72.12 F
Washington DC
June 13, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

“ከሞጣ ሌላ ምን ይምጣ” | አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን

“ከሞጣ ሌላ ምን ይምጣ”

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 18/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የሞጣ ከተማ በ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በልእልተ ወለተ እስራኤል የተመሠረተች እድሜ ጠገብ ከተማ እንደሆነች ነዋሪዎቿ ይናገራሉ። ብርሃናማዋ የሞጣ ከተማ ለእንግዳ ቀለል ያለች ብርቅ ከተማ ናት።

እንደ ሌሎች ነባር እና ጥንታዊ ከተሞች ሁሉ ሞጣም ቀደምትነቷን የሚናገሩ መንፈሳዊ እና ቁሳዊ ሃብቶች በብዛት ከትመውባታል።

በልእልተ ወለተ እስራኤል እንደተመሠረተ የሚነገርለት የሞጣ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን፣ ተቀራራቢ እድሜ እንዳለው የሚነገርለት የአዳሻው ጌታው ሸህ ኢብራሂም መስጊድ፣ የአባይ ሰባራ ድልድይ፣ ከከተማዋ መመስረት ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያላቸው ሰባቱ ዋርካዎች እና ሌሎችም ታሪካዊ፣ ባሕላዊ እና መንፈሳዊ ትውፊት ያላቸው ሃብቶች ባለቤት ነች– ሞጣ።

ከዋሸራ እስከ ጎንጅ፣ ከጵላሎ እስከ ደብረ ወርቅ፣ ከዲማ ጊዮርጊስ እስከ ጨጓዴ ሀና፣ ከደምበጫ እስከ ጎንቻ የሚዘረፈው ቅኔ ሞጣ ቀራኒዮ መክተሚያው ነው አሉ።

ምነው አይታረስ ሞጣ ቀራኒዮስ፤

በሬ ሳላይ መጣሁ ከዛ እስከዚህ ድረስ።

የሚለውን ጥንታዊ ቅኔ ማስታወስ ሞጣ ቀራኒዮ አንዱ የቅኔ ቤት ማደሪያ ለመሆኑ ምስክር ነው።

በአምስቱ ዓመት የአርበኝነት ዘመን እምቢ ለነጭ ያሉ አርበኞች በዱር በገደሉ እየተሰወሩ ወራሪውን የጣሊያን ጦር አፈር ድሜ ሲያበሉት ጊዜ ያ ትውልድ እርሻ ትቶ ነጭ ማረስ መጀመሩን ያዩ የቅኔ ተማሪዎች እንደተቀኙት አንድ የአካባቢው ሰው አጫዎቱኝ።

ሞጣ ስተነሳ ለበርካቶች አብረው የሚታወሱት ሊቁ እና እውቁ የሃይማኖት አባት አራት ዓይና ጎሹ ናቸው። አራቱን የቤተክህነት ትምርቶች ጠንቅቀው ያወቁት እና የበቁት እኒህ አባት ከስንት ዘመን አንዴ ከስንቶች ለአንዱ ብቻ የሚሰጠውን የጠቢብ ስያሜ “የአራት ዓይና” ሊቅነት የተሰጣቸው የሞጣ ሊቅ ነበሩ አሉ። መንፈሳዊ ልጆቻቸው ዛሬም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ዘንድ አይተኬ ሚና አላቸው።

ጌታው ሸህ ኢብራሂም መስጊድ በስማቸው እስኪሰየምላቸው የበቁ፣ በኢትዮጵያ የእስልምና አስተምህሮ ጥቂቶች ብቻ የሚያገኙትን “ጌታው” የሚል ክብር የተቀዳጁ “ሸህ” የሚል የሊቅነት ማዕረግ የታደሉ የሞጣ ምልክት ናቸው አሉ። ጥንታዊው የአዳሻ መስጊድ በስማቸው የተሰየመላቸው ጌታው ሸህ ኢብራሂም በርካታ አሊሞችን እና ኡላማዎችን በማፍራት የኢትዮጵያ እስልምና ሃይማኖት ባለውለታ የሞጣ ከተማ ደግሞ ልዩ ምልክት ናቸው ይባላል።

“ከሞጣ ሌላ ምን ይምጣ” ሲል ጋሽ አበራ ሞላ የተቀኘላት ይህች ሽቅርቅር ግን ደግሞ ጥንታዊት ከተማ እንደ አልቦ እና ድሪ፣ እንደ አምባር እና ጥርስም፣ እንደ ቁንጮ እና ጋሜ የተስማማ ዘመናትን ያሳለፈ ሕብረ ወርቅ አብሮነት አላት። ክርስቲያን እና ሙስሊሞች በጋራ የሚኖሩባት፤ አዛን እና ቅዳሴ ወደፈጣሪ የሚደርስባት፤ አባሎ፣ ወይራ፣ እጣን እና ሽቶ የሚያውዷት ባለመዕዛ ከተማ ነች ሞጣ።

ለአብሮነት፣ ለፍቅር፣ ለሕብር እና ለኢትዮጵያዊ መልካምነት ከሞጣ ሌላ ምን ይምጣ?

ዘጋቢ: – ታዘብ አራጋው – ከሞጣ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

Source link

Related posts

የካይሮ  ወርቅ  ማውጫ  በቤኒሻንጉል… ወርቁን ይዝቃል…. ግድቡን ይሰልላል….!!! (እስሌማን አባይ)

admin

የትራንስፖርት ዘርፍ ስራዎች ችግር ፈቺ በሆኑ ጥናቶች ላይ መመስረት አለበት – የትራንስፖርት ሚኒስቴር

admin

“የፋሲል ከነማ ተጫዋቾች ኢትዮጵያን የሚመስሉ፣ የምንኮራባቸውና የድል ተምሳሌት ናቸው” የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ወርቀሰሙ ማሞ

admin