79.66 F
Washington DC
June 19, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

የመኸር ወቅት እርሻቸውን በዘር ለመሸፈን በቂ ዝግጅት እያደረጉ መኾኑን አሚኮ ያነጋገራቸው አርሶ አደሮች ገለጹ፡፡

የመኸር ወቅት እርሻቸውን በዘር ለመሸፈን በቂ ዝግጅት እያደረጉ መኾኑን አሚኮ ያነጋገራቸው አርሶ አደሮች ገለጹ፡፡

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 10/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ወይዘሮ እድሜዓለም ዋነኛው በምዕራብ ጎጃም ዞን ቡሬ ዙሪያ ወረዳ አለፋባሲ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ ኑሮአቸውን በግብርና ሥራ የሚመሩት ወይዘሮ እድሜዓለም ሰብል ታጭዶ እንደተነሳ ማሳቸውን የማረስ ልምድ አላቸው፡፡አርሶ አደሯ በዚህ ዓመትም ማሳቸውን ሰብሉ እንደተነሳ ነው ማረስ የጀመሩት፡፡

በዚህ ዓመት ሦስት ሄክታር መሬት በዘር በመሸፈን 80 ኩንታል ምርት ለማግኘት እንዳቀዱ ነግረውናል፡፡ ለዚህም የበቆሎ ማሳቸውን ሦስት ጊዜ፣ የበርበሬ ማሳቸውን ደግሞ ሁለት ጊዜ ማረሳቸውን ከአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር በነበራቸው የስልክ ቆይታ ገልጸዋል፡፡

አርሶ አደሯ በ2013/14 የመኸር እርሻ ጥቅም ላይ የሚውል ስምንት ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ እና 3 ነጥብ 5 ኩንታል የበቆሎ ምርጥ ዘር ገዝተው ማዘጋጀታቸውንም ነግረውናል፡፡ ለግብርና ሥራቸው ውጤታማነትም ከግብርና ባለሙያዎች ድጋፍ እያገኙ መኾኑን አርሶ አደሯ ተናግረዋል፡፡ አርሶ አደር እድሜዓለም ሌሎች አርሶ አደሮች ማሳቸውን ደጋግመው እንዲያርሱ፣ ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ በአግባቡ እንዲጠቀሙ፣ የአረም እና የተባይ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ የምርት ጭማሪ ለማምጣት እንዲሠሩ መክረዋል፡፡

ሌላው አሚኮ ያነጋገራቸው በሰሜን ወሎ ዞን የራያ ቆቦ ወረዳ አራዳ ቀበሌ ነዋሪው አርሶ አደር መለሰ አስፋው ናቸው፡፡ ከመኸር እርሻው በተጨማሪ የከርሰ ምድርና የገጸ ምድር ውኃ በመጠቀም የቆላ አትክልትና ፍራፍሬ ችግኝ በማፍላት ለአርሶ አደሮች ያቀርባሉ፡፡ በመኸር ጤፍ እና ማሽላ ያመርታሉ፡፡

አርሶ አደር መለሰ በአሁኑ ወቅት ማሳቸውን በበልግ ዝናብ በሽንኩርትና በቲማቲም ሸፍነዋል፡፡ አርሶ አደሩ የእርሻ ማሳን ደጋግሞ ማረስ ሰብሉን እንደሚያፋፋው፤ በአረም እና ተባይ እንዳይጠቃ እንደሚያደርገው ተናግረዋል፡፡ ይህን ጠቀሜታ በመረዳት እንደ ሰብሉ አይነት ማሳቸውን በሚገባ ለማረስ ትራክተር በኪራይ ይጠቀማሉ፡፡ አርሶ አደር መለሰ እንዳሉት በትራክተር ማረሥ ጊዜን እና ጉልበትን ይቆጥባል፤ የአፈር ለምነትን በመጨመር ምርትና ምርታማነትን ያሳድጋል፤ በዓመት ሁለትና ሦስት ጊዜ ለማምረት እድል ይሰጣል ብለዋል፡፡

ምርትን ለማሳደግ የሚጠቀሙባቸው ግብዓቶች በወቅቱ እየቀረቡላቸው እንደኾነም ተናግረዋል፡፡ የመኸር እርሻ የዘር ወቅት እየተቃረበ በመሆኑ ማሳቸውን በሚገባ በማረስ ዝግጁ ማድረጋቸውን አርሶ አደር መለሰ ገልጸዋል፡፡

በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የሰብል ልማትና ጥበቃ ዳይሬክተር አለባቸው አሊጋዝ እንደገለጹት፡-

•በ2013/14 የመኸር እርሻ 4 ሚሊዮን 594 ሺህ 210 ሄክታር መሬት በዘር ለመሸፈን ታቅዷል።

•ከዚህም 131 ሚሊዮን 889 ሺህ 998 ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት በትኩረት እየተሠራ ነው፡፡ ሥራውን በውጤት ለመምራትም የክልሉ የሥራ ኀላፊዎች በተገኙበት ውይይት ተካሂዷል፡፡ አቶ አለባቸው እንዳሉት በክልሉ ጤፍ፣ ስንዴ፣ በቆሎ፣ ማሽላ፣ የሠሊጥ፣ የቢራ ገብስ፣ የሩዝ፣ የአኩሪ አተር፣ የቦለቄ፣ የማሾ እና የሽንብራ ዋና ዋና ሰብሎች ተብለው ተለይተዋል፡፡

እነዚህን ሠብሎች

•በ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ በኩታ ገጠም (ክላስተር) ይለማሉ።

•ከዚህም ከ63 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ታቅዷል፡፡

እንደ አቶ አለባቸው ማብራሪያ ዋና ዋና ሰብሎች ለሀገር ውስጥ የምግብ ፍጆታ፣ ለኢንዱስትሪ ግብዓት እና ለውጭ ሀገር ግብይት ካላቸው አገልግሎት አንጻር የተለዩ ናቸው፡፡

ለሰብሎቹ ፓኬጅ የማዘጋጀት፣ እቅዱን በዞንና በወረዳ ደረጃ የማስተዋወቅ፣ የአካባቢውን የምርታማነት መጠን የመለየት ሥራም ትኩረት ተሰጥቷቸው እየተሠሩ ነው ብለዋል፡፡ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የታቀደውን ውጤት ለማምጣት የአሰልጣኞች ሥልጠና መሰጠቱንም ገልጸዋል፡፡ ሥልጠናውን እስከ ቀበሌ የማዳረስ ሥራም እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

እንደ አቶ አለባቸው ገለጻ የሚፈለገው የምርት ጭማሪ እንዲመጣ አርሶ አደሮች የሚሰጣቸውን የተግባር ሥልጠና ወደ ውጤት መለወጥ ይጠበቅባቸዋል፡፡

ዳይሬክተሩ እንዳሉት

•እስካሁን 2 ሚሊዮን 377 ሺህ 561 ሄክታር መሬት ከአንድ ጊዜ እስከ ሦስት ጊዜ በድግግሞሽ ታርሷል።

•ከታረሰው መሬት ውስጥም 66 ሺህ 555 ሄክታር መሬት በክልሉ ባሉ 256 ትራክተሮች የታረሰ ነው፤ ይህም ከእቅዱ 52 በመቶ ያህሉን የሸፈነ ነው ብለዋል፡፡

አቶ አለባቸው እንዳብራሩት ቀድመው መዘራት ያለባቸው እንደ በቆሎ እና የቢራ ገብስ የመሳሰሉ ሠብሎች እየተዘሩ ነው፤ ነገር ግን የዝናቡ ሁኔታ እየጨመረ የሚሄድ ከኾነ ለበቆሎ ዘር አስቸጋሪ እንደሚሆንም ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

አቶ አለባቸው እንዳሉት 91 ሺህ 141 ኩንታል የበቆሎ ምርጥ ዘር ቀርቧል ፤ 71 ሽህ 913 ኩንታል በሁሉም ማኅበራት ገብቶ ለአርሶ አደሮች እየተከፋፈለ ነው፡፡ በእቅድ ከተያዘው 7 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ 3 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ቀርቧል፤ ከቀረበው ውስጥም 47 በመቶ ያህሉ አርሶ አደሮች ግዥ ፈጽመዋል፡፡ ሥራውን በውጤት ለመፈጸም የቀበሌ የግብርና ባለሙያዎች ከማሳ ዝግጅት ጀምሮ ለአርሶ አደሮች ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

በ2012/13 የመኸር እርሻ 4 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር በመሸፈን ከ111 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰቡን ከክልሉ ግብርና ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

Source link

Related posts

ኢትዮጵያ ምን ዓይነት ምርጫ ያስፈልጋታል?

admin

በሶስቱ ሀገሮች ብሔራዊ ገለልተኛ የሳይንቲስቶች ቡድን ባዘጋጀው የውኃ ሙሌት መርሃ ግብር መሰረት የግድቡ ሁለተኛው ዙር የውኃ ሙሌት እንደሚካሄድ ተገለጸ።

admin

ኮሚሽነር አበረ አዳሙ በኢትዮጵያ ጉዳይ የማይደራደሩ እንደነበሩ ቤተሰቦቻቸው ተናገሩ፡፡

admin