71.98 F
Washington DC
May 17, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

የ“ሚሻ ሚሾ” ጨዋታ አመጣጡን ያውቁ ይሆን?

የ“ሚሻ ሚሾ” ጨዋታ አመጣጡን ያውቁ ይሆን?

ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 22/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በየዓመቱ በስቅለት በዓል አርብ ቀን ሕፃናት በየሰፈራቸው ተሰባስበው የክርስቶስን መሰቀል የሚያስታውሱ ግጥሞችን በማዜም የ”ሚሻሚሾ” ጨዋታን ያካሂዳሉ፡፡ አሚኮ ዛሬ በባሕር ዳር ከተማ ተሰባስበው የ”ሚሻሚሾ” ጨዋትን የሚጫወቱ ሕፃናትን አነጋግሯል፡፡

ሕፃን ዳንኤል የሻነ በማለዳ ተነስቶ ከጓደኞቹ ጋር በመሆን የሚሻሚሾ ጨዋታን እንደተጫወተ ነግሮናል፡፡ በጨዋታቸውም ዱቄት፣ ዘይት፣ በርበሬ፣ ጨውና ሌሎችንም በመሰብሰብ የስቅለት በዓሉን እያስታወሱት እንደሆነ ገልጿል፡፡ የተሰበሰበውን እህልም ከቤተ ክርስቲያን መልስ እንደሚመገቡት ነግሮናል፡፡

ሕፃን አማኑኤል ገደፉ ደግሞ “ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበትን ቀን ለመዘከር በየዓመቱ የስቅለት ቀን አርብ የሚሻሚሾ ጨዋታን እንጫወታለን” ብሏል፡፡ ሚሻሚሾን ለመጫወትም ግጥሙን እርስበርሳቸው በመማማር እንደሚለማመዱት አስረድቷል፡፡

የስቅለት በዓል ቀን ጎልተው ከሚወጡ ሃይማኖታዊና ባሕላዊ ትውፊቶች ውስጥ አንዱ የሕፃናት ጨዋታ የሆነው ”ሚሻሚሾ” ነው፡፡ የ”ሚሻሚሾ” ጨዋታን በየዓመቱ የስቅለት በዓል ዕለት ሕፃናት እንደሚጫወቱት የሃይማኖት ልሂቃን ይናገራሉ፡፡ ለመሆኑ ”ሚሻሚሾ” ምንድነው? አመጣጡ ባሕላዊና ሃይማኖታዊ ትስስሩ ምን ይመስላል? ለሚሉ ጥያቄዎች አሚኮ ምላሽ እንዲሰጡት የሃይማኖት ሊቃውንትን ጠይቋል፡፡

መምህር በትረወንጌል ካሣ በባሕር ዳር ከተማ የደብረ ምሕረት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ስብከተ ወንጌል ክፍል አገልጋይ ናቸው፡፡ ”ሚሻሚሾ” በኢትዮጵያ በስቅለት ቀን ወጣቶችና ሕፃናት የሚጫወቱት ባሕላዊ ክዋኔ እንደሆነ ነግረዉናል፡፡ እስራኤላዉያን ከግብጽ ባርነት አገዛዝ ወጥተው ወደ እርስታቸው በሚጓዙበት ወቅት ለምግብነት ዱቄት፣ ቂጣና ውኃ ይዘው እንደነበረ መምህር በትረወንጌል አስታውሰዋል፡፡ ይህ ትውፊት ዘመናትን ተሻግሮ የኢየሱስ ክርስቶስ በስጋ የመገለጽ ዘመን መድረሱን አስረድተዋል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስም የአካባቢዉን ማኅበረሰብ ባሕል ለማክበር በወቅቱ የዱቄቱንና የቂጣዉን ሥነ ሥርዓት ከማኅበረሰቡ ጋር ሲያከብር እንደነበረ ጠቁመዋል፡፡

ኢየሱስ ክርስቶስ በዕለተ አርብ የተቀበለው መከራ፣ የተሰደበው ስድብ፣ የተገረፈው ግርፋት ለሃይማኖቱ ተከታዮች ሙሉ ይዘቱን ጠብቆ እንዲተላለፍ ስለተፈለገ “ውሾ ውሾ” የሚለውን “ሚሻ ሚሾ” ወደሚለው ስያሜ በማምጣት የተዥጎረጎረ ብትር ይዘው ዱቄት እንደሚለምኑ አስረድተዋል፡፡

“ሚሻ ሚሾ” በዚያን ዘመን ጥሩ ገጽታ ባይኖረዉም በዚህ ዘመን ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስን ለመዘከር የታሰበ በመሆኑ ፈጽሞ ሊረሳ አይገባም ብለዋል፡፡ “ሚሻ ሚሾ” ሕፃናትና ወጣቶች “ኢየሱስ ክርስቶስን ስለኛ ተሰድበሀል፤ ስለኛ ተወግተሀል ብለው የሚዘክሩት ባሕላዊና ሃይማኖታዊ ጨዋታ ነው” ብለዋል መምህሩ፡፡

አሁን ላይ የ“ሚሻ ሚሾ” ጨዋታ እየተቀዛቀዘ መምጣቱን የጠቆሙት መምህሩ ወላጆችም ይሁኑ ምሁራን ትውልድን በማስተማር ባሕሉ እንዲቀጥል ሊያደርጉ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ በ“ሚሻ ሚሾ” ጨዋታ ሕፃናት ከሚገጥሟቸው ግጥሞች ውስጥ የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡

ሆ “ሚሻ ሚሾ” “ሚሻ ሚሾ” አንድ አውራ ዶሮ እግሩ ተሰብሮ እሜቴ ይነሱ ይንቦራቦሱ ስለ ስቅለቱ ካደረው ዱቄት ትንሽ ይፈሱ ጨው ጨው ማጣፈጫ፣ ዘይት ዘይት ማለስለሻ በማለት ያከብራሉ፡፡

ዘጋቢ፡- ቡሩክ ተሸመ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

Source link

Related posts

ተደብቆ ወደ አዲስ አበባ የገባ ስናይፐር፣ ብሬን፣ ሽጉጥና ከ5 ሺህ በላይ ልዩ ልዩ ጥይቶች ተያዙ

admin

መቐለን ጨምሮ የብር ቅያሪ ከተጀመረ 14 ቀናት ባለፋቸው የትግራይ ከተሞች አገልግሎቱ መጠናቀቁ ተገለፀ

admin

ሼህ ሰኢድ መሀመድ የኢድ አልፈጥር በዓልን ምክንያት በማድርግ በፈለገ ሕይወት አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ተገኝተው ሕሙማንን ጠየቁ፡፡

admin