31.01 F
Washington DC
March 2, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

“ኢትዮጵያ እና ሱዳን ብሔራዊ ጥቅሞቻቸውን አስከብረው በትብብር ከመሄድ የተሻለ አማራጭ የላቸውም” ሱዳናዊ ፕሮፌሰር ሙሃመድ ሳላህ

“ኢትዮጵያ እና ሱዳን ብሔራዊ ጥቅሞቻቸውን አስከብረው በትብብር ከመሄድ የተሻለ አማራጭ የላቸውም” ሱዳናዊ ፕሮፌሰር ሙሃመድ ሳላህ

ባሕር ዳር ፡ የካቲት 07/2013 ዓ.ም (አብመድ) ኢትዮጵያ እና ሱዳን በሀገረ መንግሥት ግንባታ አያሌ የሚባል ዘመን ባለቤቶች ናቸው፡፡ የሁለቱ ሀገራት ፖለቲካዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊ፣ እና ማኅበራዊ ግንኙነታቸውም ከሀገረ መንግሥት ግንባታ ታሪካቸው ጋር በእድሜ የተቆራኘ ነው፡፡ ሁለቱ ሀገራት ረዥም ድንበርን የሚጋሩ፣ በሚጋሯቸው ወሰን አካባቢዎች ሠፊ የባሕል፣ የቋንቋ እና ማኅበራዊ እሴቶች መጋራት የሚስተዋልባቸው ናቸው፡፡

መሠረታዊ የሆነ የምጣኔ ሀብት ትስስር እና የመሠረተ ልማት ትብብርም አላቸው፡፡ ከኢትዮጵያ ሰሜናዊ አካባቢ ከሚገኙ ከፍተኛ ቦታዎች የሚፈልቀው የዓለማችን ረዥሙ ወንዝ ዓባይ አብራኩን እንደዘንዶ ተጠምጥሞ ሲጨርስ ከባዕዳን ምድር ሱዳን ቀደምት ማረፊያው ናት፡፡ ሁለቱ ሀገራት ከልዩነት በላይ በሰፋ ተመሳስሎ እና ትስስር ዘመናትን አሳልፈዋል፡፡

ረዥም በሆነው የሁለቱ ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ግንኙነቶቻቸው ነገሮች ሁሉ አልጋ በአልጋ ነበሩ ማለት ግን አይደለም፡፡ በተለይም እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር በ1900 መባቻ አካባቢ አፍሪካን እንደ ቅርጫ ሥጋ የመቀራመት ራዕይ የነበራቸው አውሮፓዊያኑ በቀጣናው ጥለውት የሄዱት የድንበር ቆርሾ እና በዓባይ ውኃ ላይ “ከእኔ ውጭ ተጠቃሚ የለም” የምትለው ግብፅ በሁለቱ ሀገራት መልካም ግንኙነት ላይ በተደጋጋሚ ጥላ ሲያጠሉበት ተስተውሏል፡፡

በአሁኑ ወቅት ድንበር አካባቢ የተፈጠረውም ከሁለቱ ሀገራት የረዥም ዘመን ታሪክ የተመዘዘ ነው የሚሉ በርካቶች ናቸው፡፡ ይህን ጉዳይ በሚመለከት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከሱዳን ምሁራን ጋር የሁለት ቀናት ምክክር በዋናው ግቢ እያካሄደ ነው፡፡ በምክክር መድረኩ ከተሳተፉት ምሁራን መካከል በወሎ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ እና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህር ዓለማየሁ እርቅይሁን (ዶክተር) የሁለቱ ሀገራት የድንበር ውዝግብ ዛሬ እንዳልተጀመረ ገልጸዋል፡፡ በተለይም ሱዳን ከቅኝ ግዛት ነፃ ከወጣችበት እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር በ1950ዎቹ ጀምሮ ጉዳዩ የሁለቱ ሀገራት ብሔራዊ የደኅንነት ስጋት እየሆነ መምጣቱን ያወሳሉ፡፡

አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር በ1902 ሱዳንን በቅኝ ግዛት ከምታስተዳድረው እንግሊዝ ጋር ኢትዮጵያ በወቅቱ አንድ ስምምነት ተፈራርማለች፡፡ በስምምነቱ በተለይም አንቀፅ 2 ላይ “ሁለቱ ሀገራት ድንበር ሲካለሉ ወኪሎቻቸው ሊገኙ ይገባል” ይላል የሚሉት ዶክተር ዓለማየሁ ነገር ግን ካለኢትዮጵያ እውቅና እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር በ1903 በጎንደር አካባቢ የሚገኘውን ድንበር እና እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር በ1909 ደግሞ በጋምቤላ በኩል ያለውን ድንበር እንግሊዛዊው ሻለቃ ጊዊን ብቻውን እንዲያካልለው ተደረገ፡፡ ከዚያ ጀምሮ አላስፈላጊ ውዝግቦች እንዲበራከቱ በር እንደከፈተ አስረድተዋል፡፡

በኒዘርላንድ ዓለም አቀፍ (ኢንስቲትዩት ኦቭ ፖለቲካል ዲቨሎፕመንት ስተዲስ) የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር እና የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና የፖለቲካ ጉዳዮች ተመራማሪ ሱዳናዊው ፕሮፌሰር ሙሃመድ ሳላህ በቀጣናው 21 የሚደርሱ የብሔሮች እና የሀገራት የድንበር ግጭቶች እንዳሉ ጠቅሰዋል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ ድንበር በሁለት መንገድ እንደሚከለል ያወሱት ፕሮፌሰሩ በርካቶቹ የአውሮፓ ሀገራት ድንበሮቻቸውን በልማት፣ መሠረተ ልማት እና በጋራ ጥቅም አስተሳስረው ለሕዝብ ምቹ እንዳደረጉ አንስተዋል፡፡ በሌላ በኩል ግን በርካቶቹ የሦስተኛው ዓለም ሀገራት ድንበሮቻቸውን በጦር እና በግጭት ስለሚያስከብሩ በአካባቢው የሚኖሩ ዜጎች ምድራዊ ስቃይ እና ፈተና እንዲያሳልፉ ይገደዳሉ፡፡ “በሱዳን እና በኢትዮጵያ መካከል ስላለው ወቅታዊ የድንበር ጉዳይ ብዙ ማለት አልፈልግም” ያሉት ፕሮፌሰሩ ምክንያታቸው ደግሞ ሁለቱ ሀገራት ከድንበር የዘለለ የመሠረተ ልማት፣ የምጣኔ ሃብት፣ የባህል እና እሴት ትስስር ያላቸው በመሆኑ ችግሩ ከጋራ ተጠቃሚነት አያልፍም የሚል ነው፡፡

እንደ ምሁሩ ማብራሪያ ሱዳን የኤሌክትሪክ ኃይል የምታገኘው ከኢትዮጵያ ነው፣ በርካታ ባለሃብቶቿ ኢትዮጵያ ውስጥ መዋዕለ ነዋያቸዉን ያፈስሳሉ፤ እንዲሁም የሱዳን ምርቶች በኢትዮጵያ ሠፊ ገበያ አላቸው፤ በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ከሱዳን የምታገኛቸው በርካታ የንግድ እንቅስቃሴዎች መኖራቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ፕሮፌሰሩ በሰጡት አስተያየት “ኢትዮጵያ እና ሱዳን ብሔራዊ ጥቅሞቻቸውን አስከብረው በትብብር ከመሄድ የተሻለ አማራጭ የላቸውም፡፡”

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

Source link

Related posts

አቶ ስዩም መስፍን ፣አቶ አስመላሽ ወልደስላሴና አቶ አባይ ፀሃዬ ተደመሰሱ

admin

መንግስት በትግራይ ክልል ህይወት ቀድሞ ወደነበረበት ሁኔታ እንዲመለስ በትብብር እየሰራ መሆኑን አስታወቀ

admin

“ፍቅር፣ ጀግንነት፣ ትህትና፣ እንግዳ አቀባበል፣ ባህልን እና እምነትን ማክበር እንደ ኢትዮጵያዊያን” ይባል ነበር- መምህር ዘመነወርቅ ዮሐንስ

admin