76.68 F
Washington DC
June 17, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

“የአማራ ክልል ሕዝብ ተነቦ የማያልቅ ታሪክ፣ ሃይማኖት፣ ባሕል ቋንቋ፣ ሥነ ልቦና እና የእርስ በርስ መስተጋብር ያለው ኩሩ ሕዝብ ነው” አቶ አብርሃም አለኸኝ

“የአማራ ክልል ሕዝብ ተነቦ የማያልቅ ታሪክ፣ ሃይማኖት፣ ባሕል ቋንቋ፣ ሥነ ልቦና እና የእርስ በርስ መስተጋብር ያለው ኩሩ ሕዝብ ነው” አቶ አብርሃም አለኸኝ

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 26/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን አማራ ኤፍ ኤም ደብረ ማርቆስ 95.1 አካባቢያዊ ስርጭቱን በማደብረ ማርቆስ ከተማ አስጀምሯል፡፡ በስርጭት ማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር የሕዝብ ግንኙነትና አደረጃጀት ዘርፍ አማካሪ እና የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ አብርሃም አለኸኝ እንዳሉት ሚዲያ የሀሳብ ጋን ነው፤ ሀሳብ የንግግር ቋት ነው፤ በንግግር በብዕርም ሆነ በተግባር የሚገለጽ ድርጊት ምንጩ ሀሳብ ነው፡፡

ሀሳብ በሌለበት ተፈጥሯዊ ሁነት ሀሳብን በነጻነት መግለፅ መብት ብሎ ነገር አይታሰብም፤ የሁሉም ነገር መነሻ ነጻ ሀሳብ ነው ያሉት የቦርድ ሰብሳቢው “የዜጎችን ነጻ ሀሳብ ዘርተን የምናጭድበት ማሳ ማኅበራዊ መስተጋብር ነው” ብለዋል፡፡ አቶ አብርሃም እንዳሉት በጎ ነገር ስናስብ በጎ ቃላት ከአንደበታችን ይፈልቃል፤ በጎ ቃላት ከብዕራችን ይንጠባጠባል፤ የመልካም ንግግርም ሆነ የመልካም ድርጊት ምንጩ በጎ ህሊና ቀና አስተሳብ ነው፡፡ በጎ ህሊና በሌለበት ገንቢ ንግግርም ሆነ ፈዋሽ ድርጊት ማግኘት አይቻልም ነው ያሉት፡፡

ሚዲያ የሀሳብ ጋን ነው ሲባል መልካምነትን፣ ደግነትን፣ እርስ በእርስ መዋደድንና በመከባባር ላይ የተመሰረተ አንድነትን ጠምቀን ለኅበረሰብ ለውጥ የምንተጋበት የአብሮነት ጽዋ ስለሆነ ነውም ብለዋል፡፡

የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የለውጥ ኃይሎች የተሰባሰቡበት የበጎ ሃሳብ ድምር ውጤት ነው፤ ሚዲያን ለማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማትና ለፖለቲካ ሁለንተናዊ ለውጥ በመጠቀም ለኅበረሰብ ተጠቃሚነት ማዋል ካልተቻለ ፋይዳ አይኖረውም ብለዋል፡፡

ባሕላዊና ሃይማኖታዊ እሴቶቻችን እንደ እንቦይ ካብ እየተናዱ የምንይዘውን የምንጨብጠውን ባጣንበት ወቅት ሚዲያዎችን በቅጡ መግራትና ለኅበረተሰብ ለውጥ እንዲተጉ ማድረግ ከሁላችንም ይጠበቃል ነው ያሉት የቦርድ ሳብሳቢው፡፡ አሚኮ የአማራ ሕዝብ ብሎም የኢትዮጵያ ሕዝብ ድምፅ እንዲሆን መትጋት አለብንም ነው ያሉት፡፡

የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን በሁሉም ዘርፍ ለበለጸገ ሀሳብ ትርጉም ያለው ዋጋ መስጠት ይኖርበታል፤ ለዚህም እንተጋለን ነው ያሉት፡፡ ለእውቀት፣ ለፍልስፍና፣ ለምርምር፣ ለምክንያታዊነትና ለፈጠራ ሥራ አስቻይ ሁኔታን የሚፈጥር የሀሳብ ልዕልና ባለቤት መሆን ማለት ነውም ብለዋል፡፡ አሚኮ የውልደቱ እስከ እድገቱ በተግባር ያረጋገጠውም በየጊዜው እያደረገ የሚሄድ የሀሳብ ልዕልና ባለቤት መሆኑ ነው ብለዋል አቶ አብርሃም፡፡

ሀሳብ የሚበለጽገው በጥልቅ ፍለጋና በምርምር ብቻ ነው ያሉት አቶ አብርሃም በቁንጽል ንባብ የሚበለፅግ ሀሳብ፣ የሚያድግ አስተሳሰብ፣ የሚለወጥ ህሊና አይኖርም ነው ያሉት፡፡ ሚዲያው እንዲበለጽግ ከተፈለገ ማኅበረሰቡን ደጋግሞ ማንበብ ይገባልም ብለዋል፡፡ የማኅበረሰቡን ባሕል እና ሃይማኖታዊ እሴት በጥልቀት እንመርምረውም ነው ያሉት፡፡

በጽሑፍ የሰፈሩ ዶሴዎችንና ትውፊታዊ ቅርሶችን በመውል መረዳት እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡ “የአማራ ክልል ሕዝብ ተነቦ የማያልቅ ታሪክ፣ ሃይማኖት፣ ባሕል ቋንቋ፣ ሥነ ልቦናና የእርስ በእርስ መስተጋብር ያለው ኩሩ ሕዝብ ነው” ብለዋል፡፡ በሁሉም እሴቶቻችን ውስጥ የሚታየውን የመልካም ፀባይ መወራረስ የሚያጎለብት፣ አብሮነትን የሚያነግስ፣ የመለያዬትንና የመነቃቀፍን ልክፍት የሚፈውስ የበለፀገ ሀሳብ ባለቤቶች እንሁንም ብለዋል፡፡

ሚዲያው በተለያዩ ቋንቋዎች ተደራሽነቱን ሲያሰፋ የማኅበረሰብ ለውጥ ትልሙን ለማረጋገጥ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ በቀጣይም የስርጭት አድማሱን እያሰፋ ሲመጣ ሚዲያው አሁን ላይ ከሚገለገልባቸው ቋንቋዎች በተጨማሪ በአፋርኛ፣ ጉምዝኛ፣ አረብኛና ሶማሊኛን ጨምሮ የግዕዝ ቋንቋን በመጠቀም በሀገር ውስጥም ሆነ በመሥራቅ አፍሪካ ተደራሽነቱን ለማረጋገጥ እየሠራ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡

አሚኮ ትክክለኛ የሕዝብ ድምጽ ሕልሙን ሊያረጋግጥ የሚችለው የሁሉንም ኅበረተሰብ ቀና አመለካካትና ገንቢ ሂስ በመጠቀም ጭምር እንደሆነም አንስተዋል፡፡ ሚደያው በማኅበረሰብ ንቅናቄ የሚያጋጥሙ መልካም አጋጣሚዎችን የሚያሰፋ፣ ስብራቶችን የሚጠግን ሰንኮፎችን የሚያስወግድ፣ ለመላው ሕዝባችን የሞራል ልዕልና የማይመጥን ከንቱ ልማድ የሚጫነንን መጥፎ ልክፍት የሚታገል ለኅበረሰብ ለውጥ የሚተጋ እንዲሆን እንፈልጋለን ብለዋል፡፡

አቶ አብርሃም ሚዲያው ለሰላም፣ ለልማትና ለዴሞክራሲ ሁለንተናዊ እድገት አዎንታዊ ሚና እንደሚጫዎት እናምናለንም ብለዋል፡፡

“የሰላም ዋርካችን እየቆረጡ አብሮነታችንንና አንድነታችንን በመበጣጠስ ሊሳለቁብን ለሚፈልጉ የውጭ ጠላቶቻችንና የውስጥ ጋሻ ጃግሬዎቻቸው ድምጽ ከመሆን እንታቀብም” ብለዋል፡፡ በማንኛውም ሁኔታና ጊዜ ለሰላምና ለአብሮነት ዋጋ መስጠት እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

Source link

Related posts

በገቢ አሰባሰብ የተጣጣመ የአሰራር ስርዓት ለማምጣት እየተሰራ ነው

admin

በሶማሌ ክልል 5ኛው ዙር የልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራም በይፋ ተጀመረ

admin

ከ750 በላይ የቀድሞ የሕወሃት ልዩ ሃይል፣ ፖሊስና ሚሊሻ አባላት ከተሐድሶ ስልጠና በኋላ ወደየ አካባቢያቸው ሊመለሱ ነው

admin