79.57 F
Washington DC
June 13, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

እቴጌ ጣይቱ ብርሃን ዘ-ኢትዮጵያ | የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት

እቴጌ ጣይቱ ብርሃን ዘ-ኢትዮጵያ

ባሕር ዳር ፡ የካቲት 17/2013 ዓ.ም (አብመድ) ኢትዮጵያውያን ለዘመናት የማይነጥፍ ታሪካቸውን በደም ቀለማቸው የጻፉበት ነው፡፡ ‘እጄን ሳልንተራስ የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ክብር አሳልፌ አልሰጥም’ በሚል ቆራጥ ወኔም ተዋድቀውበታል፡፡ አጥንታቸውን ከስክሰው ደማቸውን አፍሰው የኢትዮጵያን ወሰን አስከብረው የዓለምን ታሪክም ቀይረውበታል፡፡ ኢትዮጵያውያን ማንነታቸውን እንዲያስተጋቡ ከማድረግ አልፎ በቅኝ ግዛት ቀንበር ውስጥ ወድቀው ለነበሩና ለመላው ጭቁን የዓለም ጥቁር ሕዝቦች ሁሉ የተስፋ ብርሃን የፈነጠቀ ነው— የዓድዋ ድል።

የዓድዋ ጦርነት ኢትዮጵያውያን ጾታ፣ ብሔር እና ሃይማኖት ሳይለያቸው በአንድነት ለነጻነታቸው የተዋደቁበት አውደ ውጊያ ነው፡፡ በዚህ ወቅት የጦር መሪ፣ የሎጅስቲክስ እና የሕክምና ዘርፉን ሲያስተባብሩ የነበሩትን ጀግና ኢትዮጵያዊት ልንዘክር ወደድን።

በኢትዮጵያ ታሪክ የጎላ ሥፍራ ካላቸው ኢትዮጵያውያን ሴቶች መካከል እቴጌ ጣይቱ በግምባር ቀደምትነት የሚጠሩ ናቸው፡፡ ብርሃን ዘ-ኢትዮጵያ ዳግማዊ አጤ ምኒልክን ካገቡ በኋላ በዘመናዊት ኢትዮጵያ የፖለቲካ፣ የአስተዳደር እና ሥልጣኔ አውዶች ያበረከቱት አስተዋጽዖ ከፍተኛ እንደሆነ ታሪክ ይዘክራል፡፡

በዓድዋ ጦርነት ኢትዮጵያ በበላይነት እንድታጠናቅቅ የነበራቸው ብልሃት የተሞላው የመሪነት ሥልት እና ወኔ ከታሪካቸው ሁሉ የላቀውን ሥፍራ ይይዛል፡፡

የእቴጌ ጣይቱ ሀገርን ከወራሪ የማዳን ጥበብና የአልደፈር ባይነት ኢትዮጵያዊ ስሜት ድንቅ ነው፡፡ ገና በውጫሌ ስምምነት የአንቀጽ 17 ጣልያንኛ ትርጉም ጣልያን ኢትዮጵያን በሞግዚትነት የማስተዳደር ፍላጎት እንዳላት በታወቀ ጊዜ ቁጣቸውን ቀድመው ያሰሙት ብርሃን ዘ-ኢትዮጵያ ናቸው፡፡

በትርጓሜው ሳቢያ በተነሣው አለመግባባትና የዲፕሎማሲ ውዝግብ እቴጌ ጣይቱ ከፍ ያለ ተሳትፎ እንደነበራቸው የታሪክ አዋቂዎች ከትበዋል፡፡ የትርጉም ስሕተቱ እንደነበር ባወቁ ጊዜ በቤተ መንግሥቱ አዳራሽ ግብር እየተመገቡ ለነበሩ መኳንንትና መሳፍንት “እንግዲህ በቃ! በአንድነት ሆነን ከጣልያን ጋር ጦርነት እንገጥማለን፤ እንፋለማለን እንጂ የጣልያን አሽከር አንሆንም” በማለት በቁጣ ጮኸው ተናግረዋል፡፡

በዚያ አቋማቸውም የውጫሌው ስምምነት ሙሉ በሙሉ እንዲሰረዝ እስከማድረግ ደርሰዋል፡፡

እቴጌ ጣይቱ፣ እነ ራስ መኮንን፣ ራስ መንገሻ ዮሐንስን፣ ራስ አሉላን፣ ራስ አባተን እና ፊታውራሪ ገበየሁን ከመሳሰሉ የጦር አዛዦች ጋር ተሠልፈው የዓድዋ ጦርነትን መርተዋል፡፡ በተሳተፉበት አውደ ውጊያም 3 ሺህ ወታደሮችን አሰልፈው በመምራትም ትልቅ ተጋድሎ ፈጽመዋል፡፡

ብርሃን ዘ-ኢትዮጵያ ወደ ዓድዋ ተራራ የዘመቱት ተዋጊ ሠራዊት ብቻ ይዘው አልነበረም፤ አዋጊ እና ወኔ ቀስቃሽ አዝማሪዎችን ጭምር አሰልፈው እንጂ፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የያሬድ ሙዚቃ ትምሕርት ቤት መምህሩ ሰርጸ ፍሬ ስብሐት ‹ደቦ› በተሰኘ መጽሐፍ ላይ እንደከተቡት እቴጌ ጣይቱ በገና ወዳድ ናቸው፡፡ በጦርነቱ ጊዜም ለሠራዊቱ የወኔ ትጥቅ እንዲያቀብሉ በርካታ አዝማርያን እና በገና ደርዳሪዎችን አስከትለዋል፡፡ አዝማሪዎቹም የዘመቻ ዘፈኖችን ፉከራዎችንና ሽለላዎችን ያሰሙ እንደነበር በታሪክ ተመዝግቧል፡፡

ከጦርነቱ ቀደም ብሎ ለዘማች ለሠራዊቱ በቂ ስንቅ ተሰናድቶ እንዲቀርብ የማስተባበር ኀላፊነት ነበረባቸው፡፡ ስንቅ ለማዘጋጀት የሚያገለግል ቁሳቁስ ተዘጋጅቶ ወረ ኢሉ እንዲከማች፣ ከዚያም ወደ ዓድዋ እንዲደርስ የማድረግ ሚናቸውን በአግባቡ ተወጥተዋል፡፡ በጦርነቱ ላይ ስንቅ ባነሰ ጊዜም የስሜን ወገኖቻቸውን በመጠየቅ እንዲቀርብ ማድረጋቸውን ታሪክ ይመሰክራል፡፡

በኢትዮ ጣልያን ጦርነት በተለይ መቀሌ የነበረው ከበባ በጣም አስቸጋሪና ከሌሎች አውደ ውጊያዎች ሁሉ ረዘም ያለ ጊዜ የወሰደ ነበር፡፡ እንዳየሱስ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ መሽጎ የኢትዮጵያን ጦር አላስጠጋ ያለው የጣሊያን ጦርን እቴጌ ጣይቱ በበሳል የውጊያ ስልት ድል ነስተዋል፡፡

በራሳቸው ከሚመራው ሠራዊት ውስጥ ተዋጊዎችን በመላክ የጣሊያን ወታደሮች የሚጠቀሙበትን የምንጭ ውኃ ተቆጣጥረዋል፡፡ ይህ ብልሀት የተሞላው ወታደራዊ እርምጃ የጣሊያን ወታደሮችን ለከፍተኛ የውኃ ችግር ዳርጓል፤ በመጨረሻም ምሽጋቸውን እንዲለቅቁ አስገድዷቸዋል፡፡

እቴጌ ጣይቱ የሚመሩት ሠራዊት በወሳኙ ጦርነት ተሰልፎ ከመዋጋቱ ባሻገር ለተዋጊዎች ውኃ በማቅረብ፣ ቁስለኛ በማንሣትና በማከም ሥራ ተሠማርተው ነበር፡፡ በድሕረ አድዋም ከፍተኛ ፖለቲካዊ ተሳትፎ ነበራቸው፡፡

ለሀገር ክብር ከከፈሉት ተጋድሎ ባለፈም በኢትዮጵያ ታሪክ እቴጌይቱ የላቀ አስተዳደራዊና ፖለቲካዊ ድርሻ ነበራቸው፡፡ ከባለቤታቸው ከአጤ ምኒልክ ጋር በመሆን ስልጣኔ ወደ ኢትዮጵያ እንዲገባ አድርገዋል።

በዘገባ ዋቢነት ብሩክ መትረየስን “እቴጌ ጣይቱ ብርሃን ዘ-ኢትዮጵያ”፣ “ደቦ” የተሰኘውን መጽሐፍ እንዲሁም አለማየሁ አበበ “የኢትዮጵያ ታሪክ” በሚል የተረጎሙትን መጽሐፍት ተጠቅመናል፡፡

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

Source link

Related posts

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የምርት መቀበያ መጋዘን ግንባታ በቴፒ ገንብቶ ማጠናቀቁን ገለጸ

admin

በአጣዬና አካባቢው በተፈፀመው ወንጀል ተጠያቂ የሚሆኑ አካላትን ለፍርድ እንደሚያቀርብ ኮማንድ ፖስቱ አስታወቀ፡፡

admin

ጎርጎራ እንደገና ስታበራ። | የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት

admin