75.45 F
Washington DC
June 20, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

ወልቃይት ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ለኹለተኛ ጊዜ ያስለጠናቸውን 86 ተማሪዎችን አስመረቀ።

ወልቃይት ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ለኹለተኛ ጊዜ ያስለጠናቸውን 86 ተማሪዎችን አስመረቀ።

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 15/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ወልቃይት ጠገዴ ቴክኒክና ሙያ ኮሎጅ በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች አስመርቋል። ኮሌጁ በደራጃ አራት በአካውንቲንግ፣ ዳታ ቤዝ እና በግንባታ ዘርፍ ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች ነው ዛሬ ያስመረቀው።

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ አስተዳደር አስተዳዳሪ አቶ አሸተ ደምለው፣ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ አስተዳደር ምክትል አስተዳዳሪ እና የሰላምና የሕዝብ ደኅንነት መምሪያ ኃላፊ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች፣ የተመራቂ ቤተሰቦችና የወፍ አርግፍ ከተማ ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

በማዕረግ የተመረቀው ይግዛው ገብሬ በነበረው ችግር ተቋርጦ የነበረው ትምህርት ተጠናቆ ለምርቃት በመብቃታቸው ደስተኞች መሆናቸውን ነው የተናገረው። በተመረቅንበት የሙያ መስክ ለማገልገል ዝግጁ ነኝ ነው ያለው።

ሌላኛዋ የማዕረግ ተመራቂ አዳነች እንኳዬነ በተመረኩበት ሙያ ቤተሰቤንና ሀገሬን ለማገልገል ዝግጁ እንደሆነች ገልጻለች፡፡

የማዕረግ ተመራቂው አዱኛ ፍስሃም ሥራ ፈጣሪ በመሆን ሌሎች አርዓያ እንዲያደርጉኝ እሠራለሁ ብሏል፡፡

በምረቃ ሥነ ስርዓቱ የወልቃይት ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ዲን መሐመድ ኑር ሲራጅ ወልቃይት ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ ትምህርት ማስተማር መጀመሩን ተናግረዋል። በአካባቢው በነበረው ችግር ትምህርት ሙሉ ለሙሉ ተቋርጦ የቆየ ቢሆንም ተማሪዎች ትምህርታቸውን ካቋረጡበት በማስቀጠል ለምረቃ መብቃታቸውን ገልጸዋል፡፡ተማሪዎች ፈተናዎችን አልፈው ለምርቃት በመብቃታቸው እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል፡፡
ተመራቂዎች በሰለጠናችሁበት የሙያ መስክ ሀገራችሁንና ራሳችሁን የምትጠቀሙ መሆን ይገባችኋል ነው ያሉት በመልዕክታቸው፡፡

ኮሌጁ የበጀት ችግርና የአሰልጣኝ መምህራን እጥረት እንዳለበትም ተናግረዋል። ኮሌጁ ዘረፋ ያጋጠመው በመሆኑ ለመማር ማስተማሩ የሚያገለግሉ ቁሳቁስ ሊተኩለት እንደሚገባም ጠቁመዋል። ኮሌጁ የመማር ማስተማር ሥራውን በተሟላ መንገድ እንዲሠራና የበጀት ድጋፍ እንዲድረግለትም ጠይቀዋል።

የወልቃይት ወረዳ አስተዳደሪ ክብረአብ ስማቸው የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ከአሸባሪው ትህነግ የአገዛዝ ሥርዓት ነፃ በወጣበት ማግሥት በመመረቃችሁ “ልዩ ናችሁ” ብለዋቸዋል። የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ በትህነግ የአገዛዝ ዘመን በደል ሲፈፀምበት ኖሯልም ብለዋል።

በተመረቃችሁበት ሙያ የወልቃይት ጠገዴን ሕዝብ በሚገባ ማገልገል ይገባችኋል ነው ያሉት።

የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ዞን አስተዳደር አስተዳዳሪ አቶ አሸተ ደምለው እንዳሉት የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ መማር እየቻለ እንዳይማር፣ መሥራት እየቻለ እንዳይሠራ፣ መራመድ እየቻለ እንዳይራመድ ታፍኖ የቆዬ ሕዝብ ነው፤ ያን ጊዜ አሳልፈን በመገናኘታችን እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል።

አሁን ላይ በለውጥ የመጣውን እድል በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባም ተናግረዋል። ለዚህ ድል ላበቁን ጀግኖች ምስጋና ይገባቸዋል ያሉት አቶ አሸተ ያገኘነውን ድል ለመንጠቅ የሚጥሩ ኃይሎችን መታገል እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ዳግም ባርነት አያስፈልገውም፤ ጠላቶቻችን መሬታችን እንጂ እኛን አይፈልጉምም ነው ያሉት። በሐሳብ እንደራጅ፣ በሐሳብ እንበልፅግ በሐሳብ ከበለፀግን ማንም ቢመጣ አይነቀንቀውም ነው ያሉት። ተመራቂ ተማሪዎችም በሙያቸው አካባቢያቸውን እንዲያገለግሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ለሀገራችን ምን ሠራን ብለን እንጠይቅም ነው ያሉት።

የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ አስተዳደር ምክትል አስተዳዳሪ እና የሰላምና የሕዝብ ደኅንነት መምሪያ ኃላፊ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ በመልዕክታቸው “ተመራቂዎች እጅግ እድለኞች ናችሁ፣ ለዘመናት የተጫነብን ባርነት ስንታገል ኖረን እውን በሆነበት ጊዜ በመመረቃችሁ እንኳን ደስ ያላችሁ ነው ያሉት። ዛሬ በቋንቋችሁ፣ በባህላችሁ አጊጣችሁ በመመረቃችሁ እድለኞች ናችሁ” ብለዋል።

የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ የራሱ ባሕልና ማንነት እያለው በሞግዚት አንተዳደረም ነበር ጥያቄያችን፣ ባሕላችን ታሪካችን እየጠፋ ነው የሚል ትግል ነበር የነበረን፣ ትህነግም የወልቃይት ጠገዴን ሕዝብ ማንነት በማጥፋት የታወቀ ነበር ፤ትህነግ የብሔር መብት ይለው የነበረው የይስሙላ እንደነበር ከወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ በላይ ምስክር የለም ነው ያሉት።

“መማር ማለት ራስን፣ ቤተሰብንና ሀገርን ማገልገል በመሆኑ ከመመረቃችሁ ማግሥት ምክንያታዊ የሆነ ሥራ መሥራት ይገባል፤ በራስ ልጆች መማር፣ ማስተማርና መመራት እየታዬ ነው። እናንተ ተመርቃችሁ የተሻለ ነገር ስትሠሩ የተሻለ ትውልድ ይመጣል። ለተሻለ ነገር ሁልጊዜም ራሳችሁን አዘጋጁ” ነው ያሉት።

ባሕላችውን፣ ወጋቸውንና ታሪካቸውን እንዲያሳድጉም ለተመራቂዎቹ ጥሪ አቅርበዋል ። << እኔ እችላለሁ ማለት አለባችሁ። የታገለንበትን ፍሬ የምናዬው በእናንተ ነው። ብዙ ኃላፊነት አለባችሁ። ለቤተሰብ፣ ለሀገርና ለወገን ታማኝ መሆን ይገባችኋል። ኮሎኔል ደመቀን ወልቃይት ላይ አየዋለሁ ያለ አልነበረም። ግን በፈጣሪ ኃይል ኹሉ ተችሎ ተገናኘን። እንችላለን ካልን እንችላለንን አደርጋዋለሁ ካልን ማድረግ እንደምንችል አሳይተናል። ወልቃይት ጠገዴ የማንንም ተፅዕኖ የመቀበል ትክሻ የለንም>> ብለዋል።

በአንድነታችሁ የሚመጣውን አሉባልታ መቀበል የለባችሁም ነው ያሉት።
ታሪክ ስለማያልፍ ለሀገርና ለሕዝብ ተቆርቁሮ መሥራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

ኮሌጁ የተሻለ ኮሌጅ ኾኖ እንዲቀጥል የተቻለንን ኹሉ እናደርጋለንም ብለዋል።

ኮሌጁ ካስመረቃቸው 86 ተመራቂ ተማሪዎቹ ውስጥ 44ቱ ሴቶች ናቸው።

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Source link

Related posts

71 ሚሊየን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው መድኃኒቶችና የህክምና ግብዐቶች ወደ ትግራይ ተልከው እየተሰራጩ ነው

admin

በ6ኛው ጠቅላላ ምርጫ ላይ ለመሳተፍ ዕጩዎች ያቀረቡ ፓርቲዎች ዝርዝር ይፋ ሆነ

admin

በቢሾፍቱ ከተማ በጥይት የአንድን ግለሰብ ህይወት ያጠፋውን ተጠርጣሪ በቁጥጥር ስር ለማዋል ምርመራ ተጀምሯል – ፖሊስ

admin