28.27 F
Washington DC
March 7, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

“የክትባት አቅርቦት እና የተጎጅዎች ቁጥር አለመመጣጠን ውሻን የሚያሳብድ በሽታ ለመከላከል ፈታኝ አድርጎታል” የአማራ ክልል ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት

“የክትባት አቅርቦት እና የተጎጅዎች ቁጥር አለመመጣጠን ውሻን የሚያሳብድ በሽታ ለመከላከል ፈታኝ አድርጎታል” የአማራ ክልል ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት

ባሕር ዳር፡ የካቲት 09/2013 ዓ.ም (አብመድ) ውሻን የሚያሳብድ በሽታ በውሻ፣ በድመት እና በሌሎች እንስሳት ንክሻ አማካይነት ወደ ጤናማ ሰው ሊተላለፍ የሚችል አደገኛ በሽታ እንደሆነ ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡

በሽታው በቫይረስ አማካኝነት ይመጣል፤ በዋናነት ደግሞ አንጎልን ያጠቃል። ማንኛውንም አጥቢ እንስሳትን የሚያጠቃ እንደሆነም ይነገራል፡፡ ገዳይ በሽታም ነው።

አብመድ በበሽታው የተጠቁ ሰዎችን አነጋግሯል። ከመተማ እና ከጭልጋ ወረዳ የመጡት ወርቁ አያሌው እና ካሳ ክብረት ክትባት ለማግኘት ወደ ባሕር ዳር መምጣታቸውን ነግረውናል፡፡ ግለሰቦቹ ባሕር ዳር አዲስ ዓለም ሆስፒታል ለ15 ቀናት ክትትል አድርገዋል። በዚህም ለከፍተኛ ወጭ ተዳርገዋል። በሽታው በእንስሳቶቻቸው ላይ ጉዳት ማድረሱንም ነግረውናል።

የውሾች የአያያዝ ችግር እና የቅድመ መከላከያ ክትባት አለመሰጠቱ ለበሽታው መስፋፋት በምክንያትነት አንስተዋል። መንግስት ለበሽታው አፋጣኝ መፍትሄ ካላበጀ የበርካታ ሰዎች እና እንስሳት ህይወት ሊያልፍ እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ምላሽ ሰጭና መልሶ ማቋቋም ባለሙያ ኃይሉ አያሌው እንደገለጹት ውሻን የሚያሳብድ በሽታ በክልሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ይገኛል፤ የሰዎችን ሕይወትም እየቀጠፈ ነው። በተለይም ደግሞ በምዕራብ ጎጃም፣ በደቡብ ጎንደር፣ በባሕርዳር እና በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር በሽታው በይበልጥ ጎልቶ የሚታይባቸው ቀጣናዎች መሆናቸውን ባለሙያው ገልጸዋል፡፡ ከሌሎች ወራት በተለየ መልኩ መስከረም እና መጋቢት ወራት ላይ እንደሚጨምርም ባለሙያው አስገንዝበዋል።

የክትባት አቅርቦት እና የተጎጅዎች ቁጥር አለመመጣጠን በሽታውን ለመከላከል ፈታኝ አድርጎታል፤ በውሾች አያያዝ ላይ የሕግ ማዕቀፍ አለመኖር ሌላኛው ፈተና መሆኑን ባለሙያው አንስተዋል። ችግሩን ለመቅረፍ ውሾችን ማስከተብ፣ በመኖሪያ ቤት ግቢ ውስጥ ማሰር እና ባለቤት አልባ ውሾችን ደግሞ ለመቀነስ መወሰኑን ገልጸዋል።

ማኅበረሰቡም ውሻ ሲያረባ በመኖሪያ ግቢው ውስጥ በማሰር ለግቢው ጥበቃ ብቻ ሊያውል እንደሚገባ አመላክተዋል።

የአማራ ክልል እንስሳት ሃብት ማስፋፊያ ኤጀንሲ የእንስሳት ጤና ዳይሬክተር ዶክተር ታምሩ ተሰማ ውሻን የሚያሳብድ በሽታን ለመከላከል ክትባት እየተሰጠ ቢሆንም በሀገር ውስጥ የሚመረተው ክትባት ዝቅተኛ በመሆኑ የተፈለገውን ውጤት ማምጣት አለመቻሉን ገልጸዋል፡፡ ለዚህም ባለፉት ወራት ክትባት የተሰጠው ለ25 ሺህ ውሾች ብቻ መሆኑ በማሳያነት አንስተዋል።

በሽታውን ለመከላከል ባለቤት አልባ ውሾችን የማስወገድ ሥራ ይሠራል ብለዋል፡፡

ለውሻ የሚያሳብድ በሽታ መከላከያ የሚሰጠውን ክትባት ከውጭ ለማስገባት ለአስመጭዎች ፈቃድ መስጠቱንም ነግረውናል፡፡

በኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የክትባት እና ዲያግኖስቲክ ምርት ዳይሬክተር አበበ መንገሻ እንደተናሩት ደግሞ በሽታው ከጊዜ ወደ ጊዜ እጨመረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ክትባቱን የሚያመርተው ቴክኖሎጅ ዘመኑን የሚመጥን ባለመሆኑ ክትባቱን በሚፈለገው መጠን ማምረት አልተቻለም፡፡ ችግሩንም ለመፍታት ካለፉት ሁለት ወራት ጀምሮ የማምረት አቅምን በማሳደግ ለተጠቃሚዎች ማቅረብ መቻሉን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

አሁን በማምረት ላይ ያለውን ቴክኖሎጅ በዘመናዊ በመቀየር የማምረት አቅምን ለማሳደግ እየተሠራ ይገኛል፡፡ ክትባቱ ከውጭ በግዥ እንዲገባም ጥናት ተጠንቶ ለጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ማቅረባቸውን አቶ አበበ ገልጸዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

Source link

Related posts

በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነው የእናቶችና ህጻናት ሆስፒታል በአዲስ አበባ ተመረቀ።

admin

የገንዲ በሽታ አሁንም ትኩረት ይሻል

admin

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የዕጩዎች ምዝገባ ማከናወን የተራዘመባቸው ክልሎችን አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫ

admin
free web page hit counter