56.68 F
Washington DC
April 21, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

“ከቀደሙት የቀደመ ርቆ ለመሄድ ያለመ”

“ከቀደሙት የቀደመ ርቆ ለመሄድ ያለመ”

ባሕር ዳር፡ የካቲት 18/2013 ዓ.ም (አብመድ) የመንግሥታትን ፖለቲካዊ ትርጉም፣ የሹማምንቱን ኩርኩም ተቋቁሞ ደብዛውን ሳያጠፋ “የዕውቀት መፍለቂያ” ተብሎ ተቀንቅኖለታል፡፡

በዘመናዊው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ታሪክ ውስጥ አይረሴና አይተኬ አሻራ አሳርፏል፡፡ የሰሜን ኢትዮጵያ የዘመናዊ ትምህርት ተቋም ብኩርና ባለቤትም ነው፡፡

የበርካታ ባለታሪኮች እና ተፅዕኖ ፈጣሪ ኢትዮጵያዊያን አስተሳሰብን የቀረፀ ተቋም እንደሆነ ከዘጠኝ አስርት ዓመታት በላይ አስቆጥሯል፡፡ በውለታው ልክ ያልተከፈለው ወይዘሮ ስኂን ትምህርት ቤት ከደሴ ሰማይ ስር ከከተሙት የዘመናት ቅርሶች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ ወይዘሮ ስኂን በሥነ መንግሥት፣ በምጣኔ ሀብት፣ በሙዚቃና ጥበብ፣ በስፖርትና በሳይንስ ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆኑ ታላላቆችን አፍርቶ ለዓለም አበርክቷል፡፡

በኢትዮጵያ ከተገነቡት ግንባር ቀደምት ዘመናዊ ትምህርት ቤቶች ውስጥ አንዱ የሆነው የወይዘሮ ስኂን ትምህርት ቤት በወሎው ንጉሥ ሚካኤል ልጅ በወይዘሮ ስኂን ሚካኤል ስም የተሰየመ ነው፡፡

በ1920 ዓ.ም ወይዘሮ ስኂን ሚካኤል ከራሳቸው 25 ሺህ ማርትሬዛ (ጠገራ ብር) እና በራሳቸው ርስት ኑዛዜ መሰረት በ1922 ዓ.ም በአራት የመማሪያ ክፍሎች ተመሠረተ፡፡በየጊዜው በርካታ ለውጦችን እያደረገ በ1950 ዓ.ም 63 ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተናገድ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትነት አደገ፡፡

በ1953 ዓ.ም ደግሞ የመጀመሪያዎቹን የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች የብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና አስፈተነ፡፡ በቀድሞው የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ በአሁኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስማቸው ጎልቶ ከሚታወሱ የወቅቱ ተማሪዎች መካከል ከብርሃነ መስቀል ረዳ እና ዋለልኝ መኮንን የወይዘሮ ስኂን ትምህርት ቤት ፍሬዎች ነበሩ፡፡ በ1953 ዓ.ም ከቀለም ትምህርቱ ጎን ለጎን በመምህርነት ሙያ፣ በእርሻ እና የተግባረ እድ ሙያዎች ስልጠና መስጠት ጀመረ፡፡ ይህም ትምህርት ቤቱ በሀገሪቱ የመጀመሪያው አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንዲሆን አድርጎታል፡፡

በ1956 ዓ.ም የሙዚቃ ትምህርት ቤት በመክፈት 40 ተማሪዎችን ተቀብሎ በአሜሪካዊው ሮናልድ ቤል አማካኝነት ማሰልጠን ጀመረ፡፡ ከ1956 ዓ.ም እስከ 1984 ዓ.ም የተለያዩ የሙያ ስልጠናዎችን ከቀለም ትምህርቱ ጎን ለጎን ሲሰጥም ቆይቷል፡፡

በየወቅቱ በሀገሪቱ በተፈራረቀው የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ጉልህ ድርሻ የነበረው ወይዘሮ ስኂን በየዘመኑ የመጡ መንግሥታት የስም እና የይዘት ለውጥ እንዲያስተናግድ ተገድዷል፡፡ ለመጨረሻ ጊዜም በደርግ የተቀየረው ስሙ በ1984 ዓ.ም ወደ ቀደመ ስሙ ተመልሶ “ወይዘሮ ስኂን የቀለም፣ ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ቤት” ተብሎ ተሰየመ፡፡

ከቀለም ትምህርቱ ጎን ለጎን የሙያ ስልጠናዎችን የሚሰጠው ወይዘሮ ስኂን በ1993 ዓ.ም የቀለም ትምህርቱን ለሆጤ ሰጥቶ ሙሉ በሙሉ የቴክኒክና ሙያ ተቋም ሆነ፡፡ በቀለም ትምህርቱ ከአዲስ አበባው ዳግማዊ ምኒልክ፣ ከሀረር መድኃኒዓለም እና ከአዳማው አፄ ገላውዲዎስ ትምህርት ቤቶች ጎን ይሰለፋል፡፡

ወይዘሮ ስኂን በሙያ ትምህርቱ ዘርፍም ከጀኔራል ዊንጌት፣ ከተግባረ እድ እና ከኢትዮ-ጣሊያን የሙያ ትምህርት ቤቶች ተርታ የሚሰለፍ አንጋፋ ተቋም ነው፡፡

የደሴ እና አካባቢው ሕዝብ እንደዓይኑ ብሌን የሚሳሳለት ወይዘሮ ስኂን በማኅበረሰቡ ዘንድ እንዲታይ የሚፈለገው በተለያየ መልክ ነበር፡፡ ገሚሱ ወደ ቀለም ትምህርት ቤትነቱ ተመልሶ የቀደመ ዝናው እንዲመለስ ይፈልጋል፡፡ ከቀለም ትምህርቱ ውጭ የሚታወቅባቸውን የሙያ ትምህርቶች አጠናክሮ እና አድጎ ማየት የሚፈልጉም ነበሩ፡፡ ነገር ግን ከጊዜ በኋላ የደሴ እና አካባቢው ሕዝብ የወይዘሮ ስኂን ትምህርት ቤት ፍላጎት ወደ ዩኒቨርሲቲ አድጎ መመልከት ሆኗል፡፡ ለዚህም ሲባል ከሀገር ውስጥ እስከ ውጭ ሀገር ድረስ እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል፡፡

የወይዘሮ ስኂን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የቀድሞው ዲን አቶ ጌታቸው ዓለምነህ ወይዘሮ ስኂንን ሲገልፁ “ቀድሞ ተፈጥሮ፤ ቀድሞ የተረሳ ተቋም” ብለውታል፡፡ ወይዘሮ ስኂን በየትኛውም መንገድ ለማደግ ቢለካ ከትርፍ በላይ እንደሆነ አቶ ጌታቸው ገልጸዋል፡፡ በሰው ኃይል፣ በቁሳቁስ፣ በቦታ እና በድጋፍ እርሾ እንዳለው በመጥቀስ፡፡

አቶ ጌታቸው እንዳሉት አሁን ወደ ዩኒቨርሲቲ እንዲያድግ በሕዝብ የሚታየው እንቅስቃሴ የረጅም ዘመን ጥያቄ ነው፡፡ የአሁኑን ለየት የሚያደርገው በውጭ ሀገር የሚገኙ የቀድሞ ተማሪዎች እና ደጋፊዎችም ተሳታፊ መሆናቸው ነው፤ መንግሥት የሕዝብን ጥያቄ ሊመልስ ይገባል፡፡

ወይዘሮ ስኂን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ አምስት ካምፓሶች፣ በቂ የሰው ኃይል፣ የረጅም ዘመን ልምድ እና ሃብት ያለው ተቋም መሆኑን ያነሱት ደግሞ የኮሌጁ ዲን አቶ ሰለሞን ይመር ናቸው፡፡

“ሕዝብ ሁልጊዜም ያደገ ተቋም ይፈልጋል” የሚሉት አቶ ሰለሞን “እንደ ወይዘሮ ስኂን የተረሳም ሆነ በሕዝብ የበረታ ጥያቄ የቀረበበት ተቋም ይኖራል ብየ አላስብም” ነው ያሉት፡፡

ከፌዴራል የመጡ ባለሙያዎች የተቋሙን አደረጃጀት አይተው ተስፋ ሰጭ ግብረ መልስ እንደሰጧቸውም ነግረውናል፡፡

መንግሥት የሕዝቡን ጥያቄ ለመመለስ እና ትምህርት ቤቱ ለሀገር ያበረከተውን የዘመን ውለታ በተገቢው መንገድ ሊመልስ ይገባልም ብለዋል፡፡

ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆችን ወደ ዩኒቨርሲቲ የማሳደግ ስልጣን ያለው የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በጉዳዩ ላይ ምን ይላል ስንል አነጋግረናል፡፡

የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት እና ኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር አመለወርቅ ሕዝቅኤል ተቋማቸው በረጅም ጊዜ 10 ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆችን ወደ ዩኒቨርሲቲ የማሳደግ እቅድ እንዳለው ጠቁመው በቅርቡ አምስት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆችን ለመለየት የሚያስችል ጥናት ይካሄዳል ብለዋል፡፡

በሀገር ደረጃ በጥናት የሚለዩት አምስት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆች ያሉበት ደረጃ ታይቶ እና የአቅም ግንባታ ድጋፍ ተደርጎላቸው እንዲያድጉ እየተሠራ ነው ብለዋል ወይዘሮ አመለወርቅ፡፡

ተጨማሪ የመረጃ ምንጭ፡-የወይዘሮ ስኂን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የሕዝብ ግንኙነት ቲም በ2007 ዓ.ም ቁጥር 2 ያዘጋጀው ጽሑፍ ተጠቅመናል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

Source link

Related posts

በ25 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነባው የይስማ ንጉስ ሙዚየም ተመረቀ

admin

ለኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከል ስራ የተመደበ ገንዘብ ያለአግባብ ጥቅም ላይ ያዋሉ ሀላፊዎች በእስራትና በገንዘብ ተቀጡ

admin

የስኳር ፋብሪካዎች ተሽጠው ዕዳቸውን እንዲከፍሉ ተወሰነ

admin