59.29 F
Washington DC
April 21, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

የሱዳን ወታደራዊ ክንፍ በኢትዮጵያ ላይ የፈጸመውን ወረራ ሱዳናዊያን ሊያወግዙት እንደሚገባ በዘርፉ ጥናታዊ ጽሑፍ የሠሩ የታሪክ ምሁር ገለጹ።

የሱዳን ወታደራዊ ክንፍ በኢትዮጵያ ላይ የፈጸመውን ወረራ ሱዳናዊያን ሊያወግዙት እንደሚገባ በዘርፉ ጥናታዊ ጽሑፍ የሠሩ የታሪክ ምሁር ገለጹ።

ባሕር ዳር ፡ የካቲት 17/2013 ዓ.ም (አብመድ) በሀገራቱ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ያነጋገርናቸው ዓለማየሁ እርቅይሁን (ዶክተር) በወሎ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና የቅርስ አስተዳደር መምህርና በዘርፉ ጥናትና ምርምር የሠሩ ምሁር ናቸው፡፡ የኢትዮጵያና የሱዳን ሕዝቦች በረጅም ጊዜ ከሀገረ መንግሥት ምሥረታ ጀምሮ በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ክንውኖች የጋራ ታሪክ የሚጋሩና ጥብቅ ቁርኝት ያላቸው መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ዶክተር ዓለማየሁ እንዳስረዱት የሀገራቱ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር ኢትዮጵያዊያን ሱዳንን እንደ ሁለተኛ ሀገራቸው፣ ሱዳናዊያን ደግሞ ኢትዮጵያን እንደ ሁለተኛ ሀገራቸው አድርገው እንዲቆጥሩት ያስቻለ ነው ብለዋል።

በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ገደማ ሱዳን ግብፅን ስትወር በወቅቱ ኢትዮጵያዊያን የሱዳን ሕዝቦችን በመቀበል በመተማ፣ በምዕራብ አርማጭሆ፣ በሰቲት ሁመራና በሌሎችም አካባቢዎች በሠላም ተቀብለው ማስተናገዳቸውን ዶክተር ዓለማየሁ ተናግረዋል።

ይህ ብቻም ሳይሆን ኢትዮጵያ እንግሊዞች ሱዳንን በወረሩበት ወቅት የእንግሊዝን ቅኝ ግዛት የተቃወሙና በዚህ ምክንያት በሀገራቸው መኖር ያልቻሉ ሱዳናውያንን የመከራ ጊዜ ያሳለፉባት ባለውለታ ሀገር ናት —ኢትዮጵያ፡፡ ይህንና ሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦችን ውለታ በማሰብ በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻ የሱዳን መሪ የነበሩት ካሊፍ አብዱላሂ ከዳግማዊ አፄ ምኒልክ ጋር ጠንካራ ግንኙነት መስርተው እንደነበረም የታሪክ ምሁሩ አውስተዋል።

ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅትም የኢትዮጵያ አርበኞች የሱዳን ጫካዎችን ተጠልለዉባቸው እንደነበር ዶክተር ዓለማየሁ ተናግረዋል፡፡ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ከስደት ወደ ሀገር ሲመለሱ የሱዳን ሕዝቦችና ግመሎች በክብር እንደሸኟቸው ታሪክ ምስክር ነው፤ ከዚያም በኋላ በ1950 (እ.አ.አ) አካባቢ በሱዳን ከፍተኛ የርዕስ በርዕስ ግጭት ሲከሰት በርካታ የአፍሪካ መሪዎች እልባት መስጠት ያልቻሉትን ውዝግብ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ሠላም እንዲሰፍን የጎላ ሚና ተወጥተዋል፤ በመሆኑም የኢትዮጵያ መኖር ለሱዳን ሕዝቦች ሠላምና መረጋጋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ከታሪክ ክስተቶች መረዳት እንደሚቻል ዶክተር ዓለማየሁ አስታውቀዋል።

የቅርብ ጊዜ ክስተትን በመጥቀስ በሱዳን መፈንቅለ መንግሥት ሲከሰት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጣልቃ በመግባት በሀገሪቱ ሠላም እንዲሰፍን ያበረከቱት አስተዋጽኦ ከፍ ያለ መሆኑን ዶክተር ዓለማየሁ አንስተዋል፡፡ ይህም የኢትዮጵያ መንግሥት እና ሕዝብ ከጥንት እስከ አሁን ለሱዳን ሕዝብ ሠላምና መረጋጋት ትኩረት ሰጥተው የሚሠሩ መሆናቸውን ማሳያ ነው ብለዋል።

የሱዳን ሕዝብም የሀገራቱን ታሪካዊ ግንኙነት ግምት ውስጥ በማስገባት ወታደራዊ ክንፉ እየፈጸመ የሚገኘውን ወረራ ማውገዝ እንደሚገባው ምሁሩ መክረዋል።

የሱዳን ወታደራዊ ክንፍም በኢትየጵያ ውስጥ የነበረውን ሕግ የማስከበር ዘመቻ እንደ አጋጣሚ በመጠቀም በድንበር አካባቢ ወረራ መፈጸሙ ተገቢ አለመሆኑን ገልጸዋል። ወታደራዊ ክንፉም በኃይል ከያዘው መሬት ለቆ መውጣት አለበት ብለዋል።

ዶክተር ዓለማየሁ በሀገራቱ መካከል በውል የሚታወቅ ድንበር አለመኖሩን ገልጸው ጉዳዩ ሠላማዊ በሆነ መንገድ እስኪስተካከል ድረስ በነበረበት እንዲቆይ የተደረሰበትን ስምምነት ሀገራቱ ማክበር እንዳለባቸው ነው የገለጹት፡፡

ድርጊቱ የኢትዮጵያ ሕዝቦች የህልውና ጉዳይን የሚፈታተን በመሆኑ የሱዳን ሕዝቦች ወታደራዊ ክንፉን ማውገዝ አለባቸው ብለዋል። ጉዳዩን የኢትዮጵያ መንግሥት፣ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የሚኖሩ ዜጎች እና ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ አቋም በመያዝ መታገል እንዳለባቸውም አመላክተዋል::

ዘጋቢ:- አዳሙ ሽባባው

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

Source link

Related posts

የህወሃት መሪዎች ላይ የተወሰደው ርምጃና የመተከሉ ጥቃት…!!! (D.W)

admin

አምባሳደር አለማየሁ ተገኑ ከሩሲያ ምክር ቤት የዓለም አቀፍ ጉዳዮች ኮሚቴ ሊቀመንበር ጋር ተወያዩ

admin

የገንዘብ እጥረት የባሕር ዳርን ስታዲዬም ጣሪያ እንዳይለብስ አድርጎታል፡፡

admin