65.28 F
Washington DC
June 15, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የሚሰጠውን ክትባት ኅብረተሰቡ መጠቀም እንደሚገባው የሃይማኖት አባቶች ተናገሩ፡፡

የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የሚሰጠውን ክትባት ኅብረተሰቡ መጠቀም እንደሚገባው የሃይማኖት አባቶች ተናገሩ፡፡

ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 20/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የሥራ ኀላፊዎችና አገልጋዮች የኮሮናቫይረስ መከላከያ ክትባት ዛሬ በባሕር ዳር ጤና ጣቢያ ተገኝተው ወስደዋል። ክትባቱን በመውሰድ ለሕዝብ አርአያነታቸዉን ካሳዩት የሃይማኖት አባቶች ውስጥ ሼህ አህመድ ዘይን ያሲን አንዱ ናቸው፡፡ ማኅበረሰቡ የጤና ባለሙያ የሚመክረዉን ከመስማት ባለፈ አሉባልታን የሚሰማ ከኾነ መዳረሻው አደገኛ ነው ብለዋል፡፡

“የሰው ልጅ በመመሪያ ነው መተዳደር ያለበት፤ ታላቁ ቅዱስ ቁርዓን የማታውቁትን ከሚያውቁ ጠይቃችሁ ተረዱ የሚል መመሪያ አስቀምጦልናል” ያሉት ሼህ አህመድ ዘይን የኮሮናቫይረስን ለመከላከል በአሉባልታ ከመመራት ይልቅ የጤና ባለሙያዎችን ምክረ ሐሳብ መተግበር ተገቢ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ክትባቱ ጉዳት የማያስከትል መኾኑን ለማሳየትም ዛሬ ክትባቱን መውሰዳቸዉን አስገንዝበዋል፡፡

አቡነ ልሳነክርስቶስ ማቲዎስ የባሕር ዳር ደሴ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስትያን ሀገረ ስብከት ጳጳስ የቫይረሱን መከላከያ ክትባት ወስደዋል። ማንኛውም ሰው ቢኾን በራሱ ቸልተኝነት ምክንያት እንዲሞት አንፈቅድም ያሉት አቡነ ልሳነክርስቶስ በምድር ላይ ለመቆየትም ቢኾን ትዕዛዝን ማክበር ያስፈልጋል ብለዋል። ማኅበረሰቡ የኮሮናቫይረስን ለመከላከል፣ ጤንነቱን ለመጠበቅና በሕይወት ለመቆየት የጤና ባለሙያዎችን ምክር መስማትና መተግበር አለበት ነው ያሉት።

ሰሞኑን በኮሮናቫይረስ ምክንያት ሕይወታቸዉን ያጡ ካህናትና የሃይማኖት መሪዎች መኖራቸውን ያነሱት አቡነ ልሳነክርስቶስ አማኞች ክትባቱን ወስደው በሕይወት እንዲቆዩ መልእክታቸዉን አስተላልፈዋል፡፡

የኮሮናቫይረስ መከላከያ ክትባት ወረርሽኙን ከመከላከል አንፃር ከፍተኛ ሚና እንዳለው ታምኖበት ክትባቱን የወሰዱ መኾኑን የነገሩን ደግሞ በባሕር ዳር ከተማ የመካነ ኢየሱስ ቤተክርስቲያን መጋቢ እሱባለው ጌታቸው ናቸው፡፡

ክትባቱን አስመልክቶ የተዛቡ አሉባልታዎች ሕዝቡን ሊያሳስቱ ስለሚችሉ ክትባቱ ጠቃሚ እንደኾነ ለማሳየት መከተባቸውን ነው የነገሩን፡፡ “ክትባቱ ከእምነታችን ጋር የሚቃረን ባለመኾኑ መውሰድ አለብን” ብለዋል፡፡

በአማራ ክልል የኮሮናቫይረስ ክትባት መሰጠት ከጀመረበት እስከ አሁን ድረስ ክትባቱን ወስዶ የጤና ጉዳት የደረሰበት ሰው እንደሌለ የክልሉ ጤና ቢሮ አስታውቋል፡፡ ክትባቱን የወሰዱ ሰዎች የቅርብ ክትትል እየተደረገላቸው እንደኾነና እስከ አሁን ድረስ ምንም አይነት የጤና ችግር የገጠመው ሰው አለመኖሩንም የቢሮው ምክትል ኀላፊ ታሪኩ በላቸው አስረድተዋል፡፡

መዘናጋቱና ወረርሽኙ ጎን ለጎን እየጨመሩ እንደሆነ ያስረዱት ምክትል ኀላፊው ኅብረተሰቡ ተጨባጭ ያልኾነ መረጃን ከማመን ተቆጥቦ ክትባቱን ሊወስድ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በአማራ ክልል ክትባቱን መስጠት ከተጀመረ እስከ አሁን ድረስ መከተብ ከሚጠበቅባቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች ውስጥ 47 በመቶ ብቻ መከተባቸውን አቶ ታሪኩ ጠቅሰዋል፡፡

የኮሮናቫይረስ ክትባት የወሰዱ ሰዎች ከሁለት ወራት በኋላ ሁለተኛውን ክትባት መውሰድ እንደሚጠበቅባቸው ተገልጿል፡፡

ዘጋቢ፡- ቡሩክ ተሾመ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

Source link

Related posts

ኮቪድ19 ባላንጣዎቹ ህንድና ፓኪስታንን በጋራ እንዲቆሙ አድርጓቸዋል

admin

የኢትዮጵያ የዳኝነት አገልግሎት ክፍያ ደንብ ሊሻሻል ነው

admin

አምባሳደር ሙሉ ሰለሞን ለጀርመን ፓርላማ አባላት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ገለጻ ሰጡ

admin