82.62 F
Washington DC
June 21, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

“ኢየሩሳሌምን መሠላት፣ ገነትን በምድር ሠራት”

“ኢየሩሳሌምን መሠላት፣ ገነትን በምድር ሠራት”

ባሕር ዳር፡ ጥር 10/2013 ዓ.ም (አብመድ) በምድር እንደርሱ ጥበብ የተሰጠው ያለ አይመስልም። የጥበቡ አምሳያ አልተገኜም። ፈጣሪ እንደ ኢትዮጵያ አድርጎ የሚወደው ያለ አይመሰልም። ትዕዛዛቱ ያረፈበትን ፅላተ ሙሴን፣ ደሙ የተቀዳበትን ፅዋ፣ የተሰቀለበትን ግማደ መስቀልና ለምድር ሁሉ የተሰጠውን ሁሉ ሰጥቷታልና።

ጥበብ ለዚያ ጥበበኛ እንደተሰጠው ለማንም አልተሰጠውም፣ መላእክትን ያያቸዋል፣ ሰማየ ሰማያትን ጎብኝቷል፣ ድንጋይ እንደ ዳቦ ይቆረስለታል፣ ጥበብ እንደ ምንጭ ውሃ ይፈልቅለታል፣ በረከት በቤቱ በሚገዛት ሀገሩ ሁሉ ሞልቶለታል።

በሥልጣኔ የደመቀች፣ በአኩሪ ታሪክ የታወቀች፣ ከዘመኑት በፊት የዘመነች፣ ከኃያላኑ በላይ ኃያል የሆነች ኢትዮጵያ የእግዚአብሔር ሚስጥራት ያረፉባት ናት። “የእስራኤል ልጆች ሆይ! እናንት ለእኔ እንደ ኢትዮጵያ ልጆች አይደላችሁምን?” እንዳለ የተወደደችና የተመረጠች ሀገር ናት ኢትዮጵያ።

ያጥበበኛ ንጉሥ በምክርና በጥበብ፣ በስልትና በእውቀት አደገ። ውብ የእግዚአብሔር መንፈስ ያደረበት ሆነ። ከግርማውና ከሥራው፣ ከውበቱና ከእውቀቱ፣ ከሚጣፍጠው ንግግሩ ከመልካም ምግባሩ፣ ከጥሩ ሰውነቱ፣ ከመንፈሳዊ ሕይወቱ፣ ትህትናው እና ታዛዥነቱ የተነሳ ሕዝቡ ሁሉ ይነግሥ ዘንድ ተመኘለት። ዝሙት፣ ስስት፣ ምቀኝነት፣ ሀሰት፣ ውሸት፣ ክፉ ዓመል ሁሉ በእርሱ ዘንድ አይታወቁም።

በነገሠም ጊዜ ደሃን አይበድልም። ፍርድ አያጓድልም። ተገዢዎቹን አይጨቁንም። አያስጨንቅም። የእርሱ ጥበብ ያረፈባቸውን የእነዚያን አብያተክርስቲያናት ሥራ መናገር የሚቻለው በምን አንደበት ይሆን? ያየ አይጠግባቸውም። ልቡ አርፎ ከማድነቅ ቸል አይልም። ታሪኩን ይቆጥር ዘንድ ለሰው የማይቻለው በላልይበላ ድንቅ የሆነ ታሪክ ተሰርቷል።

በላልይበላ እጅ የተሰሩትን አብያተክርስቲያናት ያይ ዘንድ የሚወድ ሰው ቢኖር ይምጣ፣ በዓይኖቹም ይይ፣ እንደሙሴ ድንኳን የላል ይበላ ሕንፃዎች የሚያረጁ አይደሉምና። እንደሰለሞንም አዳራሽ ጠላቶች የሚያፈርሱት አይደለምና። የላል ይበላ ሕንፃዎችስ ኢየሩሳሌም ሰማያዊት በምድር ላይ እስክትታይ ድረስ አይናወጥም፣ አይጠፋምም።

ጴጥሮስና ጳውሎስ በእግዚአብሔር ትዕዛዝ በሦስት ድንጋዮች የቅድስት ድንግልን የቤተ መቅደስ ሥራ ጨረሱ። ላልይበላም ፀጋ እግዚአብሔር እየረዳው ከአንድ አለት ላይ አብያተክርስቲያናትን ሠራ። ጴጥሮስና ጳውሎስ በአንድ ጭንጫ ላይ አብያተክርስቲያናትን ሠሩ። ሥራቸው ግን የጣሪያው እንጨት በገመድ የተታታ(የታሰረ )፣ ግድግዳውም እንጨት ነው። ምርጊቱም ጭቃ መሰሶዎችም እንጨቶች ናቸው።

ላልይበላ ግን ከአለት ላይ አብያተክርስቲያናትን ሢሠራ ለግድግዳቸው እንጨት፣ ለምርጊታቸውም ጭቃ የለውም እንዳለ መፃፍ። ሥራው እፁብ ነው። ሊቃውንት ሰው ሁሉ ኢትዮጵያዊ ሆኖ ካንዲት ድንጋይ የተሠሩትን አብያተክርስቲያናት ዜና ሰምቶ ቅድስት ወደሆነችው ወደሮሃ ያልደረሰና ይህንም ያላየ የጌታን ዓይን ያይ ዘንድ የማይወድ ሰው ይመስለል ይላሉ።

“የፀሐይ ክብሩ ልዩ ነው፣ የጨረቃም ክብሩ ልዩ ነው፣ የከዋክብትም ክብራቸው ልዩ ነው” እንዳለ የቅዱስ ላልይበላ ክብር እንደሌሎቹ ቅዱሳን አይደለም። እንደ ፀሐይም አይደለም። እንደፀሐይ ሁለት እጅ የሚያበራም አይደለም። ከጠቢባን በሚመስለው በሌለ በሕያው ጥበብ የተሰራ ልብሱ ከፀሐይ ሰባት እጅ ያበራል እንጂ እንዳለ መፅሐፍ።

“በመከራ ብንመስለው በክብር እንመስለዋለን፣ በሞት ከመሰልነው በሕይወት እንገኛለን። በሕይወትም ብንመስለው መንግሥተ ሰማያትን እንወርሳለን” እንዳለ ቅዱሱ ንጉሥ የመሰለውን መሰለው። ሙሴና ሰለሞን ደብተራ ኦሪትን እና ቤተመቅደሱን ሲያንፁ ጠበብትና አዋቂዎች ረድተዋቸዋል። ለእርሱ ግን ረዳት የሆኑት መላእክት ናቸው። መላእክትን ያያቸዋል፣ ቃል ለቃልም ይነጋገራቸዋል፣ ከአጠገቡ አይርቁትም። ከእርሱ ውጭ ግን ማንም አያያቸውም።

ጌታ ማደሪያውን ይሠራለት ዘንድ ለላልይበላ በነገረው ጊዜ ላልይበላም እንዴት ይደረግልኛል አለው። ጌታም “አትዘን አትተክዝ አይዞህ እኔ የሰው ኃይል የምፈልግ አይደለሁም እንደ አንተ በሚፈሩኝ ላይ ነኝ” አለው። ምድራዊ ነገሥታት በጳጳሳት እጅ ተቀብተው ይነግሳሉ ቅዱሱና ንጉሡ ግን በጌታው እጅ ቅብዓ መንግሥት ተቀባ። በምድር ነገሠ። በሰማይ ተቀደሰ። መልካሙን ሥፈራም ወረሰ። ምድራዊ ሆኖ እንደሰማያዊ ኖረ። በምድር ኖሮ የሰማይን በምድር አኖረ። ከጌታውም ጋር ተነጋገረ።

ላልይበላ መፅሐፍ ቅዱስን እና ቅዱሳት መጻሕፍትን በጥበቡ ተረጎመ። በአለት ላይ ምሳሌያቸውን አስቀመጠ። በሮሃ ከተማ የደረሰ ሁሉ በደስታ ያነባል፣ በጥበቡ ይገረማል፣ አቤቱ እፁብ ድንቅ ነህ ይላል፣ ኢትዮጵያዊ የሆነው ሁሉ ጌታ ሆይ በዚህች ምድር ስለፈጠርከኝ ተመስገን ይላል። በዚያች ምድር ከነገሡት አራቱ የተቀደሱ ነበሩ። ቅዱስ ይምርሃነ ክርስቶስ፣ ቅዱስ ገብረ ማርያም፣ ቅዱስ ላልይበላና ቅዱስ ነአኩቶ ለአብ። ሰውንም እግዚአብሔርም ያገለግሉ ነበር። የቅዱስ ይምርሃነ ክርስቶስ ባለቤት ቅድስት ሕዝባ፣ የቅዱስ ገብረማርያም መርኬዛ፣ የቅዱስ ላልይበላ መስቀል ክብራና የቅዱስ ነአኩቶ ለአብ ንፅሒት ይባላሉ።

ይምርሃነ ክርስቶስ ሚስት ነበረው፤ ፍትወተ ስጋን ግን አልፈፀመም ይባላል። ጌታ ላልይበላን ጥበብህንም ሰምተው ለሚያዩህ እስከዘላለም ሲያደንቁህ ይኖራሉ በምትሰራበት ጊዜ የሚያግዙህ መላእክት እንጂ ሰዎች አይደሉም እንዳለው ያየው ሁሉ ይደነቃል። ወደ ኢየሩሳሌም ላልሄዱትም ቃል ኪዳኔን በዚህ ቦታ አስቀምጣለሁ ሲልም ቃል ገብቶለታል። “ሰማይና መሬት ያልፋሉ ቃሌ ግን አያልፍም” እንዳለ ቃሉ ላያልፍ በሮሃ ፀንቶ ይኖራል።

ላልይበላ እነዚያን የተቀደሱ የጌታው ማደሪያ የሚሆኑትን ሢሰራ የተቀደሱ መሆናቸውን አስቀድሞ ያውቅ ነበርና ለክብራቸውና ለንፅሕናቸው ሲል በአጠገባቸው አያድርም ነበር። ጥበብ የተቸረው ቅዱሱ ንጉሥ ጥበቡን በምድራዊ ቤት አላበከነውም። ይልቁንስ በድንኳን እየኖረ፣ የማያልፍ ስራ አኖረ።

ላል ይበላ ፀሐይ ስትገባ የፀሐይን መግቢያ ተከትሎ ወደ ምዕራብ በመጓዝ ያርፋል። ፀሐይ ስትወጣ ደግሞ መውጣቷን ተከትሎ ወደምስራቅ በመጓዝ ይሰራል። የላል ይበላ መኖሪያ ከአብያተክርስቲያናቱ በስተ ምዕራብ በኩል በሚገኝ ኮረብታ እንደነበር ይነገራል። ሥፍራውም መካነ ልዕልት ይባል ነበር። የልዕልት መቀመጫ እንደማለት ነው። አሁን ግን መካልት በመባል ይታወቃል።

ሰለሞን ከጥበበኞች ሁሉና ከሰው ልጅ ሁሉ ጥበበኛ ተባለ። እርሱም ርዝመታቸው ስምንት ክንድ፣ ሰባት ክንድ በሚሆኑ በታላላቆች ድንጋዮች ቤተ መቅደስን በኢየሩሳሌም ሠራ። የጢሮስ ንጉሥ ኪራም የፅድ፣ የዝግባ፣ የዋንዛ እንጨቶችን እየረዳው ሁለቱን ቤቶች ቤተ እግዚአብሔርና የራሱን ቤት በጀመረ በሃያ ዓመት ፈፀመ። ላልይበላ ግን እግዚአብሔር እየረዳው በአንድ ቋጥኝ ሠራ። ከሰሎሞን ጥበብ የላልይበላ ይልቃል ይላሉ ሊቃውንት።

ላልይበላ ሥራዎችን በሦሥት ምድብ መደባቸው። ቤተ መድኃኔዓለም፣ ቤተ ማርያም፣ ቤተ ጎለጎታ(ቤተ ሚካኤል )፣ ቤተ መስቀልና ቤተ ደናግል ምድብ አንድ ናቸው። አምስቱ አብያተ ክርስቲያናት የአምስቱ ቅንዋተ መስቀል ምሳሌዎች ናቸው። ሳዶር፣ አላዶር፣ ደናት አዴራና ሮዳስ። አሰራራቸውም መስቀል የሠራ ነው። በምድራዊት ኢየሩሳሌም ይመሰላሉ።

ቤተ ገብርኤል፣ ቤተ አባ ሊባኖስ፣ ቤተ መርቆሬዎስና ቤተ አማኑኤል በሁለተኛው ምድብ ናቸው። ምሳሌያቸውም በሰማያዊት ኢየሩሳሌም ነው።

ቤተ ጊዮርጊስ ብቻውን የተሰራ ነው። አምሳለ ኖህ መርከብ ነው። ቤተ መድኃኔዓለም ትልቁ ነው በአንድ አለት ተሰርቶ ያን ያክል የሚሆን ሕንጻ ቤተክርስቲያን በምድር አልታየም ይባላል። ቤተክርስቲያኑ በውጭ 34 ከውስጥ 38 በድምሩ 72 አምዶች አሉት። የ72 አርዲት ምሳሌዎች ናቸው። የብርሃን ማስገቢያ 52 መስኮቶች አሉት 3 በሮችም አሉት። ጣርያው የማሕጠንት ጭስ አያጠቁረውም። ሁሌም አዲስ ሆኖ ይኖራል። ታምረኛው የአፍሮ አይገባ ገባሬ ታዓምር መስቀልም የሚገኘውም በዚሁ ነው።

መስቀሉ ተሰርቆ ቤልጄም ሀገር ሄዶ በራሱ ታምር ከሁለት ዓመት ቆይታ በኋላ ተመልሷል። መስቀሉ የተለያዩ ምሳሌዎች አሉት። የአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ምሳሌ፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ደም መፍሰስ ምሳሌ፣ የእሾህ አክሊል የማድረግ ምሳሌና የሙሴ በትር ምሳሌዎች ናቸው። የመስቀሉ ውስጣዊ ህብሩ ሚስጥር አይነገረም። ሁልጊዜም ሲታይ የተለያዩ ሕብረ ቀለማትን ያሳያል።

ቤተ ማርያም የላልይበላ የመጀመሪያ ሥራ ናት። አሰራሩ ፎቅና ምድር የሆነ ነው። ፎቁ ሰባት ክፍሎች አሉት የሰባቱ ሰማያት ምሳሌዎች ናቸው። 12 አምዶች ይገኙበታል የሐዋርያት ምሳሌዎች ናቸው። በቤተ ማርያም በላይ በኩል ስፋታቸውና ርቀታቸው አሠራራቸው እኩል የሆኑ መስኮቶች አሉ። እነርሱም የሶስቱ ስላሶች ምሳሌ ነው። በመካከለኛው እና በወልድ ትይዩ ያሉት የመጀመሪያው ምልክት ክርስቶስ ከሰማየ ሰማያት መውረዱን፣ ከድንግል ማርያም መወለዱን እስከ መሰቀሉ የሚያመላክቱ ጥበባዊ ምልክቶች አሉ። መሰቀሉን በሚያመላክተው ግራና ቀኝ ሁለት ጥበባዊ ምልክቶች አሉ። ከእርሱ ጋር የተሰቀሉት ዘየማንና ዘፀጋም ወይም ጥጦስና ዳክርስ ምሳሌዎች የሚሆኑም አለ፡፡

በቀኝ በኩል ለተሰቀለው ወደገነት መግቢያ የቃል ኪዳን ቁልፍ ምልክትና የክርስቶስን እርገት የሚያሳይ ምልክቶች አሉበት። የተቀደሰ ውሃም ይገኛል በዚሁ ግቢ። ላልይበላ ያለ መልዕክትና፣ ያለ ትዕዛዝ፣ ያለ ምክንያንያት የጠረበው ድንጋይ ያስቀመጠው ምልክት የለውም። ሁሉ በትርጓሜ ሁሉም በታምዕር ተቀመጠ እንጂ። ቤተ መርቆሬዎስ በገነት ይመሰላል። ቤተ አማኑኤል ፎቅና ምድር ሆኖ የተሠራ ነው። ፎቁ ዘጠኝ ክፍል አለው። ይሄም የዘጠኙ ቅዱሳን ምሳሌ ነው። አራት አምዶችም አሉት የአርባእቱ እንስሳ ምሳሌዎች ናቸው።

ቤተ አባ ሊባኖስ ከባድ ጣሪያ የተሸከመ ታምራዊ ጥበብ ያረፈበት ነው። ይህ ድንቅ ቤተ ክርስቲያን የኪሩቤል ምሳሌ ነው። ኪሩቤል የመድኃኔዓለምን ዙፋን በፍርሃት በመሸከም ቅድስ ቅደስ እያሉ ያመሰግናሉ። ቤተክርስቲያኑ አምሳለ ኪሩቤልም ጣርያው ደግሞ የዙፋኑ ምሳሌ ነው። ብቻውን የተሰራው ቤተ ጊዮርጊስ ከጣርያ እስከ ምድር በመስቀል ቅርፅ ታንጿል። ይህ አምሳለ ኖህ መርከብ የሆነው አስደናቂ ቤተክርስቲያን አያሌ ሚስጥራትን ይዟል። በዚህ ቤተክርስቲያን መርከቧ ያረፈችበት የአራራት ተራራ አምሳል የሆነም አለ። ቤተክርስቲያኑ በውስጡ ከቤተ መቅደሱ ውስጥ የሙሴ ደንኳን ምሳሌ የሆነ ጉልላት አለው።

በቤተ ጊዮርጊስ በእስተ ምሥራቅ በኩል በምድራዊት ኢየሩሳሌምና በሰማያት ኢየሩሳሌም የሚወርድ አምሳለ ዮርዳኖስ ወንዝ አለ። ከወንዙ መካከልም ከድንጋይ የተቀረፀ መስቀል ይገኛል። በወረሃ ሰኔ ታይቶ የነበረው የፀሐይ ግርዶሽ አስደናቂ ጨረር ከዚሁ መስቀል ላይ እንዳረፈ ሰምቻለሁ። በቤተ ጊዮርጊስ ያሉ የሀሳብና ታምራዊ መስመሮች ያልተፈቱ፣ ያልተመረመሩ ሚስጥራትን እንደያዙ ይነገርላቸዋል። የዓለም አያሌ ሚስጥራትን የሚጠቁሙ ሊሆኑ እንደሚችሉም ይነገራል።

ላልይበላ አብያተክርስቲያናቱን ሢሠራ እንደ ሌሎቹ ጥበበኞች ከመሠረት ወደ ጣሪያ አልዘለቀም። ከጣርያ ወደ መሠረት ሄደ እንጂ። ሌሎቹ ለጣርያ እየቀረቡ ለመሠረት እየራቁ ሲሄዱ እርሱ ከጣርያ እየራቀ ከመሠረት እየቀረበ ሄደ። ሊቃውንት ጨርሶ ጀመረ ሲሉ ጥበቡን ይገልፁታል። በቅዱስ ላልይበላ ዘመን አራት የክብር ወንበሮች ነበሩ።

የመጀመሪያው ክብር ከንጉሠ ነገሥቱ ዙፋን በቀኝ በኩል ለሚቀመጠው ባለ ወርቅ ወንበር የክብር መጠሪያውም ንቡረዕድ ግዛቱ ከምፅዋ እስከ ወርህ፤ ሁለተኛው ከንጉሠ ነገሥቱ በግራ በከል ለሚቀመጠው ባለ ብር ወንበር ለሊቀ ካህናት ዘወርወር በደብረ ላልይበላ ግዛቱ ከወርህ እስከ በሽሎ፣ ከዓባይ እስከ ዞብል፤ ሦሥተኛው ክብር ከንቡረዕድ ቀጥሎ ለሚቀመጠው ባለ ብረት ወንበር ለርዕሰ ርዑሳን ዘ መርጡለማርያም ግዛቱ ከዓለይ እስከ ዓባይ፤ አራተኛው ክቡር ከሊቀካህናት ቀጥሎ ለሚቀመጠው ባለ ብረት ወንበር ለፓትርያርክ ዘ ተድባበ ማርያም ግዛቱ ከዓባይ እስከ ሸዋ፡፡

የነገሥታት ንጉሥ ቅዱስ ላልይበላ ሆይ ፍቅርህ በልቦናዬ ውስጥ የታነፀ ነው። ዝናህ ዓለምን ሁሉ ታዳርሳለች። ለሥራዎችህ አምሳያ አልተገኜለትም። ዓይኖቼ ዓለምን አዩ፣ በምድር የተሠራ ምድራዊ ያልሆነ ሰማያዊ ዓለም፡፡ አይተውም አደነቁ፡፡ ጥበበኛውንም ጥበብን የፈጠረውንም አደነቁ፡፡ ዙሪያ ገባውን እያዩ ከመደነቅ በስተቀር ሌላ ዐቅም አልነበራቸውም፡፡ ምን አይነት ጥበብ ነው፡፡ ምን አይነት መታደል ነው፡፡ እነዚያን ጥበቦች ያዩ ዓይኖች፣ የረገጡ እግሮች፣ ስለዚያ ጥበብና ጠቢብ የሰሙ ጀሮዎችም የታደሉ ናቸው። በሮሃ ሰማይን ያያሉ። ምድርንም ያደንቃሉ።

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

Source link

Related posts

በጎንደር ከተማ በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ የሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሴቶች ፍትሐዊ የምጣኔ ሃብት ተጠቃሚነት እንደሚሠሩ ገለጹ፡፡

admin

ቀደምት የስልጣኔ አሻራዎችን ለአንድነትና ለአገራዊ ብልፅግና ጥቅም ላይ ማዋል ይገባል ተባለ

admin

ትግራይ እንዴት ሰነበተች? (ክፍል 3)

admin