68.38 F
Washington DC
June 22, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

የአማራ ምሁራን መማክርት ያወጣው መግለጫ ፡፡

“በኦሮሚያ ክልል በተለይም በምዕራብ ኦሮሚያ ዞኖች የቀጠለው አማራ ተኮር የዘር ማጽዳት በዓለም አቀፍ ወንጀል የሚያስጠይቅ ነው” የአማራ ምሁራን መማክርት።

የአማራ ምሁራን መማክርት በጉዳዩ ላይ ያወጣው መግለጫ ቀጥሎ ቀርቧል፡፡

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስትና የፌደራል መንግስት በአማራ ሕዝብ ላይ በአማፂ ኃይሎችና በመንግሥት መዋቅር ውስጥ በመሸጉ የሽብር ተኮር ተግባር ተባባሪ አካላት የጋራ ቅንጅት እየተፈፀመ ያለውን አማራን የማጥፋት ዘመቻ በቁርጠኝነት ባለመከላከላቸው እና የዘር ማጽዳት ወንጀሉን በአደጋው ልክ ባለማውገዛቸው በኦሮሚያ የተለያዩ ቦታዎች በአማራ ተወላጆች ላይ የዘር ማጥፋት ዘመቻዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን የምሁራን መማክርት ገለጸ።

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በክልሉ የሚኖሩ ዜጎችን መሠረታዊ ደኅንነት የማስጠበቅ ሕጉ መንግሥታዊ ግዴታ ቢኖርበትም ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት ካለመቻለም በላይ ድክመቱን በኢ-መደበኛ እደረጃጀቶች ውስጥ ለመሽፋፈን መሞከሩ እንዳሳዘነው የምሁራን መማክርቱ ገልጿል።

እየተፈፀመ ያለውን አማራ ተኮር እልቂት የኢትዮጵያ ሕዝብና ዓለምአቀፉ ማህበረሰብ እንዲያውቀው የክልሉ መንግስትና ሚዲያው መሽፋፈንን እንደ ስልት መከተል መምረጣቸው ኃላፊነት የጎደለው ተግባር ነው ሲል ድርጊቱን ኮንኗል።

ፍላጎታቸውን በአመጽ እና በሃይል ለመጫን የትጥቅ ትግል ምርጫቸው አድርገው የነበሩ ኃይሎች ከለውጡ ጋር ተያይዞ ወደሰላማዊ የፖለቲካ መድረክ ገብተው እንዲሳተፉ የቀረበውን ጥሪ ተቀብለው ቢመጡም የተጠናዎታቸው ክፉ የጥፋት ዐመል አልለቀቃቸውም ያለው ምሁራን መማክርቱ፣ ባለፉት ሦስት ዓመታት በኦሮሚያ ክልል በተለይም በምዕራብ ኦሮሚያ ዞኖች የቀጠለው አማራ ተኮር የዘር ማጽዳት በዓለም አቀፍ ወንጀል የሚያስጠይቅ መሆኑን ጠቅሷል።

አንድ የረዥም ዘመን የሀገረ-መንግሥት ታሪክና ሥርዓት፣ ባላት ሀገር ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ እማራውን ዒላማ ያደረጉ የዘር ማጽዳት ወንጀሎች ያለማቋረጥ ሲፈጸም የፌደራሉም ሆነ የክልሉ መንግሥት አማጺ ኃይሎችን ከጥፋት ተልዕኳቸው መግታት አለመቻሉ አሳስቦኛል ያለው ምሁራን መማክርቱ፤ የፌዴራሉና የክልሉ መንግሥት የዜጎች ደኅነንት የማስጠበቅ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ አለመወጣታቸው ዜጎች በሥርዓቱ ላይ ተስፋ እንዲቆርጡ የሚያደርግ እና የሀገር ሀልወናን አደጋ ላይ የሚጥል መሆኑን ገልጿል።

ኢትዮጵያ እንደ ሀገር የተደቀነባትን የህልውና ስጋት እንድትሻገረው ከተፈለገ፣ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ መሽገው የዜጎችን ደኅንነት አደጋ ላይ በሚጥል ተግባር የተሰማሩ የጥፋት ኃይሎችን ማስቀጠል፣ ወንጀልንና ወንጀለኞችን ከለላ መስጠት፣… መንግሥታዊ ተግባር አለመሆኑ ታውቆ መንግሥት የዜጎችን ሠላምና ደኅንነት በሚያረጋግጥ መልኩ የሕግ የበላይነትን ብቻ በማስከበር ተግባሩ እንዲጸና ምሁራን መማህርቱ አሳስቧል።

በፈዴራሉ መንግሥት በኩል እየተወስዱ ያሉ የፖለቲካና የሕግ አግባብ እርምጃዎች የማያባራውን እልቂት የሚመጥኑ አይደለም ያለው መማክርቱ የመንግሥት ሆደ ሰፊነትም ሆነ ታጋሽነት በዜጎች መቃብር ላይ በመቆም የሚገለጽ አይደለም ብሏል፡፡ የዜጎቹን ሞት እንደዋዛ የሚያልፍና የሚመለከት መንግሥት ኃላፊነቱን ለመወጣት ቁርጠኝነቱ እና ፍላጎቱ የሌለው መንግስት እንጂ ዲሞክራሲን እየተለማመደ ያለ መንግስት አይደለም። ስለሆነም የፌደራሉ መንግሥት በኦሮሚያ ክልል የሚኖሩ ዜጎቹን ደኅንነት የማረጋገጥ ግዴታውን ሊወጣ ይገባል ብሏል።

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በሕግ የተሰጠውን ሥልጣንና ኃላፊነት በአግባቡ ሊወጣ ይገባል ያለው መማክርቱ የሕዝብ አብሮነትንና እሴቶችን የሚሸረሽሩ መግለጫዎችን ከማውጣትና ከከፍተኛ አመራር የማይጠበቁ ተንኳሽ ንግግሮች ከማሰማት ተቆጥቦ በክልሉ የሚኖሩ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ዜጎች ከጥቃት እንዲከላከል ጠይቋል፡፡

የሕግ የበላይነት ይከበር የምንለው የትኛውንም አካል ዘር፣ ቀለም፣ ሃይማኖት፣… ሳይለይ በእኩል እንድንዳኝ ስለምንሻ ነው ያለው መማክርቱ፤ መንግስትም በክልሉ የሚንቀሳቀሱ አማጺ ኃይሎች ላይ ተገቢውን ሕጋዊ እርምጃ እንዲወስድ እንጠይቃለን ብሏል።

የመንግሥት ተግባር የዜጎችን ሠላምና ደኅንነት ማስጠበቅ፣ ወንጀለኞችን ሕግ ፊት ማቅረብ ሆኖ እያለ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በተቃራኒው በክልሉ የሚኖሩ የአማራ ተወላጆች ደኅንነት አደጋ ላይ ወድቆ፣ በየዕለቱ የተጠናና የተቀናጀ የሚመስል አማራ ተኮር የዘር ማጽዳት ወንጀል እየተፈጸመ ባለበት ሁኔታ ችግሩን በመግለጫ ሸፋፍኖ ለማለፍ ከመሞከር ተቆጥቦ በክልሉ የሕግ የበላይነትንና ተጠያቂነትን ሊረጋግጥ ይገባል። ጥቃቱን ማንም ይፈጽመው በቡድን የጦር መሳሪያ የተደገፉ ወንጀሎችን መሽፋፈን በሕግ የበላይነት ላይ መሳለቅ ውሎ አድሮ በክልሉ መንግሥት ላይ ተጠያቂነትን ያመጣል ያለው መማህርቱ፤ ለወንጀለኞቹ መዋቅራዊ ከለላ መስጠት የመንግሥትነት ባህሪ አይደለም ብሏል፡፡

የኦሮሞ ሕዝብ ከወንድሙ የአማራ ሕዝብ ጋር የመናር ዕሴቱን በመጠበቅ የአማራ ሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን የዘር ማጥፋት ወንጀል እንዲያወግዝ እንዲከላከል ጥሪውን ያቀረበው መማክርቱ ፤ የአማራና የኦሮሞ ሕዝብ የዘመናት አብሮነት እና ትስስር በሴራ ፖለቲካ ሊበጠስ እንደማይችል ቁማርተኛ ፖለቲከኞች ሊያወቁት ይገባል ብሏል።

እንደ አማራ ከአያት ቅድመ አያቶቻችን የወረስናቸው የእውነት፣ የአብሮነት፣ የጽናት እሴቶቻችን ከሌሎች ወንድም የኢትዮጵያ ሕዝቦች ጋር በጋራ በመቆም እናስቀጥላቸዋለን ያለው መማክርቱ፤ በአማራ ሕዝብ ላይ እየተፈጸመ ያለውን የዘር ማጽዳት ወንጀል ሁሉም ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን፣ የዴሞክራሲ ኃይሎችና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች የግፉዓን ድምጽ እንዲሆኑ ጥሪውን አቅርቧል።

በመጨረሻም በምዕራብ ወለጋ ዞን ባቦ ጋምቤል ወረዳ ቦኔ ቀበሌ በግፍ ለተጨፈጨፉ ወገኖቻችን ቤተሰቦችና መላው ሕዝባችን መጽናናትን እንመኛለን ሲል የአማራ ምሁራን መማክርት መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡

Source link

Related posts

ቴክኖ ካሞን 17 ወደ ገበያ ገብቷል

admin

ከግንቦት ወር አጋማሽ ጀምሮ የክረምት ዝናብ በተወሰኑ የኢትዮጵያ ክፍሎች ተፅዕኖ እንደሚኖረው ተገለጸ

admin

ባለፉት ሦስት ዓመታት 56 ሽህ 790 የከተማና የገጠር ውኃ ተቋማት ግንባታ በማጠናቀቅ ከ15 ሚሊየን በላይ ነዋሪዎችን የንጹሕ መጠጥ ውኃ አቅርቦት ተደራሽ ማድረግ መቻሉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ፡፡

admin