74.3 F
Washington DC
June 16, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ተቀራርባ መሥራት እና መደገፍ እንዳለባት የአሜሪካው ሪፐብሊካን ፓርቲ ሴናተር ጂም ኢንሆፍ ገለጹ፡፡

አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ተቀራርባ መሥራት እና መደገፍ እንዳለባት የአሜሪካው ሪፐብሊካን ፓርቲ ሴናተር ጂም ኢንሆፍ ገለጹ፡፡

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 19/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የአሜሪካው ሪፐብሊካን ፓርቲ ሴናተር ጂም ኢንሆፍ ሀገራቸው አሜሪካ በኢትዮጵያ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ላይ የጣለችውን የጉዞ እገዳ እና በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጫና የማሳደር ፍላጎትን አጥብቀው ተቃውመዋል፡፡ ትናንት በትዊተር ገጻቸው የባይደን አስተዳደር በኢትዮጵያ ላይ የጣለው እገዳ እንደማይገባት ገልጸው በግልጽ የተቃወሙት ሴናተሩ በአሜሪካ የእንደራሴዎች ምክር ቤት ስለ ኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ እውነታውን ከነታሪካዊ ዳራው አስረድተዋል፡፡

ሴናተር ጂም ኢትዮጵያን ጠንቅቀው እንደሚያውቋት እና 19 ያህል ጊዜ በተለያየ አጋጣሚ እንደጎበኟት ገልጸዋል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) እና ከሌሎች የሀገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር በተለያዩ ጉዳዮች በቅርበት መነጋገራቸውን እና እንደሚያውቋቸው አንስተዋል፡፡

ሴናተር ጂም ኢንሆፍ ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በላይ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት እየሠራች መሆኗን አብነት እየጠቀሱ ነው ለምክር ቤቱ ያቀረቡት፡፡ ገለልተኛ የሆነ የሰብዓዊ መብት ተቋም መቋቋሙን፣ በአሸባሪው የትህነግ ቡድን ታሰረው የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት፣ ጋዜጠኞችና ግለሰቦች መፈታታቸውን፣ ከኤርትራ ጋር የነበረው ቁርሾ ተፈትቶ ወደ ትብብር ማምራታቸውን እያነሱ ሞግተዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ለቀጣናው ሰላም እና ደኅንነት መረጋገጥ እየሠራው ያለውንም ሥራ አስረድተዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ሰላማዊ መፍትሔዎችን ለማምጣት ያላሰለሰ ጥረት እያደረገ መሆኑን እና በሀገሪቱ ሰላምንና አንድነትን ከማምጣት ውጪ ሌላ አካሄድ አለመከተሉን ተናግረዋል። ሽብርተኛው ትህነግ ከለውጡ በኋላ ጠብ ጫሪ ተግባራትን ሲከውን እንደነበር ሴናተሩ አስረድተዋል፡፡ ኢትዮጵያ አሁን ላለችበት አጣብቂኝ የዳረጋትን የአሸባሪው ትህነግ የሀገሪቱ መከላከያ ሠራዊት የሰሜን እዝ ላይ የፈጸመው ጥቃት እና ዝርፊያ መሆኑን ሴናተር ጂም አቅርበዋል፡፡ በዚህም የኢትዮጵያ መንግሥት ሕግ ለማስከበር መገደዱን ነው ሴናተሩ የገለጹት፡፡

በክልሉ የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለመመርመር እና ጥፋተኞችን ለሕግ ለማቅረብ መንግሥት ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና ሌሎች አጋር አካላት ጋር ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን እና እየሠራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡ እናም የአሜሪካ መንግሥትም ይህንን ሂደት በመደገፍ ከኢትዮጵያ ጎን ሊቆም ይገባል ብለዋል።

በሀገሪቱ ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ሕጋዊ ሥልጣን ይዞ ሁለንተናዊ ሰላም ለማምጣት እየሠራ ያለውን መንግሥት እና ከሥልጣን ተወግዶ ወንጀል እየፈጸመ ካለ ሽብርተኛ ቡድን ጋር ማነጻጸር ተገቢ አለመሆኑን ነው ሴናተሩ አበክረው ያስረዱት፡፡ በግልጽ መታወቅ ያለበት “ትህነግ ሽብርተኛ ድርጅት ነው” ሲሉ ነው ሴናተሩ የገለጹት፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትም ከዚህ የሽብር ቡድን ጋር የሚተባበር ማንኛውም አካል ተጠያቂ እንደሚሆን ማስታወቁን አስረድተዋል፡፡ አሜሪካም ችግሩን በዚህ መልክ መረዳት እንዳለባት እና የኢትዮጵያ መንግሥት በሀገሪቱ ሰላም፣ ዲሞክራሲ እና አንድነት እንዲመጣ እየሠራ መሆኑን መገንዘብ ያስገልጋል ብለዋል፡፡ እናም አሜሪካ እገዳ ከመጣል ይልቅ በምን መልኩ ማገዝ እንዳለባት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ተቀራርባ መነጋገር እንደሚገባት ነው የተናገሩት፡፡

ሴናተር ጂም በንግግራቸው መጨረሻ ኢትዮጵያ ያለችበትን ሁኔታ በሚገባ እንደሚረዱ እና መፍትሔ ለማምጣት በምታደርገው ጥረት ሁሉ ድጋፋቸው እንደማይለይ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

በየማነብርሃን ጌታቸው

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Source link

Related posts

አድማስ ሁለገብ የገበሬዎች የኅብረት ሥራ ማኀበራት ዩኒዬን ወጣቶችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እያደረገ ነው።

admin

ተስፋ የቆረጠው ኦነግ ሸኔ ህዝብ ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ፈፅሟል-ኮሚሽነር ጄኔራል አራርሳ

admin

የጃፓን መንግስት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ለሆኑት አቶ ሆርዶፋ በቀለ የክብር ኒሻን አበረከተ

admin