91.11 F
Washington DC
June 21, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

‹‹ እነሆ ወደ ዮርዳኖስ ወረደ የእዳ ደብዳቤውም ተቀደደ››

‹‹ እነሆ ወደ ዮርዳኖስ ወረደ የእዳ ደብዳቤውም ተቀደደ››

ባሕር ዳር፡ ጥር 10/2013 ዓ.ም (አብመድ) ረቂቅ መልዕክት፣ ረቂቅ ፅንሰት፣ ረቂቅ ውልደት፣ ረቂቅ እድገት፣ ረቂቅ ጥምቀት፣ ረቂቅ ትምህርት፣ ረቂቅ ስቅለት፣ ረቂቅ ሞት፣ ረቂቅ ትንሳኤ፣ ረቂቅ እርገት፣ ረቂቅ ምኅረት፣ ረቂቅ ሕይወት፣ ረቂቅ መለኮት፤ እንኳን ምግበሩ ስሙ አይመረመርም ይላሉ ሊቃውንት፡፡ ለምን ቢሉ ከሚስጥርም በላይ፣ የሚስጥር ባለቤት የሆነ የማይመረመር ረቂቅ አምላክ ስለሆነ፡፡

ያለ ፈቃድ ከፍ ለማለት የተመኘ፣ ዝቅ ይላል፣ በገነት መኖርን ያልወደደ፣ መኖሪያው ሲኦል ይሆናል፡፡ ፈጣሪ ለሰው ልጆች የሚያስፈልጋቸውን ይሰጣል፣ የማያስፈልጋቸውን ይነሳል፡፡ ሁሉን ያውቃል፣ የትም ይገኛል፣ ሁሌም ይኖራል፣ የኖረበትና የሚኖርበት ዘመን አይቆጠርም፣ አይፈፀምም፣ ጅማሬ መንግሥትና ፍፃሜ መንግሥት የሚባል የለውም፡፡ ክበሩ ከዘላለም እስከ ዘላለም ነው፡፡

አዳምና ሄዋን መኖሪያቸው በገነት ተደረገ፤ የሚያስፈልጋቸውንና የሚበቃቸውን መሰጠታቸውን አላወቁምና ሌላ ክብርና ለሌላ መሰጠት ተመኙ፡፡ ሕግ ተላለፉ፣ ያን ጊዜም መንገዳቸውን ሳቱ፣ ከእውነት ወጡ፣ በሕግ ይኖር ዘንድ ግድ ነውና ሕግ ጣሱ፣ ከተሰጣቸውም ከተመኙትም ሳይሆኑ ወደ ሲኦል ወረዱ፡፡ የክብር ልብሳቸው ተገፈፈ፣ ግርማ ሞገሳቸው ኮሰሰ፣ መልካም ፍሬ ራቃቸው፣ የእሳት ላንቃ ገረፋቸው፣ የማያንቀላፋ ትል ነደፋቸው፣ ብርሃን ጠፍቶ ጨለማ ወረሳቸው፣ ከንፈራቸውን ነከሱ፣ አብዝተው አለቀሱ፣ ተፀፀቱ፣ ስለ ጥፋታቸው ይቅርታ ያገኙ ዘንድ ተማፀኑ፡፡

ያን ጊዜ ፈጣሪ ልቡን አራራ፣ ከሲኦል የሚወጡበትን ዘመን ነገራቸው፤ አምስት ቀን ተኩል ሲፈፀም ከሰማያት ሰማያት ወርዶ፣ ከድንግል ማርያም ተወልዶ፣ ተጠምቆ፣ ተሰቅሎ፣ ሞቶ፣ ከሙታን ተለይቶ ተነስቶ እንደሚያድናቸው ቃል ኪዳን ሰጣቸው፡፡ አምስት ቀን ተኩል በፈጣሪ አቆጣጠር ቅርብ ነበረች፤ አንድ ሺህ ዓመት አንድ ቀኑ ነውና፤ በሰው ልጅ አቆጣጠር ግን ረጅም ነበር፡፡

የተባለው ቀን ደርሶ፣ ቃል ሰው ሆኖ እስኪመጣ ድረስ አዳምና ሄዋን የዲያቢሎስ ተገዢዎች ሆኑ፡፡ የምህረት ቀን ቀረበ፣ የመዳን ቀን መጣ፣ ቃልም ሰው ሆነ፣ ‹‹ከአባቱ ሳይወጣ መጣ፣ ከአኗኗሩ ሳይለይ ወረደ፣ ከሶስትነቱ ሳይለይ መጣ፣ ከአንድነቱም ሳይለይ ወረደ፣ ከዙፋኑም ሳይለይ በስጋ ልጅ አደረ፣ ከመልዓቱ ሳይወሰን በማሕፀን ተፀነሰ፣ በላይ ሳይጎድል በማሕፀን ተወሰነ፣ በታችም ሳይጨመርበት ተወለደ›› እንዳለ ቃልም አስቀድማ በተመረጠች፣ በስጋ፣ በነብስና በሀሳብ ንጽሒት ከሆነች እመቤት አደረ፡፡

ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተልሔም ተወለደ፡፡ የብርሃን ቀን መጣ፡፡ ዓመተ ፍዳው አልፎ ዓመተ ምህረቱ ተጀመረ፡፡ ጥቂት በጥቂት አደገ፡፡ እንደ አምላክ እየሠራ እንደ ሰው ኖረ፡፡ 30 ዘመን ሲሆነውም ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ወርዶ በእደ ዮሐንስ ተጠመቀ፡፡ የአዳምና የሔዋን የእዳ ደብዳቤ በእምነ በረድ ተፅፎ አንደኛው በዮርዳኖስ፣ ሁለተኛው በሲኦል ተቀምጦ ነበር፡፡ ዲያቢሎስ የአዳምና የሔዋን ልጅነትን እንዲመለስ በተጠየቀ ጊዜ ምስክር ይሆነው ዘንድ ነበር ‹‹አዳም የዲያቢሎስ ተገዥ፣ ሔዋን የዲያቢሎስ ተገዥ›› ሲል በእምነ በረድ አፅፎ ያስቀመጠው፡፡

ጌታ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ወረደ፡፡ በዘመኑ መጥምቀ መለኮት ዮሐንስ የንስሃ ጥምቀት ያጠምቅ ነበር፡፡ ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ሐዲስ ያን ጊዜ ሲገልፁት ጌታም ዮሐንስን አጥምቀኝ አለው፡፡ ዮሐንስም ‹‹እኔ አንተን ማጥመቅ እንዴት ይቻለኛል?፣ አንተ አምላክ እኔ ፍጡር አንተ ፈጣሪ እንደምን ይሆናል? አንተ ወደ እኔ ትመጣለህን? እኔ ወደ አንተ እመጣለሁ እንጂ›› አለው ጌታም “አንድ ጊዜ አጥምቀኝ ይህ ለእኛ ተድላ ነው፤ አንተ መጥምቀ መለኮት ተብለህ ስምህ ሲጠራ ይኖራል፣ እኔም በዮሐንስ እጅ የተጠመቀ ተብዬ ትህትናዬ ሲነገር ይኖራል” አለው፡፡

ዮሐንሰ በእናቱ በኤልሳቤጥ ማሕፀን እያለ የጌታ እናት ማርያም ወደ ኤልሳቤጥ ቤት ሄዳ ሰላምታ በሰጠቻት ጊዜ በደስታ ዘሏል፡፡ ዮሐንስ ጌታውን ያጠምቅ ዘንድ አስቀድሞ የተመረጠ ንፁሕና ደግ አገልጋይ እንደሆነም ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ነግረውኛል፡፡ ዮሐንስ የኦሪት መጨረሻ የወንጌል መጀመሪያ የሆነ ቅዱስ ነውም ብለዋል፡፡

ዮሐንስ ጌታውን ያጠምቅ ዘንድ እሺ አለ፡፡ ጌታም ወደ ዮርዳኖስ ወረደ፡፡ ዮርዳኖስ ሸሸ፣ ባሕራት አልችሉት አሉ፡፡ ጌታም በዮርዳኖስ የአዳምና የሔዋን የእዳ ደብዳቤ በተቀበረበት ሥፍራ ቆመ፡፡ እንደ ሰውነቱ ረግጦ፣ እንደ አምላክነቱ አቅልጦ ያጠፋው ዘንድ፡፡ በእደ ዮሐንስ ተጠመቀ፡፡ ሰማያት ተከፈቱ፣ ተራራሮች ተንቀጠቀጡ፣ ዮርዳኖስ በብርሃን ተመላ፣ ዕፁብ ድንቅ ሆነ፡፡

የጌታ ጥምቀት በ30 ዓ.ም ተጀመረ፡፡ የንስሃ ጥምቀት ግን ከዚያ በፊትም ነበረ ብለውኛል ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ሀዲስ፡፡ እከበር አይል ክቡር፣ እቀደስ አይል ቅዱስ፣ እነግሥ አይል ዘላላማዊ ንጉሥ ሆኖ ሳለ የአዳምና የሔዋንን ልጅነት ለመመለስ፣ ምድርን ለመቀደስ፣ ክብሩን ለማውረስ፣ የእዳ ደብዳቤውን ለመደምሰስ ሲል ተጠመቀ፡፡ ‹‹ ከውኃና ከመንፈስ ያልተወደለ መንግሥቱን ሊያይ አይችልም›› እንዳለ ይህ ልደት የማይመረመር ረቂቅ ልደት ነው ያሉኝ ሊቁ፡፡

ወንዶች በአርባ ቀን ሴቶች ደግሞ በሰማንያ ቀን ይጠመቃሉ፡፡ ይህም ከጌታ የመንፈስ ልጅነት የሚያገኙበት ነው፡፡ ጌታ ግን በ30 ዘመን ተጠመቀ፡፡ ሊቁ ይሄን ሲያስረዱ ‹‹አዳም ተፈጠረ እንጂ አልተወለደም፡፡ ሲፈጠርም የ30 ዓመት ጎልማሳ ሆኖ ነው፡፡ ጌታም የአዳምን ልጅነት ሊመልስ ስለወደደ አዳም በተፈጠረበት የ30 ዘመን ሲሞላው ተጠመቀ፡፡ አዳምንም ወደ ቀደመ ልጅነቱ መለሰው››

ጌታም ሐዋርያትን ሲያጠምቁ በአብ በወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ያጠምቁ ዘንድ አዝዟቸዋል፡፡ ወንጌል እያስተማሩ ያጠምቁም ነበር፡፡ የኦሪቱ ጥምቀት የንስሃ ጥምቀት ነበር፤ ይሄኛው ግን ልዩ ጥምቀት ነው ይላሉ ሊቀ ሊቃውንት፡፡ ጌታ በዮርዳኖስ ሲጠመቅ ሚስጥረ ስላሴ ተገልጧል፤ ሐዋርያት የጌታን ጥምቀት አክብረውታል፣ ከዘመነ ሐዋርያት ዘመነ ሰማእታት፣ ወደ ዘመነ ሊቃውንት (ሰለስቱ ሚት)፣ ወደ ዘመነ መነኮሳት፣ እስካሁንም ድረስ እየተከበረ አለ ጥምቀቱ፡፡ በዓለ ጥምቀቱ ሐዋርያት ከባዕለ ሀምሳ በኋላ ማጥመቅ ከጀመሩበት ጀምሮ ዋና በዓል አድርገው ያከብሩት ነበር፡፡ ክርስቲያኖች አሁንም ያከብሩታል፡፡

ክርስቶስ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ እንደ ወረደ ሁሉ በጥምቀት ታቦታት ከመንበረ ክብራቸው ወጥተው ወደ ጥምቀተ ባሕር ይወርዳሉ፡፡ ታቦታትም በጌታ ጉዞ ይመሰላሉ፡፡ ካህናቱና አገልጋዩ የዮሐንስ፣ ባሕሩ ደግሞ የዮርዳኖስ አምሳል ነው፡፡ ምስጋናው የመላዕክትን ምስጋና የሚያስብ ነው፡፡

ጥምቀት በኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች ዘንድ ደምቆ ይውላል፣ የኢትዮጵያዊያንን አከባበር የሚመስል የለም፡፡ ክቡር የሆነው በዓል በተከበረች ሀገር ሲከበር ባሕሉንና ሃይማኖቱን ጠብቆ መሆን ይገባዋል ነው ያሉት ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ሀዲስ፡፡

እነሆ የጌታ ጥምቀት ዛሬ ነው፤ ታቦታት ወርደዋል፣ ባሕራት ተባርከዋል፣ ክርስቲያኖች ተቀድሰዋል፣ ምድር ተባርካለች፣ ነብስም ረክታለች፡፡ እንኳን አደረሳችሁ፡፡

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

Source link

Related posts

በጋምቤላ ክልል የሚንቀሳቀሱ ስድስት የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት መሰረቱ

admin

ለአዲሱ የሲዳማ ክልል መስተዳድር የተደረገው የክልሎች ድጋፍና አንደምታዎቹ | ዘ-ሐበሻ (ZeHabesha)

admin

ዝክረ ዓድዋ ዝግጅት የሁሉም አፍሪካውያን መሆን እንዳለበት በዩጋንዳ ማኬሬሬ ዩኒቨርስቲ የታሪክ ምሁር አስገነዘቡ፡፡

admin