55.89 F
Washington DC
April 13, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

ኢትዮጵያዊ አንድነት በእኩልነት – ጆቢር ሔይኢ ከሁስተን ቴክሳስ | Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider

04/07/2021

የዛሬይቷ ኢትዮጵያ በተሟላ መልኩ የተመሠረተችው  በዳግማዊ አጼ ምንሊክ ነበር። ንጉሡም ሥልጣነ መንግሥታቸውንና እምነታቸውን  ከውጭ ወረራ ለመከላከል፣ኤርትራን ለኢጣሊያን ጂቡቲን ለፈርንሳይ አሳልፈው በመስጠት፣በምትኩ መድፍና ነፍጥን ተቀብለው፣ ግዛታቸውን፣ በደቡብ፣ በምዕራብና በምሥራቅ አስፋፉ።

የዳግማዊ አጼ ምንሊክ ጦር መሪ፣ ራስ ጎበነ ዳጪ ሲሆኑ፣ እርሳቸውም ነፍጥ የታጠቀ ሠራዊት በመምራት ነበር በቱለማ ኦሮሞዎች ላይ ዘምተው ብዙዎችን በመግደል ያስገበሩት።ከዚህ በኋላ ነፍጠኛውን ጦር በሰው ኃይል በመጠንከር ነበር ወደ ምዕራብ ደቡብና ምሥራቅ በመዝመት ሌሎች ብሄሮችን ተራ በተራ ያስገበሩት፡፡ በዚህም የአገረ መንግሥት ምሥረታ፣ትግሬ፣አማራ ኦሮሞ፣ጉራውጌ፣ሱማሌ፣ አፋር፣ ወለይታ፣ከፋ, ሳይባል ቄሱም ሼኪውም ሁሉም ተባብረዉበታል።

ይሁን እንጂ እንደ ተሳትፎአቸው ሁሉም እኩል የሥርዓቱ ተጠቃሚዎች አልነበሩም። ከፊሎቹ የብሔር ጭቆና ሌሎች የሃይማኖት ጭቆና፣ ብዙዎቹ፣ደግሞ ደርብና ድርብርብ ጭቆና ነበረባቸው።

የእነዚህ ጭቆናዎች ምንጩ ፍትሐ ነገሥት ነበር። አጼ ምንሊክ አገሪቱን የገዙት፣ከአረቢኛ ወደ ግዕዝ ቋንቋ በተተረጎመ፣ ፍትሐ ነግሥት ነበር።በፍትሐ ነግሥት ደግሞ፣ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ፣ እንደ እግዚአብሔር ሕዝብ፣ ሌላውን ሕዝብ ደግሞ እንደ አረመኔ የሚቆጥር ነበር።ከዚህም የተነሳ በኢትዮጵያ መንገሥ የሚችል፣ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ ብቻ ነበር። ንጉሱን ቀብቶ የማንገሥ ሥልጣን ያለውም የኦርቶዶክስ ካህን ብቻ ነበር።

ስለሆነም አጼ ምንሊክ ከእምነታቸውና ከብሔራቸው የተነሣ፣ በሰሜን ሕዝብ ላይ ነፍጠኛ ጦር አላዘመቱም፣ሕዝቡንም ባሪያና ገባር አድርገው አልገዙም። ባላባቱንና ካህናቱን በግዛታቸው ሁሉ ላይ ፈላጭና ቆራጭ አድርገው በመሾም፣የሥርዓቱ ተጠቃሚ አደረጓአቸው እንጂ። ይህም የአጼው የጭቆና ሥርዓት የፈጠረውን ቅራኔ ለማስታረቅ ነው፣ጠቅላዩና ምክትሉ የመደመርን ፖሊሲ ያወጡት። ፖሊሲው ደግሞ የቀደመውን የፊውዳል ሥርዓት በአዲስ መልኩ በመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የሚመልስ በመሆኑ፣የመሬት ወራሪዎች በደስታ ሲቀበሉት፣የብዝበዛው ሥርዓት ተቃዋሚዎች ደግሞ አምረው እይታገሉት ናቸው።

ስለዚህም ትግሉ እየተካሔደ ያለው ከብልጽግና ፓርቲ የገዥ መደብና ከጭቁን ብሔር በሔረሰቦች መካከል በመሆኑ፣የብሔር ጥያቄ ትኩረት፣ሕገ መንግሥቱም አስከባሪ በማጣቱ ነው፣ ቅራኔው ከርሮ ፣ብሔር ብሔረሰቦችን እርስ በርስ በማፋጀት ላይ የሚገኘው።

ይህም በአጼ ምንሊክ ዘመነ መንግሥት የተጠነሰሰው የብሔር ቅራኔ፣ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ ሳይፈታ፣በጥገናዊ ለውጥ እየተሸፈን እስከ አሁን ለመቆየቱ ማረጋገጫው፣  የኦርቶዶክስ እምነት የበላይነት፣ የአማራ ቋንቋ፣ ባህልና ታሪክ አገር አቀፋዊነት፣ በፌድራል ሕገ መንግሥት ጭምር ተደገፎ የሚገኝ መሆኑ ነው።

ይህም አገሪቷ በሕገ መንግሥቷ መሠረት የፌድራል መዋቅር ዘርግታ፣ መንግሥት መሥርታ የምትተዳደር ሲሆን፣የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ግን መዋቅሩንም ሆነ ስያሜውን በመቃወም፣ በቀደመው መዋቅርና ስያሜዋ፣በዙፏኗ ላይ መሳፍንቷን ቀብታ ዘውድ ደፍታ በማንግሥ፣ በሐገር ስብከትና፣በሰበካ ጉባዔ ውስጥ መዋቅሯን ዘርግታ፣ የመቃብር ሥፍራና የሰፈር ዕድርን በመቆጣጠር፣የአንድን ብሔር ቋንቋና ባኅል በማስከበር ፣ የሌላውን ሕዝብ ቋንቋ፣ ባህልና እምነት፣በማጥላላት ተቀባይነትን በማሳጣት  ላይ የምትገኝ መሆኗ ነው።

ቤተ እምነቷ በዚህ መዋቅሯ ሕዝቡን በማንቀሳቀስ፣ በመንግሥት አስተዳደር ውስጥ ጣልቃ በመግባት፣የፌድራል መንግሥትን፣ የአዲስ አበባ ከተማንና ክልሎችን በማስፈራራት፣ የበዓል ማክበሪያ ቦታዎችን፣ የሕዝብ መናፈሻና የስፖርት ሜዳዎችን በስሟ በማስመዝገብ ላይ ትገኛለች።

ሌላው  የሕዝባችን መሠረታዊ ችግር፣ የሕገ መንግሥት አስከባሪ ማጣት ነው።በሕገ መንግሥቱ፣ “አዲስ አበባ፣ በኦሮሚያ እምብርት የሚትገኝ፣ የፌድራልና የኦሮሚያ ዋና ከተማ ስለሆነች፣የኦሮሚያ ልዩ መብት ሊከበር ይገባል”ሲል ይደነግጋል።ይህም ልዩ መብት፣ የሲዳማ ብሔራዊ ክልል በአዋሳ ከተማ ላይ፣የአማራ ብሔራዊ ክልል በባሕር ዳር ከተማ ላይ፣የትግራይ ብሔራዊ ክልል በመቀሌ ከተማ ላይ ካለው መብት አንጻር የሚጣጣም ሊሆን ይገባዋል።

ነገር ግን ይህ ሕገ መንግሥታዊ መብት እስከ አሁን በተግቢው መልኩ ባለማከበሩ፣ አንዳንድ ጸረ ኦሮሞና ጸረ ሕገ መንግሥት አቋዋም ያላቸው ሰዎች፣ይህን ሕገ መንግሥታዊ መብት ለመጻረር በፖለቲካ አቁዋም ተደራጅታው፣በምርጫ ቦርድ እውቅና ተስጥቶአቸው፣ የአመጽ ቅስቀሳና የተቃውሞ ስልፍ በማድረግ ላይ ይገኛሉ።

ስለሆነም ሕገ መንግሥቱን የማስከበሩ ሃላፊነት የፊድራል መንግሥትና የመከላከያ ሠራዊትም በመሆኑ፣በጸረ ሕገ መንግሥት አቋዋም ለተደራጁት ቡድኖች የሕግ ሰውነት መሥጠት፣ አመጻን ማበረታታትና በአመጽ ተግባራቸው መተባበር በመሆኑ፣ የተሰጠው ዕውቅና ተሰረዞ፣ሕገ መንግሥትን ባማስከበር፣ከአመጻ ተግባራቸው ሊገቱ ይገባል።

ከሁሉም ይልቅ ሕዝባችን በጥልቀት ሊያስተዉሉት የሚገባው፣ የአገራችንን  ነባራዊ ሁኔታን ነው።ይህም ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ያልተያዘች አገር ናት ማለት፣ በአገራችን የብሔር ብሔረሰቦች ጭቆና አልነበረም ለማለት አይደለም።ገዥ መደብ እንዳለ ሁሉ፣ገዥ ብሔርም ነበር።የብሔር፣ የቋንቋ፣የእምነት፣ የታሪክና፣የባህል ልዩነት እስካለ ድረስ፣ መጠኑ ይለያይ እንጂ እንደ ሌሎች አገሮች ሁሉ፣የተለያዩ ጭቆናዎች በአገራችንም ይኖራሉ።

ረሺያ በቅኝ አልተገዛችም።እርሷ ራሷ ሌሎችን በቅኝ ተገዛ ነበር፣ጃፓን በቅኝ አልተገዛችም፣ እርሷ ራሷ ቅኝ ገዥ ነበረች፡፡በቅኝ ግዛት ሥር የቆዩ ሁሉም የአፍሪካ አገሮች ወደ ብሔር ደረጃ ያደጉ በመሆናቸው የመደብና የቀለም ልዩነት ካልሆነ በቀር ፣የቋንቋ የባህልና የታሪክ ጭቆና የለባቸውም።

በእኛም አገር የባርያ ነጻ አውጪ ችሎት ነበር፣”ወርቅ ረከሰ መዳብ ነገሠ” የሚሉ ነበሩ።አሁንም ቢሆን “ቀዮ” የሚለው ቅጽል፣ሌላው የዘር መለያ ነው።ስለሆነም ቅራኔዎች ሁሉ በአገራችንም ነበሩ።እንዲሁ ላይ ላዩን ተነካክተው፣ ወቅቱ እስኪፈታቸው ድረስ ‘ተከድነው እንዲበስሉ’ የተተዉ ናቸው።ስለሆነም የእኛ ፌድራሊዚም ከሩሲያም፣ከቻይናም፣ ከህንድም፣ከናይጄሪያም ሆነ ከጀርመን ጋር የሚያመሳስለው ቢኖርም፣ የተለየ ኢትዮጵያዊ ባሕርይም አለው።

ምርጫን በሚመለከት፣

በተለያዩ ስም የተደራጁ የአማራ የፖለቲካ ድርጅቶች ቀደም ብለው ነው ግምባር የፈጠሩት።የተቀሩትም በአቅዋም አንድ በመሆናችው፣ በምክር ቤቱ መድረክ ላይ ይዋኸዳሉ። የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች ግን አስተባባሪ በማጣት እርስ በረስ እየተጠፋፉና ከመርጫውም እየተወገዱ ናቸው። ሕዝቡ ግን “ሳትከፋፈሉ አንድ ሁናችሁ ቅረቡ”በማለት ቀድሞ አስጠንቅቆአቸዋል።ሰሚ ግን አላገኘም።አሁንም ቢሆን ሰሚ ካለ፣ ጊዜ አላ።እኔ ያልኩት ካልሆነ የምንል ከሆነ፣ በእልህ ቅራኔ ይከራል፣የከረረ ቅራኔ ደግሞ ይበጠሳል።

ስለዚህም በእውነት የሠላም ሰዎች ከሆን፣ከወድሞች ሲቃይና ሞት ምን እናተርፋለን? የግዚአብሔር ቃል “ወንድሙን የሚጠላ ነፍሰ ገዳይ ነው፣ነፍሰ ገዳይ ደግሞ መንግሥተ ስማያት አይገባም” ይላል።ይቅርታ ማድረግ መብት ሳይሆን ትዕዛዝ ነው።ስለዚህም የአቢይን አሻጋሪነት በመተማመን ተሸውደው፣ ለእስር የተዳረጉትን በምሕረት በመፍታት፣ ከድርጀት የተባረሩትን በአመክሮ ወደ ነበሩበት በመመለስ፣ የኦሮሞን ሕዝብ ልብ በመማረክ፣ በአንድነት ማሰለፍ ይገባል።

በመሆኑም አገርን ከውድቀት ሕዝብን ከጭንቀት ለመታደግ፣ ታሪካዊ ሃላፊነት የተጣለባቸው ሁሉ፣ በመተባበር የጭቆና ፈርጆችን ሁሉ በጋራ መከላከል ይገባቸዋል። በብልጽግና ፓርቲና በሕወሐት መካከል የነበረው ቅራኔ፣ በሕገ መንግሥቱ መሠረት፣ በወቅቱ ተፈትቶ ቢሆን ኖሮ፣ ከቁጥጥር ውጭ በመውጣት ለከፍተኛ እልቂት፣ ለብዙዎች ስደት፣እስራትና ለኢኮኖሚ ድቀት ባልዳረገንም ነበር።ያኔ እርቅን ሲያጥላሉ፣ጁሐርን ለማሳሰር ይወተውቱ፣አጫሉን ለማስገደል ይዝቱ የነበሩት እነ ማን እንደሆኑ  ሕዝባችን ያውቃል፣ታሪክም ሲያስታውሳቸው ይኖራል።

ይህ ደግሞ ሁሉን ለእኔ ከሚል፣ከስግብግብ የንዑስ ከበርቴ ጠባይ የመጣ ነው።ከበርቴው የራሱን ብሔር በመበዝበዝ አይረካም።ጥቅምና ሥልጣንን ለማሳደድ ሲል ጎረቤቶቹን ይወራል።ይህ ነበር የአውሮፓ አገሮችን እርስ በርስ ሲያፋጅ የነበረው። ከዚህም የተነሳ ነበር የአፍሪካ አገሮችን በቅኝ የገዙት፡፡በአገራችንም በልሙጥ ባንዲራ ሥር የተሰባሰቡት አላማ የኦሮሞ መሬትን መወረራና ኢትዮጵያዊያንን ሁሉ ያለ ገደብ ለመበዝበዝ አፍኖ መግዛት ነው።

በመሆኑም ይህን የሕዝባችንን መከራና ሲቃይ ከምንጩ ለማድረቅ፣ የብሔር ብሔረሰቦችን መብት በሕገ መንግሥቱ መሰረት ማስከበር የግድ ይላል።ፌድራሊዝም የሕዝባችንን ራስን በራስ የማስተዳደር መብት የማያስከብር ከሆነ ደግሞ፣ ግንኙነታችን ወደ ኮንፌድሬሽን ከፍ ማለት ይኖርበታል።በአገራችን የፌድራል ግንኙነትን ለማስፈን ለሰላሳ አመት የተካሄደው ጥረት ሊያግባባን ሲገባው ሊለያየን የቻለው፣የፌድራል መንግሥቱ የሥራ ቋንቋ፣ የአንድን ብሔር መብት ብቻ የሚያሠፍን፣ የሌሎች ብሔሮችን መብት የሚያቀጭጭ በመሆኑ ነው።

ይህን ሐቅ በመሠወር ነው፣ የልሙጥ ባንዲራ አምላኪዎች ፣ግድለቱን ሁሉ የሕገ መንግሥትና የፌድራል ሕብረት በማስመስል፣ የብሔር ብሔረሰቦችን መብት የሚጻረሩት፡፡ስለሆነም በፌድራል መንግሥቱ የአንድን ብሔር ቋንቋ ብቻ የሚያስፍን አድላዊ የሕገ መንግሥት አንቀጽ በሥራ ላይ እስከ አለ ድረስ፣ የጭቁን ሕዝቦች መብት በእኩልነት ሊከበር አይችልም።ስለሆነም ዶከተርም ሆነ ፕሮፌሰር፣በአገር ውስጥም ሆነ ውጭ ያሉት ሊያሳምኑን የሚፈልጉት የራሳቸውን ሥልጣንና ጥቅም የሚያስከብረውን ፍልስፍና ነው።ለዚህም ነው የድብብቆሹ ጨዋታ ሥር የሰደደው።

ስለዚህም ብሔር ብሔረሰቦች፣እንደ ብዛታቸውና እንደ እምነታቸው፣  በብሔራዊ መስተዳድር፣በዞን ራስ ገዝና በወረዳ ራስ ገዝ ተደራጅተው፣ ቋንቋቸውን፣ እምነታቸውን ባኅላቸውንና ታሪካቸውን በማበልጸግ ራሳቸውን በራስ ሊያስተዳድሩ ይገባል።ይህ ደግሞ የማንም ችሮታ ሳይሆን፣ዓለም አቀፍ መርህ ነው።

የዚህም መብት መከበር፣ በክልሎች መካከል ሰላምን በመፍጠር፣ግጭትን በማስወገድ፣ ሕዝባችን በሙሉ ልብ ለምርትና ምርታማነት እንዲደመር ይረዳዋል። ይህ ከሆነ ዜጎች በአገራቸውና በአስተዳደራቸው በመርካት፣ ለአንድነት ተግቢውን ትኩረት ይሰጣሉ። ሕዝባችን በነፃነት መሪዎቹን መምረጥ ከቻለ፣ በየደረጃው የሚገኙ ባለሥልጣናትም የመረጣቸውን ሕዝብ ድምፅ ላለማጣት፣ ሁሉንም በእኩልነት ለማስተናገድ ይገደዳሉ። ቋንቋውና ባህሉ የተከበረለት ሕዝብ ደግም እርሱም በተራው የሌሎችን ስብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት በእኩልነት ያከብራል።

የፌድራልን የሥራ ቋንቋ፣ በሚመለከት

ኢትዮጵያ የብዙ ብሔር ብሔረሰብ አገር በመሆኗ፣ አንዱ ብሔር በሌላው ላይ፣ አንዱ ቋንቋ በሌላው ቋንቋ ላይ የበላይ ሆኖ፣ ጥላቻ፣ መናናቁና ብሔርተኝነት እንዳይቀጥል፣ለሁሉም ብሔርና እምነት እኩል የሆነ እንግሊዘኛ የፌድራሉ የሥራ ቋንቋ ቢሆን፣ከቅኝ ግዛት የወረስነውን የቋንቋ ጭቆናን በማስወገድ በሕዝባችን መካከል እኩልነትንና መተሳሰብን ያሰፍናል።ህንዶችም የብሔር ችግራቸውን ሊፈቱ የቻሉት በዚሁ ዘይቤ በመጠቀም ነበር።

የፌድራል ሕገ መንግሥትን በሚመለከት

ሕገ መንግሥቱ አገራችን ለሃያ ዘጠኝ አመት የተመራችበት በመሆኑ፣ ሕዝቦችን  በሰላም አብሮ ለመኖር በሚያግዝ መልኩ አሁን ቢሻሽል ይበጃል።የፌድራል ሕገ መንግሥቱም፣ በፌድራል ሥልጣን፣ተግባርና አገልግሎት ላይ ብቻ መወሰን ይገባዋል። ብሔራዊ ክልላዊ መስተዳድሮች በሥልጣን ክልላቸው ባለው ተግባር በክልል ሕገ መንግሥት የመጠቀም መብታቸው ተከብሮ ከጣልቃ ገብነት ሊጠበቅ ይገባል። ይህም የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ከምርጫው ቀድሞ ቢደረግ የበጃል። ምርጫው አሁን ባለው ሕግና ደንብ መሠረት ከተደረገ ውጤቱም ያው እንደነበረ የሚቅጥል ይሆናል።

ይህን ግልጽ ለማድረግ ፣በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ሥልጣን ይዘው የሚገኙት የብልጽግና ፓርቲ አባላት ናቸው። የብልፅግና ፓርቲ ሕጋዊነትም የሚመነጨውም ከእነዚሁ የፓርላማ አባላቱ ነው።የሌሎች ፓርቲ አባላት ውድድር የሚያደርጉት ከእነዚህ የፓርላማ አባላት የመንግሥት ሥልጣን ለመንጠቅ ነው።

የብልጽግና ፓርቲም እንደ ሌሎች ተወዳዳሪ ፓርቲዎች ሁሉ፣ አዳዲስ ዕጩዎችን አቅርቧል።አንድ የሕዝብ እንደራሴ የመራጩን ሕዝብ ድምጽ ሳያጣ፣ እንዴት በራሱ ፓርቲ ከምርጫ ውድድር ይገለላል?።ሕዝቡ በሕገ መንግሥታዊ መብቱ የመረጠውን የምክር ቤት አባል፣ ፓርቲው የሚሽረው በየትኛው የሕግ አንቀጽ ነው?ፓርቲው ከእጩነት ያገለለው የምክር ቤት አባል ተግባርና ሥልጣን ምን ይሆናል?

አገር ሲመሩ የቆዩ የምክር ቤት አባላት ለምርጫ ቀርበው መልካም የሠሩት ዳግም ካልተመርጡና፣ ደካሞችን ደግሞ ሕዝቡ በድምጹ ካልሻረ፣ የምርጫ ትርጉሙ ምን ሊሆን? በዚህ መልኩ ፓርቲዎች በሕዝብ ሥልጣን ውስጥ ጣልቃ ገብተው ተወካዮችን የሚሾሙና የሚሽሩ እስከሆነ ደረስ፣ ለምንድ ነው ለይስሙላ ምርጫ አገራችን ከፍተኛ ሀብት ንብረትና ጊዜን በከንቱ ታባክናለች?ይህ ከትናንቱ የኢሕአዴግ ምርጫ በምን ይለያል?

ጆቢር ሔይኢ ከሁስተን ቴክሳስ፣

Source link

Related posts

ከተማ አስተዳደሩ በመሬት ወረራ፣በባለቤት አልባ ህንጻዎች፣ በጋራ መኖሪያ ቤቶች ዙሪያ ያካሄደውን ጥናት ይፋ አደረገ

admin

የፌቤላ ዘይት ፋብሪካ ምርት ወደ መዲናዋ መግባት ጀመረ

admin

አብይ፣ ለማና የጃዋር ካልኩሌተር (አበበ ገላው)

admin