79.57 F
Washington DC
June 14, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

“የተለያዩ ሲመስላቸው አንድ አድርጎ አሳያቸው”
“የተለያዩ ሲመስላቸው አንድ አድርጎ አሳያቸው”
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 21/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ፋሲል ጌጥ ነው አርማውን ለብሰው የሚዋቡበት፣ ፋሲል ጥበብ ነው የአጼውን
የእጅ ሥራ የሚያዩበት፣ ፋሲል ድል ነው የቴዎድሮስ ወኔ ያረፈበት፣ ፋሲል ባሕር ነው በፍቅር የሚዋኙበት፣ ፋሲል ገመድ ነው በፍቅር
የሚያስተሳስር፣ ፋሲል ወታደር ነው ለሰላም ውጊያ የሚያብር፣ ፋሲል መድብል ነው የጎንደርን ታሪክ የሚዘክር፣ ፋሲል ደስታ ነው
የሚያስጨፍር፣ የሚያዘምር፣ ጀግንነት ነው አሸንፎ የሚያኮራ የሚያስከብር። ጥበብን ከፋሲለደስ፣ አሸናፊነትንና አንድነትን
ከቴዎድሮስ የወረሰው ፋሲል፣ በጎንደር ተፀነሰ፣ በአማራ ጎለመሰ፣ በኢትዮጵያ ነገሠ።
ስፖርት አንድነት፣ ዓለምዓቀፋዊነት ነው። በስፖርት የተፋቀሩ፣ በስፖርት የከበሩ፣ በስፖርት የጥልን ግድግዳ የሰበሩ፣ ስለ ስፖርት
የጥላቻን መርዝ የቀበሩ ብዙዎች ናቸው። ስፖርት ስለ ፍቅር፣ ስለ ክብር፣ ስል ሕብር ያስወራል። እግር ኳስ በሜዳ ላይ ኳስን
ከመግፋት፣ ከተቃራኒ ጋር ከመፋለም፣ ድል አድርጎ ግብ ከማግባት፣ ውጤት ሰብስቦ ዋንጫ ከማንሳት በላይ ነው። እግር ኳስ 22
ተጨዋቾች በሜዳ የሚነግሡበት፣ ሺዎች በሜዳው ዙሪያ የሚደሰቱበት፣ ሚሊዮኖች ከፍ ሲል ቢሊዮኖች በቴሌቪዥን መስኮት
የሚሰባሰቡት ስለ አሸናፊነት የሚዘምሩበት ስለ ፍቅር የሚያወሩበት ነው።
ፋሲል ትውልዱ ጎንደር፣ ህልሙ ሀገር፣ መዳረሻው ክብር ነው። ሰዎች የተለያዩ ሲመስል ፋሲል ሰበሰባቸው፣ በፍቅር
አስተሳሰራቸው። ኢትዮጵያ የሚያምርባት አንድነት፣ የማይሸነፍ ፅናት፣ የማይደፈር ሕብረት ነው። የተሸረሸረ የሚመስለውን
አንድነት፣ የደከመ የሚመስለውን ኢትዮጵያዊነት ፋሲል አጠነከረው፣ በአሸናፊነቱ ማግሥት የበለጠ እንድጠናከር፣ እኔም ከብሬ
ሀገሬን እንዳከብር አግዙኝ ባለበት ወቅት የኢትዮጵያ እጆች በጋራ ተዘረጉ። ከምስራቅ ንፍቅ እስከ ምዕራብ ንፍቅ፣ ከደቡብ ንፍቅ
እስከ ሰሜን ንፍቅ የሠፈሩ ኢትዮጵያዊያን በፋሲል ድግስ ተገናኝተው፣ በፍቅር ባሕር ውስጥ በጋራ ዋኝተው፣ ከድግሱ ቀምሰው፣
ተጎራርሰው፣ ያላቸውን ለግሰው፣ የፍቅርን ካባ በጋራ ለብሰው፣ አንድነትን አንግሠው አመሹ። ፍቅር ድንበር፣ ዘር፣ ክፋትና ምቀኝነት
የለውም። ፍቅር መልካም ልብ ብቻ ነው ያለው። ጠመንጃ አንግቦ በበረሃ የወረዳው ወታደር ለውድ ሀገሩ ደሙን እየሰጠ የፋሲልን
ደስታ ሲሰማ በርሃ ነድዶ የሚያገኛትን ገንዘብ ስለ ፍቅር ሲል ለገሰ። ከዚህ በላይ መወደድ የለም። ከዚህ በላይ ክብር የለም።
ፍቅርም እንዲህ ነው።
ፋሲል በአዲስ አበባ ብዙዎችን ሰበሰባቸው፣ በጋራ ስለ ጋራ ጉዳይ አስወራቸው። በፍቅር አገናኛቸው፣ ስለ ፍቅር አሳሰባቸው፣
በፍቅር አነጋገራቸው። ኢትዮጵያውያን አወደሱት፣ አሞገሱት፣ አመሰገኑት፣ አምባሳድርም ሆኑት። ፋሲል መዝናኛ ሲመስለን የፍቅር
ገመድ ሆኖ አስደመመን፣ ታላላቅ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ፋሲልን አብረውት እንደሚሆኑ ቃል ገቡለት። ያሰባሰብከን፣ አንድ
ያደረከን አንተ ነህና ከፍታህን እነመኛለን አሉት። ከተሰበሰበው ብር ይልቅ የተሰበሰበው ፍቅር ያይላል። ፍቅር አፍስሷል፣ ማዕረግ
አልብሷልና።
ፋሲል ከነማ ወደ ባሕርዳርም መጣ። ነዋሪዎቹ ከመቀመጫቸው ተነስተው እያጨበጨቡ ተቀበሉት። እያደነቁ መልካም እድል
ተመኙለት። በፍቅር ራት ደግሰው፣ ቀጤማቸውን ነስንሰው፣ በጣና ዳርቻ አነገሡት። ፋሲል ብዙዎችን ዳግም አገናኘ። የደስታ
ምሽት ታለፈ። በአዳራሹ ውስጥ ያሉትን ብቻ ሳይሆን ሌሎችም በመንፈስ አገናኘ። ፍቅሩ ይገርማል። አንድነቱ ያስደምማል።
ደስታው አጀብ ያሰኛል። በጋራ ተጨፈረ። በጋራ ተዘመረ።
የፋሲል የደስታ ጊዜ አላለቀም። በጎንደር ይደምቃል። የአጼዎቹ ከተማ ልጆቿን ታከብራለች። ጎንደር በደስታ ትደምቃለች። በጃን
ተከል ዋርካ ግርጌ ይጠለላሉ። በቆብ አስጥል ጎዳና ይንሸራሸራሉ። በቤተ መንግሥት ግቢ ውስጥ ይሞሸራሉ። በገነት ተራራ አናት
ላይ ደስታቸውን ይገልጻሉ። ኢትዮጵያዊነት አንድነት፣ ኢትዮጵያዊነት ፅናት፣ ኢትዮጵያዊነት አይሸነፌነት፣ ኢትዮጵያዊነት አርቆ
አሳቢነት፣ ኢትዮጵያዊነት ዛሬን በጥበብ ኗሪነት፣ ነገን አሻጋሪነት ናት። ኢትዮጵያውያን አንድ ሲሆኑ ማቅ የሚያጠልቁ፣ የተለያዩ
ሲመስላቸው ደግሞ ጦር የሚሰብቁ፣ ጥል የሚናፍቁ፣ በኢትዮጵያ የሚሳለቁ ብዙዎች ናቸው። የኢትዮጵያ አንድነት ያስፈራቸዋል።
የኢትዮጵያ ክንድ ይሰብራቸዋል።
ኢትዮጵያ በሚስጥር የተፈጠረች፣ በሚስጥር የኖረች፣ በሕብረት የተጠበቀች፣ ከከበሩት ሁሉ የከበረች ናት። በኢትዮጵያ ሀዘን
ነጭ ካባ ሊለብሱ የሚመኙትን አንድ ሆነህ ማቅ አልብሳቸው። በአሻገር ጥል የሚከጅሉትን ከድንበር ወዲያ መልሳቸው። አንድነት
ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን የተሠጠ በረከት እንደሆነ በታሪክ ተነግሮሃል፣ በጀሮህ ሰምተሃል ፣ እድል ቀንቶህ በዓይን አይተሃልና።
አፍሪካውያንን ከጨለማ ጥላ ሥር ያወጣቸው፣ ቀኝ ገዢዎችን ያሳፈራቸው፣ ያስደነገጣቸው፣ የግፍ ምድር ሊያደርጓት ከከጀሉት
ጠራርጎ ያስወጣቸው አንድነት ነው። የዓድዋ አንድነት ፀሐይ ሆኖ በዓለም ያበራል። ታሪክ ሆኖ እስከ ወዲያኛው ይዘከራል፣ ዜማ
ሆኖ ለዘላለም ይዘመራል። ቋንቋ ሆኖ ለሁልጊዜ ይነገራል። ግርማ ሆኖ ጠላትን ያስፋራል። ታዲያ በዓድዋ ላይ የታዬውን አንድነት፣
እስከሞት የዘለቀ ኢትዮጵያዊነት፣ ወጀብ የማይመልሰው ጀግንነት፣ ጥርጣሬ የሌለው ድፍረት ለማጥፋት የማይከጅል የለም። አንተ
ግን ፊት አትስጣቸው፣ ለነካኝ ሁሉ ሌላ ዓድዋ ዛሬም አለ በላቸው። ስትለያይ የኢትዮጵያ ጠላቶች እልፍ ናቸው፣ አንድ ስትሆን ግን
እፍኝ ሙሉ ናቸው። ለምን ካልክ በአንድነትህ ስለምትጨብጣቸው። አንድነት የኢትዮጵያ መሠረት ነውና አንድነትህን አጠንክር።
አንድ ስትሆን ትከበራለህ፣ ችግሩን ታልፋለህ፣ ስትናገር ትሰማለህ።
በታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m


Previous article> ዶክተር ፈንታ ማንደፍሮ


Source link

Related posts

የጎርጎራ፣ወንጪና የኮይሻ ፕሮጀክት ኢትዮጵያ ተጨማሪ የቱሪዝም ምርትና አገልግሎት እንዲኖራት በማድረግ አለም አቀፍ ተወዳዳሪነቷን የሚጨምር ነው – የኢትዮጵያ የቱሪዝም ባለሙያዎች ማህበር

admin

ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ ለዐርበኞች ቀን የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

admin

የዓባይ ወንዝ መነሻን በዓለም አቀፍና በሀገር አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ እየሠራ መሆኑን የሰከላ ወረዳ ባህልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።

admin