44.76 F
Washington DC
February 26, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

‹‹እነሆ ቤተመቅደሱን ይጠብቁ ዘንድ ነብሮች ታዘዙ››

‹‹እነሆ ቤተመቅደሱን ይጠብቁ ዘንድ ነብሮች ታዘዙ››

ባሕር ዳር፡ የካቲት 09/2013 ዓ.ም (አብመድ) ምድር ጨለማ ለብሳ ተኝታለች። የሰው ልጅ ሁሉ ወደ ጎጆው ገብቷል። በውጭ ላይ ያሉ ጥቂት ሰዎችም ድምፅ አያሰሙም። ምድርን የሚያደነቁሯት ድምፆች ሁሉ ፀጥ ረጭ ብለዋል። መቼም የፈጣሪ ሥራ እፁብ ነው። ቀን ሰጥቶ በጎዳና የሚያመላልሰውን ሕዝብ ሌሊት ሰጥቶ ያሳርፈዋል። እርሱ አይተኛም ፍጡር ግን ይተኛል። ግሩም ነው።

ጨለማ ስልጣኑን ለብርሃን ሊያስረክብ ተቃርቧል። በእውን እና በህልም መካካል ላይ እያለሁ ከማደሪያዬ አጠገብ ካለው ደብር ለስለስ ያለ የቄስ ድምፅ ይሰማኝ ጀምር። ከብዙ ነገር ያዘገየኝ እንቅልፍ ይታገለኝ ጀምሯል፡፡ በማለዳ ላቀናበት የወጠንኩት መንገድና መልካሙ የቄስ ድምፅ ተባብረው አነቁኝ፡፡ ከአልጋዬ ጋር ተሰናብቼ ፊቴን በውሃ አራስኩት፡፡ ለጉዞዬ የሚያስፈልጉኝንም አዘጋጀሁ፡፡ ጠባቧ ቤተን ተሰናብቼ ወጣሁ፡፡ እግሬም በቀስታ ልብን እያረሰረሰ ወደ ሚወርደው የቄሱ ድምፅ በኩል አዘገመ፡፡ ነጫጭ የለበሱ ምዕመናን ወደ ደብር መሄድ ጀምረው ነበር፡፡

ፀጥ ረጭ ባለው በድቅድቅ ጨለማ

ሄድ መጣ የሚል የካህናት ዜማ

አየሩን ሰንጥቆ ለጀሮ ሲሰማ

ድምፁ ቀስቅሷቸው ለፅድቅ የተነሱ

ተመስገን እያሉ ነጭ እየለበሱ

በድቅድቅ ጨለማ እየገሠገሱ

ድምፁ ወዳለበት ወደዚያው ደረሱ፡፡

እኔም የቄሱን ድምፅ ተከትዬ ደረስኩ፡፡ ዕለተ እሁድ ነበር፡፡ በማለዳ መነሳቴ አንድ ወዳጄ ‹‹ታላቅ ቦታ ታይ እንደሆነ ጉዞ ተዘጋጅቷል›› ብሎ ጋብዞኝ ወደዚያ ለመሄድ ነበር፡፡

በባሕርዳር ባለ እግዚአብሔር ቤተክርስቲያን በምሥራቅ ንፍቅ ምዕመናንን ወደ ታሪካዊው ቦታ የሚያደርሱ መኪናዎች ተደርድረው ቆመዋል፡፡ ነጫጭ የለበሱ ምዕመናንም ተሰልፈው ወደ መኪናዎቹ መግባት ጀምረው ነበር፡፡ እኔም እንደ እነርሱ ሁሉ ተሰለፍኩ፡፡ ለጉዞ የምታስፈልገኝን ወረቀት አሳይቼ ከአንደኛው መኪና ገባሁ፡፡ ምዕምናን የጋራ ፀሎት አድርሰው ብዙ ሳይቆይ የገባሁበት መኪና ተንቀሳቀሰ፡፡ ጨለማው ምድርን ለብርሃን አስረክቦ አለቀቀም፡፡ የሥልጣን ዘመኑ ግን ሊጠናቀቅ ተቃርቧል፡፡

መኪናው ፊቱን ወደሰሜን አዙሮ ጉዞ ጀመረ፡፡ የባሕርዳር ጎዳናዎች ባዶ እንደሆኑ ናቸው፡፡ ጣናን መጎናፀፊያ፣ ዓባይን መቀነት ዘንባባዎቹን ደግሞ የወርቅ ጥላ አድርጋ የምትኖረው ባሕርዳር ከቀኑ በሌሊት የምታምር መሰለኝ፡፡ ፀጥ ባለው ሌሊት ውብ ናት፡፡ ረጅሙን የዓባይ ድልድይ ተሻገርን ገሰገስን፡፡ ከእኔ በስተቀር በመኪናው ውስጥ ያሉት ዝማሬ ላይ ናቸው፡፡ በጋራ ከሚዘምሩት ዝማሬ አንድም ስንኝ አለማወቄ ገረመኝ፡፡ ከእነርሱ ጋር የጋራ የሚያደርገኝ ከአንድ መኪና ውስጥ መሆኔና ሲያጨበጭቡ ማጨብጨቤ ብቻ ነው፡፡ ራሴን ታዘብኩት፡፡ አብዝቶም ገረመኝ፡፡ ጉዟችን ቀጥሏል፡፡ የጨለማው ጉልበት ደክሟል፡፡ ብርሃን ስልጣኑን ሊረከብ እየቋመጠ ነው፡፡ ዘንዘልማን አልፈን ገሰገስን፡፡

ትንንሽ የገጠር ከተማዎችን አልፈን ተጓዝን፡፡ የጨለማ ዘመን ተጠናቀቀ፡፡ ብርሃን ዙፋኑን ጨበጠ፡፡ ንግሥቲቷ ፀሐይ በምሥራቅ እስክትወጣ እየተጠበቀች ነው፡፡ ሀሙሲት ከተማ ስንዳረስ ከመንገዳችን በስተ ግራ በኩል ካለው ሜዳ ነጫጭ ድንኳኖች ተመለከትን፡፡ ከድንኳኖቹ አጠገብ መኪናዎች በሰልፍ ቆመዋል፡፡ ከመንገዱ በስተቀኝ በኩል ደግሞ በጥቅጥቅ ደን የተሸፈነ ደብር ይታያል፡፡ መኪናችን መንገዱን ለቆ በሜዳው ወደ ተደረደሩት መኪናዎች ወሰደን፡፡ እንወርድ ዘንድም ተፈቀደልን፡፡

በየመኪናዎቹ የሚወርዱ ነጫጭ እርግቦች የሚመስሉ ምዕምናን ፊታቸውን ወደ ምሥራቅ አዙረው መንገዱን እያቋረጡ ከፍ ብሎ ወደ ተሠራው፣ ግርማው በአሻገር ወደ ሚያሥፈራው ደብር ተጓዙ፡፡ እኔም ተከትዬ አዘገምኩ፡፡ የገዳሙ ግርማ አስቀድሞ ያስፈራል፣ ልብን ያርዳል፣ ጥቅጥቅ ደኑ ዙሪያውን በካብ ታጥሯል፡፡ ምዕመናን በስተ ምዕራብ በኩል ባለው በር እያለፉ ወደ ውስጥ ይዘልቃሉ፡፡ ከመንገዷ በቀኝና በግራ የቆሙት እፅዕዋት እንግዳ ለመቀበል የቆሙ አገልጋዮች ይመስላሉ፡፡ ልዩ ልዩ እፅዕዋት በእርጋታ ቆመዋል፡፡ አዕዋፋት ይዘምራሉ፡፡ የእሸ ዛፎች መልካም ፍሬ ሰጥተዋል፡፡ በቀጭኗ መንገድ ወደ ውስጥ ሲዘልቁ መንፈስ የሚያድስ ማዕዛ ይመጣል፡፡ ማዕዛውን እያጣጣሙ ወደ ውስጥ ሲጠጉ በካብ የታጠሩ በአንድ ቅጽር ሁለት ደብር ያያሉ፡፡ አንደኛው የቀደመውን አንደኛው ደግሞ የአሁኑን ጥበብ የሚያሳዩ አብያተክርስቲያናት፡፡

ስትጠበቅ የነበረችው ፀሐይ ወጥታ መታዬት ጀምራለች፡፡ ገዳመ ወንጨጥ ቅዱስ ሚካኤል ወደብረ ሰላም መድኃኔዓለም ገዳም ውስጥ ነኝ፡፡ ገዳሙ በደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት በደራ ወረዳ ቤተክህነት ሥር ይገኛል፡፡ ዓይኔ የሚያዬውን፣ ጀሮዬ የሚሰማውን፣ እጄ የሚዳስሰውን፣ እግሬ የሚረግጠውን፣ አፍንጫዬ የሚያሸተውን ያደንቅ ጀመር፡፡

ኢትዮጵያ የምድር መሰሶ ናት። ምድራዊት ዓለም ከእርሷ ውጭ አትቆምም፡፡ ፈጣሪዋን ያልረሳች፣ መልካም ሥራን ያልዘነጋች፣ ትሕትናን ያልተወች፣ ስለ ሠው መኖርን የጠበቀች ሀገር ናት፡፡ ታዲያ ምድራዊውን ያቆማቸውን መሰሶ ሊጥሉ ይገፉታል። ዳሩ ትጠነክራለች እንጂ ሊጥሏት አይቻላቸውም፡፡

ፈጣሪ ሰማይና ምድርን ፈጠረ። ሰማይን በጥበቡ አስዋባት፣ የዙፋኑ መቀመጫ ትሆን ዘንድም መረጣት። የሰማይ ካስማ የለውም፣ ምድርም መሠረት የላትም፤ እርጉ ተብለው ረጉ እንጂ። ምድርንም በልዩ ልዩ ጌጥ አስጌጣት፣ የእግሩ መረገጫም አደረጋት። ለምድር የተለዬች ጌጥ ትሆን ዘንድም ኢትዮጵያን መረጣት። ሥሙ እንዲወደስባት፣ ጥበብ እንዲፈስባት፣ ፍቅር እንዲሰፋባት፣ ለምድር ተስፋ የሚታይባት ትሆን ዘንድ አስዋባት፣ አነፃት፣ ጠበቃት።

ዝምታው ያስፈራል። ያልተነካካው የዛፍ ጥላ ግርማ ሞገስ ሆኗል። በስርዓት ከቆመው ዛፍ በቀስታ የሚወድቀው ቅጠልና ፍሬ በምድር ላይ ወድቆ ከቆዬው ጋር ተጋጭቶ ሲገናኝ ልዩ ድምፅ ይሰጣል።

ወደ አውደ ምኅረቱ የተጠጋ ሁሉ አምላኩን ይማፀናል። ‹‹አምላኬ ልመናዬን ስማ፣ ይቅርም በለኝ፣ ሀገራችን ኢትዮጵያን ባርክ›› እያለ የሚማፀን ድምፅ በለሁሳሳው ይሰማል። በግርማ ከቆመው ደብር ውስጥ ሿ..ሿ የሚለው የፅህና ድምፅና ከፅህናው የሚወጣው መልካም ማዕዛ ነብስን ያረጋጋል። ዲያቆኑ የሚያቃጭለው የቃጭል ድምፅም በተደጋጋሚ ይሰማል። አዕዋፋት ይዘምራሉ፣ ለፀሎት የሚፋጠነው ሰው አጀብ ያሰኛል። ቅጠል የለበሱ የማሕብርና የቀብር ቤቶች በዙሪያው ይታያሉ፡፡ በጥሻው ውስጥ ቀጫጭን መንገዶች ይታያሉ፡፡ ዙሪያ ገባው ያስደምማል፡፡

ገዳመ ወንጨጥ ቅዱስ ሚካኤል ወደብረ ሰላም መድኃኔዓለም ገዳም በብሉይ ኪዳን ጀምሮ የነበረ ታላቅ ገዳም ነው፡፡ በፀጋ የሚመሩ ካህናት ቤተመቅደስ ሊያንፁ ወደ ሥፍራው አቀኑ፡፡ አካባቢው በዱር የተመላ ነበር፡፡ ፈጣሪ የፈቀደው ሥፍራ ላይ እየስኪደርሱ ድረስ እየመነጠሩ ይሄዱ ነበር፡፡ በመካከል የወይን እንጨት አገኙ፡፡ ከዚያም “ኧረ የወይን እንጨት!” አሉ፤ ስያሜው ከዚያ ተገኘ፡፡ የወን እንጨት፡፡ እየቆዬ ሲሄድ ወንጨጥ መባሉን የደራ ወረዳ ሥራ አስኪያጅና የገዳሙ አስተዳደሪ መጋቤ ስርዓት ቆሞስ አባ ገብረ ማርያም አለነ ነግረውኛል፡፡ ፈጣሪ የፈቀደው ቦታ ተገኘ፡፡ ቤተመቅደስም ታነፀ፡፡ ይሄን ቤተመቅደስም ቡልሌ የተባሉ ጻድቅ ሰው እንደተከሉት አስተዳደሪው ነግረውኛል፡፡

በ332 ዓ.ዓ ታነፀ፡፡ መስዋዕተ ኦሪት ተሰውቶበታል፡፡ ይህ ዕፁብ ድንቅ የሆነ ቤተመቅደስ በዚያ ዘመን እንደተሠራ አልታደሰም፡፡ የጣሪያው አሠራር ጉድ ያሰኛል፡፡ ክዳኑ ቆርቆሮ ለብሷል፡፡ ቅኔ ማሕሌት፣ ቅድስትና መቅደሱ ውብ ነው፡፡ ጣሪያው ቆርቆሮ ቢለብሥም መቅደሱን ግን የነካካው የለም፡፡

በቀደመው ዘመን ጥበብ ያለው የቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ነው፡፡ ወደ ውስጥ ዘለኩ፡፡ በሰማሁት ነገር አብዝቼ ተገረምኩ፡፡ ገዳሙ የሚጠበቀው በነብር ነው፡፡ ከተመሠረተበት ዘመን ጀምሮ አናብርት ቤተመቅደሱን ይጠብቁ ዘንድ ስልጣን ተሰጣቸው፡፡ ማደሪያቸውም ከቤተመቅደሡ ዓናት ላይ በተሠራው ሰገነት ነው፡፡ ዲያቆናቱ መኖሪያቸውን በእጃቸው እየጠቆሙ አሳዩኝ፡፡ ሠው ሳይበዛ ሲቀር ከማደሪያቸው ወርደው ምግባቸውን ይመገባሉ፡፡ የውኃ መጠጫ ገንዳ በቅድስቱ ተዘጋጅቶላቸዋል፡፡ እርሱንም አየሁ፡፡ አናብርቱ በገዳሙ ላይ ያልተገባ ነገር ሊያደርግ የሄደን ይቀጣሉ፡፡

ሳይነፁ ወደ ቤተመቅደስ የሚገቡትንም ይከለክላሉ፡፡ ቤተመቅደሱን ሊያረክስ የወደደውን ሁሉ አያስገቡም፡፡ በገዳሙ እንደደረሰኩ በነበር እንደሚጠበቅ ቢነገረኝም በቤተመቅደስ ውስጥ እንደሚኖሩ ግን አላወኩም ነበር፡፡ አስቀድሜ ባውቅ ኖሮ ወደ ውስጥ ለመግባት ባልደፈርኩ ነበር፡፡ የሐጥያቴን ብዛት ሳስብ ፍርሃት ተጫነኝ፡፡

አቤቱ ጌታ ሆይ ነብሴን አስባት፣ እንደ በደሌ ሳይሆን እንደቸርነትህ ጠብቃት፣ እነሆ አልተዘጋጄችምና ለነብር ጎረሮ አሳልፈህ አትስጣት፣ ይልቁን ፈጣሪዋ አንተን እየፈራች ትዘጋጅ ዘንድ የንስሐ ጊዜ ስጣት፣ በስጋ ኃይል ተሸንፋለችና አትቅጣት አልኩ። ልቤ ራደች፣ መንፈሴ ተጨነቀች፣ እግሬ ተንቀጠቀጠች። ‹‹የመዳንህን ደስታ ስጠኝ በእሽታ መንፈስም ደግፈኝ›› የሚለውን አሰብኩ። አናብርቱ ከሚቀጡት ሰው አንደኛው እንደምሆን ልቤ ይወተውተኛል፡፡ በቅድሥቱ ዙሪያ ስዞር ከቤተመቅደሱ አናት ላይ ያሉት አናብርት መቸ ወርደው ይይዙኝ ይሀን እያልኩ እጨነቅ ነበር፡፡

ቅዱሱን ሥፍራ ይጠብቁ ዘንድ አገልጋዮች ሆነው ተመርጠዋል እና ይቀጣሉ። በሌላው ዓለም በብረት አጥር ውስጥ የሚኖሩ አናብርት ሊኖሩ ይችላሉ። በኢትዮጵያ ግን እንደ ሰው ሁሉ ገዳማዊ የሆኑ የገዳም ጠባቂዎች አናብርት ይገኛሉ። እፁብ ነው፡፡ አናብርቱ አገልግሎት ሲደምቅ በሰገነቱ ወጥተው፣ ከመኝታቸው ተነስተው የሚሆነውን ሁሉ እንደሚያዩ መጋቤ ስርዓት ቆሞስ አባ ገብረማርያም ነግረውኛል፡፡ በቸርነቱ አተረፈኝ፤ ከአናብርት ጉረሮ ዳንኩ፡፡

‹‹እንደ አባቶች ቤተ መቅደሱ ውስጥ ፀበል አለ፡፡ በአራቱ ማዕዘን ሕዝቡ የሚገለገልበት ፀበል አለው። በእነዚህ ነው ሕዘቡ እየተፈወሰ ያለው›› ነው ያሉኝ መጋቤ ስርዓት ቆሞስ አባ ገብረማርያም፡፡ የቤተመቅደሱ ፀበል እንዳለ ይነገር እንጂ ፈቃደ እግዚአብሔር ስላልደረሰ ያወጣው የለም፡፡ ‹‹አባቶች ብዙ ቅዱሳን አሉ ነው የሚሉን፣ እኛም በዓይናችን ያዬናቸው አሉ፣ ሌሊት ስንመጣ ብዙ ቅዱሳን ይታያሉ›› ነው ያሉት፡፡ የሚታዩት ካህናት ለአገልግሎት ወደ ቤተክርስቲያን በሌሊት ሲሄዱ የማይታዩት አባቶች በቤተመቅደስ እያመሰገኑ እንደሚሰሙም ሰምቻለሁ፡፡

ገዳሙን ከመነኮሳት ውጭ ህጋዊ ካህናት አያስተዳድሩትም፡፡ ያለ ፈቃድ የገዳሙን ቅጠል እንኳን የሚቆርጥ አይችልም፡፡ ጠባቂው ረቂቅ ነውና፤ እስከዛሬም ጉዳት አልደረሰበትም ይባላል፡፡

የመድኃኔዓለም ቤተክርስቲያንን በዚህ ዘመን ሥራ የተሠራ ነው፡፡ ስለዚህ ቤተክርስቲያን አሠራር አበው ሲናገሩ ‹‹ጥንታዊውን የቅዱስ ሚካኤልን ቤተክርስቲያን ልናድስ ነበር መሳሪያውን ያመጣነው፡፡ ልናፈርስ ወደ ጣሪያው ስንወጣ እሳት እየነደደ አልሆን አለን፡፡ ስድስት ቆርቆሮወችን እንደነቀልን ማውረድ አልተቻለንም፡፡ መወጣጫ መሠላሉ ከሁለት ይቆመጣል፡፡ የሚያፈርሰው ሰው ይወድቃል፡፡ ፈቃደ እግዚአብሔር አልደረሰም ተባለ፡፡ የተነቀሉት ቆርቆሮዎች ዳግም ተገጠሙ፡፡ ለማደሻ በመጣው ቁሳቁስ ሌላ ቤተክርስቲያን ተገነባ፡፡ ከቅዱስ ሚካኤል ጋር የነበረው ታቦተ መድኃኔዓለም ገባበት›› ነው ያሉኝ፡፡

‹‹ቦታው በእኛ አቅም የሚነገር አይደለም፡፡ እንዲሁ በድፍረት ነገርኩህ እንጂ፤ ሕዝቡ ይወቀው ብለን እንጂ በእኔ አንደበት የሚነገር አይደለም፡፡ ወደፊት እራሱ ሲፈቅድ ያወጠዋል ብዬ አምናለሁ›› ነው ያሉኝ መጋቤ ስርዓት ቆሞስ አባ ገብረማርያም፡፡

ባሕር ላይ ቁጭ ብላ ከሰማይ ዝናብ እንደምትጠብቅ ወፍ አትሁኑ እንዳለ ኢትዮጵያ ባሕር ናት፤ ጥልቅ ባሕር፤ ታዲያ ልጆቿም ከባሕሩ ይጠጡ እንጂ ከሌላ የሚመጣን ብቻ አይመልከቱ፡፡ ዘላለም እንደሚኖር ሰው ሥራ ዛሬ እንደሚሞት ሰው ተዘጋጅ። ደስታህን በፈጣሪህ ላይ አድርግ። የተጠሩ ብዙኃን ናቸው። የተመረጡት ግን ጥቂቶች ናቸው፡፡ የተመረጡት በዚያ ገዳም በቅድስና ይኖራሉ፡፡ በባዶ እግራቸው የነበሩት ዘመንን ተጉዘው ጨረሱ። በጫማ የተጓዙት መጓዝ አቃታቸው። ኢትዮጵያ ልዩ ናት፡፡

‹‹አዲስ ልብ እሰጣችዘኋለሁ አዲስም መንፈስ በውስጣችሁ አኖራለሁ። የድንጋዮችንም ልብ ከሥጋችሁ አወጣለሁ። የሥጋንም ልብ እሰጣችኋለሁ። መንፈሴንም በውስጣችሁ አኖራለሁ ፍርዴንም ትጠብቃላችሁ። ታደርጉትማላችሁ›› እንዳለ ህጉን የሚጠብቁ በዚያ ይኖራሉ፡፡ መኖር ያልቻሉት ደገሞ ሥፍራውን እየሄዱ ያያሉ፡፡ በቅዱ በመንፈሱ ይረካሉ፡፡ ፍርዱን የጠበቁት ለአገልግሎት ይፋጠናሉ። ተግተው ይፀልያሉ። አብዝተው ይማፀናሉ። ‹‹ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳልና፤ ራሱንም የሚያዋርድ ሁሉ ከፍ ይላል›› እንዳለ በገዳሙ ያሉ መነኮሳት ራሳቸውን አዋርደው ከፍ ማለትን መርጠዋል። አይኮሩም፣ ስለ ሁሉም ነገር ፈጣሪያቸው ይቅደም ይላሉ። ሊቃውንት ትሕትናን ተከተሏት ገንዘብም አድርጋት ይላሉ። እነርሱም ትሕትናን እየተከተሏት ነው፡፡

በገዳሙ ውስጥ ጥንታዊ መስቀሎች፣ የአንበሳ ለምድ፣ በጥቂት ሰው መንቀሳቀስ የማይችል ኢየሱስ ክርስቶስ በቀራንዮ የተሰቀለበትን መስቀል የሚመስል ትልቅ መስቀል፣ ጥንታዊ የብራና መፃሕፍት እና አያሌ እፁብ የሆኑ ቅርሶች ይገኙበታል፡፡ ዲበ መስቀሉ በዓመት እንድ ጊዜ ብቻ ነው የሚወጣው፡፡ አባቶች ገዳሙ እንዲታይ ሰውም እንዲበዛት ስለማይፈልጉ ታላቁ ሥፍራ ሳይታይ መኖሩን ሰምቻለሁ፡፡ አሁን ግን በፈጣሪ ፈቃድ በሩን ለመክፈት እየተሠራ ነው፤ ታላቅ ቦታ ያዩ ዘንድ የወደዱ ሁሉ መምጣት ይችላሉ ነው ብለዋል አባቶች፡፡

በማይገባኝ ሥፍራ አያሌ ነገሮችን ተመለከትኩ፤ አብዝቼም አደነኩ፡፡ በተቀደሰችው ምድር ተወልጄ እኖር ዘንድ የፈቀደልኝን ፈጣሪዬን አመሰገንኩ፡፡ ቤተመቅደሱን በአናብርት የሚያስጠብቅ አምላክ ቅዲስቲቷን ሀገር በመላዕክት እንደሚያስጠብቃት አሰብኩ፡፡ እግሬ ከገዳሙ ወጥቶ ወደ ሜዳው ወጣ፣ ልቤ በዚያው መሰንበትን መረጠ፡፡ መንገዱን እንደተሻገሩ በገዳሙ የሚገነባ አዲ የቅዱስ ጊዮርጊስ ሕንፃ ቤተክርስቲያን አለ፡፡ በሜዳው በተዘጋጄው ጉባኤ ለምታደም አዘገምኩ፡፡ በዚያውም ተቀመጥኩ፡፡ የአዕዋፋት ዝማሬ፣ የገዳሙ ግርማ፣ የካህናት ጥዑመ ዜማ በእዝነ ልቦናዬ አልለይህ አሉኝ፡፡ ኢትዮጵያን እናውቅ ዘንድ ይርዳን፡፡

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

Source link

Related posts

አብይ፣ ለማና የጃዋር ካልኩሌተር (አበበ ገላው)

admin

ትግራይ እንዴት ሰነበተች? – (ክፍል 1)

admin

የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት በመተከልና ትግራይ ክልል ለሚገኙ ዜጎች ድጋፍ አደረጉ

admin