76.62 F
Washington DC
June 15, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

“የውጭ ሀገራትን ጫና መቋቋም የምንችለው አንድነታችንን አጠንክረን ከድህነት መውጫ መንገዱን ስናመቻች ነው” የአማራ ክልል ሕዝብ ሽምግልና ሥርዓት ማኅበር

“የውጭ ሀገራትን ጫና መቋቋም የምንችለው አንድነታችንን አጠንክረን ከድህነት መውጫ መንገዱን ስናመቻች ነው” የአማራ ክልል ሕዝብ ሽምግልና ሥርዓት ማኅበር

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 27/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ ላይ እየተደረገ ያለውን የውጭ ሀገራትን ጫና መቋቋም የሚቻለው ከድህነት በመውጣት መሆኑን የአማራ ክልል ሕዝብ ሽምግልና ሥርዓት ማኅበር ጸሐፊ አለሙ ጥሩነህ ተናግረዋል፡፡

የአማራ ክልል ሕዝብ ሽምግልና ሥርዓት ማኅበር፣ የአማራ ክልል አረጋውያን ማኅበር፣ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር የባሕር ዳር ቅርንጫፍ እና በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር አረጋውያን ማኅበር በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ሠጥተዋል፡፡

የአማራ ክልል ሕዝብ ሽምግልና ሥርዓት ማኅበር ጸሐፊ አለሙ ጥሩነህ የውስጥም ሆነ የውጭ ጫናን ለመቋቋም ከድህነት መውጣት ዋና መፍትሔ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ “ኢትዮጵያ በድህነት በመኖሯ በርካቶች ጫና ሊያሳድሩ ይፈልጋሉ፤ የውጭ ሀገራትን ጫና መቋቋም የምንችለው አንድነታችንን አጠንክረን ከድህነት መውጫ መንገዱን ስናመቻች ነው” ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያዊያን አንድነትን አጠንክረው መያዝ እንደሚጠበቅባቸውም አንስተዋል፡፡ በዘርና በቋንቋ የሚደረገው ልዩነት ለ30 ዓመታት የተሠራው የተሳሳተ ትርክት መሆኑን ነው አቶ አለሙ የገለጹት፡፡ ሽማግሌዎች የኢትዮጵያን ታሪክ ለወጣቶች እና ለልጆቻቸው በሚገባ የማሳወቅ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር አረጋውያን ማኅበር ሊቀመንበር ሊቀ ሕሩያን በላይ መኮንን አሁን የሚስተዋለውን የውጭ ሀገራት ጫና መመከት የሚቻለው በአንድነት መቆም ሲቻል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን አስጠብቃ ከመኖር በተጨማሪ የማንንም በር ያላንኳኳች፣ የሌላ ሀገር ድንበር ያልደፈረች፣ የማንንም ነጻነት ያልተጋፋች፣ ሊደፍሯት የመጡትን ግን በጀግኖች ልጆቿ ተጋድሎ አይቀጡ ቅጣት ቀጥታ የመለሠች ሉዓላዊት ሀገር መሆኗን ተናግረዋል፡፡

ቱርኮች፣ ግብጻውያን፣ ኢጣሊያ እና ሶማሊያ ድንበሯን ተሻግረው ሊወሯት እና ቅኝ ተገዥ ሊያደርጓት ቢፈልጉም ሳይሳካላቸው እንደቀረ ለአብነት አንስተዋል፡፡

አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር የምታደርገው ጥረት እና ጣልቃ ገብነት ሚዛናዊነት የጎደለው መሆኑን ነው የገለጹት፡፡ አሜሪካ ከግብጽ የምታገኘውን ጥቅም ለማስጠበቅ ስትል በኢትዮጵያ ላይ የምታደርገውን ጫና ማቆም አለባትም ብለዋል፡፡

ሊቀ ሕሩያን አሜሪካ ለማእቀቡ እንደመነሻ ያደረገችው ሕግ ማስከበር ዘመቻውን ይሁን እንጅ ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጋር በነበረው ድርድር የጀመረችው ጣልቃ ገብነት ባለመሳካቱ ነው ብለዋል፡፡

ሊቀ ሕሩያን ኢትዮጵያ ዓባይን ጨምሮ የበርካታ ተፈጥሮ ሃብት ባለቤት ናት፤ ይይን ፀጋዋን ባለመጠቀሟ ደግሞ ሕዝቦቿ በድህነት እየኖሩ ነው፤ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ደግሞ ከዚህ የድህነት አረንቋ መውጫ መሰላል ነው፤ የአሜሪካ መንግሥት ይሄን የድህነት መውጫ መሰላል ለመስበር እያደረገ ያለው ያልተገባ ጣልቃ ገብነት ሊቆም ይገባል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ሰላም በማድረግ ያበረከተችውን አስተዋጽኦ ጠቅሰዋል፡፡ በተለይ ሶማሊያ የተረጋጋች ሀገር ሆና እንደ ሀገር እንድትቀጥል ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጋር በጥምረት የሠራችው ሥራ ሰላምን አጥብቃ የምትሻ ሀገር መሆኗን ማሳያ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ለአፍሪካውያንም ብሎም ለዓለም የነጻነት ተምሳሌት የሆነች ሀገር እንደሆነችም ገልጸዋል፡፡

“የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያውያን ኹለተኛው የአድዋ ድል ነው፤ የተጋረጠብንን የድህነት አረንቋ መውጫ መሰላላችን ነው” ብለዋል ሊቀ ሕሩያን በላይ፡፡ በዚህ ጉዳይ ጎረቤት ሀገሮችም ሊያግዙን ይገባል ነው ያሉት፡፡

ሊቀ ሕሩያን በላይ በማብራሪያቸው ኢትዮጵያ ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አጠናቃ ሕዝቦቿ የተሻለ ኑሮ እንዲኖሩ ለማድረግ በምታደርገው ጥረት ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

Source link

Related posts

71 ሚሊየን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው መድኃኒቶችና የህክምና ግብዐቶች ወደ ትግራይ ተልከው እየተሰራጩ ነው

admin

የኢትዮጵያ ሳምንት ሊከበር ነው፡፡ | አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን

admin

የከተማው አስተዳደር ያዘጋጀው የጸሎተ ሀሙስ እና የረመዳን የኢፍጣር መርሐግብር ትናንት ምሽት ተካሂዷል

admin