38.12 F
Washington DC
March 5, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

የኢትዮ ሱዳን ጉዳይ የእርሻ ወቅት ሳይደርስ መፈታት እንዳለበት የአካባቢው ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

የኢትዮ ሱዳን ጉዳይ የእርሻ ወቅት ሳይደርስ መፈታት እንዳለበት የአካባቢው ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

ባሕር ዳር፡ የካቲት 09/2013 ዓ.ም (አብመድ) መንግሥት ትኩረቱን በትግራይ ክልል ሕግ ማስከበር ላይ ባደረገበት ወቅት ሱዳን የኢትዮጵያን ድንበር ጥሳ መግባቷ ይታወቃል፡፡ ኢትዮጵያና ሱዳን በሚዋሰኑባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ የሁለቱ ሀገራት ዜጎች ለዘመናት የቆየ ጠንካራ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ትሥሥር አላቸው፡፡

ሱዳናውያን ወደ ኢትዮጵያ ገብተው የፈለጉትን ይሸምታሉ፤ ኢትዮጵያውያንም ወደ ሱዳን ገብተው ግብይት ፈጽመው ይመለሳሉ፡፡ ከዚህ አልፎ በሃዘንና በደስታ እስከመገናኘት የዘለቀ ጥብቅ ማኅበራዊ ትሥሥር እንዳላቸው አብመድ በስልክ ያነጋገራቸው የምዕራብ ጎንደር ዞን ነዋሪዎች አስረድተዋል፡፡

ይሁን እንጂ በግለሰቦች መካከል አልፎ አልፎ የሚፈጠሩ ግጭቶች እንደነበሩ በዞኑ ሰላምበር ቀበሌ በእርሻ ኢንቨስትመንት የተሰማሩት አቶ ጌታቸው ተፈራ ተናግረዋል፡፡ አስተያዬት ሰጪው እንደሚሉት ታጣቂዎች ድንገት በመግባት ንብረት ዘርፈው ይመለሱ ነበር፡፡ የአሁኑ ክስተት ያልተጠበቀ መሆኑን ያነሱት አቶ ጌታቸው የሱዳን መንግሥት ታጣቂዎች ወረራ ማካሄዳቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ሱዳን የኢትዮጵያን ድንበር ጥሳ በመግባት በተለይ በምዕራብ ጎንደር ዞን ከቋራ እስከ አቡጢር ድረስ ሰፊ ቦታ በጉልበት መቆጣጠሯንም የዞኑ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኀላፊ ሁናለም አሻግሬ ተናግረዋል፡፡

በወረራው ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል፤ ከ 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት የንብረት ዝርፊያ መደረጉንም ገልጸዋል፡፡ በተለይ ከምድረገነት በቅርብ ርቀት በምትገኘው ሰላም በር ቀበሌ በርካታ የአካባበው ነዋሪዎች ከመኖሪያቸው መፈናቀላቸውን አስታውቀዋል፤ የአርሶ አደሮችና የባለሀብቶች ሰብል፣ ትራክተሮችና ካምፖች ውድመትና ዝርፊያ እንደተፈጸመባቸውም ተናግረዋል፡፡

የምድረ ገነት ከተማ ከንቲባ አይሸሽም ጓንቼ እንዳሉት የሱዳን ታጣቂዎች አስካሁን ድረስ በማኅበረሰቡ ላይ ትንኮሳ እያደረጉ ነው፤ የአካባቢው ነዋሪዎችም ስጋት አድሮባቸዋል፡፡ የአካባቢው መስተዳደር አካላት፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ማኅበረሰቡን ለማረጋጋት ጥረት እያደረጉ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

አቶ ሁናለም እንዳሉት የኢትዮጵያ መንግሥት በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ሱዳን ከጥቅምት 24 በፊት ወደነበረችበት እንድትመለስ እየሠራ ነው፡፡

ጉዳዩን በከፍተኛ ትግስትና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለመፍታት እየተደረገ ያለው ጥረት የሚደነቅ መሆኑን የአብመድ የዜና ምንጮች ተናግረዋል፡፡ የመንግሥት ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ውጤታማነት የሚለካው ሱዳንን ወደነበረችበት መመለስ ሲቻል መሆኑንም ጠቅሰዋል፤ ለዚህም ተጨማሪ ሥራ መሥራት እንደሚጠበቅ ነው አስተያየት ሰጪዎቹ ያነሱት፡፡

የእርሻ ጊዜ አልፎ የሱዳን ታጣቂዎች ካደረሱት ጉዳት የከፋ ችግር እንዳይገጥም በተጀመረው አግባብ ፈጣን መፍትሔ እንዲገኝ ጥረቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡ የአካባቢው ማኅበረሰብም የኢትዮጵያ መንግሥት የሚያሳልፈውን ውሳኔ በትግሥት እየተጠባበቀ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

Source link

Related posts

የድሮን ቴክኖሎጂን በትብብር በማልማት ለልዩ ልዩ አገልግሎቶች መጠቀም የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ

admin

“ከቀደሙት የቀደመ ርቆ ለመሄድ ያለመ”

admin

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከ4 ሺህ 858 በላይ ተማሪዎችን አስመረቀ

admin