71.98 F
Washington DC
May 17, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

የትንሣኤ በዓል ሲከበር በተለያዩ ምክንያቶች የተፈናቀሉ ወገኖችን በማሰብና በመደገፍ መሆን እንዳለበት የሃይማኖት መሪዎች አሳሰቡ፡፡

የትንሣኤ በዓል ሲከበር በተለያዩ ምክንያቶች የተፈናቀሉ ወገኖችን በማሰብና በመደገፍ መሆን እንዳለበት የሃይማኖት መሪዎች አሳሰቡ፡፡

ባሕር ዳር፡ ሚያዚያ 22/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የትንሣኤ በዓል ሲከበር በሰላም እጦት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን በማሰብና በመደገፍ ሊከብር እንደሚገባ ነው የሃይማኖት መሪዎች ጥሪ ያቀረቡት።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ-ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ሱራፌል እና የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ጠቅላይ ጸሐፊ ቄስ ደረጀ ጀምበሩ የትንሣኤ በዓልን አስመልክተው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በመልእክታቸው የትንሣኤ በዓል ሲከበር የተቸገሩ ወገኖችን በማሰብና በመርዳት መሆን አለበት ብለዋል።

በሀገሪቷ አንዳንድ አካባቢዎች በተፈጠረ የሰላም እጦት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ወገኖች በችግር ውስጥ በመሆናቸው ሁሉም እገዛ በማድረግ በዓልን ተደስተው እንዲውሉ ማድረግ እንደሚገባ ብጹዕነታቸው አሳስበዋል።

በዓሉን ሁሉም በደስታ እንዲያሳልፍ ለማድረግ የሀገሪቷን ሰላም ለማስጠበቅ ዘብ የቆሙ ኀይሎችም ሰላምና መረጋጋት እንዲመጣ የበኩላቸውን ጥረት እንዲያደረጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ሱራፌል በበኩላቸው ማኅበረሰቡ የትንሳኤ በዓልን ሲያከበር የተቸገሩትንና አስታዋሽ ያጡትን በማሰብና በመርዳት መሆን ይኖርበታል ብለዋል። በዓሉ ሲከበር እየተስፋፋ የመጣውን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ለመከላከል የተላለፈውን ምክረ ሀሳብ በመተግበር መሆን እንዳለበትም ገልጸዋል።

በክርስቶስ ትንሣኤ ሁሉም ሰው ክፋትን ከልቡ በማስወገድ በክርስትና ሕይወቱ ውስጥ ክርስቶስን መምሰል አለበት ብለዋል። ከተበላሸ ሕይወት በመጽዳት የፈጣሪን አብነት መከተልና የሰላም ተምሳሌት መሆን ያስፈልጋልም ነው ያሉት።

በዓሉን በመተሳሰብና በፍቅር ማክበር እንደሚገባ የገለጹት ደግሞ የአትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ጠቅላይ ፀሐፊ ቄስ ደረጀ ጀምበሩ ናቸው። ከፈጣሪ የተሰጠውን ወንጌል ከቃል ባለፈ በመተግበር እርስ በርስ ተከባብሮ በፍቅርና በሰላም መኖር ይገባል፤ ”እኛ ታርቀን ሌሎችን ማስታረቅ የዕለት ተዕለት ተግባራችን ሊሆን ይገባል” ብለዋል።

“ከገባንበት የጨለማ ጉዞ መዉጫዉ የአምላክን አብነት መከተል ነው“ ያሉት የሃይማኖት አባቶቹ አሁን በኢትዮጵያ የሚታየውን የሰላም እጦት ለመሻገር በአንድነትና በጋራ ተወያይቶ ችግሮችን ለመፍታት የተከናወነው ተግባር እዚህ ግባ የሚባል አለመሆኑ ያመጣው በመሆኑ ዕርቅና ይቅርታ ላይ ሊሠራ ይገባል ነው ያሉት፡፡

የሐሳብ ልዩነትን በኀይል ለመፍታት መሞከር ጥላቻን መዝራት ነዉና ለሰላም እርስ በርስ መጠባበቅና መደማመጥ ተገቢ ነው ያሉት የሃይማኖት አባቶቹ፡፡

ምዕመናን በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ጾምና ጸሎታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉም የሃይማኖት አባቶቹ አሳስበዋል።

ዘጋቢ፡- ጋሻው ፈንታሁን – ከአዲስ አበባ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

Source link

Related posts

ጣት በመጠቋቆም ችግራችንን መፍታት አንችልም (ከጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ)

admin

ኢትዮጵያኒዝም የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ጉልላት!

admin

ጁንታው የህወሓት ቡድን በመሰረተ ልማት ላይ ባደረሰው ጉዳት ሃገሪቱ ከአገልግሎት ከ2 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር በላይ አጥታለች

admin