73.2 F
Washington DC
June 14, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እያስከተለ ያለውን የከፋ ጉዳት በመረዳት ቅድመ መከላከል ሥራዎች ላይ ማተኮር እንደሚገባ ተገለጸ፡፡

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እያስከተለ ያለውን የከፋ ጉዳት በመረዳት ቅድመ መከላከል ሥራዎች ላይ ማተኮር እንደሚገባ ተገለጸ፡፡

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 20/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ወደ ሀገራችን ከገባ 14 ወራትን አስቆጥሯል፡፡ የፌዴራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እስከ ትናንት 19/2013 ዓ.ም ባወጣው መረጃ መሰረት

•በሀገር ደረጃ 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ያህል ሰዎች ተመርምረዋል፤

•270 ሺህ 527 ያህል ሠዎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል፤

•234 ሺህ 426 ያህሉ አገግመው ወደ ቤታቸው ሄደዋል፤

•4 ሽህ 127 ያህል ሰዎች ለህልፈት ተዳርገዋል፡፡

•ከ 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የኮሮናቫይረስ ክትባት ወስደዋል፤

እንደ አማራ ክልል ጤና ጥበቃ ቢሮ በ19/2013 ዓ.ም ባወጣው መረጃ መሰረት ደግሞ

•እስካሁን 287 ሽህ 637 ያህል ሰዎች ተመርምረዋል፤

•11 ሺህ 403 ያህል ሠዎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸውል፤

•7 ሺህ 457 ያህሉ አገግመዋል፤

•263 ያህል ሰዎች ለህልፈት ተዳርገዋል፡፡

ይህ መረጃ የሚያሳየው ወረርሽኙ እየከፋ እና እያስከተለ ያለው ጉዳት እየጨመረ መምጣቱን ነው፡፡ በዛ ልክ ደግሞ ቅድመ መከላከልን በተመለከተ መዘናጋቱ እየጎላ መምጣቱን መታዘብ ይቻላል፤ ለዛም ክትባቱን ተደራሽ ለማድረግ ከሚደረገው ጥረት ጎን ለጎን ቅድመ መከላከል ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ዘመቻዎች እየተካሄዱ ነው፡፡ ኅብረተሰቡ አሁንም የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ቅድመ መከላከል ላይ ሊያተኩር እንደሚገባ ነው አሚኮ ያነጋገራቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች የገለጹት፡፡

አቶ መሳፍንት እሸቴ በባሕር ዳር ከተማ የቀበሌ 16 ነዋሪ ናቸው፡፡ አቶ መሳፍንት ራሳቸውን እና ቤተሰባቸውን ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለመከላከል አዘውትረው የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ይጠቀማሉ፡፡ ቤተሰቦቸቻውም ለብሰው እንዲንቀሳቀሱ በየጊዜው የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ይገዛሉ፡፡ አቶ መሳፍንት እንደገለጹት በተለያዩ የብዙኃን መገናኛ የሚተላለፉ መረጃዎችን መሠረት አድርገው ጥንቃቄ እያደረጉ ነው፡፡ ሰዎች በብዛት በሚገኙበት ቦታ በሚሄዱበት ጊዜ የንፅህና መጠበቂያ ዘዴዎችን በአግባቡ ይጠቀማሉ፡፡ “በማኅበረሰቡ በኩል የሚታየው መዘናጋት ዋጋ እንዳያስከፍለንም እሰጋለሁ” ብለዋል፡፡ አስተያየት ሰጪያችን እንዳሉት ማኅበረሰቡ በብዛት ለቅድመ መከላከል ተብለው የተቀመጡ የንጽሕና መጠበቂያ መንገዶችን ተግባራዊ እያደረገ አይደለም፤ አንድም የግንዛቤ እጥረት አለበት፤ በሌላ በኩልም መረጃው ኖሮትም የማይጠቀመው ሰው በርካታ ነው፡፡ መንግሥት ያወጣቸውን መመሪያዎች ተግባራዊ በማድረግ የማኅበረሰቡን ደኅንነት ሊጠብቅ ይገባል ሲሉም ጠይቀዋል፡፡

ከአዲስ አበባ እንደመጣች የነገረችን ትዕግስት አስችሎ አዲስ አበባ ማንኛውም ሰው የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ሳያደረግ አይንቀሳቀስም፡፡ ወጣት ትግስት ቫይረሱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ ጉዳት እያደረሰ በመሆኑ ማኅበረሰቡ ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል ብላለች፡፡ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ መጠቀም ትንሹ መስዋዕትነት ነው ያለችው ትዕግስት ሰዎች ራሳቸውን ሊጠብቁ ይገባል ብላለች፡፡ መንግሥትም አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ አለበት ባይ ናት፡፡ አስገዳጅ ሁኔታ ተጠቅሞ የማኅበረሰቡን ጤንነት ሊጠብቅ ይገባል ብላለች፡፡

ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪያችን ወይዘሮ ትዝታ ገዛኸኝ ራሳቸውን እና በዙሪያቸው የሚኖሩ ሰዎችን ከቫይረሱ ለመጠበቅ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ አዘውትረው እንደሚጠቀሙ ነግረውናል፡፡ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሁሉንም ሰው የሚያጠቃ በሽታ በመሆኑ ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ ነው ብለዋል፡፡

“እኔ የቤተሰቦቼን እና የራሴን ጤንነት የመጠበቅ ኀላፊነት አለብኝ፤ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል አድርጌ ስንቀሳቀስ በሽታው የያዘኝ የሚመስለው ሰው አለ፤ ይህ ስህትት ነው፤ ሊስተካከል ይገባል” ብለዋል፡፡ በተለይ ሰው በሚበዛባቸው ቦታዎች መገኘት ግድ ከሆነ ሁሉንም የመከላከያ ዘዴዎች እንደሚጠቀሙ ተናግረዋል፡፡ “ማኅበረሰቡ በአካባቢዬ የሚኖሩ ሰዎች ጉዳት የእኔም ጉዳት ነው ብሎ ማሰብ አለበት፤ እኔ በሽታውን እቋቋመዋለሁ በሚል ስሜት በዘፈቀደ ሊራመድ አይገባም” ነው ያሉት፡፡ የሚመለከተው አካልም ኀላፊነቱን በአግባቡ ሊወጣ እንደሚገባ ጠቅሰዋል፡፡

በአማራ ክልል ጤና ቢሮ የክትባት ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ወርቅነህ ማሞ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ነግረውናል፡፡ አቶ ወርቅነህ እንዳሉት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ወደ ሀገራችን በገባ ወቅት ሁሉም ሰው ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረጉ የወረርሽኙን ስፋት መቀነስ ተችሎ ነበር፡፡ አሁን ቫይረሱ የከፋ ጉዳት እያደረሰ ነው፡፡ በየቀኑ በቫይረሱ የሚያዘውና የሚሞተው ሰው ቁጥሩ እየጨመረ ነው፡፡ ማኅበረሰቡ ይሄን ተገንዝቦ ከመዘናጋት መውጣት አለበት ብለዋል፡፡

አቶ ወርቅነህ መንግሥት ችግሩን ለመቀነስ “ዳግም ትኩረት ለኮቪድ-19” በሚል የንቅናቄ ዘመቻ መጀመሩን ጠቅሰዋል፡፡ በዘመቻውም በየደረጃው ላሉ ባለድርሻ አካለት ግንዛቤ የማስጨበጫ ስልጠና እየተሰጠ ነው፡፡ ማኅበረሰቡም የችግሩን አሳሳቢነት ተረድቶ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ በመጠቀም፣ እጁን በውኃና በሳሙና ደጋግሞ በመታጠብ፣ ርቀትን ጠብቆ በመንቀሳቀስ እና ክትባት በመከተብ የቫይረሱን ስርጭት ሊከላከል ይገባል ብለዋል፡፡

አቶ ወርቅነህ እንዳሉት የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ተጋላጭ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ክትባት ለመስጠት ባቀደው መሰረት እስካሁን ከ337 ሺህ በላይ ለሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ክትባት መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡ በክትባቱ የጤና ባላሙያዎች፣ እድሚያቸው ከ18 ዓመት በላይ የሆኑና ተጓዳኝ ችግር ያለባቸው ሰዎች እንዲሁም እድሜያቸው ከ65 ዓመት በላይ የሆናቸው ሰዎች ተሳትፈዋል፡፡

በቀጣይም ሁለተኛውን ዙር ክትባት ለማምጣት ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡ አቶ ወርቅነህ ማኅበረሰቡ ከታመነ ምንጭ የሚያገኘውን መረጃ ወደ ተግባር በመለወጥ ሊጠቀምበት እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ የኮሮናቫይረስ በቀላሉ ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍ፣ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል የሚያጠቃ በመሆኑ ተገቢውን ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችም የእጅ መታጠቢያ እቃዎችን ለዳግም ሥራ ማዘጋጀት አለባቸው ብለዋል፡፡ የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ከኅብረተሰብ ጤና ኢንስትቲዩት ጋር በመቀናጀት ግብረ ኃይል አቋቁሞ እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ማኅበረሰቡ የቫይረሱን ሥርጭት ለመግታት የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

Source link

Related posts

ኩባ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት በተለያዩ ዘርፎች  ማሳደግ እንደምትፈልግ ገለጸች

admin

የአድዋ ድል ነጻነታችንን ያወጅንበት እና ታላቅ ተጋድሎ ያደረግንበት ታሪካዊ ክስተት ነው – አቶ እርስቱ ይርዳ  

admin

ሱዛን ራይስን ጨምሮ የባራክ ኦባማ ዘመን ባለስልጣናት ሚሊየን ዶላሮችን ይዘው ወደ ነጬ ቤተ መንግስት ተመልሰዋል

admin