የኢትዮጵያ ዳር ድንበር፤ ያልተቋጨ የቤት ሥራ

6 mins read

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ፕሬስ ያሳተመውን የኢትዮጵያ ዳር ድንበር፤ ያልተቋጨ የቤት ሥራ የተሰኘ መጽሐፍ አስመረቀ፡፡

በዶክተር በለጠ በላቸው ይሁን ተጽፎ በኢትዮጵያ አካዳሚ ፕሬስ የታተመው መጽሐፍ የመንግሥት ከፍተኛ አመራሮች፣ ምሁራን፣ የተለያዩ የዘርፉ ባለሞያዎችና ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት ነሐሴ 28 ቀን 2013 ዓ. ም በሂልተን ሆቴል  በይፋ ተመርቋል፡፡

በዚህ ጥራቱን አስጠብቆ መጽሐፉን ባሳተመው የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ እና የሕትመት ወጪውን በመሸፈን ድጋፍ ባደረገው በፍሬድሪሽ ኤበርት ስቲፍቱንግ በትብብር በተዘጋጀው የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ የፍሬድሪሽ ኤበርት ስቲፍቱንግ ፕሬዚደንት ተወካይ  አቶ ማይክል ትሮስተር የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር አድርገዋል፡፡

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ የመክፈቻ መልእክት ያስተላለፉት የኢ.ሰ.አ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ፅጌ ገብረ ማርያም ሀገራችን ኢትዮጵያ  ጥንታዊ ምድረ ቀደምት መሆኗን ጠቅሰው በየጊዜው ከውጪ ጠላቶች ሊወሯት ሲሞክሩ እና የውስጥ ግጭቶችን ተጠቅመው አንዳንድ የጎረቤት ሀገሮች ድንበሯን ቢደፍሩም  በኢትዮጵያዊ አንድነት እና ወኔ ወረራዎች ተቀልብሰው ዳር ድንበሯ ተጠብቆ እንደቆየ ተናግረዋል።

አያይዘውም በዕለቱ የተመረቀው መጽሐፍ በዓለም አቀፍ እና በድንበር ጉዳዮች ላይ ለሚሠሩና ጥናት ለሚያካሂዱ ከፍ ያለ ቁምነገር የያዘ መኾኑን አብራርተዋል፡፡

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላ በክብር እንግድነት ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የኢፌዲሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በበኩላቸው የኢትዮጵያን የድንበር አከላለል በተመለከተ በተለያዩ ዘመናት የነበሩ ሂደቶችን፣ የተደረጉ ጥረቶችን፣ የተመዘገቡ ድሎችን እና የገጠሙ እክሎችን በሰፊው የተነተነ መረጃ በመጽሐፉ መቅረቡን ጠቅሰዋል፡፡

በምረቃው ሥነ ሥርዓት ላይ  አቶ ሙሉነህ ወሂብ እና ዶክተር  ወንድማገኝ ታደሰ  በዳር ድንበር እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ዙሪያ ካላቸው ልምድ አንጻር ስለመጽሐፉ ሙያዊ  ዳሰሳዎቻቸውን አቅርበው  ውይይት ተደርጓል።

የመጽሐፉ ደራሲ ዶክተር በለጠም ለመጽሐፉ ሕትመት መሳካት ጉልህ አስተዋፅኦ ላበረከቱ አካላት ምስጋናቸውን አቅርበው መጽሐፉ የሀገሪቱን የግዛት ዳርቻ አስመልክቶ በጭፍን እና በዘልማድ የሚታወቀውን ግንዛቤ የሚያሰፋ ሐሳብ ይዞ የተነሳ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

አክለውም የአገሪቱን ዳር ድንበር በተመለከተ እስካለንበት ዘመን ድረስ በአግባቡ በመሬት ላይ የተከለለው ከ15 በመቶ እንደማይበልጥ፣ ገና ብዙ የሚቀር የቤት ሥራ መኖሩን በማስረጃዎች አስደግፈው አቅርበዋል፡፡

በውይይቱ ወቅት  መጽሐፉ ለንባብ የበቃው ወሳኝ በሆነ ወቅት መሆኑንና  በሕዝቡ ዘንድ  በጉልህ የማይታወቁ የኢትዮጵያ ዳር ድንበር አከላለል ጉዳይ ገሃድ ያወጣ የመጀመሪያው መጽሐፍ መሆኑን አምባሳደር ኢብራሂም እድሪስ እና ሌሎች አስተያየት ሰጪዎች ገልጸዋል፡፡

በምሥጢር ተይዘው የነበሩና ለብዙኃኑ አዳዲስ የኾኑ ነጥቦችን ከሰፊ ማብራሪያ ጋር የያዘው እና በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሰነድ ላይ የተመረኮዘ ሥራ መሆኑም በውይይቱ ተጠቅሷል፡፡

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ተከተል ዮሐንስ  በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ መዝጊያ ላይ ባደረጉት ንግግር ለአያሌ አመታት ብዙ ውዝግቦችን ሲያስተናግዱ በቆዩ የኢትዮጵያ ዳር ድንበር ታሪኮች ላይ ያለውን የተዛባ ግንዛቤ ለማስተካከል  ፈር ቀዳጅ ሥራ መሆኑን ጠቅሰው ለዚህ ስራ ሥኬት  ጉልህ ሚና የተጫወቱትን ፍሬድሪሽ ኤበርት ስቲፍቱንግ እና ሌሎች አካላትን አመስግነዋል።

“የኢትዮጵያ ዳር ድንበር፤ ያልተቋጨ የቤት ሥራ” የተባለው መጽሐፍ ከፍሬድሪሽ ኤበርት ስቲፍቱንግ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ የታተመ መጽሐፍ እንደመሆኑ፣ አካዳሚው የመጽሐፉን የመጀመሪያ ሕትመት በከፍተኛ ቅናሽ ለገበያ አቅርቧል፡፡

Source link