“እኛ መለዮአችንን አወለቅን እንጅ ልባችን ከመከላከያ ሠራዊት አልወጣም” ተቀናሽ የመከላከያ ሠራዊት አባላት
ባሕር ዳር፡ የካቲት 14/2013 ዓ.ም (አብመድ) ተቀናሽ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት ማኅበር በጸጥታ ሥራዎች ላይ መሥራት የሚያስችለውን ውይይት ከአባላቱ ጋር በአዲስ አበባ አድርጓል፡፡
የማኅበሩ ሊቀመንበር አስር አለቃ ደጀኔ ሸዋረጋ ማኅበሩ ተቀናሽ የመከላከያ ሠራዊት አባላት የተረጋጋ ህይወት እንዲመሩ የማስቻል ዓላማ ይዞ እየሠራ ነው ብለዋል።
ማኅበሩ በሀገራዊ የጸጥታ ጉዳዮች ሥራ ላይ ተሳትፎ እያደረገ ነው ፤ቀ ጣዩ ስድስተኛ ሀገራዊ ምርጫም ሰላማዊ እንዲሆን የራሱን ሚና ለመወጣትና ተሳታፊ ለመሆን ለምርጫ ቦርድ ጥያቄ አቅርቧል ነው ያሉት። ከመንግሥትና ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋርም በትብብር እንደሚሠራ ገልጸዋል።
ሠራዊቱ ለሀገር መስዋዕትነት የሚከፍለው ለችሮታ ወይም ውለታ ለመቀበል ሳይሆን ለክብሯ መስዋዕት መሆን ስለሚገባ ነው ብለዋል።
መንግሥትና የተፎካካሪ ፓርቲዎች ምርጫው የተረጋጋ እንዲሆን ከጸጥታ ተቋማት ጋር በመሆን በቅድመ ምርጫ፣ በምርጫ ጊዜና ከምርጫ በኋላ ኀላፊነታቸውን እንዲወጡ ማኅበሩ ጥሪ አቅርቧል።
የማኅበሩ አባላት በበኩላቸው “እኛ መለዮአችንን አወለቅን እንጅ ልባችን ከመከላከያ ሠራዊት አልወጣም፤ አሁንም የሀገርን ሰላም ለመጠበቅ ዝግጁ ነን”ብለዋል፡፡
ያሉ ልዩነቶቻችን ለሀገር ዘብ እንዳንቆም አያደርጉንም ፤ የሀገር ቀዳሚ ጉዳይ ዜጎቿ እንደሆኑ ተረድተን ለሰላሟ እንቆማለን ነው ያሉት።
ትናንት በመከላከያ ሠራዊቱ ቤት እያለን ከጎናችን ያጣናቸው ጓዶቻችን የወደቁት ለሀገር በመሆኑ እኛም ሀገር የማስቀጠል ኀላፊነታችንን እንወጣለን ብለዋል።
በሠራዊቱ ውስጥ ሲያገለግሉ የቆዩና አሁን የወገናቸውን ድጋፍ የሚሹ አባላትን መደገፍ እንደሚገባም አንስተዋል። በርካታ ተቀናሽ የመከላከያ ሠራዊት አባላት በአሰሪ ድርጅቶች ስር ተቀጥረው ስለሚሠሩ ድርጅቶች የሚያካሂዱትን የጉልበት ብዝበዛ ማቆም እንደሚገባቸውም ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡- ዘመኑ ታደለ – ከአዲስ አበባ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡