገረሸ እንደሆነ አንስተዋል፡፡ በወተት እና ስጋ ምርት ላይም ከፍተኛ መቀነስ እያስከተለ እንደሚገኝ ነው የገለጹት፡፡

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

Source link

Related posts

በመዲናዋ የሚስተዋለውን የትራንስፖርት እጥረት ለመፍታት በትራንስፖርት ዘርፍ ከተሰማሩ ማህበራት ጋር ምክክር ተካሄደ

admin

‹‹የኢትዮጵያን አፈር ጭረው፣ ልጅ አሳድገው፣ ተምሮ ሀገርና ቤተሰብ ይቀይርልናል የሚሉ ዜጎች በገዛ መሬታቸው ላይ መጤ ተብለው ሲገደሉ ሲሳደዱ፣ መስማትና ማዬት ያማል›› ታማኝ በየነ

admin

የህወሃት መሪዎች ላይ የተወሰደው ርምጃና የመተከሉ ጥቃት…!!! (D.W)

admin
free web page hit counter