76.66 F
Washington DC
June 13, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

“የስንዴ ሰብልን በመስኖ በማልማታችን ተጠቃሚ አድርጎናል” አሚኮ ያነጋገራቸው አርሶ አደሮች

“የስንዴ ሰብልን በመስኖ በማልማታችን ተጠቃሚ አድርጎናል” አሚኮ ያነጋገራቸው አርሶ አደሮች

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 04/ 2013 ዓ.ም (አሚኮ) የአየሁ ጓጉሳ ወረዳ አርሶ አደሮች በግብርና ባለሙያዎች በተፈጠረላቸው ግንዛቤ በ2013 ዓ.ም የስንዴ ሰብልን በመስኖ አልምተዋል፡፡ የተሻለ ዘርና ግብዓት በመጠቀማቸውም በስንዴ ምርት ውጤታማ መሆናቸውን አርሶ አደሮቹ ገልጸዋል፡፡ በ2014 ዓ.ም ስንዴን የበለጠ በመስኖ እርሻ ለማምረት ከወዲሁ ዝግጅት መጀመሩንም የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታውቋል፡፡

ወጣት ደሴ አስማረ የአየሁ ጓጉሳ ወረዳ የአምበላ ቀበሌ ነዋሪ ነው፡፡ በ2013 ዓ.ም በበጋ የስንዴ መስኖ ልማት በአንድ ሄክታር መሬት ላይ 20 ኩንታል ስንዴ አምርቷል፡፡ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ባይከሰት ኖሮ የስንዴ ምርታማነትን ከዚህ በላይ ማሳደግ እንደሚቻል ገልጿል፡፡ ቀደም ሲል በመስኖ እርሻ የማምረት ልምድ ቢኖረውም ያገኝ የነበረው ምርት ግን አነስተኛ እንደነበርም ተናግሯል፡፡ የአዴት ግብርና ምርምር ማዕከል ያቀረበውን የስንዴ ምርጥ ዘር በመጠቀሙም ውጤታማ እንዳደረገው አስረድቷል፡፡ ካሁን በፊት ይጠቀምበት ከነበረው ዘር የተለዬ በመሆኑ የሰብሉ አበቃቀልና ፍሬ አያያዝ የተሻለ መሆኑን ተናግሯል፡፡

ወጣት ደሴ በቀጣይ ዓመት ግብርና ምርምሩ በሚያደርገው የሙያ ድጋፍ ከዚህ በበለጠ የበጋ ስንዴን ለማምረት እቅድ ይዟል፡፡ ሌሎች አርሶ አደሮችም የክረምት ዝናብን በመጠበቅ ብቻ ከማምረት ወጥተው በመስኖ ስንዴን እንዲያመርቱ መክሯል፡፡

ሌላው አርሶ አደር ተመስገን ጥላሁን አየሁ ጓጉሳ ወረዳ ችባችባሳ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ አርሶ አደር ተመስገን በ2013 ዓ.ም የበጋ ወቅት በአንድ ሄክታር መሬት ላይ ስንዴ በመስኖ አምርተዋል፡፡ አርሶ አደሩ እንዳሉት የአዴት ግብርና ምርምር ማዕከል የስንዴ ምርጥ ዘር ድጋፍ አድርጎላቸዋል፡፡ ከምርጥ ዘር በተጨማሪ የተደረገላቸው ሙያዊ ድጋፍ የተሻለ ዘር እና ማዳበሪያ እንዲጠቀሙ ረድቷቸዋል፡፡ በዚህም ከአንድ ሄክታር መሬት 34 ኩንታል ስንዴ አግኝተዋል፡፡ አቶ ተመስገን ሌሎች በአካባቢው ያሉ አርሶ አደሮችም በትኩረት ወደ ሥራው እንዲገቡ መክረዋል፡፡

አርሶ አደሮች በኩታ ገጠም እርሻ (ክላስተር) በመስኖ ስንዴ ማምረታቸው በኑሯቸው ላይ ለውጥ እንደሚያመጣ ከአሚኮ ጋር በነበራቸው የስልክ ቆይታ ገልጸዋል፡፡ በቀጣይ 2014 ዓመት ቀድመው በመዘጋጀት በበጋ ወቅት ስንዴ በማምረት ለገበያ ለማቅረብ እንደሚሠሩም ነግረውናል፡፡

በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የሠብል ሠርቶ ማሳያ ባለሙያ እናና ደሴ እንዳሉት በ2013 ዓ.ም የበጋ ወቅት

• 50 ሽህ 200 ሄክታር መሬት ላይ ስንዴ በመስኖ በማልማት 2 ሚሊዮን 8 ሺህ ኩንታል ምርት ለማምረት ታቅዷል፡፡

• በስምንት ዞኖች፣ በኹለት የመስኖ ፕሮጀክቶች በ63 ወረዳዎች ውስጥ በሚገኙ 223 ቀበሌዎች 13 ሺህ 334 ሄክታር መሬት በዘር ተሸፍኗል፡፡

• 35 ሽህ 596 አርሶ አደሮች ተሳትፈዋል፡፡

• 156 የውኃ መሳቢያ ፓምፖች ጥቅም ላይ ውለዋል፡፡

• 20 ሺህ 90 ሀገር በቀል እና ምርጥ ዘር ጥቅም ላይ ውሏል፤

• 26 ሺህ 563 ኩንታል የአፈር እና የቅጠል ማዳበሪያ ጥቅም ላይ ውሏል፤ አፈጻጸሙ 26 ነጥብ 5 በመቶ ነው፡፡

እንደ ወይዘሮ እናና ማብራሪያ የተመረጡ ማሳዎች በመኸር እርሻው በአጭር ጊዜ በሚደርሱ ሠብሎች አለመሸፈናቸው፣ ወቅቱን ያማከለ የግብዓት አቅርቦት አለመኖር፣ የውኃ መሳቢያ ሞተር መለዋወጫዎች በተገቢው መንገድ አለመቅረብ፣ የአርሶ አደሮች ፍላጎት አናሳነት ለውጤቱ ዝቅተኛ መሆን በምክንያትነት አንስተዋል፡፡ በቀጣዩ ዓመት እቅዱን ለማሳካት አርሶ አደሮች ማሳቸውን ቀድመው በሚደርሱ ሠብሎች እንዲሸፍኑ፣ ግብዓት በወቅቱ እንዲቀርብ ለማድረግ ሥልጠናዎች ተሠጥተዋል፡፡

በቀጣይ 2014 ዓ.ም ወይና ደጋ የአየር ንብረት ባላቸው አካባቢዎች የሚኖሩ አርሶ አደሮች ከኅዳር 15 በፊት፣ በቆላማ አካባቢዎች የሚኖሩ አርሶ አደሮች ደግሞ ከታኅሣሥ 15 በፊት ማሳቸውን በዘር መሸፈን እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

Source link

Related posts

የትግራይ ሕዝብ ከገጠመው ችግር እንዲወጣ የአፋር ሕዝብ ከጎናችን አልተለየም – ዶክተር ሙሉ ነጋ

admin

ትግራይ እንዴት ሰነበተች? (የመጨረሻ ክፍል)

admin

አቶ ደመቀ መኮንን ከአውሮፓ ህብረት አምባሳደሮችና ከሀገራቱ ተወካዮች ጋር ተወያዩ

admin