71.98 F
Washington DC
May 17, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

“እነሆ ሁሉም ነገር ተፈጸመ” | አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን

“እነሆ ሁሉም ነገር ተፈጸመ”

ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 22/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የብሉይ ኪዳን ማብቂያ፣ የአዲስ ኪዳን መባቻ መካከለኛ ቀን ናት፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የተለየች ቀን ተብላለች፡፡ የማይታመም የታመመባት፤ የወደቁትን ከትቢያ የሚያነሳ የተንገላታባት፤ በአልጋ ቁራኛ በደዌ ዳኛ የተያዙትን የሚፈውስ፤ ከባርነት ነፃ የሚያወጣ የተገረፈባት፣ ዲያቢሎስ ከነወጥመዱ ድል የተነሳባት ምስጢራዊ ዕለት ነች – ዕለተ ዓርብ የስቅለት ቀን፡፡

በሰው ልጆች የሕይወት ለውጥ ላይ መሠረታዊ የሚባሉ የውድቀትና የትንሣኤ ታሪክ የተጻፈባቸው ሁለት ቀናት ናቸው፡፡ አንዷ አዳም ዕጸበለስ በልቶ የተሳሳተባት የውድቀት መነሻ ቀን ናት፡፡ ሁለተኛዋ ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስ አዳምን ለማዳን የተሰቀለባት ቀን ናት፡፡

በሁለቱም ቀናት የታዩ ገቢረ ተዓምራት በተመሳሳይ ሰዓት የሆኑ ናቸው፡፡ ስቅለት የሰው ልጆች የዕዳ ደብዳቤ በኢየሱስ ክርስቶስ መስዋእት ለመጨረሻ ጊዜ የተደመሰሰበት፤ የሰው ልጅ ከዲያብሎስ አገዛዝ ነጻ የወጣበት ነው፡፡ ለዚህም “የድኅነት ቀን” ወይም “መልካም ዓርብ” ይባላል፡፡ የኢየሱስ ክርስቶስ ስቅለት ሐጢያት የጠፋበት፣ ቤተክርስቲያን በክርስቶስ ደም ተዋጅታ ነጻ የወጣችበት፣ የሰው ልጆችም የደም ዋጋ ተከፍሎላቸው ነጻነት ያገኙበት ነው፡፡

“ከምድር ከፍከፍ ባልኩ ጊዜ ሰውን ሁሉ ወደኔ እስባለሁ” ባለው መሠረት (ዮሐ ምዕራፍ 10) የሰውን ልጅ ከፍ አድርጎ ያሳረገባት ወደ ልዕልና ሕይወት የመለሰባት ዕለት መሆኗ በሃይማኖቱ ተከታዮች ይታመናል፡፡

በባሕር ዳር ሀገረ ስብከት የአራቱ ጉባዔያት መምህርና የሊቃውንት ጉባኤ ሰብሳቢ ሊቀ ሊቃውንት ስምዓኮነ መላክ “ኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ላይ በወጣ ጊዜ የቅዱሳን ነፍስ ሁሉ አብረውት መስቀል ላይ ወጥተዋል” በማለት ቤተክርስቲያን ዛሬም መኖሪያዋ በመስቀል ላይ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ኢየሱስ የጸሎተ ሐሙስ ማታ ለደቀ መዛሙርቱ የመጨረሻውን እራት መግቦ ካስተማረ እና ምሥጢረ ቁርባንን ከመሠረተ በኋላ ሌሊቱን በአይሁድ ጭፍሮችና በሊቃነ ካህናት ሎሌዎች ተይዞ ስቃይና እንግልት ደርሶበታል፡፡

በመጀመሪያ ወደ ሐና ዘንድ ከዚያም ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ቀያፋ፣ ቀጥሎም ወደ ጲላጦስ፤ ከጲላጦስ ደግሞ ወደ ሔሮድስ ከዚያም እንደገና ወደ ጲላጦስ እያመላለሱ እንዲንገላታና እንዲሰቃይ ተደርጓል፤ ፌዝ፣ ዛቻ እና ድብደባም ደርሶበታል፡፡ ሊቀ ሊቃውንት ስምዓኮነ መላክ እንዳሉት በዕለተ ዓርብም ቅድስት ነፍሱን ከቅዱስ ሥጋው በራሱ ፈቃድ እስከለየባት ዘጠኝ ሰዓት ድረስ ብዙ መከራዎች ተቀብሏል፣ በጅራፍ ተገርፏል፤ መስቀሉን ተሸክሞ እንዲወድቅ እንዲነሳ ተደርጓል፣ ምራቃቸውንም እየተፉበት ወደ ቀራንዮ ተራራ ወጥቷል፣ እጆቹን እና እግሮቹን በችንካሮች መትተው በመስቀል ላይ ሰቅለውታል፤ በጦር ወግተውታል፤ የእሾህ አክሊል በራሱ ላይ በማጥለቅም ተሳልቀውበታል፡፡ እሱ ግን በመስቀል ላይ ሳለ “የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” ብሎ ተናገረ፡፡

በመጨረሻም “እነሆ ሁሉም ነገር ተፈጸመ” በማለት ቅድስት ነፍሱን ከቅዱስ ሥጋው በራሱ ፈቃድ ለይቶ ለሰው ልጆች ሕይወት ሲል ራሱን ለሞት አሳልፎ ሰጠ፡፡ በዕለቱ ብዙ ተዓምራት ታይተዋል፡፡ ፀሐይ ጨለመች፤ ጨረቃ ደም ሆነች፤ ከዋክብት ረገፉ፡፡ በምድርም የቤተ መቅደስ መጋረጃ ለሁለት ተቀደደ፣ ምድር ተናወጠች፣ መቃብሮች ተከፈቱ፣ ብዙ ዘመን ያሳለፉ ሙታንም ተነሱ፡፡ በሰማያትም በሲኦልም ሲሰቃዩ ለነበሩ ነፍሳት ነጻነት ተሰበከ፡፡ መቃብር ስልጣኑን ለቅቋል፣ ሞትም ኀይሉን ተነጥቋል፡፡ የሰው ልጆችም ከባርነት ወጥተው በነጻነት ኖረዋል፡፡

የስቅለት ዓርብ ጌታ ስለ ሰው ልጆች ፍቅር ሲል በቀራኒዮ አደባባይ ራሱን አሳልፎ በመስጠት የቤዛነቱን ሥራ ፈጸመ፡፡ ምዕመኑም “አቤቱ በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበን” እያሉ ዕለቱን ኢየሱስ ክርስቶስ የተቀበለውን መከራ እያሰቡ፣ ስለ ኃጢያታቸው እያዘኑ፣ ስለ ማዳኑም እያመሰገኑ በስግደት ያሳልፋሉ፡፡ የጾማቸውን ፍጻሜ በቅዱስ ሥጋው በክቡር ደሙ ማኅተም ይዘጋሉ፡፡ ሐጢያት የሌለበት ጌታ ስለሁሉ ሐጢያት ሲል ተላልፎ የሞተባት ዕለት ለሰው ልጅ የሚሰጠው መንፈሳዊ አስተምሕሮ ከፍ ያለ መኾኑን ሊቀ ሊቃውንት ስምዓኮነ ተናግረዋል፡፡

ደብድበው የሰቀሉት በፍርድ አደባባይ መቆም የማይችሉ ሐጢያተኞች ቢሆኑም፤ ክርስቶስ ግን ገርፈው የሰቀሉትን ይቅር ብሏል፤ ያልበደሉትን ብቻ ሳይሆን በደለኞችን መታገስ እንደሚገባ አስተምሯል፡፡ የሰው ልጅ የራሱ በደል ይኖርበታልና መታገስን፣ ጠላትን እስከመውደድ ድረስ ፍቅርን መለማመድ እንዳለበት ያሳያል ብለዋል፡፡

ኢየሱስ ክርስቶስ ስለበደለኞች ድኅነት የመሰቀሉ ምክንያት የሰው ልጆች በይቅርታ ማለፍን፣ ከመግደል ይልቅ አንዱ ስለ አንዱ ተላልፎ መሞትን፣ እየሞቱም ቢሆን ማስተማር እደሚገባ ለማሳየት ነው ብለዋል፡፡ ሁሉን ማድረግ እየተቻለው ማስተማርን መርጧልና፤ የሰው ልጅ ማድረግ ስለቻለ ብቻ ጥፋትን ሁሉ ማድረግ እንደሌለበት ሊማር እንደሚገባ መክረዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

Source link

Related posts

ጁንታው በዋሻ ውስጥ ሆኖ የትግራይን ህዝብ ለማደናገር የሚያደርገው ጥረት አይሳካም- መከላከያ ሰራዊት

admin

ዓለም ባንክ ኢትዮጵያ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ዘርፎች የጀመረቻቸውን ሥራዎች መደገፉን እንደሚቀጥል ገለጸ፡፡

admin

ለፍትሕ ስርዓቱ ግልጽነት የሚፈጥሩና የሕግ የበላይነትን የሚያረጋግጡ ሕጎችና አዋጆች ማሻሻያ እየተደረገባቸው ነው-ጠቅላይ አቃቤ ሕግ

admin