78.12 F
Washington DC
June 15, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

የክረምት መግባትን ተከትሎ ለወባ ወረርሽኝ እንዳይጋለጡ ከወዲሁ ጥንቃቄ እያደረጉ መሆናቸውን የባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳ ነዋሪዎች ተናገሩ።

የክረምት መግባትን ተከትሎ ለወባ ወረርሽኝ እንዳይጋለጡ ከወዲሁ ጥንቃቄ እያደረጉ መሆናቸውን የባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳ ነዋሪዎች ተናገሩ።

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 11/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳ ከሚገኙ ቀበሌዎች አስሩ ከጣና ሐይቅ ጋር ባላቸው ጉርብትና እና ከቦታ አቀማመጣቸው አንጻር በ2013 ዓ.ም የወባ ወረርሽኝ የሚያሰጋቸው ተብለው ተለይተዋል፡፡ የስጋት ቀጣና ተብለው ከተያዙ ቀበሌዎች ውስጥ ወንጀጣ፣ ሮቢትና አንዳሳ ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ወይዘሮ አንጓች ይልማም የወንጀጣ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ ወይዘሮዋ አጎበር የመጠቀም ልምድ አላቸው፡፡ ይህም በወባ በሽታ እንዳይያዙ አግዟቸዋል፡፡ የጤና ባለሙያዎች የሚሰጡትን የቅድመ መከላከል ትምሕርት ተግባራዊ በማድረጋቸው ለወባ በሽታ እንዳይጋለጡ ረድቷቸዋል፡፡ ወይዘሮ አንጓች “የምንኖርበት አካባቢ ውኃ የሚተኛበት በመሆኑ የአካባቢው ማኅበረሰብ በተደጋጋሚ ለወባ በሽታ ይጋለጣል፤ ይህን ችግር ለመቅረፍ አጎበር በአግባቡ መጠቀም ይገባል” ብለዋል፡፡

ወይዘሮዋ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ለሌሎች ልምዳቸውን በማካፈል በሽታው በሰዎች ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ ተፅዕኖ እንዳይፈጥር እያደረጉ መሆኑንም በስልክ በነበረን ቆይታ ነግረውናል፡፡

አቶ ምስጋናው ነጋ ደግሞ የሮቢት ባታ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ አቶ ምስጋናው እንዳሉት የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች በሚሰጡት ትምሕርት መሰረት አጎበር በአግባቡ ይጠቀማሉ፤ በዚህም እሳቸውና ቤተሰቦቻቸው ወባ ታመው እንደማያውቁ ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ነግረውናል፡፡ አቶ ምስጋናው እንደገለጹት የአካባቢውን ማኅበረሰብ ከወባ በሽታ ለመከላክል በአደረጃጀት መሠረት በየጎጡ ትምሕርት ይሠጣል፡፡ ቤት ለቤት በሚደረግ ልምድ ልውውጥ የእሳቸው ቤት በአርአያነት ይጎበኛል፡፡ በአካባቢያቸው ውኃ የሚያቁሩ ቦታዎችን የማዳፈን እና የማፋሰስ ሥራ ይሠራል ብለዋል፡፡

አቶ ምስጋናው ማኅበረሠቡ የወሠደውን አጎበር በአግባቡ በመጠቀም እራሱን እና ቤተሠቡን ከወባ በሽታ ሊከላከል ይገባል ብለዋል፡፡ በተጨማሪ የሕመም ሥሜት ሲኖር በአፋጣኝ ወደ ጤና ተቋም በመሄድ ሕክምና ማግኘት እንዳለበት መክረዋል።

በባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳ የወንጀጣ ጤና ጣቢያ ኀላፊ ያብባል ዘመነ ባለፈው ሳምንት በተደረገ ዳሰሳ በጤና ጣቢያው መጥተው ከተመረመሩ ሠዎች ውስጥ አራቱ የወባ በሽታ ተገኝቶባቸዋል ብለዋል፡፡ እንደ ያብባል ገለጻ በጤና ጣቢያው ሥር የሚገኙ ቀበሌዎች የስጋት ቀጣና ተብለው የተለዩ ቢሆንም በተደረገው ርብርብ ችግሩን መቅረፍ ተችሎ ነበር፤ ነገር ግን የዝናቡን መጣል ተከትሎ አሁን በአዲስ የወባ በሽታ እየተከሰተ ነው፡፡ ችግሩን ለመቅረፍም ለአካባቢው ነዋሪዎች የወሰዱትን አጎበር በአግባቡ እንዲጠቀሙ እና የወባ ትንኝ የምትፈለፈልበትን ውኃ ያቋቱ አካባቢዎች በማዳፈን እና በማፋሰስ ችግሩን እንዲቀንሱ ግንዛቤ እየፈጠሩ እንደሆነ ኀላፊው ገልጸል፡፡

የወባ በሽታ በአብዛኛው ሴቶችን፣ ሕጻናትን እና አቅመ ደካሞችን የሚያጠቃ ቢሆንም በመካከለኛ እድሜ ላይ የሚገኙ ጎልማሶችን በማጥቃት በኢኮኖሚው ላይ የሚያስከትለው ችግርም ከፍተኛ በመሆኑ ሁሉም ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል ብለዋል፡፡ በተለይ ተመርምረው የወባ በሽታ የተገኘባቸው ሰዎች ቤተሰቦቻቸውን እንዲያስመረምሩ እየተደረገ መሆኑንም ኀላፊው ገልጸዋል፡፡

የሮቢት ባታ ጤና ጣቢያ ኀላፊ ፀጋዬ ሞትባይኖር በሳምንቱ በጤና ጣቢያ መጥተው ከተመረመሩ ሕሙማን 15 ሰዎች የወባ በሽታ ተገኝቶባቸዋል ብለዋል፡፡ የጤና ጣቢያው ኀላፊ እንደገለጹት እስከ ታኅሣሥ 30/2013 ዓ.ም ድረስ በጤና ጣቢያው ሥር ለሚገኙ ነዋሪዎች አጎበር ተሰራጭቷል፡፡ ማኅበረሰቡ የወሰደውን አጎበር በአግባቡ በመጠቀም በሽታው እንዳይስፋፋ ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል ነው ያሉት፡፡ በቀጣይም አጎበር ያልደረሳቸው ቤተሰቦች ካሉ በተመደበላቸው መሠረት መውሰድ የሚችሉ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ በተጨማሪ ማኅበረሰቡ የአካባቢ ቁጥጥር ሥራውን አጠናክሮ እንዲቀጥልም አሳስበዋል፡፡

በባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽሕፈት ቤት የወባ መከላከል ኦፊሰር ደመወዝ አታለው እንደገለጹት በተደጋጋገሚ ዝናብ መጣሉን ተከትሎ የወባ በሽታ አምጭ ትንኞች በብዛት ይፈለፈላሉ፤ ይህም የወባ ወረርሽኝ እንዲከሰት እድል ፈጥሯል፡፡ አቶ ደመወዝ እንዳሉት እንደ ባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳ በ2012 ዓ.ም መጨረሻ እና በ2013 ዓ.ም መግቢያ ላይ ወባ በከፍተኛ ሁኔታ የተከሰተ ቢሆንም በተደረገው ርብርብ መቆጣጠር ተችሎ ነበር፡፡

ጽሕፈት ቤቱ በየሳምንቱ ከጤና ጣቢያዎች የሚደርሰውን ሪፖርት መሰረት በማድረግ የስጋት ቀጣናዎችን የመለየት ሥራ ሠርቷል፤ በዚህም በተለያዩ ቀበሌዎች የወባ በሽታ ሥርጭቱ እያደገ መምጣቱን ገምግመናል ብለዋል፡፡

የስጋት ቀጣናውን መለየት ብቻ ሳይሆን ግብረ መልስ በመሥጠት የከፋ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች ተገቢው ጥንቃቄ እንዲደረግ ጥረት እያደረጉ መሆኑን አቶ ደመወዝ ገልጸዋል፡፡

ማኅበረሰቡ አጎበር በአግባቡ በመጠቀም፣ የአካባቢ ቁጥጥር ሥራ በመሥራት እና የሕመም ስሜት ሲኖር በወቅቱ በመታከም የወባ በሽታን ሊከላከል ይገባል ብለዋል፡፡ የወባ በሽታ አምራች የሆነውን የማኅበረሰብ ክፍል በማጥቃት በማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ ተጽእኖ እንዳይፈጥር አስፈላጊው የመከላከል ሥራ እየተሠራ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ ፡- ትርንጎ ይፍሩ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

Source link

Related posts

የሸኔን እንቅስቃሴ ለማምከን የፌደራል ፖሊስ አባላት ከአካባቢው ሚሊሻ ጋር እየሰሩ ነው

admin

ከ475 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው የጎዴ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ተመረቀ

admin

ቀደምት የስልጣኔ አሻራዎችን ለአንድነትና ለአገራዊ ብልፅግና ጥቅም ላይ ማዋል ይገባል ተባለ

admin