56.68 F
Washington DC
April 21, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Latest News

እንዳሰብነው አልሆነም፤ እንደ ፈራነው ሆነ

ሰው ከሞላ ጎደል የግንኙነቶቹ ውጤት ነው። ከወላጅ ቤት ትምህርት ቤት። ከደደቢት ከአሲምባ ምንሊክ ቤት። ከዳንስ ቤት ጸሎት ቤት። ከእሥር ቤት ፍርድ ቤት፤ ወደ ስደት ወደ አገር ቤት። የውጣ ውረዱ ተፅእኖ ቀላል አይደለም። መንገዱ ረጂም ዘወርዋራ ነው። ለያንዳንዱ ተሸክሞት የሚዞረው ኮሮጆ ታድሎታል።

ይኸኛው፣ ኮሮጆውን ከመቅመል ብዛት ስንዝር አሳብ መራመድ አቅቶታል። ያኛው፣ እንደ ሰነፍ ተማሪ ኮሮጆውን ያረገበትን አያውቅም። የቋጠረውን በጊዜ ፈትቶ አለመመርመር ግን አለማስተዋል ነው። ኮሮጆው ሊጣል በተገባው በብዙ ነገር ታጭቋል። ሸክም ከብዶት ይወላገዳል። ቅምቢቢት ተወልዶ እንዴት ፓሪ(ስ) እንደገባ ለመተረክ ጊዜ አይበቃንም። ባጭሩ፣ ስሙን መቀየር ነበረበት። ስሙን ለምን ቀየረ? በቅያሪ ስም “አቤት!” ሲል ከርሞ ምክንያቱ ተረስቶታል። አባቱን በቊም ክዶ ዜግነቱን ሁለቴ ሽጧል። ከእናቱ የተዋሰው ልሳን ዛሬ በፈረንሳዮች ተጠልፏል። አገር ቤት ሲመለስ ብቻ የብሔር ጠኔው ያገረሽበታል።

ይቺኛዋ፣ እሥሥት ስምና መልክ አላት። በደፈናው ከሰሜን ነኝ ትላለች። የት ቆማ ነው ሰሜን? ግልጽ አይደለም። ተቀላቅላ “ሥራ” እንድትሠራ በግርድና ወደ ዐረብ አገር ተጫነች።በገባች በስድስተኛ ወር ግሪክ አቴና ተገኘች፤ ካቴና ቡልጋሪያ። ቡልጋሪያ ኖራ ኖራ መገኛዋን ስትቃኝ፣ ይቅርብኝ ብላለች። ይኸኛው፣ ከአርባ ዓመት በኋላ እንኳ ማርሼ ባስቲ ላይ ቆሞ መርካቶን ይናፍቃል።

በአሥራ ሁለት ዓመቱ በቊንጮና በቊምጣ ሸገር ገባ፤ ሲስቊበት ተላጨ፤ እናቱ ሞታበት ነው አሉ፤ አጎፈረ፤ አባቱ ሞቶበት ነው አሉ። ምን ይሻለኛል ሲል ዘመነ አፍሮ ከች አለ፤ ምድረ አጋሚዶን ተቀላቀለ። ከሠላሳ ዓመት በኋላ ያቺው ቊንጮ ተወልውላ የባህር ማዶ ስም ወጥቶላት፣ በአገር መሪ አናት ላይ ቂብ ብላ በቴሌቪዥን መስኮት ታየች። በቴሌቪዥን ከታየች ድሮውንም ሐቀኛ ብትሆን ነው አለ። የልጅነት ጠጒሩ ግን መቀመጫ አድራሻዋን ቀይራ፣ ነገር ወደ ቀድሞው ሊመለስ አልቻለም!

እያንዳንዱ ሰው ቢያንስ የአመጋገቡ የአስተሳሰቡ የውሎው ድምር ነው። ልብ ከሰጠው ከአደባባዩ የሚማረው አለው።ልብ ከነሳው እፊቱ ቀርቦለት አይታየውም፤ ይገጫጫል፤ አልፎት ይሄዳል፤ የኋሊት የኋሊት ይከጅላል። እውነትን ይረጋግጣታል። ረግጧታልና መራራ እውነት አትምረውም።

“ውሸት ለመናገር አትሻም ምላሴ” የተባለበትና የተኖረበት ዘመን ነበር። ዛሬ ውሸት ለመናገር የሚሹ እንደ ለግዝትነ ተጣድፈው ይጠቃቅሱታል። የተናገርከው ውሸት ነው ሲባሉ፦ላንተ ውሸት ሊሆን ይችላል፤ ለኔ ግን እውነት ነው! ብለው ያፈጥጣሉ፤ ያድማሉ፤ ስም ያጠፋሉ። “ውሸት ለመናገር አትሻም ምላሴ” ማለቱን ይሉታል። “ለእውነት እሞታለሁ አልሳሳም ለነፍሴ”ን ግን ቢሞቱ አይጨምሩም። የያዙት “እውነት” ትርፍ እንጂ ዋጋ አያስከፍል! ነፍሳቸውን አጫርተዋልና፣ ትርፋቸው ክብረ ቢስ ነው!

ልብ የሰጠው፣ የእውነት እና የፍጻሜን ሞፈር ከደጁ ያገኘዋል፤ ፍጻሜን ባያስብ ግን ዐይኑ እያየች ሌሎች ሞፈሩን ቆርጠው ይጠቀሙበታል፤ እርሱም በጊዜ ተግቶ አላረሠምና እንደደኸየ ከሕይወት ይወገዳል። የብዙዎችን ፍጻሜ ያየ፤ ከፍጻሜ አፋፍ የተመለሰ፦ምን ሊበጀኝ? ይበል።ትርፍ ማጋበስ ከሞት አያስጥል! አብረውን የዋሉ፣ ፍቅርና ኃጢአታቸውን ያሰሙን ምነው ዝም አሉ? ልብ ላለው፣ አደባባዩ የሚናገረው አለው፦

ሃብቴ ተርፎ በዝቶ፣ ብዙ ቢያደረጀኝ| ስሞት ስንቅ አይሆነኝ፣ ኋላ ምን ሊበጀኝ አጊጬ ለብሼ፣ ብመስል ጨረቃ| ህይወቴ ለምልማ፣ ብትታይም ደምቃ ማነው ከሞት ነጥቆ፣ እኔን የሚያድነኝ| የዛሬው አበባ፣ የነገ ትቢያ ነኝ~[ሰይፉ ኃይለማርያም፣1964]

“ማነው ከሞት ነጥቆ፣ እኔን የሚያድነኝ?” በሁሉ ልብ የተማገረ የነፍስ ናፍቆትና ጥያቄ ነው። ናፍቆት ካለ፣ ምላሽ አለ፤ ናፍቆት ወደ ምላሽ ጠቋሚ ነው።ረሓብ ናፍቆት ነው፤ እንጀራ ምላሽ። ሞት ጠቋሚ ነው፤ ሕይወት ምላሽ። ጥጋብ ጥያቄውን እንዳያዘናጋው ሰው ይጠንቀቅ። ከሞት የሚያስጥለውን አለማወቅ አስፈሪ ፍጻሜ ነው።

© 2020 by Mitiku Adisu. All Rights Reserved

Source link

Related posts

Ataye entirely hit hard as Oromo radicals launch attack

admin

News Alert: EU Council to discuss “next steps of policy” to support peace, reflect on upcoming elections in Ethiopia

admin

Ethiopia reported 783 new coronavirus recoveries over the past 24 hrs

admin