41.94 F
Washington DC
March 3, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

ከባሕር ዳር-ጢስ ዓባይ የአስፋልት መንገድ ግንባታ በወሰን ማስከበር ችግር ግንባታው እየተጓተተ ነው፡፡

ከባሕር ዳር-ጢስ ዓባይ የአስፋልት መንገድ ግንባታ በወሰን ማስከበር ችግር ግንባታው እየተጓተተ ነው፡፡

ባሕር ዳር ፡ የካቲት 16/2013 ዓ.ም (አብመድ)

አቶ ጌታሰው ብርሃኑ የሚኖሩት በባሕር ከተማ አስተዳደር በጢስ ዓባይ ከተማ አካባቢ ነው። ባሕር ዳር ከተማን ከጢስ ዓባይ የሚያስተሳስራት የአስፋልት መንገድ ሥራ መጀመሩ እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን መንገዱን ለማስጀመር የመሠረት ድንጋይ ካስቀመጡ ጊዜ ጀምሮ በከተማዋ መነቃቃት እንደፈጠረ ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ ግንባታው በታሰበው ልክ እየሄደ አለመሆኑን ተናግረዋል። “በርግጥ ለግንባታው መጓተት አንዱና ትልቁ ምክንያት ከካሳ ክፍያ ጋር ያለው አሠራር ነው፤ መንግሥት የካሳ ክፍያዉን ሳይፈጽም፣ የካሳ ክፍያ ውል እንኳ ሳይዝ እንዴት አድርጎ ነው ከሦስተኛ ወገን ነፃ ማድረግ የሚያስበው?” በማለት ጠይቀዋል።

ሥማቸው ማሩ የተባለ የአካባቢው ወጣት ደግሞ የጢስ ዓባይ ከተማ ለዘመናት የናፈቃት የአስፋልት መንገድ መጀመሩ ለአካባቢው ሁለንተናዊ ዕድገት ወሳኝ እንደሆነ አንስቷል፡፡ ባንክን ጨምሮ የተለያዩ መሠረተ ልማቶች በከተማዋ አለመኖራቸው የከተማዋን እድገት ወደ ኋላ እንዳስቀረው ተናግሯል።

“እዚህ እኮ ከክልሉም አልፎ ሀገርን የሚያኮራ መስህብ (የጢስ እሳት ፏፏቴ) አለ፤ ከመንገድ ግንባታው በተጨማሪ ከተማዋን ከተማ የሚያሰኙ መሠረተ ልማቶች ያስፈልጋሉ” ነው ያለው ወጣቱ።

የመንገዱን መገንባት ኅብረተሰቡ ለዓመታት ሲያነሳ የነበረው ጥያቄ መሆኑን ያስታወሰው ሥማቸው፣ መንግሥት ለነዋሪዎች በወቅቱ ካሳዉን ከፍሎ መንገዱን ከሦስተኛ ወገን ነፃ እንዲያደርግ ጠይቋል።

አብመድ በቦታው ተገኝቶ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች መንገዱ ዘግይቶ ከመጀመሩ ባሻገር ሂደቱ የኤሊ ጉዞ ስለሆነባቸው ቅር እንደተሰኙ ገልጸዋል።

ኢንጂነር ሚሊዮን ጌታቸው ከባሕር ዳር ጢስ ዓባይ የመንገድ ሥራ ፕሮጀክት ተቆጣጣሪ ናቸው፡፡ መልኮን የተባለ ተቋራጭ በ2012 ዓ.ም ግንባታዉን ቢጀምርም ከሦስተኛ ወገን ነፃ የሆነ ቦታ በማጣቱ ሥራዉን በተፈለገው መልኩ ሊገፋበት እንዳልቻለ አስረድተዋል።

“በዚህ ወቅት የፕሮጀክቱ አፈፃጸም 35 በመቶ መድረስ ነበረበት፤ ነፃ ቦታ በማጣታችን ከአምስት በመቶ የዘለለ ሥራ መሥራት አልቻልንም፤ አሁን በተቆራረጠ መልኩ ነው መሥራት የጀመርነው፤ የቀበሌና የወል ቦታን ብቻ በማግኘታችን እንጂ ለፕሮጀክቱ ሥራ የተነሳ አንድም የአካባቢው ነዋሪ የለም፤” ብለዋል።

ፕሮጀክቱ ንዑስ ተቋራጮችን ጨምሮ ሙሉ አቅሙን በመጠቀም ለመሥራት ቢያስብም ከሦስተኛ ወገን ነፃ የሆነ ቦታን ባለመረከቡ ሥራው እየተጓተተ እንደሆነ አስገንዝበዋል።

የባሕር ዳር ጢስ ዓባይ የመንገድ ሥራ ፕሮጀክት 21 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለውና በ767 ሚሊዮን ብር ወጪ ለመገንባት ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን ተቆጣጣሪው ጠቁመዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ሥራዉን ሲጀምር ለመገንባት ያቀደው የአስፋልት መንገድ ስፋቱ በከተማ 30 ሜትር፣ በገጠር ደግሞ 7 ሜትር ነበር። ይሁን እንጂ ከሕዝቡ የመንገዱ ፍላጎት፣ አካባቢውንና ከተማዋን ከማሳደግ አንፃር የመንገዱን ስፋት ለመጨመር መወሰኑን ኢንጂነር ሚሊዮን ጠቁመዋል፡፡ በዚህ መሠረት የመንገዱ ስፋት በከተማ 34 ሜትር፣ በገጠር ደግሞ 25 ሜትር መሆኑን አስረድተዋል።

ለመንገዱ ስፋት ተጨማሪ ገንዘብ ስለሚያስፈልግ ስምምነት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል። ከጥራት ጋር ተያይዞ አሁን በሚሠሩበት ቦታ ላይ ረግረጋማ የሆኑ ቦታዎችን በድንጋይ እየጠቀጠቁ እንደሆነ፣ ክረምቱ ከመግባቱ በፊት የውኃ ማፋሰሻ ሥራቸዉን እንደሚያጠናቅቁም አስረድተዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ያነሳው ቅሬታ በከፊል ትክክል እንደሆነ የጠቆሙት በባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳ የገጠር መንገድ አስተዳደርና አጠቃቀም ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አቶ ጥላሁን ፈጠነ ናቸው፡፡ ከማኅበረሰቡና ከቀበሌ አመራር ጋር በመሆን ከአትክልት ነፃ የሆኑ የወልና የተቋማት መሬቶችን ከካሳ ክፍያ ጋር ችግር የማይፈጥሩትን ቦታዎች የካሳ መረጃን በመያዝ ፕሮጀክቱ ሥራዉን እንዲቀጥል ተደርጓል ብለዋል።

“ፕሮጀክቱ በሚፈልገው ልክ በተለይ ከዋናው መንገድ ግራና ቀኝ ያሉት ቤቶችና አትክልቶች ከሦስተኛ ወገን ነፃ ሆነዋል የሚል ሀሳብ የለኝም” ያሉት ኀላፊው ፕሮጀክቱ ሙሉ አቅሙን ተጠቅሞ እንዲሠራ አላስቻሉትም ብለዋል። ይሁን እንጂ ከካሳ አከፋፈል ጋር ተያይዞ የክልሉና የፌዴራል መንግሥታት አዲስ በወጣው አዋጅ፣ ደንብና የመመሪያ አተረጓጎም ችግር ስለነበረ በወቅቱ ካሳ መክፈል እንዳልተቻለ አስረድተዋል። ይህ በመሆኑ ለማኅበረሰቡ ካሳን ማሳወቅና መክፈል እንዳልተቻለ ነው ኀላፊው የተናገሩት።

የካሳ ክፍያ ማብራሪያዉ ሲመጣ መረጃዎቹ በእጃቸው ስለሚገኝ ካሳዉን በማሳወቅ የመንገዱን ግራና ቀኝ ከሦስተኛ ወገን ነፃ በማድረግ ለፕሮጀክቱ እንደሚያስረክቡ አቶ ጥላሁን አረጋግጠዋል።

“ይህ መፍትሔ እስኪመጣ ብለን እጃችንን አጣጥፈን አልተቀመጥንም፤ ፕሮጀክቱ ለማኅበረሰቡ አስከሠራ ድረስ ከማኅበረሰቡ ጋር በመነጋገርና በመተማመን ሥራዉን እንዲቀጥል በማድረግ ላይ እንገኛለን” ብለዋል። ፕሮጀክቱ ሥራ ከጀመረ በኋላ በመንገድ ዳርቻ አትክልትና ቤት የሚገነቡ ሰዎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡም ኀላፊው አሳስበዋል፡፡

የሕጋዊ ባለ ይዞታዎች መረጃ ቀድሞ የተለየ እና የተያዘ በመሆኑ ሕጋዊ አሠራሮችን ብቻ የሚከተሉ መሆኑንም አስገንዝበዋል።

ከወሰን ማስከበር ጋር ተያይዞ ከባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር በኩል ያለውን ምላሽ ለማግኘት ባደረግነው ጥረት የሚመለከታቸው መሥሪያ ቤቶች መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም።

ዘጋቢ፡- ብሩክ ተሾመ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

Source link

Related posts

የአድዋን ድል ስናከብር የተሸረሸረውን አንድነትና ኢትዮጵያዊ እሴት ለመመለስ ቃል እየገባን መሆን አለበት – ዶክተር ሙሉ ነጋ

admin

አገር አቀፍ የማኅበረሰብ ተኮር የምክክር መድረክ በባሕር ዳር እየተካሄደ ነው።

admin

አበሻ የማይለምደው የለም:-  የወገንን እልቂት የዘር ጭፍጨፋንም ለምዶት ቁጭ አለ…?!? (መርእድ እስጢፋኖስ)

admin