56.68 F
Washington DC
April 21, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

‹‹እነርሱ ሕይወት ሰጥተው እኛን አኖሩን፤ እኛ ያለንን ሰጥተን ሕይወት ማኖር አለብን›› የዝክረ ዓድዋ ደም ለጋሾች

‹‹እነርሱ ሕይወት ሰጥተው እኛን አኖሩን፤ እኛ ያለንን ሰጥተን ሕይወት ማኖር አለብን›› የዝክረ ዓድዋ ደም ለጋሾች

ባሕር ዳር: የካቲት 20/2013 ዓ.ም (አብመድ)‹‹ሰው መሆን ክቡር›› በሚል መሪ ሀሳብ ዝክረ ዓድዋ የደም ልገሳ መርሃ ግብር በባሕር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።

የዓድዋ ጀግኖች መተኪያ የሌለውን ሕይወት ሰጥተው ሕዝብን ከነ ክብሩ፣ ሀገርን ከነ ድንበሩ አቆይተዋል፤ለሕይወት አልሰሰቱም። ስለሀገር ፍቅር ስለወገን ክብር ዓለም ያላሰበውን ድል አሳይተዋል።

ኢትዮጵያዊያንም የአባቶቻቸውን የድል በዓል በልዩ ልዩ ሁነት ይዘክሩታል።

125ኛ የዓደዋ የድል በዓል በባሕር ዳር ከተማ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ነው። የባሕር ዳር ደም ባንክ አገልግሎት ከአማራ ክልል ጤና ቢሮ ጋር በመተባበር ‹‹ሰው መሆን ክቡር›› በሚል መሪ ሀሳብ ዝክረ ዓድዋ የደም ልገሳ መርሃ ግብር አዘጋጅቷል።

በዝክረ ዓድዋ ደም የለገሰችው ትዕግሥት ዓባይ ዓድዋ ሲነሳ የጀግና ልጅ በመሆኗ ኩራትና ክብር እንደሚሰማት ተናግራለች። ‹‹ዓድዋ ላይ ከተሰራው ታሪክ አንፃር እኛ የሚቀረን አለ›› ያለችው ትዕግሥት ለዝክረ ዓድዋ ደም መለገስ ትንሹ ስጦታ እንደሆነ ነው የገለጸቸው።

‹‹እነርሱ በአንድነት የሰጡንን ሀገር እኛም በአንድነት መጠበቅ አለብን፤ አሁን በልዩ ልዩ ምክንያት መከፋፈል የለብንም፤ እነርሱ የማይቻል የሚመስለውን ችለው አሳይተውናል ፤እኛም የምንችልውን ሁሉ ማድረግ አለብን›› ነው ያለችው። ሌላኛው ደም ለጋሽ በለጠ ካሳሁን ‹‹ዓድዋ ሲነሳ ደስታ ይሰማኛል፤ መሥዋዕትነት ትዝ ይለኛል፤ ጀግንነት ጥንካሬ ይታወሰኛል›› ነው ያለው።

ዓድዋን ሥንዘክር ትንሿን የደም ስጦታ በመስጠት በዓድዋ ላይ የታየውን የአንድነትና ኢትዮጵያዊነት ስሜት ማስቀጠል እንደሚገባ አሳስቧል።

ለ13ኛ ጊዜ ደም ሲለግሡ ያገኘናቸው በላይ አዲሱ ‹‹ያልተገዛ ሕዝብ፣ ያልተገዛ ሀገር ውስጥ ስንኖር ደስታና ኩራት ነው የሚሰማኝ›› ነው ያሉት። ‹‹እኛ የዓድዋን አንድነትና ጀግንነት መሸከም አቅቶናል›› ያሉት በላይ ዓድዋ የህብረት ውጤት ነው፤ በህብረት መኖር እና ማደግ እንዳለብን ገልጸዋል። ‹‹ዓድዋ የአንድነት የኢትዮጵያዊነት ስጦታ ነው፤ እነርሱ ያላቸውን እኛ ግን የተረፈንን ነው የምንሰጠውም፤ እነርሱ ሕይወት ሰጥተው እኛን አኖሩን እኛ ያለንን ሰጥተን ሕይወት ማኖር አለብን›› ነው ያሉት።

ዓድዋ በየካቲት ብቻ መታሰብ እንደሌለበት እና ሁልጊዜም ከልብ ውስጥ መውጣት የማይገባው ኃያል በዓል እንደሆነም ነው የገለጹት። እኛ በእነርሱ እንኮራለን፣ እኛ የሚቀጥለው ትውልድ እንዳያፍርብን መሥራት አለብንም ብለዋል።

እንደ አስተያየት ሠጪው በጋራ ሆነን ድህነትና ኋላ ቀርነትን ማሸነፍ አለብንም፤ቀና አገልጋይ፣ ለወገን ታማኝ መሆንና መግባባት አለብንም፤ አንድ የፖለቲካ አጀንዳ ይዞ ከመፍሰስ በመቆጠብ መግባባት እና መተማመን ያስፈልጋልም፤ ተንኮልና ቂመኞች ካልሆን ዓድዋን መጠበቅ ነው፡፡

በባሕር ዳር ደም ባንክ ባለሙያ ሡራፌል ማርቆስ የዓድዋ የድል በዓልን ምክንያት በማድረግ ያለው የደም ልገሳ ተሳትፎ ጥሩ መሆኑን ተናግረዋል። ያን ዘመን ዛሬ ማድረግ ባንችልም የአሁኑ ትውልድ የሚችለውን ደም መለገሥ ዓለበትም ብለዋል።

በርካታ የኅብረተሰብ ክፍሎች የበጎ ፈቃደኞችን ደም እንደሚጠባበቁ የተናገሩት ሡራፌል አባቶች ደም ሰጥተው ሀገር እንዳቆዩት ሁሉ አሁን ላይም ደም በመለገስ ሕይወት መታደግ ይገባል ብለዋል።

የደም ልገሳ በማንኛውም ጊዜ የተለመደ መሆን እንዳለበትም ነው መልእክት ያስተላለፉት፡፡

ኅበረተሰቡም ደም መለገሥ ምንም አይነት ጉዳት እንደማያደርስ በመገንዘብ ደም የመለገሥ ባሕሉን እንዲያዳብር ጠይቀዋል።

በባሕር ዳር ከተማ የደም ልገሳ እንቅስቃሴ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱትንም ተናግረዋል።

ዘጋቢ:-ታርቆ ክንዴ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

Source link

Related posts

በአማራ ክልል የቆላ ስንዴን ለማልማት ከታቀደው 24 በመቶው በዘር መሸፈኑን ግብርና ቢሮ ገለጸ፡፡

admin

ሱዳን ኢትዮጵያን የወረረችባቸው 10 ምክንያቶች (መስፍን ሙሉጌታ)

admin

14ኛው የስልጤ ባህል፣ ታሪክና ቋንቋ ሲምፖዚየም ተከበረ

admin