40.51 F
Washington DC
April 17, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋው ይቁም፣ጨፍጫፊዎቹም ለፍርድ ይቅረቡ! | Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider

በኢትዮጵያ ላለፉት ሰላሳ ዓመታት በሕዝብ ላይ በተለይም በአማራው ማህበረሰብ ላይ ዘርንና ሃይማኖትን የለዬ ጭፍጨፋ በተከታታዬ መፈጸሙ አገር ያወቀው ጸሃይ የሞቀው ወንጀል ነው።ይህ ወንጀል በዓለምአቀፍ ሕግ የሚያስጠይቅና ወንጀሉንም የፈጸሙትንና ያስፈጸሙትን ለከፍተኛ ቅጣት የሚዳርግ ነው።

በተደጋጋሚ በማስረጃ እንደተረጋገጠው የዘር ማጥፋቱ ወንጀል የተቀነባበረው ላለፉት ሰላሳ ዓመታት በጉልበት አገሪቱን የተቆጣጠረው ኢሕአዴግ በሚል ጭንብል የተደራጀው የጎሳ ፖለቲካ የሚያራምደው አምባ ገነን ቡድን ነው።ይህ አምባገነን ቡድን በጋራ በሕዝብ ላይ የፈጸመው ልዩ ልዩ ወንጀል ተጠራቅሞ በሃያ ሰባት ዓመቱ የግፍ ጽዋው ሲሞላ በሕዝቡ ትግልና ተቃውሞ የሥልጣን መንበሩን የነቀነቀው ሲሆን፣አብሮ ብዙ ወንጀሎችን የፈጸመው ስብስብ በውስጥ ሽኩቻ ተንጦ አንዱ በሌላው ላይ እንዲነሳ አድርጎታል።የሥልጣን ባለቤትነቱንም ተነጣጥቋል።ይህ የሥልጣን ግብግብ ግን ስብስቡ የተነሳበትን የዘር ፖለቲካ ዓላማውን አጠናከረው እንጂ የተለዬ አላደረገውም።በነደፈው አገር አጥፊና ሕዝብ አጫራሽ መመሪያ ሰነድ እዬታገዘ ይባስ ብሎ ጭፍጨፋውና አገር የመናዱ ሴራ በአንድ የተጠናከረ፣ሥልጣኑን በተቆጣጠረው የኦሮሞ ጎሳ ድርጅት፣ኦነግ/ኦህዴድ/ብልጽግና እያለ ስሙን እዬቀያዬረ በሚያምታታው ቡድን መዳፍ ላይ ጥሎታል።ወንጀሉም በዚሁ ተረኛ ቡድን የሚፈጸም ለመሆኑ ከበቂ በላይ ማስረጃዎች ያመላክታሉ።

በለውጥ ሽፋን ላለፉት ሶስት ዓመታት ሥልጣኑን የነጠቀው የኦነግ /ኦህዴድ ቡድን ብልጽግና በሚል የዳቦ ስም በተለያዩ ያገሪቱ ክፍሎች ግድያና ዘረፋውን በተቀናጀ፣መንግሥታዊ ተሳትፎና ትዕዛዝ የተፈጸመ መሆኑን በጥቅም ከተለዩት ከራሱ ደጋፊዎችና ከሞት የተረፉ ጥቃት ከደረሰባቸው ዜጎች አንደበት በተደመጠው የቃል ምስክርነት፣እንዲሁም ከሰብአዊ መብት ድርጅቶችና ጋዜጠኞች የክትትል ጥናት ተረጋግጧል።

ይህ የዘር ጭፍጨፋ ወንጀል በመንግሥት የሚደገፍና የወንጀሉም ማስፈጸሚያ መሳሪያ በመንግሥት እንደሚታደል ወንጀለኞቹ ከያዙት መሳሪያና ትጥቅ እንዲሁም በፈለጉት ቦታ ለመንቀሳቀስ የሚያስችል ነጻነት፣የመጓጓዣ አቅርቦት፣የኮምፒውተርና የስልክ አገልግሎት መሟላት በተራ ሽፍታ አቅም እንዳልሆነ ያረጋግጣል።መንግሥት በሚቆጣጠረው ከተማ መሃል እዬተንጎራደደ፣ነጭ ዳስ ጥሎ ቅስቀሳ የሚያደርግ ሽፍታ በታሪክ ታይቶ አይታወቅም።

ይህንን የተቀናጀ የመንግሥት ወንጀል ለመሸፋፈን የቡድኑና የተረኛው ጎሳ መሪ የሆነው ጠ/ሚኒስትር ነኝ ባዩ አብይ አህመድ ለፓርላማ ተብዬው ለራሱ አጨብጫቢ ስብስብ በቅርቡ ማብራሪያ በሰጠበት ወቅት ፣ለይስሙላ ለሚገደለው ዜጋ የሚቆረቆር መስሎ “ ኦሮሞን አምኖ የመጣ ነው፣በጊዜ ብዛት ኦሮሞ ሆኗል፣መገደል የለበትም” ሲል ተደምጧል።ይህ ማለቱ ኦሮሞ የሆነው ወይም የኦሮሞን ጥቅም የሚያስጠብቀው፣በሞጋሳ ህሳቤ የተጠመቀው አይገደል ሌላው ግን ይገደል የሚል ውስጠ ወይራ መልእክት ያዘለ ነበር።በሌላም መልኩ “ኦሮሞን ኦሮሞ አይገለውም” በማለት ኦሮሞ ያልሆነው ቢገደል አግባብ እንደሆነ በሾርኒ ገልጾታል።የዚህ ህሳቤ ባለቤት ደግሞ ኦነግ የተባለው የአብይና የመሰሎቹ የጡት አባት የሆነው ድርጅት ነው።የዚሁ የኦነግ መሪዎች እነ ዲማ ነገዎ፣አሁን የአብይ አህመድ አማካሪ የሆኑት ከሰላሳ ዓመት በፊት በአደባባይ ከአዲስ አበባም ሆነ በሌላው የኦሮሞ መሬት የሚኖረው ኢትዮጵያዊ የሚጠቅመው መኖሪያ ፈቃድ ተሰጥቶት ይኖራል፤የማይጠቅመው ደግሞ ወደ ዬመጣበት ተጠፍንጎ ይመለሳል ብለው ነበር።ይህንን አባባል ነው ሰሞኑን ከሰላሳ ዓመታት በዃላ አብይ አህመድ በአደባባይ የደገመው። በተጨማሪም ባሰማው ዲስኩር ኢትዮጵያውያኑ” በሰላም እንኖራለን ብለው ወደ ኦሮሞ አገር የመጡ ምስኪኖች ናቸው” በሚል ሁኔታውን የአንድ አገር ዜጋ ወይም ዜጎች ወደ ሌላ አገር ሄደው ስደተኝነት ጠይቀው እንደሚኖሩት አስመስሎ ገልጾታል።በአገራቸው በመረጡት መሬትና ቦታ የመኖር መብት እንዳላቸው እውቅና የሚሰጥ ንግግር አልነበረም።የአብይ አህመድ ቡድን በሚናገረውና በሚሠራው የመሸፋፈን ሥራ፣ የዘር ማጥፋቱ ወንጀል በዚህና በተመሳሳይ አቋሞች ላይ የተቀናበረ ለመሆኑ ግልጽ ማስረጃ ነው።”ኢትዮጵያ አትፈርስም” በሚል ቃል እያነሆለለ የማፍረሻ ደባውን ግን ውስጥ ለውስጥ እያራመደ ነው።ኢትዮጵያን የሚያፈርሰውን መመሪያም ሕገመንግሥቴ ነው ብሎ መጠቀሙ ኢትዮጵያ አትፈርስም የሚለውን አባባሉን ፉርሽ ያደርገዋል።የሚባለው

ሌላ ፣የሚሆነው ሌላ፤ ውዥንብሩ መጥራት አለበት።አባ ገዳም የተባለው የኦሮሞ ባህላዊ መሪዎች ስብስብ ሰሞኑን ለጥቃት የተጋለጡትን “ የሚከላከልላችሁ ስለሌለ ለቃችሁ ውጡ” ሲሉ የአዘኝ ቅቤ አንጓች ምክራቸውን ለግሰዋል።ግራ የተጋባውና የጨነቀው ለዓመታት የኖረ ሕዝብ በተለይም የአማራ ተወላጅ ህይወቱን ለማትረፍ ሲሄድ ባዶ እጁን እንዲወጣ ተፈርዶበታል።ልብስ ሳይቀር የኦሮሞ ንብረት ነው ተብሎ ተነጥቋል።በብዙ ሽህ የሚቆጠር ሕዝብ ያፈራውን ንብረት ጥሎ እግሩ እንደመራው እዬነጎደ ነው።ሲወጣም በዬኬላው የኮቴ ግብር እንዲከፍል ይገደዳል። በሄደበት ቦታ መጠለያና ምግብም በማጣት ለስቃይ ተዳርጓል።ህጻናት፣ሴቶችና አዛውንት፣ ለዳግመኛ መከራ ተጋልጠዋል።ይህም የወንጀሉ አካል ተደርጎ መወሰድ ይኖርበታል።ኢትዮጵያውያን በሙሉ ለነዚህ ወገኖቹ የተቻለውን እርዳታ እንዲያደርግ ጥሪ እናደርጋለን።

የዓለም አቀፍ የኢትዮጵያውያን የትብብር መድረክ የተመሰረተበት ዓላማ የተበታተነውን ለአንድነትና ለዴሞክራሲ የሚታገለውን ሃይል ለማስተባበር በመሆኑ አሁንም ሁሉም አገር ወዳድ በአንድ ላይ እንዲቆም ጥረት ያደርጋል። ለመተባበር ከሚያስችሉት የጋራ ጉዳዮች መሃል አሁን በሕዝብ ላይ የሚፈጸመው የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ ወንጀል ነው። አሁን በሥልጣን ላይ ያለው የኦህዴድ/ብልጽግና መንግሥት በወለጋ፣በቤንሻንጉል፣በትግራይ እንዲሁም በሌሎች ያገሪቱ ክፍሎች ለሚፈጸመው ለዘር ማጥፋቱ ጭፍጨፋ ወንጀል ተጠያቂ ነው ብሎ ያምናል።ይህ ቡድን ከወንጀል አስፈጻሚና ፈጻሚዎቹ ጋር ለፍርድ መቅረብ አለበት ይላል።ይህንን ለመተግበር ለሕግ ባለሙያዎችና ለሰብአዊ መብት ድርጅቶች ጥሪ ያደርጋል።

ለቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ማስተላለፍ የሚወደው መልእክት፣ ግፍ የሚፈጸምባቸውን ወገኖቹን በተለይም የግፍ ሰለባ የሆነውን የአማራ ማህበረሰብና የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ ለማዳን፣ የአገሩን ህልውናና የራሱን የመኖር መብት ለማስከበር ተባብሮ በተቀናጀ መልኩ እንዲነሳ ጥሪ ያደርጋል። በሕግ አደባባይ የሚፈታውን በሕግ፣በጦርሜዳ የሚፈታውን በጦር ሜዳ ለመፋለም ዝግጁና ቆራጥ መሆን እንዳለበትም ሊያስገነዝብ ይወዳል።የአገር አንድነትና የሕዝብ መብት በልመናና በፍርሃት የሚረጋገጥ ሳይሆን ወቅቱና ሁኔታው የሚጠይቀውን ዝግጅትና ፍልሚያ ሲያደርጉ መሆኑን በአጽንኦት ሊያሳስብ ይወዳል።ሕግ ያልገዛውን መብት ሃይል ይገዛዋል!።ለዚህ የሕዝብና የአገር ህልውና የዓለም አቀፍ ኢትዮጵያውያን መድረክ የድርሻውን ለማበርከት ዝግጁ ነው።ቀደም ሲልም በኔዘርላንድ ዴንሃግ ውስጥ ለሚገኘው ለዓለም አቀፍ የወንጀለኞች ፍርድቤት የአቤቱታ ደብዳቤውን አቅርቧል፣አሁንም ለማቅረብ ማስረጃዎችን እያሰባሰቡ ካሉት ጋር ለመተባበር ዝግጁ መሆኑን ይገልጻል።ምርጫችን ጦርነትና ግጭት ባይሆንም በሰላማዊ መድረክም ላይ ቢሆን መደመጥ የሚቻለው የሚያስተማምን ሃይል፣ጉልበትና እውቀት አጣምረው ሲገኙ መሆኑን ያምናል።

ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ የአገር ልዑላዊነት በውጭ አገር ወራሪ ሃይሎች መደፈርና የድንበር መሬት በወረራ መያዙ፣ ከዚሁ ብሔራዊ ግዳጅ ተነጥሎ መታዬት እንደሌለበትና አገራችንን ለዚህ ተጨማሪ ውድቀት ያበቃት፣በር የከፈተው፣ቀድሞም ሆነ አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት የሚከተለው ጸረ ኢትዮጵያ የሆነው የጎሳ ፖለቲካው እንደሆነ አይካድም።ይህ ደግሞ ትግሉን በውጭና በውስጥ ባሉ መንታ ጠላቶች ላይ የሚሰነዘር ጣምራ ትግል ያደርገዋል።ለዚህ ትግል ብቃትና ዝግጅት ይጠይቃል።

አሁን የውጭ ሃይሎች የሚያደርጉት እርብርቦሽ የተወገደውን ህወሃት መልሶ የዓላማው ተሸካሚ ከሆነው አጋሩ

ኦነግ/ኦህዴድ/ብልጽግና ቡድን ጋር አስማምቶ ስርዓቱን የማስቀጠሉ ደባ ስለሆነ ከበጎ የሰብአዊ መብት ተግባርና ቅንነት አኳያ መታዬት የለበትም።ለኢትዮጵያና ለሕዝቡ ቢያስቡ ኖሮ የጎሳ ፖለቲካን ያወግዙ ነበር።የነሱ ጸረ ኢትዮጵያዊነት በአባይ ግድብ ዙሪያ ግብጽን ደግፎ ከመቆምና ሱዳን ወረራ መፈጸሟን በዝምታ ማለፋቸው አመላካች ነው።የኤኮኖሚም ተአቅቦ ማድረጋቸውና ለማድረግም መከጀላቸው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዴሞክራሲና ለአንድነት ከበቃ በሌሎቹም የአፍሪካ አገራት ምሳሌ ሆኖ ጥቅማቸውን ሊጻረር የሚችል ሃይል ሊፈጠር ይችላል ከሚል ስጋት በመነሳት ነው።ስለዚህ ለመቀጣጫ ኢትዮጵያ ብትበታተንና የጭዳ በግ ብትሆን ደንታ የላቸውም። ስለሆነም የኢትዮጵያ ሕዝብ በነሱ መተማመኑንና መለመኑን ትቶ በራሱ አቅም መተማመን አለበት፤የነጻነትም ሃሁ ከዚህ ይጀመራል።በሌሎቹ አገሮች የደረሰው ጉዳት የባዕዳኑ ጣልቃ ገብነት ውጤት መሆኑን መዘንጋት አያስፈልግም። በተቃውሞ ጎራ ተሰልፈናል የሚሉትም የፖለቲካ ድርጅቶች የተሻሉ ፈረሶች ለመሆን የባእዳኑን ቡራኬ ከመሻት ይልቅ ለሕዝባቸውና ለአገራቸው ታማኝና ቀናኢ ሆነው መቆም ይኖርባቸዋል።በመካከላቸው ያለውን ሽኩቻ አቁመው ተባብረው ሕዝቡን እንዲያስተባብሩ የዓለም አቀፍ የኢትዮጵያውያን የትብብር መድረክ ጥሪ ያደርጋል። በየጊዜውና በዬቦታው በተበታተነ መልክ የሚደረገው የገንዘብ ማሰባሰብና የዲፕሎማሲ ትግል በአንድ የጋራ “አገር አድን” መርሆ በተደራጀ ግንባር ስር ቢሆን ከብክነትና ከድክመት ያድናል።አብሮ የመሥራቱንም ባሕል ያጎለብታል።

ኢትዮጵያ በልጆቿ አንድነትና ትግል ለዘለዓለም ተከብራ ትኑር!

 

 

 

Source link

Related posts

“ሩጫው የተገታው ባቡር” | የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት

admin

በአማራ ክልል ሰሜን ሽዋ ዞን በአጣየ አካባቢ የተከሰተውን የጸጥታ ችግር መንግሥት በአስቸኳይ እንዲፈታ ነዋሪዎች ጠየቁ፡፡

admin

የጋምቤላ መምህራን ትምህርና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ 2496 ተማሪዎችን አስመረቀ

admin