51.91 F
Washington DC
May 11, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

“የብሔር፣ የቋንቋ እና የሃይማኖት ልዩነት ከኢትዮጵያ ታሪክ ጋር የተሳሰረ የሕዝብ ጌጥ እንጂ የ30 ዓመት ታሪክ ያለው የጸብ ምንጭ አይደለም”

“የብሔር፣ የቋንቋ እና የሃይማኖት ልዩነት ከኢትዮጵያ ታሪክ ጋር የተሳሰረ የሕዝብ ጌጥ እንጂ የ30 ዓመት ታሪክ ያለው የጸብ ምንጭ አይደለም”

“ሠላም ከሌለ ቁርሱ አይጣፍጥም፣ እንቅልፍ አይወስድም፣ ሀብትና ንብረት ማፍራት ቀርቶ ያለውንም መጠቀም አይቻልም”

በየትኛውም አካባቢ በዜጎች ላይ የሚደርስን ግድያ፣ መፈናቀልና የንብረት ውድመት መንግሥት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ማስቆም እንዳለበት የሀገር ሽማግሌዎች ጠየቁ።

ባሕር ዳር፡ መጋቢት 15/2013 ዓ.ም (አብመድ) ሕዝብ ክፉና ደጉን፣ ኃዘን እና ደስታውን በጋራ ያሳለፈባት፤ ለዲሞክራሲ ሥርዓት መዳበርና ለሀገር ነፃነትም በጋራ የታገለላት፣ ለዘመናት የቆየ የአብሮነት ባህል፣ ዕሴት እና የጋራ ታሪክ ያላት ሀገር ናት-ኢትዮጵያ፡፡ ይሁን እንጂ የዛኑ ያሕል ውስብስብ ችግሮችም አሉባት፤ የአብሮነት ዕሴቶች እየተሸረሸሩ አንዱ ሌላውን በጥርጣሬ ማየት ልምድ እየሆነ መጥቷል፤ በሰላም ወጥቶ መግባትም ፈተና መሆኑም ተስተውሏል፡፡ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ማንነትን መሠረት ያደረጉ አሰቃቂ ግድያዎች እየተፈጸሙ ነው፡፡ በዚህም ሰዎች ሞተዋል፣ ቁስለኛ ሆነዋል፣ ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል፣ በሀብትና በንብረት ላይም ውድመት ደርሷል፡፡

በዚህ ወቅት በኢትዮጵያ ላይ ተደራራቢ ችግር ተጋርጧል፡፡ በትግራይ ክልል የተከናወነውን ሕግ ማስከበር ምክንያት በማድረግ ዓለም አቀፍ ተቋማት በውስጥ ጉዳይዋ ጣልቃ ለመግባት እንደሾተል አሰፍስፈዋል፡፡ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተደራዳሪዎችም ለኢትዮጵያ ሰላም ቅን አያስቡም፡፡ የትሕነግ ርዝራዦችን ጨምሮ ከግጭት የሚያተርፉና በሕዝብ የሚነግዱ አካላትም ሕዝብን ለማተራመስ በትኩረት እየሠሩ ነው፡፡

አብመድ ያነጋገራቸው የሀገር ሽማግሌዎች እንዳሉት ኢትዮጵያውያን በአንድነት የሀገራቸውን ሕልውና ማስቀጠል አለባቸው፡፡ በሃይማኖት፣ በብሔርና በጎሳ ሳይከፋፈሉ በጥልቅ ሀገራዊ ስሜት መሰለፍ ይጠበቅባቸዋል፡፡

የጎንደር ሰላምና ልማት ሸንጎ ሰብሳቢና የኢትዮጵያ ሀገር ሽማግሌዎች ምክር ቤት አባል ባዩህ በዛብሕ እንዳሉት በብሔርና በጎሳ የተከፋፈለ ሀገር የተረጋጋ መንግሥት መመስረት አይችልም። ለዚህም ከዚህ ቀደም በጎሳ የተከፋፈሉ ሀገሮች የደረሰባቸውን የመፍረስ አደጋ መረዳት በቂ ነው ብለዋል፡፡

“የብሔር፣ የቋንቋ፣ እና የሃይማኖት ልዩነት ከኢትዮጵያ ታሪክ ጋር የተሳሰረ የሕዝብ ጌጥ እንጂ የ30 ዓመት ታሪክ ያለው የጸብ ምንጭ አይደለም” ብለዋል አቶ ባዩህ፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ከስሜታዊነት ወጥቶ በምክንያት የሚያምን እንዲሆን የጎሰኝነትን አስተሳሰብ ማስወገድ ይገባል፡፡ ሀገር ከሌለ ምንም ነገር ሊኖር እንደማይችል በሚገባ በመረዳት ለሀገር ሰላም፣ ለሕዝብ አንድነት፣ ለዴሞክራሲ መዳበርና ለጋራ ብልጽግና የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ መክረዋል፡፡

አቶ ባዩህ እንደሚሉት በየአካባቢው የሚነሳ የሰላም ችግር የብሔር ጉዳይ አይደለም፣ የፖለቲካ ጥቅም እንጂ፡፡ በየትኛውም አካባቢ ሕግ የማስከበር ኀላፊነት የመንግሥት በመሆኑ ጠንክሮ መሥራት አለበት ብለዋል፡፡

የመንግሥት ሥርዓትን ለማስከበር፣ ሠላም ለማስፈንና ሀገርን ለመመሥረት፣ የመንግሥት እና የሕዝብ ቁርጠኝነት ያስፈልጋል፡፡ ሕግና ሥርዓት ማስከበር በልመና አይሆንም ያሉት አቶ ባዩህ የሀገርን ሰላም የሚያደፈርስ አካል ተገዶ ሕግ እንዲያከብር ማድረግ ይገባል፡፡

በመሆኑም የመንግሥትም የሕዝብም ዋስትና የሆነውን የሕግ የበላይነት ለማስከበር ሁሉም አካል ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ መክረዋል።

በየትኛውም አካባቢ በንጹሃን ዜጎች ላይ የሚደርስን ግድያ፣ መፈናቀል፣ የንብረት ውድመት መንግሥት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ማስቆም እንዳለበት ነው አቶ ባዩህ የተናገሩት፡፡

የደሴ ከተማ አስተዳደር መጅሊስ ሊቀመንበርና የሀገር ሽማግሌው ሸሕ እንድሪስ በሽር በበኩላቸው የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ መረዳት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

“ሠላም ከሌለ የመኖር ትርጉሙ አይታወቅም፣ ወጣት፣ አዛውንት፣ ጎልማሳ፣ ቄስ፣ ሸህ፣ እስላም፣ ክርስቲያን፣ እንዲሁም የብሔር ጉዳይም ሊነሳ አይችልም” ብለዋል፡፡ “ሠላም ከሌለ ቁርሱ አይጣፍጥም፣ እንቅልፍ አይወስድም፣ ሀብትና ንብረት ማፍራት ቀርቶ ያለውንም መጠቀም አይቻልም” ብለዋል፡፡

በብሔር ለሚጣሉ አካላት “ነብያችን ዘርኝነት ጥንብ ነው ይላሉ፣ ዘርም የሚፈለገው እኮ ሀገር ሰላም ስትሆን ነው” በማለት ምክር አስተላልፈዋል። ለመኖር ሰላም ያስፈልጋል ያሉት ሸህ እንድሪስ የሀገርን ሰላምና የሕዝብን ደኅንነት ለመጠበቅ መንግሥት ከሚወስደው ርምጃ ባለፈ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ሊታገል እንደሚገባ አሳስበዋል።

“ያለችን ኢትዮጵያ ናት፣ አባቶቻችን አንድነቷን ጠብቀው እንዳስረከቡን፣ እኛም ለልጆቻችን የማስተላለፍና የማልማትም ግዴታ አለብን” ብለዋል። ሃይማኖት ላለውም ሆነ ለሌለው የኢትዮጵያ ሰላም ለሁሉም ዋስትና መሆኑን በማንሳት ሰላም የሚገኘው በምኞት ሳይሆን ለውጥ ማምጣት የሚያስችል ሥራ በመስራት እንደሆነ ጠቅሰዋል። የሃይማኖት ተቋማትም ይሕንን ማስተማር አለባቸው ብለዋል፡፡

እንደ ሸህ እንድሪስ ማብራሪያ ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ችግር አለባት፣ በኢኮኖሚው ዝቅተኛ ሕዝብ በጉያዋ አቅፋ የያዘች፣ ቴክኖሎጂን በአግባቡ መጠቀም ያልቻለች ሀገር ናት፤ በየጊዜው የሚከሰት የሰላም እጦትም ሀገሪቱን ወደ አዘቅት እየከተታት በመሆኑ ሁሉም አካል ሊያሳስበው እንደሚገባ ተናግረዋል። ሰላም የሚያደፈርሱ አካላትም ከድርጊታቸው ሊታቀቡ ይገባል ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

Source link

Related posts

በቢሾፍቱ ከተማ በጥይት የአንድን ግለሰብ ህይወት ያጠፋውን ተጠርጣሪ በቁጥጥር ስር ለማዋል ምርመራ ተጀምሯል – ፖሊስ

admin

ሦስቱ አንደኛ ውሸታሞች – አምባቸው ደጀኔ (ከወልዲያ) | Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider

admin

“የሰው ሕይወት ተከፍሎ የሚሳካ ማንኛውም ምድራዊ ፍላጎት እና ዓላማ ጠባሳው ለትውልድ ይተርፋልና ለሀገር ሰላም እና ለሕዝብ ደኅንነት ሁላችንም በጋራ እንቁም” የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን

admin