69.89 F
Washington DC
June 20, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

የደብረታቦር ጠቅላላ ሆስፒታል የሚያረካ አገልግሎት እየሰጠ አለመሆኑን ተገልጋዮች ገለጹ፡፡የደብረታቦር ጠቅላላ ሆስፒታል የሚያረካ አገልግሎት እየሰጠ አለመሆኑን ተገልጋዮች ገለጹ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 18/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የደብረታቦር ጠቅላላ ሆስፒታል ከተመሠረተ ዘጠና ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡
በተያዘው ዓመት መጀመሪያ ደግሞ ወደ ጠቅላላ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ተሸጋግሯል:: ሆስፒታሉ የሰሜን ወሎ እና ማዕከላዊ
ጎንደር አጎራባች ወረዳዎችን ጨምሮ ሁለት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ለሚገመት ሕዝብ የህክምና አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል::
የሆስፒታሉን አጠቃላይ አገልግሎት አስመልክቶ ያነጋገርናቸው ተገልጋዮች እንዳሉት በሆስፒታሉ በቂ የመድኃኒት አቅርቦት እና
ምርመራ እያገኙ አይደለም፡፡
ተገልጋዮች መካከል አቶ አበባው ጀምበር እንደነገሩን በልብ ድካምና ደም ግፊት የታመሙት እናታቸው በሆስፒታሉ ድንገተኛ
የህክምና ክፍል ለመታከም 16 ቀናትን መጠበቅ ነበረባቸው፡፡ ይሁን እንጅ ህክምናውን ካላገኙ ለሕይወታቸው አደጋ መሆኑን
በመረዳት ሁለት ሺህ ብር ከግል ጤና ተቋማት ናሙና ለማሠራት መገደዳቸውን ነግረውናል፡፡ ይህም ለከፍተኛ ወጭ
እንደዳረጋቸው አንስተዋል፡፡
በሆስፒታሉ የህጻናትና የድንገተኛ ክፍል ባለሙያው ፋሲል ብርሃኑ የሆስፒታሉ ደረጃ ካደገ በኋላ ከሠሜን ወሎ አጎራባች
ወረዳዎች ጭምር አገልግሎቱን ለማግኘት ተግልጋዮች ወደ ሆስፒታሉ የሚያቀኑ በመሆኑ የተገልጋዩ ፍሠት ጨምሯል፤ የግብዓት፣
የማስፋፊያ፣ የመሠረተ ልማት ግንባታ አለመሟላት እና የባለሙያ እጥረት የአገልግሎት አሰጣጡን አውርዶታል::
በጥር/2013 ዓ.ም ብቻ በስድስት አልጋዎችና በ10 ባለሙያዎች 1 ሺህ 500 ህጻናት ማስተናገድ መቻሉን ለአብነት ጠቅሰዋል።
ህሙማን ተኝተው የሚታከሙበት አልጋ ባለመኖሩ ምክንያት በወንበርና በህሙማን መቀበያ የተሸከርካሪ አልጋ ላይ ለመስጠት
መገደዳቸውን ጠቁመዋል:: ድንገተኛ የሆነና ያልሆነው ተለይቶ ክትትል የሚደረግበት፣ እያንዳንዱ ራሱን የቻለ ክፍል
ቢያስፈልገውም በአሁኑ ወቅት አገልግሎቱ እየተሰጠ ያለው በአንድ ክፍል መሆኑን ተናግረዋል። ይህም በተገልጋይ ፍሠቱ ልክ
አገልግሎት መስጠት እንዳይቻል ማድረጉን አስረድተዋል።
በሆስፒታሉ የላብራቶሪ ባለሙያ አቶ ፍቅር ደስታው እንዳሉት የጉበት እና የኩላሊት ምርመራ ቁሟል። የኬሚስትሪ ማሽን
በግብዓት አቅርቦት እና መቆራረጥ ችግር ምክንያት ከአገልግሎት ውጪ የሚሆንበት ጊዜ ሰፊ መሆኑንም ነግረውናል፡፡ ብዙ
የላብራቶሪ ምርመራዎች በኬሚካል አቅርቦት ችግር ከሆስፒታሉ ውጪ እንዲሠራ እየተላከ መሆኑን በመግለጽ በማሕበረሰቡ
የተነሳው ቅሬታ ተገቢነት ያለው መሆኑንም ባለሙያው አንስተዋል፡፡
የሆስፒታሉ ተወካይ ሥራ አስኪያጅና ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር አዲስ ደርበው እንደገለፁት ሆስፒታሉ በመሠረተ ልማት፣ በሰው
ኀይል፣ በህክምና መሣሪያና በግብዓት ሙሉ መሆኑ ሳይረጋገጥ በጠቅላላ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ደረጃ ማደጉ የተገልጋይ
ፍሠቱን እንዲጨምር ከማድረግ ውጭ ያስገኘው ውጤት የለም፤ አሁንም ወደ ሌሎች ሆስፒታሎች ህሙማንን ከመላክ
አልወጣም፡፡ ባለፈው ዓመት ሁለት ሺህ፣ በተያዘው ዓመት የመጀመሪያው ስድስት ወራት ብቻ ደግሞ አንድ ሺህ 50 ህሙማንን
(የአጥንት ህክምና ሳይጨምር) ወደ ሌላ ጤና ተቋም መላኩን ለአብነት አንስተዋል:: በተለይም ደግሞ የሲቲ ስካን፣ የእንቅርት
ምርመራ፣ የቀዶ ጥገና ህክምና፣ የነርቭ ችግርና የራዲዮሎጂ ምርመራ ባለሙያ ባለመኖሩ ምክንያት ወደ ሌላ የጤና ተቋም
ከተላኩት ከፍተኛውን ደረጃ ይይዛሉ፡፡ በሆስፒታሉ የሚስተዋለውን የውኃ ችግር ለመፍታት 700 ሺህ ብር መጠየቁን ገልጸዋል፡፡
ለዚህ ደግሞ የመንግሥት ድጋፍ እንደሚያስፈልግ እና የሆስፒታሉን የ90ኛ ዓመት ምስረታ ምክንያት በማድረግ ቴሌቶን
በማዘጋጀት በሚገኘው ገቢ የውኃ ችግሩን ለመፍታት መታሠቡን ነግረውናል። በዚህም ሁሉም ኅብረተሰብ ለሆስፒታሉ
የበኩላቸውን እንዲወጡ የድጋፍ ጥሪ አስተላልፈዋል። ሆስፒታሉ የደረጃ እድገት ከተሠጠው በኋላ የጽኑ ህሙማን ህክምና፣
የአጥንት ህክምና፣ የላብራቶሪ አገልግሎት መስጫ ክፍልን ማስፋት፣ የኮሮና ቫይረስ ምርመራ፣ የካልቸር ላብራቶሪ ምርመራ
(ህመሙ የሚፈልገውን መድኃኒት ለመለየት የሚያግዝ) አገልግሎት አስጀምሯል።
በአማራ ክልል ጤና ጥበቃ ቢሮ የህክምናና ተሀድሶ አገልግሎት ዳይሬክተር አበበ ተምትሜ እንደገለጹት የጤና ተቋማት የደረጃ
ማሻሻያ ሲሠራ የሰው ኀይል፣ አሠራር፣ ግብዓትና የግንባታ ጉዳዮችን መሰረት ተደርጎ ነው የተሰራው፤ በዚህም ዝቅተኛ መስፈርቱን
አሟልተው የተገኙ 12 ሆስፒታሎች ወደ ጠቅላላ ሆስፒታል አድገዋል፤ ደብረታቦር እና ወልዲያ ሆስፒታሎች ደግሞ ወደ ጠቅላላ
ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል አድገዋል፡፡ ጠቅላላ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታሎች የደረጃ ማሻሻያ ሲሠጣቸው በሂደት ሙሉ አገልግሎት
የሚሠጡበትን ግብዓት ለማሟላት ታሳቢ በማድረግ እንደሆነም አንስተዋል፡፡ የበጀት ውስንነት እና ልዩ ሙያን የሚጠይቁ
የአገልግሎት ዘርፎች መኖራቸው በሆስፒታሎች ለሚነሱ ችግሮች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት መቸገራቸውን አቶ አበበ አንስተዋል::
ጠቅላላ ሆስፒታሎች ሊኖራቸው የሚገባው ከፍተኛው የሰው ኀይል ከ 315 እንደማይበልጥ የገለጹት ባለሙያው በአሁኑ ወቅት
ግን ደብረታቦር ጠቅላላ ሆስፒታል ወደ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በማደጉ የሰው ኀይል ቁጥሩ ወደ 503 ማደጉን ዳይሬክተሩ
ገልጸዋል::
የዓይን፣ የሥነ ዐዕምሮ፣ የአጥንት፣ የአዋቂና የሕፃናት ጽኑ ሕሙማን ሕክምና አገልግሎቶች መጀመራቸው በደረጃው ልክ ሕክምና
ለመስጠቱ ማሳያ መሆኑንም አንስተዋል፡፡ የነርቭ እና ከአንገት በላይ ህክምና በሆስፒታሉ ለማስጀመር የሰው ኀይል በገበያ ላይ
ለማግኘት አለመቻሉን አንስተዋል፡፡ በቀጣይ ከግንባታ፣ ከግብዓትና ከሰው ኀይል ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመፍታት የአጭር፣
የመካከለኛ እና የረጅም ጊዜ ዕቅድ ተይዞላቸዋል:: ቦርዱም ሆስፒታሉን ከሕዝቡ ጋር ከማገናኘት ባለፈ ሀብት የማፈላለግ ሥራ
በመሥራት ውድ የህክምና መሳሪያዎችን ለማሟላት እንዲሠራ ይደረጋል ብለዋል፡፡ ወደ ሆስፒታሉ የሚደረገውን የህሙማን ፍሰት
ለመቀነስ የመጀመሪያ ደረጃ እና የጠቅላላ ሆስፒታሎችን አቅም ማጎልበትና አገልግሎት አሠጣጣቸውንም ማሻሻል ላይ ትኩረት
መደረጉን ተናግረዋል:: ለዚህም የውስጥ ደዌ፣ የጠቅላላ ቀዶ ህክምና፣ የማህፀንና ጽንስ ስፔሻሊስት እንዲሁም የህጻናት
ህክምና ስፔሻሊስት ሀኪሞችን በሁሉም ጠቅላላ ሆስፒታሎች ለማሟላት ጥረት እየተደረገ ነው::
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
Previous articleየኮሮናቫይረስ ስርጭት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን የአማራ ክልል የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
Next articleወደ ሀገር ዉስጥ ሊገባ የነበረ ከመቶ ሰማንያ ሺህ በላይ የእጅ ገጀራ በቁጥጥር ስር ዋለ::

Source link

Related posts

የተፈራው አልቀረም ሙሉ ነጋ(ዶ/ር)  ዳግማዊ ስብሃት ነጋን ሆነው መጥተዋል!?! (ታምሩ ገዳ)

admin

በአማራ ክልል ውስብስብ መሬት ነክ ችግሮችን በቀላሉ ለመምራት፣ ሕገወጥነትን ለመከላከልና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት እየሠራ መሆኑን ኤጄንሲው አስታወቀ፡፡

admin

ሕዝቡ የተገነባበትን የባህላዊ፣ የዘመናዊ እርቅና የሰላም ተቋማትን በማጠናከር ሀገርና ሕዝብን ማዳን እንደሚገባ ተገለጸ፡፡

admin