82.62 F
Washington DC
June 21, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

ዘመን ገፋት ዘመን ደገፋት – የጣና ዳሯን እመቤት፡፡

ዘመን ገፋት ዘመን ደገፋት – የጣና ዳሯን እመቤት፡፡

ባሕር ዳር፡ መጋቢት 16/2013 ዓ.ም (አብመድ) የጣና ዳሯ እመቤት፣ የዝመና ጊዜዋን ያላጌጠችው፣ መልካሙን ዘመን ያልጠገበችው፣ በጨለማ ተዳፍኖ የቆዬው ውበቷ የተገለጠ ይመስላል፡፡ በዘመነ ደርግ ታላቅ ትኩረት፣ በዘመነ ኢህአዴግ ታላቅ ክህደትና መረሳት የገጠማት እመቤቷ መልካሙን ቀን እስኪመጣ ድረስ ስትጠብቅ ዓመታት አልፈዋል፡፡ የቀድሞው የኢትዮጵያ መሪ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም የራዕይ ከተማዋ ጎርጎራ ዘመናዊነትን ጀምራው ሳታጌጥበት ዓመታትን ተቀምጣለች፡፡ ከደንቢያ እስከ ቀይ ባሕር ድረስ የንግድ ማዕከል የነበረችው ጎርጎራ የአስመራ ሜሎቲ ቢራ፣ የደንቢያ ጤፍ፣ ማር፣ ቅቤና ሌሎችም ምርቶች ያደምቋት ነበር፡፡

በዘመነ ደርግ የነበሩ የጦር መኮንኖች ከበረሃ ሲመለሱ የእረፍት ጊዜያቸውን ለማሳለፍ የሚመርጧት ከተማም ነበረች ጎርጎራ፤ በመንግሥቱ ኃይለ ማርያም ታላቅ ትሆን ዘንድ ተስፋ የተጣላባትና ራዕይ የተጀመረባት ይህችው የውብ መንደር የደርግ ዘመን ሲጠናቀቅ የእርሷም የጫጉላ ዘመን አብሮ ደበዘዘ፡፡ የአስመራው ሜሎቲ ቢራ ቀረባት፣ ከባሕር ዳር ጎንደር ጎርጎራ ይመላለስ የነበረው የንግድ ጀልባ ናፈቃት፤ ደርግን ተከትሎ የመጣው ስርዓት ፈፅሞ ረሳት፡፡ መንግሥቱ የሠሩአቸው ቤቶች፣ ያሰመሯቸው መስመሮች፣ የጎርጎራ የጫጉላ ቤቶች ተክዘው ደስታቸው እስኪመለስ ድረስ ጠበቁ፡፡ “ዘመን ይጥላል ዘመን ያነሳል” ነውና ነገሩ ዘመን አልፎ ጫጉላዋን ሳትጨርስ በውብ ጎጆ ስር ተጠልላ የቆዬችው ጎርጎራ የሚያያት አገኘች፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ሊያስገነባቸው ካሰባቸው ሦሥት የገበታ ለሀገር ፕሮጄክቶች አንደኛዋ ነች-ጎርጎራ፡፡ የጎርጎራ መልካም ጊዜ መመለስ ከመጀመረ ጀምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ባለሀብቶች በውቧ ከተማ ለማልማት ፈቃድ እየጠየቁ መሆናቸው ተስምቷል፡፡

የማዕከላዊ ጎንደር ዞን የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኀላፊ ዮሐንስ አማረ የገበታ ለሀገር ፕሮጄክት ይፋ ከሆነበት ጊዜ በኋላ ከ130 በላይ ባሀብቶች በጎርጎራ ለማልማት ጥያቄ ማቅረባቸውን ተናግረዋል፡፡ ለማልማት የጠየቁት ባለሀብቶች አዋጭ የሆኑ የልማት ፕሮጄክቶችን እንዳቀረቡ ተናግረዋል፡፡

የልማት ጥያቄዎቹ በገንዘብ፣ በልምድና በሥራ እድል ፈጠራ የተሻሉ መሆናቸውንም አስታውቀዋል፡፡ የሚቀርቡት በአብዛኛው በሆቴል ቱሪዝም እንደሆነ የተናገሩት ኀላፊው በአሳ ማቀነባበር፣ በንብ ማነብ፣ በእንስሳት ማድለብና እርባታ ላይም ለማልማት ጥያቄ መቅረቡን አስታውቀዋል፡፡

የገበታ ለሀገር ፕሮጄክት የሚያርፍበት ቦታ እስኪታወቅ ድረስ ባለሀብቶችን ሳይቀበሉ መቆየታቸውንም ተናረዋል፡፡

አሁን ላይ ግን የገበታ ለሀገር ፕሮጄክት ትክክለኛ ማረፊያ ስለታወቀ የክልሉ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ በሚሰጠው የውሳኔ ሀሳብ መሠረት ለባለሀብቶች ፈቃድ የመስጠት ሥራ ይሠራልም ብለዋል፡፡ የአካባቢው ማኅበረሰብና የዞን የአስተዳደር አካል ከፍተኛ የሆነ የመልማት ፍላጎት እንዳለውም ኀላፊው ገልጸዋል፡፡

በሥፍራው የሚተገበሩ ልማቶች የአካባቢውን ታሪክ፣ ወግና ባሕል ታሳቢ ያደረጉ ስለመሆናቸውም አቶ ዮሐንስ አማረ ተናግረዋል፡፡ አካባቢው ሃይማኖታዊ ተቋማት ያሉበት በመሆኑ እነርሱን ታሳቢ ያደረገና የበለጠ ተጠቃሚ የሚያደርግ ሥራ እንደሚሠራም አስታውቀዋል፡፡ የአካባቢውን ወግ፣ ባሕል፣ ታሪክና ሃይማኖት የሚያውክ ፕሮጄክት ተግባራዊ እንደማይሆንም ኀላፊው አስታውቀዋል፡፡

ይህ ዘገባ እከተጠናቀረበት ድረስ ከ30 ሚሊዮን እስከ 1 ነጥብ 28 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያላቸው የፕሮጄክት ልማት ጥያቄዎች መቅረባቸውን ነው አቶ ዮሐንስ የተናገሩት፡፡ ይህም ከገበታ ለሀገር ፕሮጄክት የማይተናነስ የገንዘብ አቅም እንዳለውም ነው የገለጹት፡፡ በጎርጎራ ባለሀብቶችን የሚያስተናግድ ያልተነካ ሀብት እንዳለም ጠቁመዋል፡፡

ለሆቴል ቱሪዝምና ለአገልግሎት ዘርፎች የሚውል 170 ሄክታር፣ ለአትክልትና ፍራፍሬ ልማት 60 ሄክታር፣ ለማንፋክቸሪንግ 270 ሄክታር፣ ለሌሎች የግብርና ልማት የሚውል 70 ሄክታር፣ ለደን ልማት የሚውል 30 ሄክታር መሬት ተለይቴ ለአልሚዎች ዝግጁ ተደርገዋል ብለዋል፡፡ በጎርጎራ የሰራባ የመስኖ ፕሮጄክቶችን መጠቀም እንደሚቻልም ጠቁመዋል፡፡

ጎርጎራ ለጎንደርና አካባቢው የቱሪዝም ማዕከል በመሆን እንደሚያገለግልም ነው የተናገሩት፡፡ የፕሮጄክት ሀሳቦቹ ጎርጎራን መነሻ በማድረግ እስከ ደልጊ ድረስ ለመሄድ ፍላጎት መኖሩንም ተናግረዋል፡፡ በጎንደር ዙሪያ ወረዳ ምጥረሃ አካባቢ የጣናን ዙሪያ መነሻ በማድረግ ባለሀብቶች ጥያቄ ማቅረባቸውንም አቶ ዮሐንስ ተናግረዋል፡፡ ፕሮጄክቶቹ በአካባቢው ተዳፍኖ የነበረውን የልማት አቅም እንደሚያነቃቁም ኀላፊው ገልጸዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

Source link

Related posts

የፖለቲካ ሽግግሩ በታሰበው ልክ ለውጥ እያመጣ አለመሆኑን የፖለቲካ ምሁራን ተናገሩ።

admin

የደብረታቦር የባሕል ማዕከልና አዳራሽ ቢሮ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ከተያዘለት በጀት ከ30 በመቶ በላይ የዋጋ ጭማሪ ሊያስከትል እንደሚችል ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ ገልጿል።

admin

በግለሰቦችና ቡድኖች እየተፈጸመ ያለውን የግድያና ዝርፊያ ወንጀል ለመከላከል እየተሰራ ነው – የትግራይ ክልል ጸጥታ ቢሮ

admin