70.74 F
Washington DC
May 15, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

እስከመቼ ሻማ እናብራ? – ጌታቸው ለገሰ | Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider

31.03.2021
ጌታቸው ለገሰ

ላይነሱ ተቀብረው፣ ላይመለሱ ተሰናብተው ፣በቀረቻቸው ትንሽ ምላስ ኢትዮጵያዊነትን ክደው ዛሬ በ “ዳውን ዳውን” ታጅበው ያዙኝ ልቀቁኝ የሚሉትን የሙት መንፈሶች እንደ ትላንቱ የጥፋቶች ሁሉ ማላከኪያ ማድረጉንና በስማቸው መደበቁን ትተን አሁን ላለው ችግር ትክክለኛውን ተጠያቂ  “ና ተጠየቅ!’’ ማለቱ ያስፈልጋል። በሃገራችን ታሪክ ያልሰማነው፣ ያላየነውና በአንድ ዘር ላይ ያነጣጠረ “አማራን ካዳከምን ኢትዮጵያን በምንፈልጋት መልክና ቅርጽ እንሰራታለን” የሚለውን በግልጽም እየነገሩን በስውርም እየተገበሩት ያለው ኢትዮጵያን የማጥፋት ስራቸውን ማስቆም ግድ የግድም ግድይለናል።    ሃገር መበተንን ስራዬ ብለው የተያያዙት የውስጥ እኩይ አካላት  እና የውጭ ሃይላት በያዙትና እየፈጸሙት ባሉት አላማዎች፣ ህመማችን ከቀን ወደቀን እየተባባሰ መጥቷል።

 • ህዝብን እንደሃገር ማስለቀስ፣
 • ለጄኖሳይድ መለኪያ ሙሉ የሆነውን፣በአሰቃቂና በሚያሸማቅቅ መልኩ የዘር ማጥፋት፣ ይህንንም እውነታ አለመቀበል፣
 • የመጣውን ለውጥ በመደገፍ፤ ኢትዮጵያን እናድን፣ እንገንባ … ብሎ የተነሳውን ህዝብ ተስፋ ማስቆረጥ፣ ብሎም ለራሱ ህልውና ተነስቶ ለእነሱ እኩይ ተግባር ማስፈጸሚያ እንዲሆን ማሰለፍ፣
 • የለውጥ ሃይሉን በጥርጣሬ ብቻ ሳይሆን አጥፊው እሱ ነው በማለት የቁልቁለት ዘመቻውን እንድንቀላቀል መግፋት፣
 • በየቦታው በሚለኩሱት እሳት ተለብልበን ሃይላችንን በታትነው ህልማቸውን እውን ሊያደርጉ ማሰፍሰፋቸው፣

ሌላም ሌላም ታክሎበት ስቃያችን ከቀን ወደ ቀን እየበዛ መጥቷል።

 

ኢትዮጵያን ከዳር እስከዳር በደም ጎርፍ ለሚያጥለቀልቀው የመተላለቅ ዘመቻ እያመቻቹን ያሉት ዘረኞችና የጥፋት ሃይሎች፣ እኩይ ተግባራቸውን በደረጃ እያሳደጉ የሚያሳዩን፤ እነሱ ጠንክረው አሸናፊ ሆነው ወጥተው ሳይሆን፤

 • ኢትዮጵያ አሁን የገባችበት የውስጥም የውጭም ውጥረት ለነሱ አመቺ ሰአት መስሎ መታየቱ፣
 • መንግስት በእነርሱ ላይ ያለው አጥፊ የሆነው አቋሙና ስልቱ፣
 • ከሩቅ በሚሳኤል ሳይሆን፣ አፍንጫው ስር ተደራጅተው ለሚጨፈጨፉን ድጋፍና ከለላ በመስጠት የሚያግዘው በክልሉ ልዩ ሃይል  ውስጥ የመሸገው በጎጥ ብቻ የሚያምነው የዘር መረብ አለመበጣጠሱ፣
 • የየክልሉ መሪዎች ሆን ብለውና አስበውበት በየአደባባዩ የሚፎክሩብን ዘር ተኮር ዲስኩሮች፣
 • ከተጎጅዎቹ መንደር መከላከያን አንስቶ አስጨፍጫፊዎቹን አዲስ አበባ በአጀብና በጥበቃ ማኖር፣
 • በጎጥ በመንደር ከመደራጀት ህዝቡን በጋራ አሰባስቦ በኢትዮጲያዊነት ብቻ የሚያንቀሳቅስ ጠንካራ ድርጅት አለመኖሩ ፣ አለመፈለጉም፣ …ቢኖሩም እንደፈለጉት እንዳይንቀሳቀሱ በማድረግ ችግሩን እያባባሱት መጥተዋል።

አዎ ወቅቱ የሚጠይቃቸው በሃገራችን ላይ የተደቀኑ መጠነ ሰፊ ችግሮች አሉ።

 • የወያኔ ቀብር ተጠናቅቆ ሁሉም እርሙን አለማውጣቱ፣
 • ሃያላን ነን የሚሉት ሃገራት ለተለያየ አላማና ፍላጎታቸው እያደረጉት ያለው ጫና፣
 • በድንበርና በአባይ ጉዳይ ኢፍትሃዊ አቋም ይዘው ወረራም ዛቻም የጀመሩት ጎረቤቶቻችን፣
 • በወረርሺኝ፣ በግጭትና በጦርነት መዳከማችን ፣
 • ዲያስፖራው በዚህም በዚያም ትኩረቱን በሚስቡ ተመሳሳይም ተቃራኒም አቋሞች መወጠሩ፣
 • ለሚያመጣው ጥሩም መጥፎም ጎኑ ዛሬ ውጤቱን መተንበይ የማንችልለት ገና ከጅምሩ የእጩዎቹን ደም የገበረበት የዘንድሮው ምርጫ ውጥረቱ፣…

ሌላም ሌላም ተጨምሮበት ሁላችንም በአንድነት በመቆም እንደ ኢትዮጵያ ድምጽ መሆን፣ በውስጥም ላለው ችግር መንግስትን ከመቸውም በላይ ማሳሰብና በመግለጫ ብቻ ከማባበል ወጥቶ በጉያው ያሉትን ገዳይና አስገዳዮች እንዲያጸዳ መጠየቅ አስፈላጊ ነው።

 

ማለቂያ የሌለው ሻማ በየቀኑ በማብራት፣ ነፍስ ይማር እያልን ለፈጣሪ ብቻ ሰጥተን ከንፈር መምጠጡ ይብቃን! በሀገር ውስጥም ሆነ በተለይም በውጭ የሉ የኢትጵያውያን ስብስቦች /ማህበራት ፣ድርጅቶች፣ የእምነት ተቋማት፣… / በሚያመቸውና ውጤት ሊያመጣ በሚችል መልኩ ጉዳዩ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚመለከታቸውን ሁሉ ማሳወቅና መንግስት ለነገ በማይባል መልኩ እርምጃ እንዲወስድ ጫናም መፍጠር፣ወቅቱ የሚጠይቀው ፈጣን መልሳችን ነው።

ኢትዮጵያን የምንል ሁሉ አንድነታችንን የሚጠይቅ ፈታኝ ጊዜ ላይ ነንና  ዘር ሃይማኖት ሳንል መንግስት ቃል በገባው መሰረት የህዝቡን ደህንነት እንዲጠብቅ በማሳሰብ፣ እኛም በሚቻለው ሁሉ እርስ በርሳችን በህብረት መቆም።

ይህም ማለት በወያኔ ህልመኞችና በኦሮሞ አክራሪዎች በተቀናጀ መልኩ ኢትዮጵያን አፈራርሰው ለማየት የጀመሩትን አዲሱን የውሸት ፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ከመንግስት ጋር ሆነን መዋጋታችንን አጠናክረን በመቀጠል ነው።   ያ ሌላ ይህ ሌላ!!!

 

የዛሬው የአማራው መራር ለቅሶ ለነገው ለኦሮሞው፣ለትግሬው፣ለሌላውም የሃገሬ ህዝብ እሪታና ዋይታ ለኢትዮጵያም መበታተን ዋዜማ መሆኑን ሳንዘነጋ ማንም ያለማንም ሙሉ አይደለምና ሁላችንም በጋራ፣ በገንቢና ሃገር በሚያድን መንገድ እንሰለፍ። በእንባ ላይ እንባ ፣ ያበራነው ሻማ ሳይጠፋ ሌላ ሻማ እያበራን እስከመቼ ??? እላለሁ።

 

ለሙታን ነፍስ ምህረትን ለተጎዱት ብርታትን ይስጥልን!

ጠላቶቿን እንደምንጊዜውም ከእግሯ ስር ይጣልልን!

ሃገራችን ኢትዮጵያን አብዝቶ ይባርክልን!

Source link

Related posts

“ፍቅር፣ ጀግንነት፣ ትህትና፣ እንግዳ አቀባበል፣ ባህልን እና እምነትን ማክበር እንደ ኢትዮጵያዊያን” ይባል ነበር- መምህር ዘመነወርቅ ዮሐንስ

admin

በመዲናዋ ለሚገኙ 828 አርሶ አደሮች እና የአርሶ አደር ልጆች የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ተሰጠ

admin

በኖርዲክ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የሚሳተፉበት የሕዳሴ ግድብ የገቢ ማሰባሰቢያ መርኃግብር በመጪው ቅዳሜ ይካሄዳል፡፡

admin