48.78 F
Washington DC
April 13, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

የአካባቢ ጥበቃ ሕጎች ተግባራዊ በማድረግ የአካባቢ ብክለትን መከላከል እንደሚገባ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የመኖሪያ አካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም የባሕር ዳር ቅርንጫፍ አስተባባሪ ገለጹ፡፡

የአካባቢ ጥበቃ ሕጎች ተግባራዊ በማድረግ የአካባቢ ብክለትን መከላከል እንደሚገባ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የመኖሪያ አካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም የባሕር ዳር ቅርንጫፍ አስተባባሪ ገለጹ፡፡

ባሕር ዳር፡ መጋቢት 25/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የጣና ግዮን የአካባቢ ጥበቃ፣ ፅዳት፣ ውበትና የማኅበራዊ አገልግሎት የበጎ አድራጎት ማኅበር በአካባቢ ጥበቃ ሕጎች ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡

በውይይቱ የተሳተፉት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የመኖሪያ አካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም የባሕር ዳር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ ዶክተር ብርሃኑ እስከዚያ እንደገለጹት ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍና ሀገር አቀፍ የአካባቢ ጥበቃ ሕጎችን ያጸደቀች ሀገር ብትሆንም ሕጎቹ ተግባራዊ ባለመደረጋቸው ህይወትን ለመምራት አስቸጋሪ እየሆነ መጥቷል፡፡ እነዚህን ሕጎች ለማኅበረሰቡ በማስተዋወቅ አካባቢውን የሚንከባከብበትና የሚያፀዳበት አግባብ መመቻቸት አለበት፤ የሕግ አካላትም ችግር በፈጠረው አካል ላይ እርምጃ ሊወስዱ እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡

ዶክተር ብርሃኑ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ይዘው ወደ ሥራ የሚገቡ አካላት የሚያቀርቧቸው የአካባቢ ተጽዕኖ ግምገማ ጥናት የፕሮጀክቶችን ባህርይ መሰረት ያላደረጉ በመሆናቸው በአካባቢ ላይ የሚደርሰው ተጽዕኖ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ሄዷል ብለዋል፡፡ “የአካባቢ ጥበቃ ሕጎችን ተግባራዊ በማድረግ የአካባቢ ብክለትን መከላከል ይገባል” ነው ያሉት፡፡ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ተጠሪ ተቋማት ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

የጣና ግዮን የአካባቢ ጥበቃ ፅዳት፣ ውበትና የማኅበራዊ አገልግሎት የበጎ አድራጎት ማኅበር ሥራ አስኪያጅ ሠዓሊ በረከት አንዳርጌ ማኅበሩ ዓባይን እና ጣናን ከብክለት ለመታደግ ዓላማ ይዞ እየሠራ መሆኑን ገልጿል፡፡ ማንኛውም ግለሰብ ከመኖሪያ ቤቱ አካባቢ 20 ሜትር፣ የንግድ ድርጅት 50 ሜትር አካባቢ ማጽዳት ግዴታ ቢኖርበትም ሕጉ ተግባራዊ ባለመደረጉ የባሕር ዳር ከተማ ለነዋሪዎቿ ጤና አደገኛ እየሆነች መምጣቷን ተናግሯል፡፡

መድረኩ ለማኅበረሰቡ እውቅና ለመፍጠርና ሕጎች ተግባራዊ የሚሆኑበትን መንገድ ለማመቻቸት ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን ገልጿል፡፡ ማኅበረሰቡ አካባቢውን ከብክለት እንዲከላከል፣ ተጠሪ ተቋማትም የተጣለባቸውን ኀላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ፣ የሕግ አካላትም ጥፋተኞችን ለፍርድ በማቅረብ የተሻለ አካባቢ መፍጠር ይገባል ነው ያለው፡፡

የአማራ ክልል የአካባቢ ደንና ዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር በላይነህ አየለ (ዶክተር) ማኅበረሰቡ ተፈጥሮ ሀብትን ጠብቆ ለመያዝ ያለው ግንዛቤ አናሳ መሆን አካባቢን ለብክለት እየዳረገ ነው ብለዋል፡፡ ዶክተሩ እንዳሉት ለአካባቢ ጥበቃ እገዛ ያደርጋሉ ተብለው የተቋቋሙ መሥሪያ ቤቶች “ውጤት ማምጣት እንዳልቻሉ” ገልጸዋል፡፡ ችግሩን በመገምገም ጠንካራ ተቆጣጣሪ ተቋም ለማድረግ እየሠሩ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

“በአንድ ከተማ መብራት ወይም ውኃ ለተከታታይ ሦስት ቀናት ቢጠፋ የአካባቢው ማኅበረሰብ ለተቃውሞ ይወጣል፤ የአካባቢ ብክለት ግን ከረጅም ጊዜ በኋላ የሚከሰት በመሆኑ በማኅበረሰቡም ሆነ በሥራ ኀላፊዎች ዘንድ የሚሰጠው ትኩረት አናሳ ነው፡፡ አካባቢን ለመንከባከብ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ ነው” ብለዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ በባሕር ዳር ከተማ የተሠሩ የቆሻሻ ማስወገጃ ቁሳቁሶች በመነሳታቸው ማኅበረሰቡ ቆሻሻን በየሜዳው እንዲጥል ተገዷል፤ ይሄን በተጠናከረ መንገድ ወደ ሥራ በማስገባት የወጣቶች የሥራ እድል መፍጠሪያ ዘዴ ለማድረግ እንደሚሠሩም ተናግረዋል፡፡

“እስካሁን አካባቢን ሲበክሉ የተገኙ ድርጅቶችን ወደ ሕግ ብናቀርብም የአንዳንድ ባለሀብቶች ረጅም እጅና የሕግ አስፈጻሚ አካላት ደካማ አፈጻጸም በሥራው ላይ ተጽዕኖ ፈጥሮ ቆይቷል” ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፡፡ ችግሩን ለመቅረፍና ውጤታማ ሥራ ለመሥራት ብክለት የሚለካ ቤተ ሙከራ ተቋቁሞ እየሠራ መሆኑንና እርምጃ የተወሰደባቸው ተቋማት መኖራቸውንም ጠቁመዋል፡፡ በአንጻሩም አካባቢያቸውን በጥሩ ሁኔታ ጠብቀው በመያዛቸው የተሸለሙ ተቋማት መኖራቸውንም አንስተዋል፡፡

የባሕር ዳር ከተማን ውበት በመጠበቅ የቱሪስት መዳረሻነቷን ማሳደግ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

Source link

Related posts

ምነዋ ኢትዮጵያ ? -ፊልጶስ

admin

የቱሪዝም ዘርፉን በዲጂታል ቴክኖሎጂ ለማዘመን የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ

admin

“…ሰብዓዊ እርዳታ እየቀረበ አይደለም የሚሉ አካላት የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ነው” – ዶ/ር ሙሉ ነጋ

admin